ብፁዕ አባታችን አቡነ መልከ ጼዴቅ! እንኳን ለአገርዎ አበቃዎ! /አዘጋጅ መጋቤ ሐዲስ ልዑለቃል...

ብፁዕ አባታችን አቡነ መልከ ጼዴቅ! እንኳን ለአገርዎ አበቃዎ! /አዘጋጅ መጋቤ ሐዲስ ልዑለቃል አካሉ ዓለሙ/

በእንተ ብፁዕ ወንዑድ አቡነ መልከ ጼዴቅ ሊቀ ጳጳስ

አጭር ታሪክ!

(አዲሱ ትውልድ ታላቁን የቤተ ክርስቲያን ሊቅና የአገር ባለውለታ ያውቃቸው ዘንድ የቀረበ አጭር ገላጭ ዘገባ)

መካነ ልደት

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር አውራጃ በፋርጣ ወረዳ ልዩ ስሟ መገንታ ቍስቋም በተባለች ደብር ከቄስ ወርቅነህ ትኩና ከወይዘሮ አንጓች አታሌ በ1916 ዓም ተወለዱ ።

ትምህርት ቤት

ገና በሕፃንነት ዕድሜያቸው ከደጉ አባታቸው ከቄስ ትኩ ፊደል ቈጥረው ንባብ ለይተው ዳዊት ከደገሙ በኋላ የቃል ትምህርት ጀመሩ ። በአቅራቢያቸው ከሚገኘው ድድም ጊዮርጊስ ከመሪጌታ ወንድም ጾመ ድጓ እና ምዕራፍ ተማሩ ። ቀጥሎም በዝነኛዋ ደብር አዛውር ኪዳነ ምሕረት ከታላቁ የዜማ መምህር መሪጌታ ጀንበር የዜማ ትምህርታቸውን አጠናከሩ ። ከዚያም ወደ ሌላኛው ዝነኛ ደብር አትከና ጊዮርጊስ ሂደው ከመሪጌታ ፈቃዱ ድጓ ተምረዋል ። ቅኔ ቈጥረው የተቀኙት ደግሞ በታላቁ ደብር ቆማ ፋሲለደስ ከሚገኙት ከሊቁ መምህር መሪጌታ ዓምደ ብርሃን ነበር ። ቀጥሎም ወደ አማራ ሳይንት ገርት አቡነ አቢብ ተጉዘው ከመሪጌታ አበበ ገርቲ ቅኔያቸውን ከነአገባቡ አጠናክረው ተቀኝተዋል ።

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ከፍተኛ የሃይማኖት ትምህርትን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ተምረዋል 

1ኛ/ ከታላቁ ሊቅ መምህር ሰይፈ ሥላሴ አዲስ አበባ በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጉም ተምረው በመምህርነት በመመረቅ ወንበር ዘርግተው አስተምረዋል ።

2ኛ/ ከሌላው ሊቅ ከመምህር ፊላታዎስ ደግሞ የአምስቱን ብሔረ ኦሪት ትርጓሜ ፣ መዝሙረ ዳዊትን ፣ መጽሐፈ ኢሳይያስን በሚገባ አጠናቀው ተምረዋል ።

3ኛ/ ከዚህ በኋላ ዘመናዊ ትምህርትን ከመንፈሳዊው ትምህርት ጋር አጠናክረው ለመማር በ1939 ዓም ወደ ቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተዋል ። በዚህ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ለአራት ዓመታት ሲሰጥ የነበረውን ሥርዓተ ትምህርት በከፍተኛ ትጋት በመከታተል እና ከጓደኞቻቸው ብልጫን በማሳየት ለሦስት ዓመታት ደጋግመው ተሸልመዋል ።

በአራተኛው ዓመትም ከወዳጅ ቤተ ክርስቲያን በተገኘው የከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት እድል (እስኮላርሽፕ) ወደ ግሪክ ኦርቶዶክስ ኢኩሚኒካል መንበረ ፓትርያርክ ወደ ቍስጥንጥንያ ተልከው ልዩ ስሙ “ሐልኪ” በሚባለው የቲዎሎጅ ትምህርት ቤት ገብተው ለአምስት ዓመታት ተምረው በከፍተኛ የቲዎሎጅ ትምህርት ተመርቀዋል ። የመጀመርያው ባለ ድግሪ ካህን በመሆንም በ1949 ዓ/ም ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ።

ሥልጣነ ክህነት

ሥልጣነ ክህነት በመቀበል ዕድሜ ልካቸውን ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የቻሉት ።

1 መዓርገ ዲቁናን ከብፅዕ አቡነ አብርሃም በ1927 ዓም ።

2 መዓርገ ቅስናን ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ በ1938 ዓም በመቀበል ሲሆን

3 የመነኮሱት ደግሞ ጣና በምትገኘው ዝነኛዋ የክርስቶስ ሠምራ ገዳም ነው ።

4 መዓርገ ጵጵስናን የተቀበሉትም በ1983 ዓም ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ነው ።

ሥራ /አገልግሎት

በግሪክ አገር የሚሰጠውን የነገረ መለኮት ትምህርት አጠናቀው እንደ ተመለሱ መደበኛ ሥራቸውን የጀመሩት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተመድበው የተማሩትን በማስተማር ነበር ። ከ1950-1952 ዓ/ም ሲያስተምሩ እንደ ቆዩ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዳይሬክተርና መምህር በመሆን ሙያቸውን በተግባር አሳይተዋል ። ከ1950-1952 ይህን ተዳክሞ የነበረ ትምህርት ቤት ነፍስ በመዝራት ሥርዓተ ትምህርቱን አሻሽለው ፥ መምህራንን አሟልተው ፥ ግቢውን አለምልመው ባጠቃላይ የጠፋውን የጠመመውን አቅንተው ከፍተኛ የሥራ ውጤት አሳይተዋል ። ለከፍተኛ ደረጃ እንዲታጩ ያደረጋቸውም በዚህ ትምህርት ቤት በጥንካሬ ያሳዩት የሥራ ፍሬ ነው ። በዚሁ ት/ቤት በዳይሬክተርነትና በአስተማሪነት ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ፥ በወቅቱ በክብር ዘበኛ ሬዲዮ ጣቢያ ተከታታይ ፕሮግራም ያቀርቡት የነበረው ስብከተ ወንጌል ታዋቂነትን አትርፎላቸው ነበር ።

