የትግል አጀንዳና ስትራቴጂውስ ምንድነው?
ኦነግ በኦሮሞ ልጆች ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ እንዳለው አይካድም። ለዚህ ደግሞ በተለይ የህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት የወሰዳቸው አፋኝ እርምጃዎች; የፈፀማቸው ግፍና በደሎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በኦነግ ሥም ብዙዎች ህይወታቸውንና አካላቸውን አጥተዋል; በእስር ማቅቀዋል; ለአካልና አእምሮ ስቃይ ተዳርገዋል; በስደት ተንከራትተዋል; ሌላም ብዙ ነገር ሆነዋል። ግን ለየትኛው ኦነግ?
መቼም ኦነግ ሲነሳ እነሌንጮ ለታን; እነዲማ ነገዎን; እነበያን አሶባን; እነአባቢያ አባጆቢርን; እነሌንጮ ባቲን. .. ወዘተ የመሳሰሉ አንጋፋ የድርጅቱ መሪዎች ሥማቸው አብሮ መነሳቱ አይቀርም። እነዚህ የትግል አጀንዳ በመቅረፅና ስትራቴጂ በመቀየስ ረገድ የድርጅቱ አርክቴክቶች ተደርገው የሚወሰዱ ጉምቱ ሰዎች ዛሬ ላይ መስመራቸውን ለይተዋል; የትግል አጀንዳና ስትራቴጂያቸውንም ቀይረዋል። ኦነግን ያለነዚህ ሰዎች ማሰብ ሶፍትዌሩ የወጣ ኮምፒውተርን እንደማሰብ ነው።
ሌላው ከኦነግ ጋር ተያይዞ ሥማቸው ጎልቶ የሚነሳው ገላሳ ድልቦ ናቸው። እኝህ በድርጅቱ መሪነት የሚታወቁ ሰው ዛሬም የኦነግ መሪ ተብለው ይጣቀሳሉ። እሳቸው የሚመሩት ኦነግ አሁን ላይ የትግል አጀንዳና ስትራቴጂው በግልፅ ባይታወቅም ከፖለቲካ መድረኩ አልጠፉም። ስለሆነም ከመንግሥት ጋር ተደራድረው ወደሀገር ገብተዋል። በዙሪያቸው ሌሎች አንጋፋ ሰዎችን እንዳሰለፉ የሚነገርላቸው ኦቦ ገላሳ አሁን ካለው የኃይል አሰላለፍ አንፃር ወዴየትኛው ጎራ እንደሚያዘነብሉም አልታወቀም።
አሁን ላይ ኦነግ ሲነሳ በመሪነት ቀድመው የሚጠቀሱት ኦቦ ዳውድ (ፍሬው) ኢብሳ አድስ አበባ ገብተው ከከተሙ ሰንብተዋል። ወደሀገር ሲገቡ በመስቀል አደባባይ (ምድር አንቀጥቅጥ በሚባል ዓይነት ሰልፍ) ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው አቦ ዳውድ የልብ ልብ ተሰምቷቸው የነለማን መንግሥት በኃይልም ጭምር እየተገዳደሩ ነው። በዚህ የተነሳ የተፈጠረው ውጥረት ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ለሀገር ወዳድ የኦሮሞ ልጆችም ትልቅ ራስ ምታትና የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።
በአንድ ወቅት የሚመሩትን ሠራዊት አስከትለው የህወሓት/ኢህአዴግን ሥርዓት በመክዳት ኤርትራ በገቡትና ኦነግን በተቀላቀሉት ብ/ጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦነግ ኃይልም ወደሀገር ገብቶ አሁን በተጀመረው የለውጥ ሂደት ውስጥ የራሱን ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው። የድርጅቱ መሪ የክልሉ የፀጥታ ኃላፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን ይህም እነኦቦ ዳውድ ኢብሳን ማስቆጣቱ አልቀረም። ከነኦቦ ዳውድ ጋር ያለፈ ቁርሾ እንዳላቸው የሚገመተው እነከማል ከኦዴፓ ጋር ለመዋሃድ መወሰናቸው የሚኖረው አንደምታ በቅጡ የተፈተሸ አይመስልም።
በዚህ ሁኔታ በተለይ ወጣቱ የኦነግን ዓርማ አንስቶ ሲንቀሳቀስ ጉዳዩ ከድርጅቱ ስያሜ; ከመሪዎቹ; ወይስ ከትግል አጀንዳና ስትራቴጂው? ሥመ-ገናናው ድርጅት በየፊናቸው “ኦነግ ነን” በሚሉ ቡድኖች ብዙ ቦታ በተሰነጠቀበት ሁኔታ ዛሬም አንድ የጋራ አጀንዳ ይኖረው ይሆን? እንደአሜባ ብዙ ቦታ የተበጣጠሰውን ድርጅት ማያያዝ የሚቻልባቸው ክሮች ቢገኙስ የኦሮሞን ፖለቲካ ከፍ አድርገው ከሰቀሉት ከነለማ/አብይ ጋር መወዳደር የሚያስችለው ተራማጅ አስተሳሰብና አጀንዳ ይኖረው ይሆን? ድርጅቱ በትግሉ ውስጥ የነበረው ድርሻና የከፈለው መስዋዕትነት የማይናቅ በመሆንም ትግሉን በረቀቀ ስልት አመራር አስደማሚ ደረጃ ላይ ላደረሱት ለነለማ/አብይ ተገቢውን ዕውቅና ይሰጣል ወይ?
አሁን ላይ የኦነግ የትግል አጀንዳና እስትራቴጂ ምንድነው?