መግቢያ
በጥር ወር 1995 ዓ.ም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን በጊዜው በህውሃት የበላይነት የሚመራው የኢህአዴግ አገዛዝ እንዳመለከተና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቅድመ-ሁኔታዎችን ለሟሟላት ሽር-ጉድ ይል እንደነበር ይታወቃል። በጊዜው ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ አባል ብትሆን የምትጎዳው ነገር የለም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል በሚል የህውሃትን ጥድፊያ ይቃወሙ በነበሩ ኃይሎችና አባል መሆንን በሚፈልጉ መሀከል የጦፈ ክርክር እንዳካሄዱ ይታወቃል። በጊዜው ከኢንፎርሜሽን እጥረት የተነሳ ክርክሩ የቱን ያህል በሳይንስና በቴዎሪ እንዲሁም በማስረጃ ጥናት ላይ የተመረኮዘ እንደነበር ለመገመትና፣ የየትኛው ወገን አቀራረብ አሳማኝ መሆኑን ሙሉ በሙሉ እንደዚህ ነው ብሎ ለመናገር ቢያዳግትም በተለይም ከተቃዋሚው በኩል የቀረበው ትችት የሚደገፍ እንደነበር ማረጋገጥ ይቻላል።
ይህ ጸሀፊ ከዚህ ቀደም የነፃ ገበያን አስታኮ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አማካይነት በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲንና ያመጣውን ጠንቅ በተለያዩ በአገራችን ይታተሙ በነበሩ እንደ ጦቢያና አውራምባ ታይምስ መጽሄቶችና፣ እንዲሁም በተለያዩ ውጭ አገር ባሉ ድህረ-ገጾች ላይ ለህትመትና ለንባብ አቅርቦ መነጋገሪያ እንዲሆን እንዳደረገ የሚታወስ ነገር ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በጊዜው በዓለም ባንክና በዓለም የገንዘብ ድርጅትና፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ግፊት በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ባንኮች እንዲሽጡ ሲደረግ ኢትዮጵያ ባለችበት እጅግ ወደ ኋላ የቀረ የኢኮኖሚ ሁኔታ ይህ አካሄድ እንደማያዋጣና ለኢኮኖሚው ዕድገትም የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ለማሳየት ሞክሯል። በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለን የህዝብ ሀብት ወደ ግል ማዘዋወር በተለይም የውጭ ኢንቬስተሮችን ስለሚጠቅምና፣ የውጭ ኢንቬስተሮችም ሁሉንም ነገር ከትርፍ አንጻር ብቻ ስለሚያሰሉ፣ በተለይም ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በርካሽ ወለድ ብድር ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚዳፈን አመልክቶ ነበር። ከዚህ በመነሳት የአገር ውስጥ ገበያ እንዲዳብርና የቴክኖሎጂ ምጥቀትም እንዲታይ ከተፈለገ የግዴታ ሰፋ ያለ የስራ-ክፍፍል ስትራቴጂ መቀየስና በተለያዩ መስኮች መሀከል መተሳሰር እንዲፈጠርና ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ እንዲከፈት መንግስት ልዩ ዐይነት ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል እንዳለበት አመልክቷል። ይህ በእንደዚህ እንዳለ ከብዙ ድርድር በኋላ በጊዜው በነበረው የኢህአዴግ አገዛዝና በዓለም የንግድ ድርጅት መሀከል ድርድሩ አንድ መቋጠሪያ ሳያገኝ ይቆማል።
ሰሞኑን ደግሞ ሪፖርተር ጋዜጣ እ.አ.አ በ24.10.2018 ባወጣው ዕትሙ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የተቋረጠው ድርድር እንደገና እንዲጀመር የዓለም ንግድ ድርጅትን እንደጠየቀ አስፍሯል። አሁን አገሪቱ ባለችበት ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታና፣ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ የእርስ በርስ ግጭትና ግድያ እንዲሁም አፈና ባየለበት ጊዜ መንግስት የተቋረጠው ድርድር እንዲጀመር ለምን እንደጠየቀ ግራ የሚያጋባ ነው። ከዚህም በላይ ባለፉት 27 ዓመታት በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአገራችንን ኢኮኖሚ ከማሳደግና ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ ከመክፈት ይልቅ አጠቃላይ ድህነት እንዲስፋፋ ማድረጉ በግልጽ እየታወቀ አሁንም የግዴታ በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው ወደፊት መግፋት የምንችለው ብሎ አቋም መውሰድ እጅግ ግራ የሚያጋባ ነው። ከዚህም በላይ በአዲስ አበባና በአጠቃላይ በአገሪቱ ምድር ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በሚታይበትና፣ በየቤቱ ድብቅ ረሃብ በሰፈነበት አገር የግዴታ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ካልሆን ማለቱ አገዛዙ በእርግጥም የህዝብ አለኝታ ሊሆን የሚችል ነው ወይ? ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ተገደናል። አንዳንድ የውጭ አገር ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ከፖሊቲካ አንፃር ተስፋ የሚሰጥ ሁኔታ ቢፈጥርም በኢኮኖሚ ላይ የጠራ አቋም እስከሌለው ድረስ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚወድቅ እየነገሩን ነው።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝብ የህውሃትን አገዛዝ እንዲወገድ ሲጠይቅ ጥያቄው የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎችንም እንዳዘለና፣ ህውሃት ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ የድህነቱና የመዋረድ ዘመኑ እንደሚቀጥል ሙሉ ዕምነቱ ነበር። ስለሆነም በአንድነት ከዳር እስከዳር ተነስቶ የዲሞክራሲና የነፃነት እያለ በመጮህ ህውሃትን አሽቀንጥሮ ሲጥለው ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎች ይመለሱልኛል ብሎ በማመን ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ሲነሳ ህውሃት 27 ዓመታት በሙሉ ተግባራዊ ሲያደርግ የነበረውንና አገሪቱ እንድትዘረፍና በዚያውም ህዝባችን እንዲደኸይ ያደረገው በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ተዘጋጅቶ የመጣው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ከስር መሰረቱ እንዲወገድለት በማመንና በሌላ አማራጭና ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲተካለት በግልጽ በመጠየቁ ነው። ለዚህም ነው ለዶ/ር አቢይ ያልተቆጠበ ድጋፉን የሰጠው።
ከዚህ በመነሳት ይህ ጸሀፊ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና እንዲሁም ሰፋ ባለ የማኑፋክቱር እንቅስቃሴ ላይ የሚደገፍ አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሰረት በአገራችን ምድር ሊጣል እንደማይችል ያመልክታል። ለአንባቢው ግልጽ እንዲሆንና በቀላሉ እንዲረዳው ጸሀፊው በመጀመሪያ ደረጃ የዓለም ንግድ ድርጅትን ታሪካዊ አመጣጥና ሚናውን በማሳየት ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ብትሆን በተለይም የእርሻው መስክ እንደሚጎዳና አገራችንም የበለጠ ትርምስንና ድህነትን እንደምትጎናጸፍ ለማመልከት ይሞክራል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለች ገና በድህነት የምትማቅቅ አገር የእንደዚህ ዐይነት ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት ራሷን በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ነፃ ማውጣትና አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ መቆም እንዳለባት መታለፍ የማይገባው መሰረታዊ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ህግ መሆኑን ለማረጋገጥ ይሞክራል። ካለዚህ መሰረትና ሰፋ ያለ በቴክኖሎጂ አማካይነትና ውብ ውብ በሆኑ ከተማዎችና ሰፋ ባለ የስራ-ክፍፍል የማይገለጽ ህብረተሰብ በቀላሉ ከውጭ በሚመጡ ርካሽ ዕቃዎች የአገሪቱ የማምረት ኃይል እንደሚኮላሽና አገራችንም በቀላሉ ልትወጣው የማትችለው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደምትወድቅ ከጽሁፉ መረዳት ይቻላል። ስለሆነም በአገራችን ምድር ዘላቂነት ያለው ሰላምና ብልጽግና እንዲሰፍን ከተፈለገ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረገና የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን ሳይሆን፣ የግዴታ ስርዓት ያለው እርስ በእርሱ የተሳሰረ ትናንሽ፣ማዕከለኛና አልፎ አልፎም ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን መትከል አስፈላጊ እንደሆነ ለማመልክት ይሞክራል። በመጀመሪያ ግን የዓለም ንግድ ድርጅትን ታሪካዊ አመጣት እንመልከት።
የዓለም ንግድ ድርጅት ታሪካዊ አመጣጥና ሚናው !