በ1952 ዓ/ም የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልዩ ካቢኔ ሲቋቋም ፥ ለንጉሠ ነገሥቱ የሚቀርቡትን መንፈሳዊ ጉዳዮች ለማጣራት በኃላፊነት ተመርጠው የመንፈሳዊ ጉዳዮች መምሪያ ዳይሬክተር ሁነው ተሹመዋል ። ወዲያውኑም የመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት ሁነው ተሹመው ሁለቱንም ከፍተኛ ኃላፊነቶች በመሸከም እስከ 1966 ዓ/ም ድረስ ለ14 ዓመታት ከፍተኛ የሥራ ውጤት አሳይተዋል ። የሠሩአቸውም ሥራዎች እጅግ ብዙዎች ናቸው ።

ለምሳሌ ያክል ጥቂቶቹን እንጠቅሳልን ። ሙሉውን የብፁነታቸውን አገልግሎትና የሥራ ፍሬ በተመለከተ «ዜና ሕይወቱ ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ሊቀ ጳጳስ» በሚል ርእስ በ80ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው ጊዜ በታተመው መጽሐፍ ላይ ተብራርቶ ተገልጧል ። አንባብያን ያንን ቢመለከቱ ብዙ ታሪካዊ መረጃ ያገኙበታል ።

በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያሳዩት የሥራ ፍሬ በመጠኑ 

በካቴድራሉ እንደ ተሾሙ መጀመርያ ለማስተካከል የሞከሩት ውስጣዊ አገልግሎትን መልክና ሥርዓት ማስያዝ ነበር ። ካህናቱ በየሙያቸው ተለይተው ሊቃውንቱ እንዲያስተምሩ ፣ ደቀ መዛሙርቱ እንዲማሩ የውዳሴና የቅዳሴ የትምህርትን ፕሮግራም በመለየትና ጥብቅ ቍጥጥር በማድረግ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሰዓታቱ የማኅሌቱና የጸሎቱ በተለይም የቅዳሴው አገልግሎት ምእመናኑን የሚያረካ ፥ አገልጋዮቹንም የሚያስመካ እንዲሆን አደረጉ ። የወንጌል ስብከት በሠለጠኑ አገልጋዮች እንዲመራ በማድረግ ወጣቶች በሰንበት ትምህርት ቤትና በማኅበራት ተዳረጅተው እየተማሩ ቤተ ክርስቲያንን እንዲወዱና አምላካቸውን እንዲያመሰግኑ በማድረግ አድሮ የሚገኝ ሥራ ሠሩ ።

በዚህ ጊዜ ነበር «ማኅበረ ክርስቶስ የወጣት ሴቶች ማኅበር ፣ ማኅበረ እስጢፋኖስ የወጣት ወንዶች መንፈሳውያን ማኅበራትን አቋቁመው አሠልጥነው ቅዳሴ ተሰጥኦ በመቀበል ፣ መዝሙር በመዘመር ፣ አዲስ አበባን ያስደነቁት ።

ታዲያ አቡነ መልከ ጼዴቅ ይህንን በሚያደርጉበት ጊዜ ከባድ ፈተና ነበረባቸው ። «ሊቀ ሥልጣናት ሴቶችን አስቀደሱ» ተብለው ተከሰው ነበር ። ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት መልስ ሲሰጡ «እኅቶቻችን ወራዳ የዝሙት ሥራ መርጠው እሪ በከንቱ ቁመው ሲያድሩ የተከሰሰ የተወቀሰ የለም ፤ እኔ ግን መጽሐፉን ተከትዬ በቅዳሴው ላይ «ይበሉ ሕዝብ» የሚለውን ተከትለው አምላካቸውን እንዲያመሰግኑ በማደራጀቴ ተከሰስኩ ፤ ለመሆኑ ይህንን እየመጡ የሚነግሩዎት ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ፥ ቅዱስነትዎትንስ የሚያከብሩ ናቸውን?» አሉአቸው ። ቅዱስነታቸውም «አይ! ቀደሱ ስላሉኝ ነው ፣ ከመቅደሱ እንዳይቀርቡ ጥንቃቄ ይደረግ» ። አሉአቸውና እያዘኑ ተመለሱ ። ቢሆንም በወቅቱ ዘመኑን የሚዋጅ የጀመሩት ኦርቶዶክሳዊ እድገት ማለትም ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ተልዕኮ መሳካት ያቋቋሙት ሐዋርያዊ አገልግሎት በጣም የሚያበረታታ ስለ ነበር ፣ ካህናትና ምእመናን ስለ ወደዱት ፣ ንጉሠ ነገሥቱም «ይግፉበት ፥ ይበርቱ ፥ ምን እንርዳዎ» ይሏቸው ስለ ነበር የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳደር እየተጠናከረ ሥራውም እየሠመረ ሄደ ። ሥራ ፈቶ የሚታይ ካህን አልነበረም ፤ ዲያቆናቱ መንፈሳዊውንና ዘመናዊውን ትምህርት ይማራሉ ፣ መምህራንና ካህናት እርስ በእርሳቸው የተማሩትን ይቀጽላሉ ፤ እንዲሁም እስከ 12ኛ ክፍል ዘመናዊ ትምህርት ቤት ተከፍቶላቸው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ መነኮሳት ፥ ካህናት ፥ ዲያቆናት ብዙዎች ናቸው ።

