ከረሙ ገዳይ ቤት ፡ የማያልፍ መስሏቸው፣
ከዘረፈው ሃብት፡ ትንሽ ቢያሳያቸው፣
በቀመሱት ጉርሻ ፡ በበሉት እንኩቶ፣
አይናቸው ታውሮ ፡ ጆሮቸው ተዘግቶ፣
አላየንም አሉ ፡ አልሰማንም አሉ ፣
እናት ስታለቅስ ፡ በሃገር በምድሩ።
ወንድ ልጅ ሲኮላሽ ፡ ሴት ለጅ ስትደፈር፣
ወገን ሁሉ ታስሮ ፡ ደም ሞልቶ በአገር ፣
እነሱ ዘፈኑ፡ እስክስታ ወረዱ፣
በወያኔ ሰፈር ፡ ሃገር እያረዱ፣
ከርሳቸው ሞላና፡ በምላስ ለፈፉ፣
ለገዳዩ ሌባ፡ ቅኔውን ዘረፉ።
የማያልፍ መስሏቸው፡ ደግሞም የማይታይ፣
በህዝቡ ቀለዱ፡ ዋሹት እስክ ሰማይ፣
በደም የጨቀየ፡ መጠጡም ተጠጣ፣
የማያልፍ መስሎቸው ጸሃይ የማትውጣ፣
ሰው እንዴት ይኖራል ፡ለሆዱ ተግዝቶ፣
ራሱን ደብቆ ፡ ህሊናውን ሽጦ፣
ይቅርታ ለማለት ፡ እንዲህ ሲክብዳቸው፣
የወያኔው ጉርሻ እንዴት ተዋጥላቸው!
አጉራሽ ጌቶቻቸው ስለፈርጠጡ፣
ትምርት ቤት ይግቡ፡ ሰው ሁነው እንዲወጡ፣
የጠራውን ሰፈር ፡ እንዳይበጠብጡ፣
የድል አጥቢያ አርበኛ ፡ ሁነው እንዳይመጡ!