ዛሬ የዓለም ንግድ ድርጅት(WTO) በመባል የሚታወቀው የተመሰረተው እ.አ.አ በ1948 ዓ.ም ሲሆን፣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ብቅ ያለውን የኃይል አሰላለፍ የሚያንጸባርቅ ነው። እንደሚታወቀው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍጻሜ ጀምሮ የተከሰተው አዲስ የኃይል አሰላለፍ የዓለምን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ተቅዋማት በአዲስ መልክ ማዘጋጀት እንዳለበት አመነ። ይህ በአሜሪካ የሚመራው አዲስ የኃይል አሰላለፍ ከዚህ ቀደም የነበረውንና እ.አ.አ ከ1929እስከ 1945 ዓ.ም ድረስ እየተዳከመ የመጣውን የዓለም አቀፍ የስራ-ክፍፍልና(International Division of Labor) የንግድ ልውውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ንግድን ለማስፋፋትና የተወሰነ ሀብትን ከበለጸጉ አገሮች በዕድገታቸው ኋላ ወደቀሩ አገሮች ማስተላለፍ ያስፈልጋል በሚለው ሽፋን ስር በአዲስ መልክ መደራጀት እንዳለበት ተገነዘበ። በዚህም አማካይነት የበላይነቱን(Hegemony) ማስፈን እንደሚችልና የየአገሮችን የዕድገት አቅጣጫ ለመወሰን እንዲችል የነፃ ንግድን አስፈላጊነት አሰመረ።
በመጀመሪያ እ.አ.አ በ1944 ዓ.ም ሁለቱ እህትማማች ድርጅቶች፣ የዓለም ባንክና(WB) የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) አሜሪካን አገር በብሬተን ውድስ ከተማ ሲመሰረቱ፣ እ.አ.አ በ1948 አጠቃላይ የንግድና የታሪፍ ስምምነት(General Agreement on Trade and Tarif)፣ እ.አ.አ ከ1994 ጀምሮ ደግሞ የዓለም ንግድ ድርጅት(WTO) ተብሎ በመጠራት የሚታወቀው በመጀመሪያ 23 አገሮች አባል የሆኑበት ድርጅት ይመሰረታል። በአሁኑ ወቅት የንግድ ድርጅቱ አባላት ቁጥር 164 ሲሆኑ፣ 23 አገሮች ደግሞ በተመልካችነት የተቀመጡ ናቸው። በጊዜው ከደቡቡ ዓለም አስራአንድ የሚሆኑ በዕድገታቸው ወደፊት ያልገፉ አገሮች አባል ይሆናሉ። በእነዚህ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በተመሰረቱት ድርጅቶች መሀከል ግልጽ የሆነ የስራ-ክፍፍል ሲኖር፣ በተጨማሪም ሶስቱም ድርጅቶች የሚመሩበት የርዕዮተ-ዓለምና የቲዎሪ መሰረት በእነ አዳም ስሚዝ፣ ከ1880 ደግሞ በኒዎ-ክላሲካል፣ ከ1938 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ኒዎ-ሊበራሊዝም በመባል በሚታወቀው በነፃ ንግድና ገበያ ስም በዳበረው „ቲዎሪና“ ርዕዮተ-ዓለም መሰረት ነው። የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ መመሪያዎች ደግሞ እ.አ.አ ከ1950 ጀምሮ በረቀቀ መልክ በመዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአገሩ ዩኒቨርሲቲዎች እንደመጽሀፍ ቅዱስ መማሪያ የሆኑና፣ አማራጭና ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ይመስል ሁሉም አገሮች አሜን ብለው እንዲቀበሉት የተደረጉ፣ ከዕውነተኛ ዕውቀት ይልቅ ርዕዮተ-ዓለምን የሚያስተጋቡ ናቸው። በዚህ መልክ በቅኝ-ግዛት ዘመን ሰፍኖ የነበረው የስራ ክፍፍል ከአዲሱ የዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር በመቀናጀት የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮች የጥሬ-ሀብትና፣ በተለይም በኢንዱስትሪ አገሮች ሊበቅሉ የማይችሉ የእርሻ ምርት ውጤቶች አቅራቢ ሆነው እንዲቀሩ የተቀነባበር ሴራ ነው ማለት ይቻላል። በቲዎሪው መሰረትም እያንዳንዱ አገር በዓለም ንግድ ውስጥ ሊሳተፍ የሚችለው ባለው ሀብት ላይ ብቻ አትኩሮ ካደረገ ብቻ ነው።
የነገሮችን አቀማመጥ ይበልጥ ለመረዳት በሶስቱ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች መሀከል ያለውን የስራ-ክፍፍል መጥቀሱ ጠቃሚ ይመስለኛል። ዓለም ባንክ ሲቋቋም ዋናው ዓላማው በመንገድ ስራና ትናንሽ ፕሮጀክቶች ላይ ሲያተኩር፣ የገንዘብና የቴክኒካል ድጋፍ ይሰጥ የነበረው ወደ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ዕድገት ማምጣት ላይ አልነበረም ዋናው አትኩሮው። ይህም ማለት፣ የድርጁቱ ዓላማ እያንዳንዱ አገር በጸና የኢኮኖሚ መሰረት ላይ እንዲገነባ በማድረግ ወደ ማህበረሰብና ወደ ህብረተሰብ እንዲሽጋገር ማድረግ አልነበረም። በዓለም ባንክ ፖሊሲ መሰረት ወደሶስተኛው ዓለም የሚፈሱት ርዳታዎች ያለቀላቸው የቴክኒካልና „የሃሳብ ርዳታዎች“ እንጂ እዚያው በየአገሮች ውስጥ በሳይንሳዊ ምርምር ከብዙ ልምድና ሙከራ በኋላ ቴክኖሎጂዎችና ዕውቀት እንዲዳብሩና ተከታታይነት እንዲኖራቸው ማድረግ አልነበረም፤ አይደለምም። ይህን ዐይነቱን ድጋፍ ወይም ርዳታ ለማግኘት ደግሞ ርዳታውን የሚቀበለው አገር በዓለም ባንኩ የተደነገገውን የአሰራር ስልትና መመሪያ መከተል አለበት። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ርዳታው ርዳታ የሚል ሽፋን ቢሰጠውም በብድር መልክ የሚሰጥና፣ እያንዳንዱን ርዳታ ተቀባይ አገር ወደ እጅ አዙር ቅኝ- አገዛዝነት የሚጥልና ኢኮኖሚውን የሚያቀጭጭ ነው። የሳይንስና የቲክኖሎጂ ዕድገት ፀር ነው ማለት ነው። ይህም ማለት ርዳታውን ወይም ብድሩን የሚያገኘው አገር ዓለም ገበያ ላይ በሚቀርቡ የእርሻ ምርት ውጤቶችና የጥሬ-ሀብቶች ላይ ብቻ መረባረብ አለበት። የመጨረሻ መጨረሻ ብድሩ በዶላር መከፈል ሳለለበት ነው። ይህ አንደኛው ሲሆን፣ ከዚህም ባሻገር የእርሻንና የጥሬ-ሀብትን ብቻ በዓለም ገበያ ላይ የሚያቀርብ አገር ባልተስተካከለ የንግድ ልውውጥ(Unequal Exchange) አማካይነት የግዴታ ሀብት እንዲወጣና የኢንዱስትሪ አገሮች የባስውኑ በሀብት እንዲበለጽጉ ያደርጋል። በዚህ መልክ በሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ያልተሰተካከለ ዕድገትና ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ ያዘነበለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሲስፋፋ፣ በዚያው መጠንም ድህነትና ህብረተሰብአዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ያደርጋል። ዛሬ የዓለምን ኢኮኖሚ መዛባትና የካፒታሊስት አገሮችን የበላይነትና ደንጋጊነት በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በተለይም በአፍሪካ ምድር ከሰላሳና አርባ ዐመታት በላይ እዚህና እዚያ የሚካሄደውን ጦርነትና፣ በጎሳና በሃይማኖት ተሳቦ በየጊዜው የሚነሳውን ግጭት ስንመለከት ዓለም ባንክ አገሮችን በማስገደድ እንዲከተሉት በሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የቱን ያህል ላለመረጋጋት የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዳበረከተና እንደሚያበረክት መረዳቱ ከባድ አይሆንም። ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥና በየአካባቢው አለመረጋጋትና ጦርነት መከሰት በየአገሮች ውስጥ ኢኮኖሚው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ በመመስረት ሰፋ ያለ ገበያና የተሳሰረ ማህበረሰብ ለመገንባት ባለመቻሉ ነው።
የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን(IMF) የስራ ድርሻ ስንመለከት ጊዜያዊ አጠቃላይ የውጭ ንግድ ሚዛን ሲዛባ ይህንን ለማረም ወይም ለማስተካከል ለየአገሮች የአጭር ጊዜ ብድር መስጠት ነው። ይሁንና ግን ድርጅቱ ከዚህ በማለፍና የራሱን ህግ በመጻፍ በየአገሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት እሱ በሚፈልገው መልክ ፖሊሲዎች እንዲወጡ በማድረግ በመንግስታት ላይ ግፊት ያደርጋል። ይህም ማለት ብድር ተቀባዩ አገር ሁለ-ገብና ፍቱን፣ እንዱሁም ብሄራዊ ሀብት እንዲዳብር የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲዘጋጅ ወይም እንዲጻፍና ተግባራዊ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ እንዲያውም የባሰውኑ ኢኮኖሚው እንዲሽመደመድ፣ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰትና፣ እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ተዳክመው የስራ-አጥ ቁጥር እንዲበዛ የሚያደርግ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲደረግ በመንግስታት ላይ ከፍተኛ ጫና ያደርጋል። በዚህ መልክ በነፃ ገበያ ስም የገንዘብን ዋጋ መቀነስና የውጭ ገበያውን ልቅ እስከማድረግ ድረስ፣ ለልዩ ልዩ ማህበራዊ መስኮች የሚወጣውን የመንግስት በጀት እንዲቀነስ ማድረግ በመሰረቱ የየአገሩ ኢኮኖሚ በጸና መሰረት ላይ እንዲቆም ማድረግ ሳይሆን ከብድር ተቀባዩ አገር በወለድና በወለድ ወለድ(Compound Interest rate) አማካይነት ሀብት ወደ ኢንዱስትሪ አገሮች የሚፈስበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
