የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ተጠናቀቀ፤ ስለሕግ የበላይነትና አፈጻጸም የተጠቀሰ ነገር የለም

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ተጠናቀቀ፤ ስለሕግ የበላይነትና አፈጻጸም የተጠቀሰ ነገር የለም

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በተለያዩ የለውጥ ሂደቶች ዙሪያ የተስተዋሉ ድክመቶችንና ጠንካራ ጎኖችን በሚመለከት ሰፊ ውይይት በማድረግ መጠናቀቁን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በመዳሰስ የተጠናቀቀው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በትምህርት፣  በኢኮኖሚ፣  በዲፕሎማሲ፣ በወጣቶች፣  በመገናኛ ብዙሃን፣  የተፎካካሪ ድርጅቶች እና በተለያዩ መስኮች ዙሪያ የተወያየ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው በሕግ የበላይነትንና አፈጻጸም ዙሪያ በተለይም በፌዴራል መንግስትና ክልሎች መካከል ሊተግባር ስለሚገባው የህግ አፈጻጸም ዙሪያ ስለመነጋገራቸው የሚገልጽ ምንም አይነት ቃል በመግለጫው አልተመለከተም።

የአፈጻጸም አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን የሚገልጸው መግለጫው ስለተፎካካሪ ፓርቲዎችና ለውጡን ለማጨናገፍ የሚሰሩ ጽንፈኞች ዙሪያ ውይይት መደረጉን ገልጾ ለውጥን በማስቀጠል ረገድ ድርጅቱ የጀመረውን አዎንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች ላይ መምከሩን አስታውቋል።

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ይነበባል ፡-

የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን በዝርዝር ገምግሞ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቋል።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከጥር 07/2011 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው ዉይይት የለዉጡን ቀጣይነት በማረጋገጥና ተግዳሮቶቹን በመቅረፍ አቢይ አጀንዳ ላይ ሲመክር ቆይቷል። ለዉጡ ባስገኛቸው መልካም ውጤቶች፣ ባጋጠሙት ተግዳሮቶችና ወደፊት ሊያጋጥሙ በሚችሉ ሁኔታዎች ላይ በጥልቀት ከመከረ በኋላም የድርጊት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በሀገራችን በታየው ለውጥና 11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መሰረት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት የቻሉ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ስራ አስፈፃሚው አውስቷል። ከነአተገባበር ችግሩም ቢሆን ህዝቡ የመሰለውን በነፃነት የሚገልፅበት የእፎይታ ስሜት መፈጠሩ፣ ታራሚዎችና ፍርደኞች በይቅርታና ምህረት መለቀቃቸው፣ በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተፎካካሪ ሃይሎችም ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማረም የተወሰዱ ርምጃዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት መዘገብና የህዝቡን ድምጽ ማሰማት መጀመራቸው ከዴሞክራሲ ምህዳሩ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ድሎች መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ተመልክቷል።

በኢኮኖሚው መስክ የተወሰዱ ማስተካከያዎች መኖራቸውን የገመገመው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፉት አመታት በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው የፖለቲካና የደህንነት ቀውስ ከፍተኛ ስለነበር የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ማስከተሉን፤ ይህም በተራው ከፍተኛ የስራ አጥነት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የብድር ጫና ማስከተሉን አስታውሶ ችግሩን ለማቃለል የተወሰዱ አዎንታዊ እርምጃዎች ቢኖሩም አሁንም መዋቅራዊ ችግሩ ያልተፈታ መሆኑን ገምግሟል።

በስጋት ገንዘባቸውን ሲያሸሹ የነበሩ ግለሰቦች ወደ ባንኮች መመለሳቸው፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረቱ ላይ አንፃራዊ እፎይታ መፈጠሩ እንዲሁም ዲያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ያለው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ ተጠቃሽ አዎንታዊ ለውጦች ናቸው ብሏል።

ሴቶች ወደ ከፍተኛ አመራርነት በስፋት መምጣታቸውና በእምነት ተቋማትና በተከታዮቻቸው መካከል የተደረገው የእርቀ ሰላም ጥረት ፍሬያማ መሆኑ እንዲሁም በፀጥታና ፍትህ ስርዓቱ ላይ የተካሄደው ሪፎርምና ይህንኑ ዘላቂ ለማድረግ መንግስት ህግና ስርዓት ለማስከበር ያለው ቁመናና የህብረተሰቡ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በለውጡ ውጤት ማሳያነት የተመለከታቸው ናቸው።