የቢሮ አደረጃጀትን በተመለከተም –

የልደት ፥ የጋብቻ ፥ ያረፉ /የሞቱ/ ሰዎች መዝገብና ምስክር እዲዘጋጅ ፣በተለይ የክርስትናና የጋብቻ ሥርዓት ዘመናዊ ሁኖ የምስክር ወረቀት እንዲኖረው ያደረጉ ብፁዕነታቸው ናቸው ።

ሐዋርያዊ ድርጅትን በተመለከተ

የብሥራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ ሲከፈት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተመደበውን ግማሽ ሰዓት ክፍለ ጊዜ በሥራ ላይ ለማዋል ከንጉሠ ነገሥቱ መመሪያ በመቀበል ከሚኖሩበት ቤት አንዱን ክፍል የድምጽ መቅረጫ እንዲሆን በመፍቀድ እና መሣሪያዎችን በማሟላት ሠራተኛም በመመደብ አምስት ምርጥ ሰባክያንን ቀጥረው

1/ እራሳቸው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

2/ ነፍሳቸውን ይማር እና ሊቁ መልአከ ሰላም ሳሙኤል ተረፈን መደበኛ ሰባኪ በማድረግ የስብከቱን ሥራ ጀምረዋል ።

ወዲያውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሐዋርያዊ ድርጅት በካቴድራሉ ሥር ራሱን ችሎ በቦርድ እንዲተዳደር ተቋቁሞ ከፍተኛ ሥራዎች እንዲከናወኑ አድርገዋል ። በዚሁ የድርሰት እና ስብከት ክፍል «ድምፀ ተዋህዶ» ጋዜጣና «ትንሣኤ» መጽሔት እንዲዘጋጁና ለምእመናን እና ካህናት እንዲሰራጩ በማድረግ ፤ ከስብከተ ወንጌል ጋር የተያያዙ መጻሕፍትን በማሳተም ዐቢይ ሐዋርያዊ ተልእኮ ፈጽመዋል ።

ተዘዋዋሪ የስብከት ቡድንም በየበዓላቱ በመመደብ ቃለ ወንጌል እንዲዳረስ ለማድረግ ጥረዋል ። ይህ ብቻም አይደለም ትምህርቱ እና መዝሙሩ በካሴት እየተቀዳ ለሚፈልጉ ምእመናን እንዲዳረስ የመጀምሪያውን ሙከራ ያደረጉ ብፁዕ አባታችን ናቸው ።

በሐዋርያዊ ድርጅት ሥር ዘጠኝ ትምህርት ቤቶችን በአዲስ አበባ እና በክፍላተ ሀገራት በማቋቋም ከፍተኛ ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲፈጸም ጠንካራ አመራር ሰጥተዋል ። በማጅ (ከፋ) የሽናሻ ነገዶችን ፣ በመተከል (ጎጃም) ቡለን የሻንቅላ ነገዶችን ከሰዎችና ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ። እንዲያውም በቤታቸው እያስተማሩ የሚያሳድጓቸው እና ለመዐርገ ዲቁና የደረሱ ልጆች ነበሩ ። በተለይም ወላጅ የሌሉአቸው እና መንፈሳዊ ትምህርት በሕፃንነታቸው የቀሰሙ ሕፃናት በአዳሪ ትምህርት ቤቶች እየተማሩ እንዲያድጉ ከውጭ እርዳታ ሰጭዎች ጋር በመነጋገር የሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ነበር ፤ ዛሬ በሕፃናት አስተዳደግ ጉባኤ ሥር የሚተዳደሩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በእሳቸው ጥረት መሠረታቸው የተጣለ ነው ። ብፁዕ አባታችን የካቴድራሉን ንብረት ገቢ በመቈጣጠር እና በማሻሻል አዲስ የገቢ ምንጭም በመፍጠር የፈጸሙት አገልግሎት ብዙ ነው ።

የሙካሽ እና የሥጋጃ ሥራ ፋብሪካ በማቋቋም አያሌ ሴተኛ አዳሪ ሴቶች ከነውር ሥራ ርቀው በዚህ መስክ ተቀጥረው ራሳቸውን እንዲረዱ እና ካቴድራሉን በገቢ እንዲያዳብሩ ጥረዋል ።

የመኪና ስፌት ሙያንም በመጠቀም የአልባሳት እና ንዋየ ቅድሳት ማደራጃ አዘጋጅተው ዛሬ በአብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት የሚታየውን አርአያነት አስተላልፈዋል ። ካቴድራሉ ሙዚየም እና የቁም ጽሕፈት ክፍል እንዲኖረው በማድረግም የሀገር ውስጥም ሆኑ የሀገር ውጭ ጎብኝዎች ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ይትበሃል እንዲረዱ ጥረዋል ።

