ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት የሚፈጥሩ የነዳጅ አቅራቢ ተቋማትና ዴፖዎች ካሉ እርምጃ ይወሰዳል...

ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት የሚፈጥሩ የነዳጅ አቅራቢ ተቋማትና ዴፖዎች ካሉ እርምጃ ይወሰዳል – ኢ/ር ታከለ ኡማ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2011 (ኤፍቢሲ) ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በመዲናዋ በሚገኙ ሁሉም የነዳጅ ማደያዎች አፋጣኝ የማጣራት ስራ በመስራት የነዳጅ እጥረት በፈጠሩ የነዳጅ አቅራቢ ተቋማት እና ዴፖዎች ላይ እርምጃ እንወስዳለን አሉ።

ኢንጅነር ታከለ ኡማ ይህንን ያሉት ሰሞኑን በተከሰተው የነዳጅ እጥረት ዙሪያ ምክክር እያካሄዱ ባሉበት ወቅት ነው።

ውይይቱን ያካሄዱት ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር ጋር በመሆን ከማደያ ባለቤቶች እና ከነዳጅ አቅራቢ ተቋማት ጋር መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ባለመወጣታቸው የተፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።

ዘርፉ የረጅም ግዜ መፍትሄ የሚሹ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ያካተተ ግብረ-ኃይል በማቋቋም ገበያውን በቋሚነት የማረጋጋት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በመጨረሻም የከተማ አስተዳደሩ ከፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን በከተማዋ ውስጥ ያሉትን የነዳጅ ማደያ ዴፖዎችን የመፈተሽ ስራ ከዛሬ ጀምሮ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንጅነሩ በማከማቻ ነዳጅ እያለ የነዳጅ እጥረት የተፈጠረ በማስመሰል ህብረተሰቡን በማጉላላት የተዛባ ገበያ በመፍጠር ችግር እየፈጠሩ ያሉ ማደያዎች እና የነዳጅ አቅራቢ ተቋማት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ ማስታወቃቸውን ከከንቲባ ጽህፍት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

/ዘገባ – ፋና/

LEAVE A REPLY