በዲፕሎማሲው መስክም ለሁለት አስርት አመታት በሀገራችንና በኤርትራ መካከል የነበረው የሞት አልባ ጦርነት ሁኔታ በመሰረቱ ተቀይሮ ከኤርትራ ህዝብና መንግስት ጋር መልካም ግንኙነት ተፈጥሯል። በዚህም ተራርቀው የነበሩ ወንድማማች ህዝቦች ዳግም መገናኘታቸውና የሁለትዮሽ ኢኮኖሚ ትስስር መጀመሩ ትልቅ ለውጥ መሆኑን ኮሚቴው አስምሮበታል። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻሻል አካባቢውን ወደ ሰላም ቀጠና ለመቀየር መሰረት የተጣለበት በመሆኑ አለም አቀፉ ማህበረሰብም ጭምር እውቅና የሰጠው ሲሆን የሀገራችን መልካም ገፅታም የተገነባበት ሆኗል። በተጨማሪም ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር የሀገራችንን ጥቅም ማዕከል ያደረገ መልካም ግንኙነት መፈጠሩን ስራ አስፈፃሚው በጥንካሬ ገምግሟል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለዉጡ ጥልቅ፣ ሰፊና ትልቅ ተስፋ ይዞ የመምጣቱን ያህል ከተስፋው በተቃራኒ ስጋቶችንም ያዘለ እንደሆነ በአፅንኦት ገምግሟል። ለዉጡ አሁንም ህዝባዊ መሰረት ይዞና በኢህአዴግ እየተመራ ያለ ቢሆንም ህዝባዊ መሰረት የሌላቸው ፀረ ለውጥ አስተሳሰቦችም በተቀናጀ መንገድ እየተመሩ ተግዳሮት ሆነውበታል ብሏል ስራ አስፈፃሚው።

ከለውጡ በተቃራኒ ያሉ ሃይሎች ህዝቡን ለማደናገርና ድጋፍ ለማግኘት እንዲያመቻቸው ለውጡን ተከትሎ በህዝቡ ውስጥ ያሉ ብዥታዎችን እና በለውጡ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአመራር ግድፈቶችን፤ እንዲሁም ማንነትንና ሌሎች አጀንዳዎችን ምክንያት በማድረግ ፅንፈኛ አካሄድ በመከተል የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈፀም ሲሉ በዜጎች ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስና ዜጎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ እየሰሩ እንዳሉ ታይቷል። የለውጡ አደናቃፊ ሃይሎች በህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር በመታገዝ ግጭትና መፈናቀል እንዲፈጠር፣ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በመሰሉ የኢኮኖሚ አሻጥሮች በመሳተፍ ለውጡን ለመግታት እየተረባረቡ እንደሚገኙም ገምግሟል።

በድርጅቱ በራሱ ውስጥም አሁንም በለዉጡ ምንነት፣ በለዉጡ ውስጥ ባለ ሚና እና በወደፊት አቅጣጫዎች ላይ የተሟላ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ፈጥሮ በእኩል ሚዛን እየተጓዘ አለመሆኑ፣ የታችኛው መዋቅርም አለመደገፉ እና በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ያሉ የአካሄድ ዝንፈቶችና የእርስ በርስ መጠራጠር በግልፅ ተነስተው ትግል ተደርጎባቸዋል። እነዚህ ችግርች በቀጣይ እንዲስተካከሉም መግባባት ላይ ተደርሷል። በዚህም ላይ በመመስረት እንደ ሀገርና ህዝብ ያለን አማራጭ ፅንፈኝነትን በማክሰም አንድነቷ የተጠናከረ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ለዉጡን ማስቀጠል መሆኑ ላይም መግባባት ተፈጥሯል።