በዚህ መልክ ሁለቱ እህትማማች ድርጅቶች በነፃ ገበያ ስም የሚያራምዱት ፖሊሲ በመሰረቱ ነፃ ሳይሆን ደካማ አገሮችን በዚያው ቀጭጨው እንዲቀሩ የሚያደርግ ነው። እያንዳንዱ አገርና መንግስታት በራሳቸው ኃይልና የውስጥ ሀብት በመተማመንና ይህንን ሁለ-ገብ በሆነ መልክ በማንቀሳቀስ ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርገጠኝነት ድህነትን እየቀረፉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን የተሳሰረና የጠነከረ ማህበረሰብና ህብረ-ብሄር(Nation-State) እንዳይገነቡ ማድረግ ነው። በነፃ ንግድና በገበያ እኮኖሚ ስም አሳቦ የየአገሮችን ገበያ የውጭ ሸቀጣ ሸቀጦች ማራገፊያ በማድረግ ከውስጥ የማምረት ኃይላቸውን ማዳከም ነው። በዚህ መልክ የየአገሩ ነጋዴ ወይም በማደግ ላይ የሚገኝ ከበርቴ ሰፋ ያለ ሀብትን ከሚፈጥርና የስራ-መስክን ከሚከፍት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከመረባረብ ይልቅ በተለይም በውጭ ንግድና በአገልግሎት መስክ ላይ እንዲሳተፍ ይገደዳል። የየአገሩ መንግስታትም ይህንን ዐይነቱን በመሰረቱ አገር አፍራሽና ሀብትን አውዳሚ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አሜን ብለው በመቀበል ሳይወዱ በግድ ድህነትና ህብረተሰብአዊ መዝረክረክ እንዲፈጠሩ በማድረግ የራሳቸውን አስተዋፅዖ ያበረክታሉ። ከተማዎችና መንደሮች በስርዓት እንዳይገነቡና የስራ-ክፍፍልም እንዳይዳብር ሳያውቁት ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ። በተለይም የተገለጸለትና በደንብ የተደራጀ የሲቪል ማህበረሰብ እንቅስቃሴ በሌለበት አገር መንግስታት በዓለም አቀፍ ተቋማት እየተመከሩና እነሱን እያመለኩ ታሪክና ባህል እንዲወድሙ ያደርጋሉ።
ወደ ዛሬው አጠቃላይ የነፃ-ንግድ ልውውጥና በአባል አገሮች መሀከል ገበያውን ሙሉ በሙሉ ልቅ ማድረግ ያስፈልጋል ወደሚለው መደምደሚያ ላይ ከመደረሱ በፊት የመጀመሪያው የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድርና ወደ ስምምነት መድረስ ያተኮረው በኢንዱስትሪ ምርት ውጤቶች ላይ ሲሆን፣ ይህምከውጭ ወደ ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለውን ከፍተኛ ቀረጥ መቀነስ ነበር። ድርጅቱ ከተቋቋመ እ.አ.አ እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ የኬኒዲ ድርድር ወይም ዙሪያ(Kennedy Round) በመባል በሚታወቀው ድርድርና ስምምነት ላይ ድርድሩ አብዛኛውን ጊዜ የሚካሄደው በራሳቸው በኢንዱስትሪ አገሮች መሀከል ሲሆን፣ ታሪፍን በመቀነስ ውጤት ላይ ተደርሷል። እ.አ.አ እስከ 1970 ዓ.ም ድረስ በአብዛኛዎቹ ምርቶች ላይ የታሪፍ ቅነሳ ሲጠናቀቅ፣ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው ልዩ ዓይነት የኢኮኖሚ ቀውስና የዘይት ዋጋ መናር ድርድሩን አጠቃላይና የጠለቀ እንዲሆን አደረገው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለይም ታሪፍ-ነክ ባልሆኑና የንግድ ልውውጥን ያደናቅፋሉ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ መደራደርና ወደ አንዳች ስምምነት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑ ታመነበት። እነዚህም የየመንግስታትን የውስጥ ፖሊሲ የሚመለከቱ ሲሆኑ፣ ለኢንዱስትሪዎች የሚሰጠውን ድጎማ፣ ወደ ውጭ በሚላኩ ዕቃዎች ላይ የሚደረገውን ልዩ ድጋፍና ብደር(Export Subsidy and Credits)፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ ንግድን ያደናቅፋሉ ተብለው የሚገመቱ ህጎችና ስርዓቶችን ማስወገድ ነበር። ይህ ድርድር ከረጅም ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1979 ዓ.ም ስምምነት ይደረስበታል። እ.አ.አ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ ሩዋጋይ ዙሪያ(Uruguay Round) የተደረገው ድርድርና ስምምነት የዓለም ንግድ ድርጅቱን ሙሉ በሙሉ እራሱን የቻለ ተቋም ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሻ ምርትንና ምግብን የሚያጠቃልልና የነፃ ንግድን በአባል አገሮች መሀከል ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ነው። ስር እየሰደደ የመጣው የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ቀውስና የኢንዱስትሪ አገሮች መንግስታት በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች(Multinational Companies) ቁጥጥር ስር መውደቅና የነሱን ጥቅም ማስጠበቅ አስፈላጊነቱ እየጎላ ሲመጣ የዓለም የንግድ ድርጅት በአዲስ መልክ መዋቀሩና አጠቃላይ ነገሮችን መያዙ አስፈላጊ እየሆነ መጣ።
ተጫባጭ ሁኔታዎች እንደሚያረጋግጡት፣ በተለይም የኢንዱስትሪ አገሮች መንግስታት ቀስ በቀስ ከአጠቃላይ የመንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ መላቀቅና የትላልቅ ኩባንያዎችን፣ የባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የበለጠ ትርፋማና ሀብት አካባች ለማድረግ፣ እንዲሁም ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥና ከሌላው ተሽሎ ለመገኘት ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። በዚህም መሰረት ወደ ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ግፊትና ተሰሚነት እየጎላ በመምጣት መንግስታትን መፈናፈኛ አሳጥቷቸዋል ማለት ይቻላል። ይህ ሁኔታ በዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቱ ላይ በማንፀባረቅ፣ በተለይም ጥቂት የእርሻ ዘርንና ምግብን የሚቆጣጠሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የወደፊት ሩጫና የበላይነትን መቀዳጀት ድል የተነሳ በንግድ ድርጅቱ አባል አገሮችና ወደፊትም አባል ለመሆን በሚሹ አገሮች መሀከል የውጭ ንግድን ለመቆጣጠር የተጣሉ ዕገዳዎች(Protectionist Measures) ሙሉ በሙሉ ማንሳት እንደሚያስፈልግ ስምምነት ተደረሰበት። ማንኛውም አገር የየራሱን ህገ-መንግስትና ሌሎች ህጎችን በመጣስና የህዝቡን የወደፊት ዕድል በማጨለም የዓለም ንግድ ድርጅትንና የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ድንጋጌ ሳያወላውል በተግባር መመንዘር አለበት። ይህንን በሚመለከት በተዘጋ ቤት ውስጥ የዓለም ንግድ ድርጅቱና የዓለምን ዘርና ምግብ የሚቆጣጠሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መሀከል 170 የሚሆኑአከራካሪ ነጥቦችና ህጎች ላይ ድርድር ተካሂዷል። በዚህም መሰረት ማንኛውም አባል አገር የዓለም ንግድ ድርጅት ስምምነትን የሚጥስ እርምጃ ከወሰደ ከፍተኛ ቅጣት ይደርስበታል። ኢትዮጵያም አንድ ቀን አባል ከሆነች የዚህ ዐይነቱ እርምጃ ፅዋ ቀማሽ ትሆናለች። አይ አልቀበልም፣ ለቅቄ እወጣለሁ ብትል ድግሞ የሚመጣውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግፊት በፍጹም ልትቋቋም አትችልም።
