የጌታቸው አሰፋ በሕግ ጥላ ስር መዋል አንድም ለፍትሕ፤ ሌላም ለፖለቲካው፤
—————–
የደህንነቱ ቁንጮ የነበረው የጌታቸው አሰፋ እና የጠቅላይ አቃቤ ሕግ የአይጥና ድመት ጨዋታ ሊገባደድ የተቃረበ ይመስላል። የዚህ ሰው መያዝ ሁለት እንድምታ አለው።
አንደኛው የፖለቲካ ሲሆን ይህ አይነኬ መሳይ ሰው ሕውሃትን ከለላ አድርጎ መቀሌ የመሸገው በፌደራሉ እና በትግራይ ክልል መካከል ያለውን መሻከር እና ክፍተት ተጠቅሞ ነው። ስለዚህ የዚህ ሰው በሕግ ጥላ ስር መዋል እና ሕውሃት ባይዋጥላትም የግዷን አሳልፋ መስጠቷ የፖለቲካውን ውጥረት ያረግበዋል። ከጌታቸው እስር መለስ ባሉት ጉዳዮች ደብረጺዮን እና አብይ የወሰደውን ጊዜ ወስዶ በጠረጴዛ ዙሪያ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እየፈቱት ሊሂዱ ይችላሉ።
ሁለተኛው እንድምታ ደግሞ የፍትሕ ነው። ይህ ሰው አገሪቱ ውስጥ ለተፈጸሙት አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ ነው። የዚህ ሰው በሕግ ጥላ ስር ሆኖ መመርመር እና ለፍርድ መቅረብ ለብዙ ዓመታት ስንጮህለት የቆየነውን የፍትሕ ጥያቄ በከፊልም ቢሆን ምላሽ እንዲያገኝ ያደርጋል። የፍትሕ ጥያቄው ሙሉ ምላሽ ሊያገኝ የሚችለው ግን ጌታቸው ለፍርድ ስለቀረበ ብቻ ሳይሆን በዙሪያ አብረውት የመብት ጥሰቱን ይፈጽሙ የነበሩ የኢህአዴግ ሹማምንት ላይ በቂ የሆነ ምርመራ በገለልተኛ ወገን ሲደረግ እና በሕግ የሚጠየቀው ለፍርድ ሲቀርብ፤ ይቅር የሚባለውም በወጉ ይቅር ሲባል ብቻ ነው።
ሌላው አሳሳቢው ነገር የትላንቱ ሳይሆን ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ነው። ትላንት ገራፊው፣ ገዳዩ፣ አሳሪው፣ አፋኙ መንግስት እና በመንግስት ሥር የሚሰሩ የጸጥታ ኃይሎች ነበሩ። ዛሬ መንግስት ከእነዚህ እኩይ እና ሕገ ወጥ ተግባራት ሲታቀብ የጭካኔ በትሩን የወረሱ ትናንሽ የመንደር መንግስታት እና ቡድኖች መፈጠራቸው እጅግ አሳሳቢ ነው። ግለሰቦችን የሚያስፈራሩ፣ ግድያ የሚፈጽሙ፣ ዩንቨርሲቲዎችን በዘር ጥቃት የሚያምሱ፣ ሕዝብን የሚያፈናቅሉ፣ አንዳንዴም በሚዲያ እየወጡ በአደባባይ የሚፎክሩ ቡድኖች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሕዝብ ላይ ጥቃት እያደረሱ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎች ከተለያየ አቅጣጫ እየወጡ ነው።
በዚህ ሳምንት ከቡሌ ሆራ ዩንቨርሲቲ ከማንነታቸው ጋር በተያያዘ በተሰነዘረ ጥቃት ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው ባህርዳር ሜዳ ላይ የፈሰሱት የክልሉ ተማሪዎች፣ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ውስጥ ሦስት ተማሪዎች ተገለው አስከሬናቸው የቆሻሻ መጣያ ቱቦ ውስጥ መገኘቱ፣ አክቲቪስት ገረሱ ቱፋ Geresu Tufa እሱን ጨምሮ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት በማንጸባረቃቸው ብቻ ግድያ እንዲፈጽምባቸው ገንዘብ ተከፍሎት የሚንቀሳቀስ ቡድን መኖሩን መግለጹ፣ በወለጋ የኦነግ ታጣቂዎች እያደረሱት ያለው ችግርና የመብት ጥሰት፤ እንዲሁም በእነዚህ ሁለት ቀናት በማህበራዊ ድህረ ገጾች እየተዘዋወረ ያለው የኦነግ ታጣቂዎች ሕጻናትን ለውትድርና ሲያዘጋጁ የሚያሳይ የፎቶ ምስል አገሪቱ እንዳትረጋጋ እንቅልፍ አጥቶ የሚሰራ ኃይል መኖሩን ያሳያል።
መንግስት ሕግ ለማስከበር የጀመረውን ጥረት የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች በማይጥስ መልኩ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሁሉም አካላት እገዛ የሚያስፈልገው ይመስለኛል። እነኚህ ከሕግ ያፈነገጡ ኃይሎች በየቦታው የሚፈጽሙትን ግፍ እና የመብት ጥሰት ማጋለጥ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የነጻነቱ እና የመብቱ ባለቤት እንዳይሆን በማናቸውም መልኩ እንቅፋት እየፈጠሩበት ያሉ ኃይሎችን መታገለ የነጻነት ትግሉ አካል ተደርጎ መወሰድ አለበት።