ሠላም ለናንተ ይሁን!
እነሆ ለዘመናት እየተነሳ ሲወድቅ የኖረው የለውጥ ማዕበል መርከቡን ከነመልህቁ መሪውን ከነኮምፓሱ ካገኘ ዘጠኝ ወራት ተቆጠሩ። አብያዊው መንግሥት! ሲመተ አብይ ዓመት ሊሆነው ሶስት ወራት ብቻ። አጃኢብ ነው!
የስንትና ስንት ዓመታቱን ጉድ በዘጠኝ ወር አየን? በዘጠኝ ወር በሆድ ያደገ ቅሪት ሰው ሆኖ ይወለዳል። የፈጣሪ ተዓምር። እኛም በፈጣሪ ተዓምር በዘጠኝ ወራት ሩቅ ተጉዘናል። ሰው መሆን ጀምረናል። ሙሉዕ ለመሆን ግና ረዥምና ጥቅጥቅ ጥሻ ማለፍ፤ እልፍ ደረጃዎችም መውጣት ይቀረናል።
ከድቅድቁ የጨለማው ዘመን ገዢ ከህወሃት አገዛዝ ነፃ ወጥተናል። በነፃነት መኖር ግን አልጀመርንም። ስጋታችን ብዙ ሠላማችንም ስስ ነውና። የጨለማው ዘመን አጋፋሪዎች ወር አልፎ ወር ሲተካ ምሽጋቸውን እያጠናከሩና አይነኬ እየመሰሉ መጥተዋል። የጥፋት ድርጊቶቻቸውን መዘርዘር ደግሞ ታክቶናል። ፍትህን ስንቀርበው እየራቀን ይመስላል።
የህወሃቱ የመቀሌው መንግሥት ከአብያዊው መንግሥት ጋር የአይጥና ድመት ጨዋታውን አድርቶታል። ዶ/ር ደብረፅዮንኢህአዴግ <ድብብቆሽ> ላይ ነው ይለናል፤ ትግራይ ለማዕከላዊው መንግሥት እንደማትታዘዝ ደጋግሞነግሮናል። ምፀት ነው መመፃደቅ? በዚያኛው ሰፈር ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ያ ሁሉ የኦሮምያ ህዝብ ከነፈረሱ ወጥቶ የተቀበለው ኦነግ ወለጋና ቦረና መሽጎ ይፋዊ ጦርነት ከፍቷል። መሪዎቹም አዲስ አበባ ላይ እየፏለሉ አብያዊውን መንግሥት እንደራደር ይሉታል። ምን ይሉት መመፃደቅ ነው? ጎፈሬያም ጦረኞቻቸው ግን ሀገርና ህዝብ ያሸብራሉ፤ ባንክ ይዘርፋሉ፤ ነውረኛ ድርጊት በህዝብ ላይ ይፈፅማሉ፤ ስማቸው ግን ነፃ አውጪ ነው!! ተፅዕኖ ፈጣሪ ቦታ የያዙ አስመሳይ የለውጥ ደጋፊ ኦነጋውያን በርካቶች ይመስላሉ።
ደግሞ በዚያ ሰሞን ዶ/ር አብይና ዶ/ር ደብረፅዮን የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ሲከፈት እጅ ለእጅ ተቆላልፈው ሲታዩ ተጠፋፍተው የተገናኙ ወንድማማቾች ይመስሉ ነበር። የዶ/ር አብይን እጅ ጨብጦ የያዘው የህወሃቱ መሪ ግን ሽሬ ላይ መከላከያ ከነመሳሪያው እንዳይንቀሳቀስ ሠላማዊ ህዝብ አሰልፏል። ከህወሃት ዕውቅናና ይሁንታ ውጪ አንዳች በትግራይ ምድር አይደረግማና! በዛኑ ጊዜ ደግሞ በህወሃት የተደራጁ የትግራይ ተወላጆች ዶ/ር አብይንና አቶ ገዱን <ሌባ– ሌባ> እያሉ ሲሳደቡ መተማ ላይ አይተናል። ጥቂት ቀን አሳልፎ ደግሞ መከላከያን ያገቱት የሽሬ ወጣቶች<ተሳስተው> ነበር ብሎ የህወሃቱ መሪ መግለጫ ሰጥቷል። ምን ይሉት ማስመሰል እንደምንስ ያለ መመፃደቅ ነው? የትግራይ ክልል ከፌዴራል ጋር ጡንቻውን የሚለካካ ይመስላል። ይህን የተደጋገመ ድራማ መመልከት ሰልችቶናል! ምርርም እያለን ነው!
ስለ ጌታቸው አሰፋና ስለግብረበላዎቹ የምንሰማው ሁሉ የሰለቸ ሙዚቃ እየሆነብን ነው። የለውጡ ዕድሜ ሲገፋ <ኮትገልባጩ> አስመሳዩ በመበራከቱ በሲቪሉና በወታደሩ፤ በየመስሪያ ቤቱና በየማህበራዊ ህይወቱ፤ በሃይማኖቱና በፖለቲካው፤ በሥነ ጥበብና በሙዚቃው ማንን ከማን ለመለየት እየቸገረ ነው። ከለውጡ ማዕበል ጋር ነበርኩበት አለሁበትም ባዩ በዝቷልና።
በይቅርታው ጣራ በደቡብ ኢትዮጵያ የዘመነ ህወሃት ቆመጥ ነበሩት ሳይቀሩ አምባሳደርነት ተሹመዋል። እኛም ጉድ ብለናል። ለውጡ በአስመሳዮችና ተመፃዳቂዎች እንዳይወረር ያሰጋል። አስመሳዩ እስኪጠራ፤ ተመፃዳቂው እስኪገታ ስንት ጊዜ ይፈጅ ይሆን?!
ኢህአዴግን ታግለን ኢህአዴግን ደግፈናልና አሁን ኢዮባዊ ትዕግሥት ያስፈልገናል። አብያዊውን መንግሥት በንቃትና በምክንያት መደገፍና ማራመድ!! በዛም ሆነ በዚህ ግን ኢትዮጵያ ከገባችበት የታሪክ አጣብቂኝ ለመውጣትና ሲነጋ ለማየት ከአብያዊው መንግሥት ውጪ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ከቶም ሌላ ምርጫ የላትም!! ትዕግስትና ፅናቱን ይስጠን እንጂ!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይታደግ!
ጥር 2011 ዓ/ም (ጃንዋሪ 2019)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com