ይህ ዐይነቱ ስምምነት ከመደረሱና ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት በኢንዱስትሪ መስክ በተደረገው ስምምነት ሰራተኞችና ተጠሪዎቻቸው ከፍተኛ ግፊት ተደርጎባቸዋል። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የስራ መስኮች ወድመዋል። ተጨባጭ ደሞዝ በብዙ እጅ ቀንሷል። አነስተኛ ደሞዝንና አመቺ የማምረቻ ሁኔታዎችን ተገን በማድረግ ከኢንዱስትሪ አገሮች እየተነቀሉ ወደ አንዳንድ የባሪያ ደሞዝ የሚስተካከል ክፍያ የሚከፈልባቸው የሶስተኛው ዓለም አገሮች የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎች በኢንዱስትሪ አገሮች ውስጥ የስራ-አጥ ቁጥሩ እንዲጨምር ከማድረግ አልፎ የሰራተኛው የመግዛት ኃይል እየተዳከመና የመንግስታቱን በጀት እያዛባው መጥቷል። በሌላ ወገን ግን በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር ያሉትና በሶስተኛው ዓለም አገሮች የተተከሉት ኢንዱስትሪዎች ለየአገሮች ዕውነተኛ ዕድገት አለማምጣታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ ደሞዙ ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ የመግዛት ኃይሉ በጣም ደካማ ነው። ሰራተኛው በሚያገኘው ደሞዝ ራሱንና ቤተሰቡን ለማስተዳደርና ልጆቹንም ወደ ትምህርትቤት የማይልክበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ሰራተኛው ለባርነት ስራ የተፈጠረ ይመስል በነፃ ንግድና በነፃ ገበያ ሽፋን ስር ዕውነተኛ ነፃነቱ እንዲገፈፍ ተደርጓል። ይህን የመሰለ ሁኔታ ነው አባል በሆኑ ደካማ አገሮች የሚታየው አስከፊ ሁኔታ። ከዚህ ዐይነቱ አንድን አገርና ህዝብ ከዕድገት ይልቅ በዚያው ባሉበት ቀጭጨው እንዲቀሩ ከሚያደርግ ሁኔታ ስንነሳ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶችና በንግዱ መስክ በተሰማራውና ተደማጭነት ባለው የንግድ ድርጅቱ አባል ካልሆን ኢኮኖሚያችን ሊያድግ አይችልም የሚለው አባባል በቲዎሪና በተግባር የሚረጋገጥ አይደለም። አንድ አገር ልታድግ የምትችለው በንግድ አማካይነት ሳይሆን በተወሳሰበ የስራ ክፍፍል፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ በተደገፈ የምርት ክንዋኔ ብቻ ነው።
ይህ ከላይ የተዘረዘረው ጉዳይ የኢንዱስትሪ መስኩን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፣ በንግድ ድርጅቱና በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በተፈጠረው ያልተቀደሰ ጋብቻ ምክንያት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ገበሬዎች ኑሮአቸው ተናግቷል። እራሳቸውንም የገደሉ አሉ። ስለሆነም የእርሻው መስክ ከፍተኛ ቀውስ ደርሶበታል። ከትውልድ ትውልድ ከሚፈለገው ሰዓት በላይ እየሰራ በመሰረቱ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ሙያውን እንደባህል ያደረገውና ተፈጥሮን እየተንከባከበ ጤናማ የእርሻ ምርት ለተጠቃሚው ህዝብ የሚያቀርበው ትናንሽ የገበሬ የህብረተሰብ ክፍል መስኩን እንዲዘጋና መንደሩን እየለቀቀ እንዲሰደድ ተገዷል። በአዲሱ የንግድ ስምምነት መሰረት በአብዛኛዎቹ የኢንዱስትሪ አገሮችም ውስጥ ማህበራዊ መዛባት ሊከሰት ችሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን የቀሩት ገበሬዎች በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር በመውደቅ ሶስት የዓለምን የዘር ባንክ በሚቆጣጠሩ ኩባንያዎች ስር ፍዳቸውን እንዲያዩ ተገደዋል። በሌላ አነጋገር ማንኛውም ገበሬ ከትውልድ ትውልድ በሙከራና በልምድ ያዳቀለውን የእህል ዘር የመዝራት ዕድል የለውም። ከብድር ጀምሮ እስከዘርና የኬሚካል ማዳበሪያዎች፣ እንዲሁም የተባይ ማጥፊያዎች ድረስ በባንኮችና በኩባንያዎች ቁጥጥር ስር የወደቀ በመሆኑ ገበሬዎች በቀጥታ የሚሰሩት የኩባንያዎችንና የባንኮችን ሀብት ለማካበት ብቻ ነው። በሌላ ወገን ግን በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የወደቁት ገበሬዎች ከድህነት ለመላቀቅና አዲስ ህይወት የመኖር ዕድል በፍጹም የላቸውም። የነፃ ገበያ ውድድርና ይህ ዐይነቱ የተወሳሰበ ጥገኝነት ብዙ ሰዓትን መስራትንና ራስን ከሚገባው በላይ ማስጨነቅን ስለሚጠይቅ ነው።
ይሁንና የነፃ ንግድን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ቢደረስም፣ በአንድ በኩል በአሜሪካና በብዛት የእርሻ ምርትን ለዓለም ገበያ በሚያቀርቡት የኬይርነስ ተወካይ አገሮች(Cairns-Groups) ማለትም፣ አርጀንቲናና አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ብራዚል፣ ኒው ዘላንድ፣ እሩጓዋይ፣ ቺሌ፣ ኮሎምቢያ፣ ፓራግዋይ፣ ማሌዢያ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታይላንዳና ፊሊፒን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በአውሮፓ አንድነት አገሮች መሀከል የጦፈ ክርክር ይካሄዳል።የውጭውን ንግድ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ፣ ወደ ውስጥና ወደ ውጭ የሚደረገውን ድጎማ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ፣ ለንዑስ መስኮች የሚደረገውን ክፍያና ማስተካከያ ማቆም የሚሉት ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ የአውሮፓው አንድነት አሻፈረኝ ሲል፣ አሜሪካ በጥንቃቄ „እየተቀበለው“ መጥቷል። ስምምነቱ ከተደረሰ ጀምሮ በተለይም እንደ ብራዚል ያሉት አገሮች የስኳርን ምርት በዓለም ገበያ ላይ በማራገፍ የተሻለ ዕድል ቢያጋጥማቸውም፣ እንደ ኡራጓዋይ የመሳሰሉት አገሮች ደግሞ አባል ሆነውም በስምምነቱ መሰረት የተሻለ የገበያ ዕድልና ወደ ውስጥ ደግሞ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና ብሄራዊ ሀብትን ሊያዳብሩና ህዝቦቻቸውም የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ በተለያዩ ዘዴዎች የእርሻ ምርቶቻቸውን ወደ ኢንዱስትሪ አገሮች የመላክ፣ በተለይም ደግሞ ወደ አውሮፓ አንድነት ገበያ ላይ የማስገባቱ ዕድል እየጠበባቸው መጥቷል። በሌላ አነጋገር እ.አ.አ በ1994 ዓ.ም የእርሻ ምርትንና ምግብን በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ካለገደብ ለማራገፍ የተደረሰበት ስምምነት ይበልጥ የጠቀመው የአውሮፓውን አንድነት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ብራዚል በስኳር ምርት ላይ ብቻ በማትኮሯና ለምግብ የሚሆነው እርሻ አትኩሮ ስላልተሰጠው በጊዜው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ተከስቶ ስለነበር ወደ አርባ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በምግብ እጥረት ይሰቃይ ነበር። በስኳር ምርት የተነሳና መሬት በጥቂት ኦሊጋርኪዎች በመያዙ ሊያርሱ የሚችሉ ትናንሽ ገበሬዎች የማረስ ዕድል በፍጹም አላገኙም። በጊዜው ስልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዚደንት ሉላ ከዚህ ሀቅ በመነሳት ከተመረጡ በኋላ እያንዳንዱ ብራዚሊያዊ ቢያንስ በቀን ሶስት ጊዜ በልቶ እንዲውል አደርጋለሁ ብለው የገቡት ቃል እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ሊሳካላቸው ችለዋል። ይኸውም ለማህበራዊ መስክ የሚወጣውን በጅት ከፍ በማድረጋቸው ብቻ ነው።
