ማንነታችን ማን ይወቅልን? | አብርሃ በላይ

ማንነታችን ማን ይወቅልን? | አብርሃ በላይ

እ.ኤ.አ. 1994 በኬንያ እና በታንዛንያ ድንበር በሚገኝ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ በተሰራች ዘመናዊ “ሪዞርት” በተካሄደ ኮንፈረንስ ተሳትፌ ነበር። ኮንፈረንሱ ‘ጦርነት እና ድርቅ በአርብቶ አደሩ ህብረተሰብ የሚያደርሰው ውድመት (The Impact of War and Drought on the Pastoral Communities in the Horn of Africa) የሚል ነበር። ኮንፈረንሱ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ከሆኑ የአፍሪቃ ሀገሮች የተወጣጣን ጋዜጠኞች እና ተመራማሪዎች ነበርን።

ከኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጠቋሚነት እኔ ስሄድ፣ ከኤርትራ ዶ/ር ተከስተ ገብራይ (ከ1996-2000 የኢጋድ ዋና ፀሃፊ የነበረ) ነው። ተከስተና እኔ እንዳንድ ያገር ልጆች ወድያው ነበር የተግባባነው። ታድያ ኮንፈረንሱ ውስጥ እያለሁ፣ መልእክተኛ ሰው ገባና ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ አብርሃ በላይ ሰዎች ይፈልጉታል ተባለ። ደነገጥኩኝ። “አንበሳ ካልሆነ ማን እዚህ ዱር ድረስ ሊመጣ ይችላል ብዬ ሳስብ” በተላኩት ሰዎች ታጅቤ ወጣሁ።

ሦስት ወጣት ወንዶች ቁመዋል። ኢትዮጵያውያን ይመስላሉ። “እነሱ ናቸው የሚፈልጉህ” ተባልኩ።

በእንግሊዝኛ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፣ ምን እንዳመጣቸው ጠየቅኋቸው። ታሪካችን ረጅም ቢሆንም ጉዳዩ ግን እንዲህ ነው። እኛ በትውልድ ኢትዮጵውያን ነን። ቅድም አያቶቻችን የአጼ ምንሊክ ወታደሮች ሆነው ከእንግሊዝ ጦር ጋር እዚህ ድረስ መጥተው ነበር። ወጣት ኢትዮጵያውያኑ ወታደሮች ሴት ቅድመ-አያቶቻችንን አግብተው ወልደው ቀርተዋል። እኛም ምንም እንኳን ታንዛንያውያን ብንሆንም፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈሳችን በጣም ጠንካራ ነው። መልካችንም እንደምታየን ከአካባቢያችን ይልቅ ኢትዮጵያውያን ነው የምንመስለው። ለዚህ ነው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ አለ ሰምተን ልንተዋወቅህ እና ታሪካችንን ወደ ኢትዮጵያ ይዘህ እንድትመለስ፣ ተረስተን እንዳንቀር እንድትነገርልን ነው አሉን።” እንባ ተናነቀኝ። ተቃቅፈን ተሳሳምን። ከአንድ ሰዓት የሚሆን የትዝታ ጨዋታ በኋላ ተለያየን።

ሰሞኑ ጠ/ሚ አብይ የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርሱ በዘር የተያያዘ ለመሆኑ ሲያብራሩ በአድዋ ጦርነት ጊዜም ሳይቀር ከመሃል አገር የሄዱ ወጣቶች በሄዱበት ልጆች ወልደው ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ እና በአጠቃላይ ያልተነካካ ዘር እንደሌለ ለመግለጽ ሞክረዋል። ሀቅ ነው። እንኳን በአንዲት ሀገር፣ በውጭም ቅድመ-አያቶቻችንኮ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፣ እና ማን ይወቅልን የሚሉ አጋጥመውናል። ፈጣሪ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ። የዘር ፖለቲካን እንደ ነፋስ ብን ብሎ ይጥፋልን።

LEAVE A REPLY