የመጻሕፍት ኅትመትን በተመለከተ ፣ በተለይም መጻሕፍትን በማሳተምና በመጠነኛ ዋጋ አንባብያን እንዲያገኙና እንዲጠቀሙባቸው በማድረግ የፈጸሙት አገልግሎት ከፍተኛ ነበር ። ትልቁ መጽሐፍ ቅዱስ ፥ ድጓ ፥ አምስቱ ጸዋትወ ዜማ ፥ መጽሐፈ ቅዳሴ ከነምልክቱ እንዲታተሙ አድርገዋል ። መጽሐፈ ሕግጋት ዓበይት ፍትሐ ነገሥት ከነአንድምታው እና ነጠላ ትርጓሜው ወዘተርፈ የታተሙት በብፁነታቸው ጥረት ነው ። አምስቱን ጸዋትወ ዜማንም ሲያሳትሙ ነፍሳቸውን ይማር እና የድጓውን ምስክር ታላቁን ሊቅ አለቃ ጥበቡ መርሻን ከቤታቸው አስቀምጠው በመንከባከብ ጥራት ባለው ሁኔታ እንዲጻፉ እና በኦፍሴት እንዲታተሙ አድርገዋል ። በካቴድራሉ የታተሙት መጻሕፍት ብዙዎች ናቸው ።

የመጻሕፍት መደብር በአዲስ አበባ እና በክፍላተ ሀገራትም ተከፍቶላቸው የምእመናኑን እና የካህናቱን ፍላጎት በቀላሉ ለማርካት ችለዋል ። የግእዝ ቋንቋም እንዳይረሳ እና አለመሞቱን ለማብሠር “ትንሣኤ ግእዝ” በሚል ፕሮግራም ውይይት በግእዝ ለማካሄድ ሞክረው ጥሩ ውጤት ታይቶ ነበር ። ራሱን የቻለ መጽሔትም ነበረው ። (ዜና ሕይወቱ ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ገጽ 158-163 ይመልከቱ)

ብፁነታቸው ደራሲ ስለ ሆኑ ፥ ራሳቸው የደረሷቸው መጻሕፍትም ብዙ ናቸው ። እስከ ዛሬ ድረስ 20 መጻሕፍትን ደርሰው አሳትመዋል ። ሁለት ለኅትመት የተዘጋጁ ፣ ሌሎች 9 ዝግጅታቸው አልቆ የተቀመጡ አሉ ። በድምሩ 31 መጻሕፍትን ጽፈዋል ፤ ዝርዝሩን ወደ ፊት እናሳያለን ።

ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ  ጋር የነበራቸው መልካም ግኑኝነት

ብፁዕነታቻቸው ለንጉሠ ነገሥቱ ያላቸው ፍቅር በጣም ካፍ ያለ ነው። «ደጋፊዬ፣ አይዞህ ባይ፣ አላማዬን የተረዱልኝ መሪ ነበሩ፤ ያለእሳቸው ድጋፍ እንደ እንቅፋቱ ብዛት ምንም ማደረግ አልችልም ነበር» ይላሉ።« ነገር ግን ጀንሆይ ሁልጊዜ አይዞዎት ይበርቱ ተቃዋሚ የበዛቦት ሰር ያለው ስራ  ስለጀመሩ ነው፤ ፍሬ ከሌለው ዛፍ ላይ እኮ ወፎች አይጮሁም፤ እኛንም ይህ ፈላሻ እያሉ ይሰድቡናል እኮ፤ ስራ ከሰሩ ነቀፋ ያለ ነው እያሉ ያበረታቱኝ ነበር በማለት ብዙ ጊዜ ይናገራሉ።»

አቡነ መልከጼዴቅም መንግሥት ሊገለበጥ ሲል ሁኔታውን ተረድተው ወደ ሰሜን እንሂድና ጎንደር ይቀመጡ ሕዝቡ አሳልፎ አይሰጥዎትም እርስዎን ከያዘ ደግሞ ምንም ድል አይነሳውም፤ ስለዚህ ወደ ጎንደር ሂደን ይህን ጊዜ ቢያሳልፉት ብለው ጃንሆን አማክረዋቸው ነበር። ነገር ግን ጆንሆይ « የለም አይሆንም በሰላሙ ጊዜ ምንም ላለደረግንለት ሕዝብ አሁን ሁሉ ሲልያልፍ ሂደን ሸክም አልሆንበትም፤ ከዚሁ ሁነን ነው የሚመጣውን የምናቀበለው ።» ብለው እንደ መለሱላቸው ብፁዕነታቸው ተናግረዋል ጽፈዋልም። በብፁዕነታቸው አገላለጽ የቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያም ሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወርቃማ ዘመን» ነበር። ( ይህን በተመለከተ የቋሚ ምስክር የሚለውን መጽሐፍ ምዕ 1&2 እንዲሁም ዜና ሕይወቱ ለቡፁእ አቡነ መልከጼዴቅን ገጽ 192-211 ይመልከቱ)

የተሸለሙአቸው ሽልማቶች

ሀ) ከኢትዮጵያ መንግሥት

  1. የኢትዮጵያ የክክብር ኮከብ ባለ አምበል 1ኛ ደረጃ
  2. የዳግማዊ ምኒልክ የክብር ኮከብ ባለ አምበል 1ኛ ደረጃ
  3. የቅድሥት ሥላሴ ኒሻን የኮማንደር ደረጃ ያለ ፕላኩ
  4. የቅድሥት ሥላሴ ኒሻን የኮማንደር ደረጃ ከነ ፕላኩ

ለ) ከውጭ ሀገራት

  1. ከግሪክ መንግሥት
  2. ከግሪክ ቤተ ክርስቲያን
  3. ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን (በግሪክ)
  4. የላዝሩስ ኒሻን ከኦስትርያ(ቪዬና)

የተሻለሟቸው የክብር አልባሳት

1) ጥቄር ካፓ ባለራስ ማዕርግ በሙካሽ የተሠራ፤

2) ቀይ ከፋይ ላይ ወርቅ የተጠለፈበት ካባ እንዲሁም በሙካሽ የተሰራ ቀሚስ

3) ከወርቅናየተሰራ የእጅ መስቀል

የእስራት ዘመንን በተመለከተ

የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወድቆ ደርግ ሲተካ ለስምንት ዓመታት በደርግ እስር ቤት ቢሰቃዩም ከገቡበት ዕለት ጀምሮ እስከ ወጡበት ጊዜ የፈጸሙትን ሐዋርያዊ ተልእኮ በእስር ቤት አብረዋቸው የነበሩ ሲናገሩ የሚያስገርም ነው ።