ከላይ በተጠቀሱት አገሮችና በአውሮፓ አንድነት መሀከል የሚደረገው ድርድር እራሱን የነፃ ገበያ አራምዳለሁ የሚለውን የአውሮፓ አንድነትን ቅራኔ ውስጥ ከቶታል። የአውሮፓ አንድነት ለገበሬው በየዓመቱ ወደ ስድሳ ቢሊዮን ኦይሮ የሚጠጋ በድጎማ መልክ ይሰጣል። የኢንዱስትሪ አገሮች በአጠቃላይ ለገበሬዎቻቸው ወደ ሶስት መቶ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጎማ ያደርጋሉ። ይህንን ድጎማ ሙሉ በሙሉ ማንሳት ማለት ከፍተኛ የማህበራዊና የፖለቲካ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደመፍጠር ስለሚቆጠር እነዚህ አገሮች ደፍረው ይህንን ዐይነት እርምጃ በፍጹም አይወስዱም። በተለይም ኢኮኖሚው እንደሰንሰለት የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን ድጎማ የሚቀነስ ወይም እንዳለ የሚነሳ ከሆነ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል የሚል ፍርሃት አለ። ይህ ጉዳይ በአንድ በኩል በምርት ብዛት የተወጠረውን የአውሮፓ አንድነት፣ በሌላ ወገን ደግሞ እንደፈለገው በሶስተኛው ዓለም አገሮች ገበያ ላይ ምርቱን ለማራገፍ የሚያደርገውን ሩጫ ለማመቻቸት ያለውን ቀዳዳ ለመጠቀም ያለመቻል ክፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ከቶታል። ይህ ጭንቀት 10 አዲስ አባል አገሮች የአውሮፓን አንድነት ከተቀላቀሉ በኋላ ልዩ መልክ እየያዘ መጥቷል። አዲሶቹ አባል አገሮች ገበያቸውን ክፍት ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን እነሱም የብስኩቱ ተካፋይ እንደመሆናቸው መጠን የእርሻ ምርቶቻቸውን የመጀመሪያው አባል አገሮች መላክ አለባቸው። ሌላ አዲስ የታቀደ ቅራኔ መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በደንብ ያልተደራጀ የእርሻ መስክ ያላቸውና የዓለም ንግድ ድርጅት እንግባ እያሉ የሚፍጨረጨሩ አገሮች፣ የአውሮፓው አንድነት፣ የአሜሪካና ሌሎች የድርጅቱ አባል አገሮች ገበያ ላይ ምርቶቻቸውን ለመሸጥ ያላቸው ዕድል በጣም የጠበበ ነው። በተለይም የአውሮፓ አንድነት ሰበብ እየፈለገ ገበያውን ማጥበቡ የማይቀር ጉዳይ ነው። ከነዚህ ውስጥ የጥራት ጉዳይና ከምርቶች ጋር ተያይዘው ይመጣሉ ተብለው የሚገመቱ በሽታዎች እንደምክንያት ሊቀርቡ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው። የአውሮፓ አንድነት ገበያውን ለመዝጋት ሲል ብቻ ሳይሆን ከጤንነት አንፃርም ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በደንብ ይቆጣጠራል። በሌላ ወገን ግን ወደፊት እየሰፋ የሚመጣው የንግድ ልውውጥ፣ ማለትም የአገልግሎትና የጤንነት መስኩን ልቅ ማድረግ፣ የውሃና የትምህርት መስኩን በሚመለከት ለዓለም አቀፍ ተዋንያኖች ክፍት ማድረግ፣ … ወዘተ. እጅግ አስፈላጊ መሆናቸው በንግድ ድርጅቱም ሆነ በአውሮፓ አንድነት ታምኖበታል። በየአገሩ ገብተን እንደፈለግን እንፈትፍት የሚለው ዐይን ያወጣ ውትወታ በኢኮኖሚያቸው ደካማ የሆኑ አገሮችን በጣም አስጨንቋቸዋል። ወደፊት አምባገነን የሆነ ዓለም አቀፋዊ መንግስት ሊመሰረት ነው የሚል ፍርሃት ትችታዊ አመለካከት ባለቸው የሲቪል ማህበራት እንቅስቃሴዎች ዘንድ ሰፍኗል። ወደፊት ድርድሩና ስምምነቱ ሁሉንም መስክ የሚያጠቃልል በመሆኑ በተለይም የደካማ አገሮች ብሄራዊ-ነፃነት በከፍተኛ ደረጃ መገፈፉ የማይቀር ጉዳይ ነው።
የአውሮፓው አንድነት በእንደዚህ ዐይነት ቅራኔ ተወጥሮ እያለ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የአፍሪካን፣ የካሪቢክና የፓሲፊክ አገሮችን፣ ማለትም የሰባሰባት አገሮችን ቅንጅት የንግድና የዕድገት ፈለግ በአዲስ መልክ ለማደራጀትና ይበልጥ በኢኮኖሚያቸው ውስጥ ጣልቃ ለመግባት የማያወጣውና የማያወርደው ነገር የለም። በዚህም ምክንያት የአውሮፓው አንድነት ከእነዚህ አካፔ(AKP) አገሮች ጋር የኢኮኖሚ ግኑኝነት ስምምነት አስፈላጊ ነው በሚል ሽፋን ስር ከዓለም ንግድ ድርጅቱ ደንቦች ጋር በሚጣጣም መልክ ጠለቅ ያለ ድርድር እያደረገ ነው። በአውሮፓው አንድነትና በእነዚህ ሰባሰባት አገሮች መሀከል ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ1975 ዓ. ም ሎሜ ላይ፣ የሎሜ ስምምነት ተብሎ በሚጠራ ስምምነት ላይ ይደረሳል። በዚህ ስምምነት መሰረት እነዚህ ሰባሰባት አገሮች በአውሮፓው አንድነት ገበያ ላይ ዕቃቸውን ሊሸጡ የሚችሉበት ሁኔታ „ይመቻችላቸዋል።“ እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም ኮቶኑ(Cotonou) በሚባለው የቤኒን ዋና ከተማ ላይ ሰባሰባቱ አገሮችና የአውሮፓው አንድነት አዲስ የንግድ ግንኙነት ስምምነት ይፈራረማሉ። ኮቶኑ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሰባሰባቱ አገሮች ከዓለም የንግድ ድርጅት ህግ ጋር የሚስማማ የንግድ ውል መቀበል አለባቸው። ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገቡ ንግድን የሚያደናቅፉ ማንኛውም ደንቦች ቀስ በቀስ እንዳሉ መወገድ አለባቸው። ድርድሩ እ.አ.አ እስከ 2007 ዓ.ም ዓ.ም ድረስ መጠናቀቅ ሲኖርበት፣ ከ2000 እስከ 2020 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ስምምነቱ ቀስ በቀስ ተግባራዊ ይሆናል። የአውሮፓ አንድነት አካፔ ከሚባሉት አገሮች ጋር ያደረገው ድርድር ልዩና ከዚህ ቀደም ወደ አንድ አቅጣጫ ያዘነበለ፣ በሌላ አነጋገር የሰባሰባት አገሮችን ጥቅም ያስቀድም የነበረውን ውል ያሰፋ ይመስል እራሱ የበለጠ ጥቅም የሚያገኝበትን ሁኔታ ያመቻቸ ነው። በዚህም መሰረት የአውሮፓው አንድነት በእነዚህ ስምምነት በተደረሰባቸው አገሮች ውስጥ ሰርጎ በመግባት ገበያቸውን የመቆጣጠርና የየአገሮችን የማምረት ኃይል ሊያዳክም እንደሚችል ቀደም ብለው የወጡ ጥናቶች ያመለክታሉ። በእራሱ በአውሮፓው ኮሚሽን የተጠናቀረው ጥናት እንደሚያረጋግጠው፣ ስምምነቱ ከተደረሰና ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ሰባሰባቱ አገሮች ከአውሮፓ አንድነት ምርት ጋር በፍጹም ለመወዳደር እንደማይችሉና የኢኮኖሚያቸውን መዳከም እንደሚያፋጥነው ነው። በሌላ ወግን ግን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲሉ የበለጠ በውጭው ዘርፍ ላይ እንደሚያተኩሩና በዚህም ምክንያት የውስጡ ገበያ እንደሚዳከም ጥናቱ ያመለክታል። ከዚህ ስንነሳ እንደዚህ ያለው ጥናት እያለና በአጠቃላይ ሲታይ በውጭው ንግድ ላይ ማትኮር አደገኛነቱ እየታወቀ አሁን ደግሞ ከስድስት ዐመት የድርድሩ መቋረጥ በኋላ እንደገና መጀመር አለበት ተብሎ ለምን ቅስቀሳ እንደሚደረግ ግልጽ አይደለም።
በአጠቃላይ ሲታይ ያለፈው ሰላሳና አርባ ዐመታት ልምድ እንደሚያረጋግጠው ኢኮኖሚያቸውን ይበልጥ በጥሬ-ሀብትና በእርሻ ምርት ላይ እንዲመረኮዝ ያደረጉ አገሮች የውጭ ንግድ ሚዛናቸው እየተሻሻለ የመጣ ሳይሆን እያዘቀዘቀ እንደመጣ እንመለከታለን። በተለይም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የዓለም የገንዘብ ድርጅትን የአንጀት አጥብቅ ፖሊሲ በመከተላቸው በአንድ በኩል ወደ ውስጥ የማምረት ኃይላቸው ሲዳከም፣ በሌላ ወገን ደግሞ በዕዳ እንደተበተቡና የውጭ ንግዳቸውም የባሰውኑ እየተበላሸ እንደመጣ እናያለን። ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ውስጥ ያለው አስከፊ የኢኮኖሚ ሁኔታ አፍጦ አግጦ በሚታይበት ወቅትና፣ አብዛኛው ህዝብ በዋጋ መናርና በስራ እጦት በሚንገሸገሽበት ጊዜ የግዴታ ከዓለም የንግድ ድርጅቱ ጋር መደራደር አለብን ማለት ምን ውጤት ላይ ለመድረስ ነው? ይህ ብቻ ሳይሆን የአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች በዚህ ዐይነቱ ስምምነት ሊቀረፉ ይችላሉ ወይ? ስምምነት ላይ ቢደረስስ በዚህ ዐይነቱ የንግድ ልውውጥ ጠንካራ ህብረ-ብሄር መገንባት ይቻላል ወይ? እነዚህን የመሳሰሉትንና ሌሎች ለአንድ አገር እንደ ባህላዊ አገር ለመገንባትና ተከታታይነት እንዲኖረው በሚያደርጉ ነገሮች ላይ መወያየቱና መከራከሩ እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚም ይመስለኛል።
ከዚህ ሁኔታ በመነሳት የአገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታና በዓለም ገበያ ላይ ልታቀርብ የምትችለውን ምርት በመዳሰስ፣ በዚህ መልክ አገራችን አጠቃላይና አስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገት ታመጣ ትችል ወይም አትችል እንደሆን ለመተንተን እሞክራለሁ።
የአገራችን የኢኮኖሚ ሁኔታ የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን ያመቻል ወይ ?
