ገና በለጋ ዕድሜዬ በውስጤ ሰርጿል። የደሴ – የወ/ሮ ስኂንና የሆጤ ተማሪዎች ይመስክሩ። ያኔ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ወያኔና ሻዕብያ በየፊናቸው ሀገር ከመቆጣጠራቸው በፊት “ገንጣይ አስገንጣይ” በሚል በሚኒ-ሚዲያ ያቀረብናቸውን ግጥሞችና መጻጽፎች ማስታወስ ይቻላል። ወያኔ ሀገር ከተቆጣጠረም በኋላ የወ/ሮ ስኂን የተማሪዎች ካውንስል ፕሬዝዴንት ሆኜ ከጓደኞቼ ጋር የፈጠርነው ፀረ-ወያኔ ንቅናቄ እንደሰደድ እሳት በመላው አማራ ክልል ተቀጣጥሎ ሥርዓቱን ሲንጠው – ያኔ መሐመድን ማስያዝ ለቻለ እስከ መቶ ሺህ ብር ለመስጠት ቃል ሲገቡ. …
ያኔ ነበር በእግራችን ለብዙ ቀናት ተጉዘንና ድንበር አቋርጠን ከጅቡቲ ነፃ አውጭ ኃይል ጋር የተቀላቀልነው። እንደወጉማ ጅቡቲን ነፃ አውጥተን ፊታችንን ወደ ኢትዮጵያ ለማዞርና ሀገራችንን ከከፋፋይ ዘረኞች አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ነበር የትጥቅ ትግሉን የተቀላቀልነው። እሱም አልሳካ ሲል በወቅቱ “ከፋኝ” በሚል ጎንደር አካባቢ የሚንቀሳቀስ ኃይል ለማግኘት ብዙ ተንከራተትን። አለመታደል ሆነና በአገዛዙ እጅ ላይ ወደቅን። ያኔ በለጋ ዕድሜዬ የተቀበልኩትን ስቃይና እንግልት አሁንም ሳስታውሰው ያመኛል።
ወያኔ ቤተሰብ/ዘመድ/ወዳጅ እንዳያገኘኝ ከቀረቀረብኝ የስቃይ ቤት አውጥቶ ደሴ ከተማ ውስጥ እንዳልኖር በፅኑ በማስጠንቀቅና ቤተሰቦቼን በማስፈረም አገር ለቅቄ እንድሄድ ትዕዛዝ ሰጠ። የነበረኝ አማራጭ ወደ አፋር ክልል መሔድ ሲሆን ከዚያም በተደጋጋሚ እጆቼ በካቴና እየታሰሩ ለአማራ ክልል ተላልፌ እየተሰጠሁ ብዙ ተሰቃይቻለሁ። በዚህ ሁኔታ ነው ከ11ኛ ክፍል የተቋረጠውን ትምህርቴን ጨርሼ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የገባሁትና በህግ የተመረቅሁት።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተማርኩ በጦቢያ; ኢትኦጵና ሌሎችም የህትመት ውጤቶች ላይ በተለያዩ የብዕር ስሞች ጠንከር ያሉ ጽሁፎችን አቀርብ ነበር። ከዚህ በተጓዳኝ የተደራጀ ፖለቲካ ውስጥ በመግባት የአገር አቀፍ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባል መሆን ችዬ ነበር። ከዩኒቨርስቲ ተመርቄ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ሥራ ብጀምርም የኢትዮጵያ ሁኔታ ሰላም ሊሰጠኝ አልቻለም ነበር። ስለሆነም ሥራዬን አቋርጬ የሙሉ ጊዜ ፖለቲከኛ ለመሆን ወሰንኩ።
ግን ለምን? እኔ በግሌ አንድም ያጣሁትና የጎደለብኝ ነገር አልነበረም። ግና አገሬ የጠባብ ብሔርተኞች መፈንጪያ ስትሆን ከዳር ቆሞ ማዬትን ህሊናዬ ሊቀበለው አልቻለም። እናም በ1996 – 97 መኢአድን በኋላም ቅንጅትን ወክዬ በአማራ; በደቡብ; በኦሮሚያና በአፋር አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ህዝብን በማደራጀት; በመቀስቀስና ለለውጥ በማነሳሳት የበኩሌን ድርሻ ተወጥቻለሁ።
በዚያ ሂደት የኢትዮጵያን ህዝብ እስከሥር ገብቼ አይቸዋለሁ; አውቄዋለሁ። ኢትዮጵያዋነት የተዳፈነ ረመጥ መሆኑንም አረጋግጫለሁ። ኢትዮጵያዊነት ለጊዜው እክል ቢገጥመውም እንዴት በቀላሉ መልሶ ሊያንሰራራ እንደሚችል ከሚያዚያ 30/97 ዓ.ም የተሻለ ምን አስረጅ ሊኖር ይችላል? ከኢትዮጵያዊነት እንዴትስ ተስፋ ይቆረጣል?
አሁንም ከተለያዩ ወንድሞቼ ጋር እየተገናኘን በኢትዮጵያዊነትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ እንመክራለን። በእኛ ስብስብ ውስጥ ከአፋር; ከጎንደር; ከኢሉባቡር; ከባሌ; ከአሶሳ; ከደሴ; ከአዋሳ; ከባህርዳር; ከአርባምንጭ; ከመቀሌ; ከአዲስ አበባ; ከራያ-አለማጣና ከሌሎችም አካባቢዎች የመጡ; የተለያዬ የብሔርና ሃይማኖታዊ ማንነት ያላቸው ሰዎች አሉ። ጊዜና ቦታ የፈቀደውን ያህል እየተገናኘን በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታና መፃኢ ዕድሎች ላይ እንወያያለን; እንመክራለን። በሁሉም ውስጥ ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትና ቁጭት ይታያል። አብዛኞቹ እዚህ በfacebook ንቁ ተሳታፊ ስለሆኑ የምናገረው እውነት መሆኑን ሊያረጋግጡ ይችላሉ።
በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነትን እንዴት ልተወው? በተለይ ደግሞ እንዶ/ር አብይ ያሉ ኢትዮጵያዊነትን በፍቅር የሚያንቆለጳጵሱ; የህዝብ ፍቅርና አንድነትን የሚሰብኩ ሰዎች በመንግሥት ሥልጣን ላይ ባሉበት ዘመን ከኢትዮጵያዊነት እንዴት ተስፋ ይቆረጣል? መቼስ ቢሆን ኢትዮጵያዊነትን ትቶ ወዴት ይኬዳል? በተገኘው መልካም አጋጣሚ ወደከፍታው እንወጣለን እንጅ እንዴት ወደ ቁልቁለቱ ተንደርድረን የማንወጣው አዘቅት ውስጥ እንወድቃለን?
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!!