1/ ራሳቸውን አልተላጩም ነበር ።

2/ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን አላስነኩም ነበር ።

3/ እስረኞችን በጸሎት እና በስብከት ዘወትር ይረዱ ነበር ።

አቶ አበራ ጀንበሬ ስለ እስር ቤት በጻፉት መጽሐፍ እንደ ገለጹት አንድ ቀንስ እንዲያውም እስረኛው በዚያ ዕለት እንደሚፈታ ትንቢት ተናግረው ነበር ። ክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃምም “የሕይወቴ ትዝታ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 170 “ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ብቻ መጽሐፍ ቅዱስ አላስረክብም ፥ መነኩሴ በመሆኔ ከመነኩሴ በቀር ማንም ጸጉሬን አይላጭም በማለት ሲጸኑ ሌሎች ግን መጽሐፎቻቸውን ወደ ቤት ላኩ ፥ ጸጉራቸውን ተላጩ” ሲሉ መስክረዋል ።

እኒህ ብፁዕ አባት በእስር ቤት እንዳሉ ከጸሎት እና ከስብከት የሚተርፋቸውን ጊዜ የሚያውሉት መጽሐፍ በመድረስ ፣ ቋንቋዎችን በመማር ስለ ነበር ። ከግእዝ ፥ አማርኛ ፥ ግሪክኛ ፥ እንግሊዝኛ ተጨማሪ ሦስት ቋንቋዎችን አጥንተዋል ። (ዜና ሕይወቱ ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ (ገጽ 220-269 ይመልከቱ)

ከእስር ስለ መፈታታቸው

ከእስር እንደ ተፈቱም ወዲያው ሥራ ባያገኙም ቅሉ ሥራ ግን አልፈቱም ነበር ፣ በቤታቸው መጻሕፍትን እያዘጋጁ ፥ በእስር ቤት ሳሉ የጻፏቸውን መጻሕፍት ማሳተም ጀመሩ ። ኋላም የመንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን እንዲሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ተፈቅዶላቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲመድቧቸው ፥ ያንን የተጎሳቆለ ግቢ አሣምረው ፥ ተማሪዎቹን እና አስተማሪዎችን ሥርዓት አስይዘው ፥ የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ። በኮሌጁ ግቢ በሚገኘው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንም ደቀ መዛሙርቱ ተራ ገብተው አገልግሎቱን እንዲሳተፉ ጥረዋል ። የከፈሉት መሥዋዕትነት ግን ቀላል አልነበረም ። ሁኖም ሥርዓት አልበኞች ሲከሷቸው ሲወቅሷቸው ፥ ሁሉንም በጸጋ እየተቀበሉ ከተልእኳቸው ንቅንቅ አላሉም ነበር ። ከዚህም ወደ ኅትመት ድርጅት ሲዛወሩ ለዓመታት ባካበቱት የሥራ ልምድ በዚያች በተወሰነች ጊዜ ብዙ መንፈሳውያን መጻሕፍት እንዲታተሙ አድርገዋል ።

በጠቅላላ- በሀገር ውስጥ ዩኒቨርስቲውን ጨምሮ በብዙ ታላላቅ ድርጅቶች የቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል ። ሠርተውም ሆነ አሠርተው የማይደክሙ ፣ ሠርተውም ሆነ አሠርተው የማይረኩ የቤተ ክርስቲያን ችግር ካልተወገደ እንቅልፍ የማይወስዳቸው እጅግ በጣም አገር ወዳድ አባት ናቸው ። ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በትምህርት የሠለጠኑ ፥ በሥራ የተፈተኑ ቸር እና ቅን አባት ናቸው ። ትምህርትን የሚወድ ወጣት በጣም ይወዳሉ ያበረታታሉ ። ሰነፍ ሰው ደግሞ ሰብአዊነት እንኳ ያለው አይመስላቸውም ። ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ወዳጃቸው መንፈሳዊ ሥራቸው እና የዚያ ሥራ ተባባሪዎች ብቻ ናቸው ። ብዙ ወዳጆች ያሏቸውን ያህል ደግሞ መጠነኛ ጠላቶችም ነበሩአቸው ። የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓላማ የሚደግፉ ይወዷቸዋል ፣ ግለሰቦችን የሚደግፉ ይጠሏቸዋል ። ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሠሩት ሥራ ሲመዘን ግን መጠላት ቀርቶ መታማት የሚገባቸው አባት አልነበሩም ። ዕቅዳቸው ሰፊ ነውና ።

ስደትን በተመለከተ

በመጨረሻም ኢሕአዲግ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ በተፈጠረው ምስቅልቅል ፣ ሕጋዊው ፓትርያርክ ከሕግ ውጭ እንዳይነሡ ፣ ሲኖዶሱ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ተከትሎ ሥራውን እንዲያከናውን ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን እየጠቀሱ ጠንካራ ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል ። በኋላም ጠላቶቻቸው ጠላት ሲቀቧቸውና ቤተ ክርስቲያንም ሆነች አገራችን እንዳልነበሩ ሲሆኑ ዝም ብሎ ላለማየት ወስነው ከሚወዷት አገራቸውና ቤተ ክርስቲያናቸው ተለይተው በቀረው ዕድሜአቸው በስደት ያሉትን ምእመናን ለማገልገል ወስነው ለመሰደድ ተገድዋል ። እነሆም በስደት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ምእመናንን እያገለገሉ ፥ አብያተ ክርስቲያናትን ያደራጃሉ ፣ በስደት አገር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመሩት ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ሁነው አቋማቸውን አጠንክረው ላለፉት 20 ዓመታት አገልግለዋል ።