አንድ አገር አንድ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት፣ 1ኛ) አገዛዙ የአገሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያ አወቃቀር በሚገባ ማወቅ አለበት። 2ኛ) በምን ዐይነት ቲዎሪ ወይም የአሰራር ስልት የኢኮኖሚውን አወቃቀር እንደሚተነትን ቢያንስ ሊከታተልና ሊገባው ለሚችለው የህብረተሰብ ክፍል ማቅረብ አለበት። ይህም ማለት አገሪቱ የምትገኝበትን የቴክኖሎጂ፣ የሳይንስና የማህበረሰብ የዕድገት ደረጃ ማሳየት አስፈላጊ ነው። 3ኛ) ለሰፊው ህዝብ አስተማማኝ የሆነ ዕድገት ከሌለ ለምን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት የለም ብሎ መመርመር አለበት። ስለሆነም ለሁለ-ገብ ዕድገት ማነቆ የሆኑ ነገሮችን ደረጃ በደረጃ እየተነተነ ማሰቀመጥ ይኖርበታል። 4ኛ) ለምን የአንድ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት አባል መሆን እንደሚያስፈልግ ወደ ወጭ በመውጣት ለህዝቡ ግልጽ ማድረግ አለበት። በምሁሩ ዘንድም ክርክር እንዲደረግ መጋበዝ አለበት። ይህም ማለት አንድን አገር የሚመለከት ትልቅ ፕሮጀክት በተዘጋ ቤት መጠናቀቅ የለበትም። 5ኛ) የዓለምን ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል። በተለይም የግሎባል ካፒታሊዝምን ታሪካዊ አመጣጥና የየአገሮችን የጥሬ-ሀብት የመቆጣጠር ስትራቴጂ በሚገባ ማወቅ አስፈላጊ ነው። 6ኛ) እስከዛሬ ከተደረጉት ስምምነቶች ሌሎች አገሮች የቀሰሙትን ልምድና ያገኙትን ጥቅም ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። 7ኛ) እንደ ኢትዮጵያ ያለች የተዘበራረቀ ኢኮኖሚ ያላት አገር የዚህ ዐይነቱ ድርጅት አባል ብትሆን ምን ጥቅም ታገኛለች? ብሎ ሰፋ ያለ የቲዎሪ፣ የሳይንስና ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማጥናት ያስፈልጋል። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ልትቀዳጅ ትችላለች ወይ? ሰፋፊና የሚያማምሩ ከተማዎችን፣ የባቡር ሃዲዶችን ገንብታ ጠቅላላው ህዝብ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል ወይ? ብሎ አገዛዙ በአሉት ተቋማት አማካይነት መገምገምና ጥቅሙንና ጉዳቱን ማማዛዘን ይኖርበታል። ከዚህም ባሻገር ይህ ዐይነቱ ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነትና የድርጅቱ አባል መሆን ለህብረ-ብሄርና ለጠንካራ ህብረተሰብ መመስረት ሊያገለግል ይችላል ወይ? ወይስ ህብረተሰቡን የባሰውኑ ሊያዘበራርቀው ይችላል ወይ? ብሎ ጥናት ማካሄድ አስፈላጊ ይመስለኛል። 8ኛ) ከዚህም በላይ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶች ያላቸውና ጥቅምም የሚያገኙና የሚጎዱ እንደመኖራቸው መጠን ክሪቲካል አመለካካት ካላቸው የሚቀርቡትን ማደመጥ ያስፈልጋል። ይህ ከመሆኑ በፊት ዝም ብሎ የሚገባ ስምምነት ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ እንደምናየው አስቀያሚ ሁኔታ በአገራችንም ሊከሰት ይችላል። ችግሮች ከተከሰቱና ከተደራረቡ በኋላ እነሱን ለማረም በጣም አስቸጋሪ ስለሚሆን አንዳች ስምምነት ላይ ከመደረሱ በፊት በቂ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል።
በግልጽ እንደሚታወቀው በአገራችን ምድር የኒዎ-ሊበራል አመለካከት ስለተስፋፋ የአገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታ በሌላ ዐይነት የቲዎሪ መሳሪያ ትንተና ቢሰጥ በቀላሉ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ አይችልም። የኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም ደግሞ ስለምርት ግኑኝነት፣ ስለቴክኖሎጂዎች የዕድገት ደረጃ፣ ስለውስጥ ገበያ መኖርና በምን ዐይነትስ ህግ እንደሚገዛ፣ ስለገንዘብ ሚናና ገንዘብስ ወደ ካፒታል ሊለወጥ ይችላል ወይ? የሚሉትን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ፅንሰ-ሃሳቦች ግንዛቤ ውስጥ ስለማያስገባ የአገራችንን የኢኮኖሚ አወቃቀር በሌላ የቲዎሪ መሳሪያ በሚገባ ለማስረዳት እጅግ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ሁላችንም በአንድ ዐይነት አስተሳሰብ ወይም ርዕዮተ-ዓለም ስለሰለጠን ግራ ልንጋባ እንችላለን። ለማንኛውም አጠቃላዩን የኢኮኖሚ ሁኔታ በሶስት መልክ ከፋፍለን ብንመረምረው የአገራችን ኢኮኖሚ በምን ዐይነት የዕድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።
1ኛ) የኢንዱስትሪ መስኩን ስንመለከት አብዛኛው ኢንዱስትሪ ቀላል ኢንዱስትሪ የሚባለው ነው። በዚህ መስክ ውስጥ በብዛት የሚመረቱት ምርቶች ለተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል የሚሆኑ እንደምግብ ነክ ነገሮች፣ ቀዝቃዛና የአልክሆል መጠጦች፣ የጨርቃጨርቅ ውጤቶችና ጫማ ናቸው። ቀላል የሜታለርጂና የሲሚንቶ ፋብሪካዎችም እንዳሉ ግልጽ ነው። ይሁንና ግን አገሪቱ ስትራቴጅክ የሚባሉ ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ የብረታብረት ኢንዱስትሪና የማኑፋክቱር ወይም የማሽን ኢንዱስትሪዎች የላትም። ከዚህም በላይ ኃይልን ሊያመርቱ የሚችሉና ልዩ ልዩ የእሌክትሮኒክስ አምራች ኢንዱስትሪዎች የላትም። በዚህም ምክንያት የተነሳ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብሄራዊ ባህርይ ያለው ሳይሆን የተዝረከረከና ለመባዛት ወይም ሊስፋፋ የሚችል አይደለም። በተለይም አንድ አገር የማሽን ኢንዱስትሪ ከሌላት እንደ ባቡር ሃዲድና ባቡር የመሳሰሉትን ለአንድ አገር ዕድገት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ምርቶችን ልታመርት አትችልም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች መሀከል የስራ-ክፍፍልና ውስጣዊ ግኑኝነት(Linkages) የለም።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን ይህ ዐይነቱ ውስጣዊ ይዘቱ በጣም ደካማ የሆነ የኢንዱስትሪ መስክ ከውጭ በሚመጡ ተመሳሳይ ምርቶች ሊዳከም ይችላል። የምርት ክንውን ከቀዘቀዘ ደግሞ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች የተወሰነውን የሰራተኛ ኃይል ለመቀነስ ይገደዳሉ። ይህ በራሱ ደግሞ ከስራው በተባረረው ሰራተኛና በቤተሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውስ ሊደርስበት ይችላል። የሰራ-አጥ አበል በሌለበት እንደኛ ባለ አገር ከስራው የተባረረው ሰራተኛ ወደ ድህነት ዓለም መገፍተሩ የማይቀር ጉዳይ ነው።
2ኛ) የእርሻውን መስክ ስንመለከት ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝባችን ከእጅ ወደ አፍ በሚመረት የአስተራረስ ዘዴ ላይ የሚመካ ነው። አብዛኛው ገበሬ የመሬቱን ምርታማናት ለማሳደግ የሚያስችሉት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን አይጠቀምም። የመግዛት ኃይሉ እጅግ ደካማ ከመሆኑ የተነሳ አዳዲስ የማረሻ መሳሪዎችን በመግዛት ስራውን በማቃለል ከፍተኛ ምርት ሊያገኝ አይችልም። ስለሆነም የኢትዮጵያ እርሻ ሳይንሳዊ ባህርይ የሌለው ነው ማለት ይቻላል። ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ስንመለከት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በጥቂት የእርሻ ምርቶች ላይ የሚመካ ሲሆን፣ የቡና ምርት ስድሳ በመቶው የሚሆነውን ይይዛል።