ለዉጡ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ እንዲሆን በማድረግ ረገድ አሁንም ከፍተኛ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለዉጥ ችግሮች እንዳሉ ያነሳው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የለዉጡ ዘላቂነት የሚረጋገጠው ሰላምን በመገንባት፣ ፍትህን በማረጋገጥ፣ ዴሞክራሲን በማስፋት፣ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሩን በመቅረፍና፣ ሀገራዊ አንድነትና ሀገራዊ ክብርን በዘላቂነት ማረጋገጥ ሲቻል ብቻ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥቶታል። በመሆኑም ለዉጡ ካለፉት ሁሉ የተሻለና ለወደፊቱም የተሳካ እንዲሆን ባለፉት አመታት በሀገራችን በየዘርፉ የተመዘገቡ ድሎችን በሚያሰፋ፣ የተፈፀሙ ስህተቶችን በሚያርምና ዳግም እንዳይከሰቱ በሚያደርግ እንዲሁም የመፃዒ ጊዜ ተግዳሮቶችንና እድሎችን በመተንተን የሀገርንና ትውልድን ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ ወደ ቀጣዩ ምእራፍ መሸጋገር እንዳለበትም አስቀምጧል።

ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገር አለበት ሲባል ዴሞክራሲን በተግባር በመፈፀም፣ በመግባባት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አንድነት በማጠናከር፣ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ከማያባራ ቀዉስ ወደ ዘላቂ መረጋጋት ምዕራፎች የሚያሸጋግሩ ስራዎችን መስራት እንደሆነ ስራ አስፈፃሚው አፅንዖት ሰጥቶታል።

ህዝቡ አሁንም ለለዉጡ ጠንካራ ድጋፍ እንዳለውና በለዉጥ አመራሩ ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳሳደረ ኢሕአዴግ ይገነዘባል ያለው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የደህንነቱን ስጋት የሚጨምሩ ጉዳዮች ስላሉበት የሀገራዊ ሰላም ጉዳይም እንደሚያሳስበው እንረዳለን ብሏል። ስለሆነም ሰላምን በማረጋገጥና የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ሊፈፀሙ የሚገባቸውን አቅጣጫዎች አስቀምጧል።

የሀገራችን ወጣቶች ከሌሎች የለዉጥ ሃይሎች ጋር በመሆን ለዉጡን እንዳመጡ ሁሉ አሁንም ለዉጡን ለማስቀጠል የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ያሰመረበት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የወጣቶቹ ጥያቄዎች በተለይም የስራ አጥነት ችግር ከመሰረቱ ያልተፈታ መሆኑን ላይም ተግባብቷል። ወጣቶች በለዉጡ ያገኙት ነፃነትና ዴሞክራሲ ዘላቂ ነው ለማለት እንደማይቻልም ገልፃል። ስለሆነም ገዥው ፓርቲና መንግስት የወጣቱን መዋቅራዊ ችግሮች የሚፈቱ ጉዳዮች ላይ በተለይም በስራ እድል ፈጠራ ላይ መረባረብ እንደሚገባቸው አስምሮበታል። ወጣቶችም ሁሉም ችግር በመንግስት ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን ተገንዝበው በየደረጃው በሚቀርቡላቸው የስራ እድሎች ላይ ስራ ሳይንቁ በመሳተፍ ለግልና ሀገራዊ ለውጥ መትጋት እንደሚኖርባቸው አሳስቧል። ወጣቶች ከኢኮኖሚ ባሻገር ያሉባቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲቻልም እስካሁን በመስኩ የነበሩ ጉድለቶች ሊታረሙ እንደሚገባም አስምሮበታል።

በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተማሪዎችና ምሁራን ለዉጡን ለመደገፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ቢሆኑም ፀረ ለውጥ ለሆኑ ቅስቀሳዎች ሰለባ እንዳይሆኑ ይልቁንም የተጀመረውን ለዉጥ የማስቀጠል ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት ያለመወጣታቸውን ከገመገመ በኋላ ይህን ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ አስቀምጧል።

የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት የሚሰሩበት ሁኔታ የተፈጠረና ይህንኑ ተጠቅመው የህዝብ ድምፅ የመሆን ጅምር ቢኖራቸውም የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክርና የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አተያይ በመፍጠር በኩል እና ተዓማኒነታቸውን የሚፈታተን የስርጭት ችግር እንዳለባቸው ኮሚቴው ገምግሟል። ለዉጡ ያስፈለገው በትናንቱ ለመቆዘም ሳይሆን ወደፊት ለመወንጨፍ ቢሆንም ሚዲያው የህዝቡን አተያይ በመቅረፅ ረገድ ግን ብዙ ይቀረዋል። በተለይ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያው እየተጫወተ ያለው አዎንታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ አሉታዊ ሚናው እየጎላ መምጣቱን ገምግሞ ከለውጡ ጋር በተዛመደ መልኩ የሚታረምበትን አካሄድ መከተል እንደሚገባ አመላክቷል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከለዉጡ ተነስተው በሰላማዊ መንገድ መታገል እንደሚቻል አቋም መያዛቸውንና የጋራ ውይይት መጀመራቸውን ያደነቀው የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አንዳንድ ፓርቲዎች ግን ፅንፈኝነትን በመስበክ የቆየውን የህዝቦች አንድነት በመሸርሸርና የህግ የበላይነትን ባለማክበር እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ በመገምገም ከዚህ ተግባራቸው በመቆጠብ በሃሳብ ልዕልና እና በውይይት ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መጎልበት ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

በአጠቃላይ ሲታይ በሀገሪቱ አሁን ላይ ጎልተው የሚታዩት ተግዳሮቶች የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር፣ የስራ ተልዕኮ አፈፃፀም መዳከም እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ እሴት መታጣት መሆናቸውን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አስምሮበታል። ችግሮቹን ከነ መገለጫዎቹ ከገመገመና ከነባራዊ ሁኔታና የወደፊት እይታው በመነሳት ስራ አስፈፃሚው በቀጣይ መፈፀም የሚገባቸውን የድርጊት አቅጣጫዎች አስቀምጧል።

ከእነዚህም ውስጥ ሰላምን፣ የህግ የበላይነትንና ፍትህን ማረጋገጥ በተለይም ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ማድረግ የቀጣይ ቁልፍ ተልዕኮ መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚው አስምሮበታል። ለዚህም በግብርናው በተለይም በመስኖ ልማት ላይ እንዲሁም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተቀዛቀዘውን ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት መረባረብ እንደሚጠይቅ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል። ማንኛውም ለግጭት እና አለመረጋጋት የሚዳርጉ ሁኔታዎች በግልፅ ተለይተው በአስቸኳይ መታረም እንዳለባቸውና ሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች በዝርዝር ተገምግሞ የጋራ በተደረገው ስምምነት መሰረት በተግባር እንዲመሩና መንግስትም ህግን የማስከበር ቁልፍ ሃላፊነቱን በጥብቅ መወጣት እንደሚገባው አቅጣጫ አስቀምጧል። ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ ሌብነትና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፈፅሞ እንዳይደገሙ በቂ ክትትል ማድረግና ለዚህ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ዝንባሌዎችን በሁሉም የስራ መስክ እየፈተሹ መጓዝ እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጧል።

በተጨማሪም ኢሕአዴግን እንደ ድርጅት ማጠናከር፣ የሚዲያ፣ የሲቪክ ማህበረሰብና የምሁራንን አቅም መገንባት፣ ሲቪል ሰርቫንቱ በእውቀትና በትጋት ላይ ተመስርቶ እንዲሰራ ማስቻል ዋነኛ ተግባሮች መሆናቸውን በአፅንዖት አስቀምጧል። ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለውን መደጋገፍ ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም በአቅጣጫ የተመላከተ ነው።

ሀገሪቱና ህዝቦቿ ያሏቸውን ሃብቶች በሙሉ በማስተባበርና በማቀናጀት መላ ህዝቡን ወደ ልማት ስራ ማስገባትም ዋናው ሀገራዊ ዘመቻ መሆን እንዳለበት የጋራ መግባባት ተይዞበታል። በዲፕሎማሲው ረገድም የሀገራችንን ብሄራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የድርጅቱ አባላት፣ አመራርና መላ የሀገሪቱ ህዝቦች የተጀመረውን ለውጥ በማስቀጠል ሀገራችንን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለማሸጋገር በሚደረገው ርብርብ የየበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡና ለኮሚቴው አቅጣጫዎች ተፈፃሚነት ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ ማስተላለፉን የኢሕአዴግ ፅ/ቤት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት
ጥር 2011 ዓ.ም

LEAVE A REPLY