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ መጀምሪያ አሜሪካን አገር ሐምሌ 20 ቀን 1984 ዓ/ም ከቀኑ 6 ሰዓት አሜሪካ ኒውጀርሲ ኒውዋርክ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ፣ ቤተ ሰቦቻቸው እነ አቶ ተፈራ መላኩና ወይዘሮ አምሳለ አበጋዝ ከነቤተ ሰባቸው በክብር ተቀብለዋቸዋል። (ዜና/ሕ ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ገጽ 300-302 ይመልከቱ)፤

አሜሪካ ሲገቡ ሥራ የጀመሩት ኒውዮርክ ጽዮን ቅድስት ማርያምን ቤተ ክርስቲያንን በማቋቋም ነው ። በኒውዮርክና በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ የመጀመሪያው ወያኔ ጥቃት ነበረ ። ምክንያቱም አባ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን ገንጥለው ለብቻ ያቋቋሙት በዚያ ስለ ነበር ነው ።

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ከኢትዮጵያ እንደ ወጡ በዚያ አካባቢ የነበረውን ክርስቲያን ሕዝብ የራሱን ቤተ ክርስርቲያን እንዲያቋቁም ያደረጉ ሲሆን ፥ የድካማቸው ውጤትም አሁን ያለችው ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ናት ። እንዲሁም ለምን እንደ ተሰደዱ የሚገልጥ ከመንግሥት ለውጥ ጋር በተያያዘ በሀገራችን የተፈጠረውን ሁኔታ የሚገልጽ መጽሐፍ «የቋሚ ምስክርነት» በሚል ርእስ በ1995 ገጽ ጽፈው አሳተሙ ።

በኒውዮርክ ከዘመዶቻቸው ቤት ዐርፈው ከቆዩ በኋላ ለሐዋርያዊ ተልእኮ ወደ ካሊፎርኒያ አቅንተዋል ። ወደ ኦክላንድ ደበረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የአንድ ወዳጃቸውን ልጅ ክርስትና ሊያነሡ ተጋብዘው እንደ ሄዱ ። የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ሽማግሌ አባቶች ከዚያ እንዲኖሩ ስለ ጠየቁአቸው መካነ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን መንበረ ጵጵስናቸውን አድርገው በስደት በመላው ዓለም የሚኖረውን ሕዝብ ሲያገለግሉ ኑረዋል ።

ወደ በርክሊ ካሊፎርንያ በሄዱ በጥቂት ቀን ውስጥ ፥ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርቲያን ካህንና ጳጳስ በጥገኝነት ይገለገሉበት የነበረውን ቤተ ክርስቲያን ለአምልኮ እንዳይጠቀሙበት ከለከሉአቸው ። በዚህ ጊዜ እንደ አቡነ መልከ ጼዴቅ ያለ ቆራጥ አባት አስፈላጊ ነበር ። በአፋጣኝ ሕዝቡን በማስተባበር በዚያ ጊዜ በአሜሪካን አገር ከሎስ አንጀለስ የአሁኑ ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያንና ከዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቀጥሎ ሦስተኛ የራሱ ሕንጻ ያለው ቤተ ክርቲያን አድርገውታል ። ይህም የሆነው መንፈቅ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አስተባብረው የራሳቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አዲገዛ በማድረግ ነው ።

በዚህ ጊዜ አንድ የተከሠተ ዐቢይ ጉዳይ ነበር ። በዚያ ጊዜም ሆነ አሁን ሕዝቡ ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስድቲያን አስተውጽኦ ሲያደርግ የሚቆላመጥበት ማባበያ ያስፈልገው ነበር ፣ ይህን የተገነዘበው ቦርድ ገንዘበ ለማግኘት በዓቢይ ጾም አዝማሪ ቀጥሮ ፥ የጾም ምግብ እያበላ ፥ ጠንከር ያለ መጠጥ እያጠጣ ገንዘበ ለማሰባሰብ ይወስንና ለአቡነ መልከ ጼዴቅ በዐቢይ ጾም ዘፈን ይቻላል አይቻልም ? ብሎ ይጠይቃል ። ብፁነታቸውም የልባቸውን በልባቸው አድርገው ይቻላል እንጂ ለምን አይቻልም ይላሉ ። ቦርዱም ይህን ውሳኔ ከጳጳሱ በማግኘቱ ገርሞት ትኬቱ ይሸጣል ፤ ቀኑ ደርሰና ለመደሰት ሕዝብ አዳራሹን ይሞላዋል ፤ በፕሮግራሙ መሠረት እራት ይበላና ወደ ዘፈኑ ከመሄዱ በፊት አባታችን ይነሡና «ስለ መጣችሁ አመሰግናለሁ ፣ ግን ዛሬ የጠራናችሁ ልናዘፍናችሁ ሳይሆን ልናስለቅሳችሁ ስለ ሆነ ዘፋኙ የምታለቅስ ከሆን ምሾ ደርድር ፥ አለበለዚያ የአምልኮ ቦታ አጥተን እያዘን ነው አልን እንጂ ተደስተናል አልን እንዴ?» ብለው የተሰበሰበውን ሕዝብ የሚፈልጉትን ገንዘብ እንዲያወጣ ጠይቀው በዚያ ቀን ለቅድሚያ ክፍያ የሚበቃ ገንዘብ አስወጥተው ቤተ ክርስቲያናቸውን በዚያ መነሻነት ለመግዛት ችለዋል ።