የአገሪቱ ገበያ ለውጭ የእርሻ ምርት ውጤት ልቅ ከሆነ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳው ገበሬው ነው። ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአውሮፓና የአሜሪካ ገበሬዎች ከፍተኛ የመንግስት ድጎማ ይደረግላቸዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ምግብ በአጠቃላይ በየአገሮች ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ ሲላክ በጣም ርካሽ ነው። የአገራችን ገበሬ በድጎማ ከሚመረተው የአውሮፓና የአሜሪካ ምርት ጋር ስለማይወዳደር በ90ዎች መጨረሻ ላይ እንዳየነው ገበሬው ከፍተኛ ጉዳት ይደርስበታል። በሌላው ወገን ደግሞ ምግብ-ነክ ወዳልሆኑ እንደ ጨአት በመሳሰሉት የዕፅ ተከላ ላይ ሊሰማራ ይችላል። ገሚሱ ደግሞ ወደ ከተማ በመሰደድ በስራ እጦት ይሰቃያል።
ከዚህ ባሻገር ከውጭ የሚመጡ የእርሻ ምርት ውጤቶችና የተለያዩ የምግብ ዐይነቶች ለጤንነት ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎችንና ሆርሞኖችን ያዘሉ ናቸው። ይህም ማለት ባለፉት 27 ዐመታት ከነፃ ገበያና ንግድ ጋር ተያይዘው የገቡ የምግብ ዐይነቶች ያደረሱት የጤንነት ቀውስ እየተስፋፋና ሰፊውን ህዝብ እያዳረሰው ሊመጣ ይችላል። ካለምክንያት አይደለም በተለይም ባለፉት 20 ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ምድር የደም ግፊት በሽታ፣ የስኳርና የኩላሊት፣ እንዲሁም የነቀርሳ በሽታ የተስፋፉትና ወጣቱን ሁሉ ሳይቀር ለሞት የዳረጉት።
3ኛ) የአገልግሎት መስኩን ስንመለከት በጣም የተዝረከረከና ከኢንዱስትሪዎች ጋር የተያያዘ አይደለም። በገበያ ውስጥ የሚሽከረከሩ ምርቶች አብዛኛዎች ከውጭ የሚመጡ ናቸው። ከዚህ ውጭ የአገሪቱን ገበያ የሚቆጣጠረው ኢንፎርማል መስክ እየተባለ የሚጠራው የተሰበጣጠረና እርስ በእርሱ ያልተያያዘ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መስክ ነው። ስለሆነም ከውጭ የሚመጣው ዕቃና ገበያውን ያጣበበው በከፍተኛ ደረጃ የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ያዛባና፣ የፈጠራ ስራ እንዳይኖር ያገደ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ የአገራችንን ኢኮኖሚ ሁኔታ ስንመለከት ለጠንካራ ማሀበረሰብና ለህብረ-ብሄር ምስረታ የሚያገለግል አይደለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በህዝቡ ዘንድ በምሁር እንቅስቃሴ የሚገለጽ ውስጣዊ ግኑኝነት( Organic Relationship) የለም። የምርት ኃይሎች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ሰፋ ያለ በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ሊዳብር አልቻለም። ይህም ማለት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበረሰብ፣ በባህልና በኢኮሎጂ የነቃ ወይም የአገራችን ሁኔታ አንገብግቦት ይህንን በሊትሬቸር፣ በድራማና በካባሬት የሚገልጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ፍጹም የለም ማለት ይቻላል። በዚህም የተነሳ አገራችንና ህዝባችን ከውጭ በሚመጣ ማንኛውም ነገር እየተጠቁ ነው።
ከዚህ በአጭሩ ከተገለጸው ሁኔታ ስንነሳ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ዕድል ቢያጋጥማት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ ልትገነባ በፍጹም አትችልም። እንደሜክሲኮ፣ አርጀንቲናና ብራዚል፣ እንዲሁም በተቀሩት የማዕከለኛውና የላቲን አሜሪካ አገሮች የሚታዩት የህብረተሰብ መዝረክረክና ቀውሶች በአገራችንም ምድር ሊከሰቱ ይችላሉ። በተለይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከዛሬ 26 ዓመት ጀምሮ በአገራችን ምድር የተከሰተውን የማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውስ ስንመለክት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ያለውን ሁኔታ ከማባባስ በስተቀር ጤናማ ህብረተሰብ እንዲመሰረት በፍጹም አያግዝም። እንደምናየው ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ሊሸሽ ሲል በአጋጣሚዎች የሚያዘው የውጭ አገሮች ከረንሲዎችና በብዛት ሽጉጦች መያዛቸው የሚያረጋግጠው ልቅ የሆነ ስርዓት የመጨረሻ መጨረሻ የአገርን እሴት የሚበጣጠስና ሰላማዊ ዜጋን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ነው። ስለሆነም ኦሊጋሪኪ የሆኑ ኃይሎች በመነሳትና የራሳቸውን የታጠቀ ኃይል በማሰልጠን በሰፊው ህዝብ ላይ ጦርነት ያውጃሉ። በመንግስት መኪና ውስጥ ሰርገው በመግባትና አገዛዙን በቁጥጥር ስር በማድረግ ከረጅም ጊዜ አንፃር ፋሺሽታዊ ስርዓትን ሊመሰርቱ ይችላሉ። ይህ ዐይነቱ አገላለጽ ፈጠራ ሳይሆን ዛሬ በብዙ አገሮች የሚታይና ህዝቦችን ለስደት የዳረገና፣ የነቃውን ምሁር ደግሞ የማያነቃንቅ ነው። ስለሆነም ቅድሚያ መስጠት የሚኖርብን የአገር ውስጥ ገበያ ሊዳብር የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ሰፋ ያለ ምሁራዊ ኃይል ብቅ እንዲል አስፈላጊውን የባህል ለውጥ ማድረግ ነው። በአገራችን ምድር ዛሬ የተጀመረው የፖለቲካ እንቅስቃሴና መጠነኛ ነፃነት ስር ሊሰዱና የሰፊው ህዝብም ንቃተ-ህሊና ሊዳብር የሚችለው ወደ ውስጥ ያተኮረና ሰፊውን ህዝብ በዕድገት እንቅስቃሴ ውስጥ ተካፋይ የሚያደርግ ስትራቴጂ የተከተልን እንደሆን ብቻ ነው።
የውስጥ ወይስ የውጭ ገበያ ነው የአንድ አገር የዕድገት መሰረት ?
በአጠቃላይ ሲታይ የህብረተሰብን ዕድገትና የሰውን ልጅ ስልጣኔ በሚመለከት ከሶስት ሺህ ዓመት ጀምሮ የዕውቀትን ምንጭ በተለያየ መልክ በተረጎሙና በሚተረጉሙ ፈላስፋዎች ዘንድ የጦፈ ክርክር ተካሂዷል። ይህ የተለያየ ፍልስፍናዊ አመለካከት ለተከታታዩ ተመራማሪ መሰረት በመሆን አንድ ህብረተሰብ በምን መልክ ቢዋቀር ሰላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም ብልጽግና ሊመጣ ይችላል በሚለው ላይ የጦፈ ክርክር በመካሄድ የኋላ ኋላ ለአውሮፓው ህዝብ የህብረ-ብሄር መመስረቻ ዘዴ መመሪያ ሊሆን ችሏል።
በዛሬው ወቅት በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች አንድን ህብረተሰብ ለመገንባት የሚደረገው ክርክር የተለያየ ዝንባሌ ባላቸው የየአገሩ ምሁራን ሳይሆን፣ የየአገሮች መንግስታት ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በሙሉ ከውጭ የመጡና በህዝቡ ትከሻ ላይ የሚጫኑ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በእኛ ኢትዮጵያውያንም ሆነ በአብዛኛዎቹ አፍሪካ መንግስታት ዘንድ ካላንዳች ክርክርና ምርምር ከውጭ የመጣን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ እንደባህል ተወስዷል። ከውስጥ በአንዳንድ ክሪቲካል አመለካከት ባላቸው ምሁራን የተሻለ አስተያየት በሚቀርብበት ጊዜ የቀረበውን ሃሳብ እንዳልሰሙ በመጣል በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው የተደነገገው ፖሊሲ ተግባራዊ ይሆናል። እንደምናየው ውጤቱ የተወሳሰቡና በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኙ የማይችሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የስነ-ልቦናና የባህል ውድቀት ውስጥ ከቶናል።
በአውሮፓው ምድር የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ወደ ህብረ-ብሄር ከመሸጋገራቸው በፊት በመጀመሪያ ደረጃ ያካሂዱ የነበረው ትግል የማሰብ ኃይልን ወይም ንቃተ-ህሊናን ማዳበር ነበር። ይህም ማለት በየአገሩ ያለው ህዝብ ከባህላዊና ለዕድገት ጠንቅ ከሆኑ አስተሳሰቦች በመላቀቅ ተፈጥሮን ለመቃኘትና በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ለመለወጥ የሚያስችሉትን ዕውቀት ማግኘትና ንቃተ-ህሊናውን ማዳበር ነበር። በዚህም መሰረት እያንዳንዱ ዜጋ ሰው መሆኑን በመገንዘብ ዕውነተኛ ነፃነቱን የሚያገኝበትንና ውስጣዊ ፍላጎቱን ተግባራዊ የሚያደርግበትን ሁኔታ ማዘጋጀት ነበር። በመሆኑም የኢኮኖሚ ጉዳይ ከፍተኛ አትኩሮ የተሰጠው ስለነበር አገርን በጸና መሰረት ላይ የመገንባቱ ጉዳይ ተቀዳሚውን ቦታ የያዘ ነበር። ስለሆነም አገሮች ወደ ህብረ-ብሄር ሲሸጋገሩ መንግስታት ምን ምን ነገሮች በቅደም ተከተል ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው በምሁራኑ ዘንድ የጦፈ ክርክር ይካሄድ ነበር።