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በየሄዱበት ስቴት ቤተ ክርስቲያንን ለማስገንባት ባላቸው ጽኑ እምነት ይህን ያህል ገንዘብ ካልሰጣችሁኝ መድረኳን አልለቅም በማለት እያስተባበሩ ሁሉንም አብያተ ክርስቲያናት ባለሕንጻ አድርገውታል ።

ከዚህ በኋላ አሁን ካሉት አምሳ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በመቶ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ ፥ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው ሕንጻ እንዲኖራቸው የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ አሻራ የሌለበት ቤተ ክርስቲያን ፈልጎ ማግኘት አዳጋች ነው ። በሁሉም ቦታና ጊዜ እየተገኙ ከአሜሪካ አስከ ሳውዝ አፍሪካ ፣ ከሳውዝ አፍሪካ እስከዩጋንዳ፣ ከዩጋንዳ አስክ አውስትራልያ፣ ከአውስትራሊያ አስከ ካናዳ ፣ ከካናዳ አስከ እወሮፓ ድረስ ሐዋርያዊና አባታዊ አግልግሎት አበርከተዋል ። በእነዚህ አገሮች ሁሉ በተገኙባቸው ጊዜያት ምእመናንን በማስተባበር ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የራሳቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እንዲኖራቸው ገንዘብ በማሰባሰብ ይረዷቸው ነበር። ብፁነታቸው ቤተ ክርስቲያን ቁመው ለቤተ ክርስቲያን በረከት የሆነ ሥራ ሣይሠሩ የወረዱበ ጊዜ አልነበረም ።

የአገር ጉዳይን በተመለከተ ። የወያኔ መንግሥት ፣ በውጭ አገር ተጽዕኖ ፈጣሬ ሰው ማነው ? ተብሎ ቢጠየቅ ቍጥር አንድ መልሱ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ናቸው ። ስደተኛው ማኅበረ ሰብ አሁን ባለበት ቅርጽና ይዘት ስለ ሀገሩ ክብርና አንድነት እንዲነሣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል ። አቡነ መልከ ጼዴቅ ለወያኔ ፖሊሲ የማይመቹ ሦስት ትልልቅ ማንነንቶች አሏቸው።

1ኛ ኦርቶዶክሳዊ ሊቅነት ከጠንካራ ማንነት ጋራ ። አሁን ባለንበት ደረጃ በግልጥ እንደሚታየው የወያኔ መንሥት እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚጠላው የለም ። ከዚህ አንጻር ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ደግሞ ይህንን ሐሳብ ያመከኑ ታላቅ ሰው ናቸው ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በማጉላትና በማጠናከር ረገድ የማይበገር መንፈሳዊና ኢትዮጵያዊ ማንነት ያላቸው ታላቅ አባት ስለ ሆኑ ፥ ለአሁኑ መንግሥት የሚመቹ ሁነው አልተገኙም ።

2ኛ ታሪክ አዋቂነት ከኢትዮጵያዊ ምንነት ጋር ። ወያኔ የሚጠላው ነገር የጠነከረ ታሪክን ከነክብሩ ያወቀ ሰው በማኅበረ ሰቡ መኖርን ነው ። አቡነ መለከ ጼዴቅ ታሪክ አዋቂ ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው የታሪክ መዝገብ ነበሩ ። ስለዚህም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ለመናድ ለቀረጸው የወያኔ ፖሊሲ ምቹ አልነበሩም ።

3ኛ በቤተ ክርስቲያን የመስፋፋት ብቃትና አባታዊ ተሰሚነት – ከፍ ብሎ እንደ ተጠቀሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መስፋፋት በተለይም በወያኔ ተቃራኒ በኩል ያላት ጥንካሬ ለኢትዮጵያ ህልውና ዘላቂነት አጠያያቂ ሁኖ አልተገኘም ። በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የዚህ ዋና ጉልላት ናቸው ። በሀገር ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን ልታደርግ የሚገባትን ከመጠን ያለፈ ተጋድሎ አድርገዋል ። በኤርትራ መገንጠል ፥ የባሕር ወደብ በማጣታችን ፣ በሀገር ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ምን እንደሚሆን ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በሚገባ አሳስበዋል ፥ አስጠንቅቀዋል ።

ቅዱስ ሲኖዶስ በስደት ሥራውን እንዲጀምር በማድረግ ይህ አሁን አርባ ስምንተኛውን ጉባኤ ሲያካሂድ ብፁነታቸው መሥራችም ፥ ሥራ አስኪያጅም ፥ ጸሐፊም በመሆን እዚህ ያደረሱት እርሳቸው ናቸው ። ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ሲባል አቡነ መልከ ጼዴቅ ናቸው እስኪባል ድረስ አባትነታቸው ጎልቶ ይታይ ነበር።

ብፁነታቸው ለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱአቸው መጻሕፍት

1/ ዜና ሕይወቱ ለቅዱስ ጳውሎስ ፣

2/ ስለ እግዚአብሔር መኖር ፣

3/ ትምህርተ አበ ነፍስ ፣

4/ ክብረ ድንግል ፣

5/ ድንግልናዊ ሕይወት ፣

6/ የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ፣

7/ እንጸልይ ፣

8/ ማኅበራዊ ኑሮ በኢትዮጵያ ፣

9/ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት ፣

10/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ትምህርት ፣

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት በደርግ ከመታሰራቸው በፊት የታተሙ ናቸው ፤ ለሰባት ዓመት በእስር ላይ ሳሉ የጻፏቸውና ፥ ከተፈቱ በኋላ የታተሙት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው ። በእስርቤት ሳሉ 10 መጻሕፍትን አዘጋጅተው ነበር ፤ ከእስር ቤት እንደ ወጡ አምስቱን አሳትመዋቸዋል ። እነሱም የሚከተሉት ናቸው ፦

1/ ትምህርተ ክርስትና አንደኛ መጽሐፍ ፣

2/ አባታችን ሆይ ፣

3/ የስብከት ዘዴ ፣

4/ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ፣

5/ ትምህርተ ክርስትና 2ኛ መጽሐፍ ፣

በዚህ መሠረት ከመሰደዳቸው በፊት 15 መጻሕፍትን ጽፈው አሳትመው ነበር ። ከዚህ በታች ደግሞ ደርግ ወድቆ ወያኔ ከገባ በኋላ በስደት አሜርካን አገር ያሳተሙአቸው ናቸው ።

6/ የቋሚ ምስክርነት ፣

7/ The Teaching of Ethiopian Orthodox Church ፣

8/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶክትሪን ፣

9/ የኢትዮጳያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴ ፣

10/ ዜና ሕይወቱ ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ – በጥያቄና በመልስ መልክ በሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው አቀነባባሪነት የተዘጋጀ ።

ለኅትመት የተዘጋጁ-

11/ መጽሐፍ ቅዱሳችን ፣

12/ የመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ ። በተራ ቍጥር 20 እና 21 የሚገኙት ሥራቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ ናቸው ።

11/ ቤዛዊተ ኵሉ ዓለም /ነገረ ማርያም/

12/ ግእዝ ከነአገባቡ ፣

13/ የቤተ ክርርስቲያን ታሪክ ፣

14/ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ። በድሮ ታይፕ የተመታ ፣

15/ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ። በድሮ ታይፕ ተጽፎአል ፣

16/ ታቦተ ኪዳን በኢትዮጵያ ፣

17/ የንስሐ ጥሪ ፣

18/ ፍቅረ እግዚአብሔር ፣

19/ ስለ ቡዳና ዛር ጥናት ። ከተ ቍ 22-27 የሚገኙት በሽት ተባዝተው እንዲሁም በእጅ ጽሑፍ የሚገኙ ናቸው ።

ከዚህ በተጨማሪ ከሠላሳ ባላይ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን በቅድስት ሥላሴ ሕትመትና ሥርጭት ክፍል በኩል አሳትመዋል።

ሊቁ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በሊቃውንት ቅኔ በጥቂቱ

ቅኔ 1ኛ – መወድስ

ዝሁራን ደቂቅ እም ዘርዓ ዓማፂ ፣

እለ በዓመፃ ተወልዱ ኢይከይድዋ በአእጋር ፣

ለእንተ ሐነጻ እግዚእ ሀገረ ጳጳሳት ፍቅር ፣

ወኢርእየ አሰረ ፍኖታ ዓይነ ሞት ንስር ፣

እስመ ለካህናት ሀገሮሙ ፣

እምነ ፀሐይ ትበርህ ወትትሌዓል እም አድባር ፣

ለዓለም ወለዓለመ ዓለም

ውኅዘሂ ወተክዕወ በአልባሰ ክብር ፣

መዓዛ ቅዱሳን ዜናሆሙ በክነፈ ነፋስ ዘየሐውር ፣

እስከ ጽንፈ ምድር አድማስ ወእስከ ጽንፈ አድማስ ምድር ፣

ኢኀልቀ ተቀዲሆ ተስፋ ምእመናን ማየ ባሕር ።

2ኛ ኵልክሙ መወድስ ቅኔ

መልከ ጼዴቅ ሊቅ ሊቀ ሥልጣናት ፣

መልከ ጼዴቅ አብ ወሃብተ ማርያም እም ፣

መልከ ጼዴቅ በትር ምርጉዘ ኵሉ ድኩም ፣

ምዕራፍ ወምስማከ ጾታ መልከ ጼዴቅ ኦም ፣

ወእንዘ ሥላሴ ይተረጎም ፣

አጋእዝተ ዓለም ዘጾረ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ።

ለዓለም ወለዓለመ ዓለም

መኑሂ ዘፈረየ ፍሬ በረከት ጥዑም ፣

አኮኑ መልከ ጼዴቅ ጉንደ ሐረገ ወይን ዘገዳም ፣

ወይቤ መምህር ዘትማልም ወዮም ፣

ኅብስተ ግብርክሙ ኢትበሉ ለጌሰም ፣

አምጣነ ጌሰም ትሔሊ ለዘዚአሃ ተቅዋም ።

ኅብስተ ግብርክሙ ኢትበሉ ለጌሰም ።

3ኛ መወድስ ቅኔ

ዝሁራን ደቂቅ እስከ ማዕዜኑ ፣

ከንቶ ነገረ ታከብዱ ልበክሙ ፣

ወለምንት ተሐሱ ዘታፈቅሩ ቀዲሙ ፣

እግዚአብሔር በጻድቁ ፣

አእምሩ ከመ ተሰብሐ ወተአውቀ ስሙ ፣

እስመ ለጻድቃን ምስካዮሙ

ለሊሁ የአምር እግዚአብሔር ፍኖቶሙ ።

ለዓለም ወለዓለመ ዓለም

ለምንትሂ አንገለጉ አሕዛበ ከብድ ኵሎሙ ፣

እስመ ዘይነብር በሰማይ ታሪክ ይስሕቆሙ ፣

ወዘመን ይሳለቅ በላዕሌሆሙ ሶበ ይነቦሙ ፣

በመዓቱ ወበመዓቱ የሀውኮሙ ።

በሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው ለ80ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው ሲከበር የተበረከተ በ1996 ዓም (በ2003 እአአ)

አዘጋጅ መጋቤ ሐዲስ ልዑለቃል አካሉ ዓለሙ።

LEAVE A REPLY