የኋላ ኋላ መርከንታሊዝም ወይም የውስጥ ገበያን ማሳደግና ህብረተሰብን ማስተሳሰር ያስፈልጋል የሚለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቀባይነት በማግኘት በተለያየ ጊዚያት በየአገሮች ውስጥ ይህ ፖሊሲ ተግባራዊ በመሆን አገሮች ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ወደ ህብረ-ብሄር እንዲሸጋገር አስችሏቸዋል። ይሁንና የአውሮፓ አገሮችን ዕድገት ስንመለከት ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ በአንድ ጊዜ በሁሉም አገሮች በተመሳሳይ ደረጃ ተግባራዊ የሆነ አይደለም። በተለይም እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ እንግሊዝ በኢንዱስትሪና በውስጥ ገበያ ቀድማ የሄደች ስለነበረች ሌሎች አገሮች የሷን ፈለግ እንዳይከተሉና በተለይም በውጭ ንግድና በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ግፊት ታደርግ ነበር። በአዳም ስሚዝና በሬካርዶ የፈለቀው የነፃ ገበያ ቲዎሪና ዓለም አቀፋዊ የስራ-ክፍፍል ዋናው የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ እንዲሆንና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች እንዲቀበሉት ከፍተኛ ግፊት ይደረግ ነበር። በፍልስፍናና በሳይንሳዊ ቲዎሪ የገፉ አገሮች፣ ግን ደግሞ በማቴሪያል ሁኔታቸው ወደ ኋላ የቀሩ እንደ ጀርመን የመሳሰሉ አገሮች የእንግሊዝን የነፃ ንግድ ቲዎሪ አሽቀንጥረው በመጣል ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል ሁለት ትውልድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። ለዚህ ዐይነቱ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካበረከቱት ውስጥ ፍሪድሪሽ ሊስት የሚባለው ሁለ-ገብ አዋቂ መጠቀስ የሚገባው ነው። በሱ ትምህርት መሰረት አንድ በኢኮኖሚ ወደ ኋላ የቀረች አገር የእንግሊዝ ኢኮኖሚስቶች ያዳባሩትን የነፃ ንግድና የነፃ ገበያ ፖሊሲ ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነች ፖሊሲው እንግሊዝን ብቻ የሚጠቅም ነው። አንድ አገር በጥሬ ሀብት ማውጣትና በእርሻ ምርት ላይ ብቻ የምታተኩር ከሆነ በዚያው ቀጭጫ ትቀራለች። በተለያየ መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ ኃይል ለመፍለቅ ስለማይችል ብሄራዊ ነፃነቷ ይገፈፋል። ስለሆነም ይላል ፍሪድሪሽ ሊስት፣ አንድ አገር የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ከፈለገችና የውስጥ ገበያ እንዲያድግ የግዴታ ወደ ውስጥ ያተኮረ ፖሊሲ መከተል አለባት። ለዚህ ደግሞ ንቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማገዝና በኢንዱስትሪ ግንባታ እንዲሳተፉ በማድረግ የውስጥ ገበያን ማሳደግ ሊታለፍ የማይችል ጉዳይ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይም በማደግ ያሉ እንዱስትሪዎች(Infant Industries) ከውጭ በሚመጣ ተመሳሳይ ምርት እንዳይጠቁና እንዳይፈራርሱ ከተፈለገ መንግስት የግዴታ የዕገዳ ፖሊሲ መከተል አለበት። በዚህ መልክ የኢንዱስትሪዎችን ዕድገት ማፋጠን ብቻ ሳይሆን ለፈጠራ ስራ የሚያመች ሁኔታም ማዘጋጀት ይቻላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግስት ዋናው ተግባር የባቡር ሃዲዶችን፣ የካናል ሲሰትምን፣ መንገዶችንና ከተማዎችን፣ እንዲሁም መንደሮችን በመገንባት ህዝቡ እንደ ማህበረሰብ በመሰባሰብ ውስጣዊ ኃይሉ እንዲጠነክር ማድረግ የህብረ-ብሄር ግንባታ ዋናው መሰረተ-ሃሳብ እንደሆነ በተለያዩ ምሁራን በመሰበክ ከቲዎሪ አልፎ ተግባራዊ የሆነ ጉዳይ ነው። ይህንን መንገድ ያልተከተሉና የእንግሊዝን የነፃ ንግድ ምክር የተቀበሉ እንደ ፖርቹጋል የመሳሰሉ አገሮች ተግባራዊ ባደረጉት ፖሊሲ አማካይነት የተጠበቀውን ውጤት ባለማግኘታቸው በተለይም ገበሬው በረሃብ ሊጠቃ ችሏል። ምክንያቱም ገበሬው የእርሻ ምርቱን በመተው በወይን ምርት ላይ ብቻ እንዲረባረብ በመደረጉና፣ በጊዜው በዓለም ገበያ ላይ የወይን ምርት ጥያቄ እየደከመና የፖርቹጋል የውጭ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ በመናጋቱ ነው።
የውስጥ ገበያን ጥናካሬና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የመመስረትን ጉዳይ የኋላ ኋላ አሜሪካ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፣ በኋላ ደግሞ ቻይና የተከተሉትና ከፍተኛ ውጤትም ያገኙበት በመሆኑ ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ያረጋግጣል። የቻይናን ጉዳይ ብንወሰድ በመጀመሪያ የውስጥ አደረጃጀት ጉዳይና ህብረተሰብአዊ ጥንካሬ መሰረቱ የተጣለው እ.አ.አ ከ1949 ዓ.ም እስከ 1978 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ከብዙ ውዝግብ በኋላ እነ ዴንግ ሲያዎፒንግ ባሸናፊነት ሲወጡና የገበያ ኢኮኖሚ የጥገና ለውጥ ሲያካሂዱ ዝምብለው ገበያውን ለውጭ ተዋንያን ክፍት በማድረግ አልነበረም ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት። በተለይም የኢንዱስትሪው፣ የእርሻውና የሚሊታሪው መስክ መሻሻል እንዳለበት በማመን በአንድ በኩል በዚህ ላይ ሲረባረቡ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከውጭ ቴክኖሎጂ ለማግኘት ሲሉ ለውጭ ኢንቬስተሮች ልዩ የመዋዕለ-ነዋይ ቦታ በማዘጋጀት ቴክኖሎጂዎችን መቅዳትና የራሳቸው ማድረግ ነበር። በዚህ መሰረት ሰላሳ ዐመት ያህል ሙከራ ካደረጉና አንድ የዕድገት ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ እ.አ.አ በ2005 ዓ.ም ቻይና የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በቃች። አሜሪካም ሆነ የአውሮፓው አንድነት ቻይና በቴክኖሎጂ ዕድገት መንጥቃ በመሄዷ በጣም ፈርተዋል። የሚያደርጉትን ሁሉ በማጣት ቻይና አምርታ ወደ አውሮፓው አንድነትና የአሜሪካ ገበያ ላይ በምትልከውና ከእነሱ ምርት ጋር በሚወዳደሩ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ለመጨመር እየጣሩ ነው። በአጭሩ እነዚህ ሁሉ አገሮች ከውስጥ ገበያቸውን በደንብ ሳያደራጁና ህብረተሰባቸውን በፀና መሰረት ላይ ሳያቆሙ የግዴታ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንሁን ብለው በፍጹም አልተጣደፉም።
ክዚህ አጭር ሀተታና ኢምፔሪካል ማስረጃ ስንነሳ አገራችን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ እራሷን ከውስጥ ማጠናከር አለባት። ወደ ውስጥ ያተኮረና ህዝቡን ሊያሰባስብ የሚያስችልና ጥንካሬም የሚሰጠው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ ሊታለፍ የማይችል ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው አንድ ቦክሰኛምም ሆነ አንድ አገር ተፎካካሪዎቻቸውንና ጠላቶቻቸውን በደንብ ሊቋቋሙና በአሸናፊነት ሊወጡ የሚችሉት በመጀመሪይ ራሳቸውን ሲያዘጋጁና ጥንካሬ ሲያገኙ ብቻ ነው። ቦክሰኛው ካለአቅሙ በክብደትም ሆነ በጥንካሬ ከሚበልጠው ጋር ዝም ብሎ የውድድር መረብ ውስጥ ገብተን እንታገል አይልም። አቅሙን ማወቅ አለበት። አንድ አገርም እንዳትወረር ከተፈለገ በደንብ የተደራጀና የተማረ የወታደር ኃይል ያስፈልጋታል። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ መሰረት በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ከመሆኑ በፊት ትግል እናድርግ ማለት ራስን ለጠላት አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል።
መልካም ግንዛቤ !!
fekadubekele@gmx.de