ኢትዮጵያዊነት፣ ሥጋቶችና አማራጭ አደረጃጀቶች | መሐመድ አሊ መሐመድ

ኢትዮጵያዊነት፣ ሥጋቶችና አማራጭ አደረጃጀቶች | መሐመድ አሊ መሐመድ

ለውይይት የቀረበ 

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊነትን ያሉ በአደባባይ ስድብና ዘለፋን የሚያስተናግዱበት፤ በጥፋተኝነት የሚከሰሱበት አስገራሚና ለሞራል ተቃራኒ የሆነ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በርግጥ በአንድ በኩል፣ ኢትዮጵያዊነትን በሌሎች ላይ (ከፈቃዳቸው ውጭ) ለመጫንም ሆነ፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነትን የተወሰኑ ወገኖች ዕዳ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ሚዛን ላይደፋ ይችላል፡፡ በአንድ በኩል ማንነታችን በኃይል ተጨፍልቋል በሚል የተደራጁ ኃይሎችን/ወገኖችን ቅሬታ ችላ ማለት፣ በሌላ በኩል፣ ሌላው ሁሉ በብሔር ተደራጅቶ ለጥቃት በሚዘጋጅበት ሁኔታ ያልተደራጁት ወገኖች ሥጋት ላይ መውደቃቸውን አለመገንዘብ የመፍትሔውን መዳረሻ ሊያርቀው ይችላል፡፡ በርግጥም ጥቂት የተደራጁ ሰዎች በሺህ የሚቆጠሩትን አንበርክከው ሊነዱና/ሊገዙ እንደሚችሉ አይካድም፡፡ በተለይ ህግና ሥርዓት በማይከበርበትና ሥርዓት አልበኝነት በነገሠበት ሁኔታ ጉልበት ያለው ያሻውን ሊያደርግ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የጥቃት ሰለባ ሊሆን የሚችለው ማነው? መፍትሔውስ ምንድነው?

ሁሉም በየጎጡ በሚደራጅበት፣ እዚያም እዚህም ግጭቶች በሚፈጠሩበት፣ ህግና ሥርዓት በማይከበርበትና ሥርዓት አልበኝነት በነገሰበት ሁኔታ የጥቃት ሰለባ ልንሆን የምንችለው ሁላችንም ነን ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በተለይ አማራው በዘር ላይ ያነጣጠሩ ፈርጀ-ብዙ ጥቃቶች ሰለባ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አማራው አገሬ ብሎ፣ ጥሮ ግሮ፣ ንብረት አፍርቶ በሚኖርባቸው አካባቢዎች የዜግነት መብቱን አጥቶ፣ በማንነቱ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር መደረጉ አልበቃ ብሎ፣ አገር ሰላም ብሎ በተኛበት በውድቅት ሌሊት ጎጆው (በውስጡ ያሉ እንስሳት ጭምር) እየተቃጠለ፣ የሞተው ሞቶ፣ የቀረው ሀብትና ንብረቱን ጥሎ እንዲሰደድ ሲደረግ እንደነበር ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለአማራው የተደገሰውን ጥፋት ሁሉም ሲቋደሰው እያዬን ነው፡፡

ለአብነት ለመጥቀስ ያህል፣ ቀደም ሲል ጀምሮ በአኙዋክና ኑዌር ተወላጆች መካከል የነበረው/ያለው የእርስ በርስ ግጭትና መጠፋፋት፣ ቁርሾና ሥጋት አሳሳቢና አስጨናቂ ነው፡፡ እንዲሁም በቅርቡ፣ በሶማሌ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በድሬ ዳዋ፣ በሞያሌ፣ በቤኒሻንጉል፣ በጋምቤላ … ወዘተ የኦሮሞ ተወላጆች በማንነታቸው ላይ ላነጣጠረ ጥቃት ተጋልጠዋል፤ ህይወታቸውንና ንብረታቸውን አጥተዋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በሶማሌ ተወላጆች ላይም ተመሳሳይ ነገር ተፈጥሯል፤ አስከፊ የሆነ ሰብኣዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል፡፡ በአዋሳ ከተማና አካባቢው በወላይታ ተወላጆች ላይ የተፈፀመውን አረመኔያዊና ዘግናኝ ድርጊት መርሳት አይቻልም፡፡

እዚሁ አዲስ አበባ ጫፍ ቡራዩና አሸዋ ሜዳ አካባቢ በጋሞና የዶርዜ ተወላጆች ላይ የተፈፀመውን አስደንጋጭ ድርጊት መዘንጋት እንዴት ይቻላል? በቀቤና እና ጉራጌ ተወላጆች መካከል በተፈጠረው (ዘርን መሠረት ያደረገ) ግጭት የደረሰውን የህይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ማሰብ ይከብዳል፡፡ አሁን ላይ በአፋርና በባቲ ኦሮሞዎችና፣ በተለይም በአፋርና በሶማሌ/ኢሳ ተወላጆች መካከል የተፈጠረው ግጭትና ፍጥጫ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ማሰብ ያስጨንቃል፡፡ በዘመነ-ህወሓት በማንነታቸው ተፈርተው ሲኖሩ የነበሩት የትግራይ ተወላጆች ሳይቀር ዛሬ ላይ ለሥጋት የተጋለጡበትና ከየአካባቢው የሚፈናቀሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ከዚሁ በተጓዳኝ፣ በአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይም ከወልቃይትና የራያ ማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ (ከዚህ በፊት የደረሱት ጥፋቶች እንደተጠበቁ ሆነው) እያንዣበበ ያለው ሥጋት ሰላም አይሰጥም፡፡ አማራና ኦሮሚያን ጨምሮ በሌሎች ክልሎች መካከል ያሉ የወሰንና የግዛት ይገባኛል ጥያቄዎችም ባንድ ወቅት ሊፈነዱ የሚችሉ (የተጠመዱ) ቦንቦች ናቸው ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ እነዚህ፣ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል እንጅ፣ በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ ተዘርዝረው የማያልቁ ውስጣዊ ችግሮች፣ አስነዋሪ ድርጊቶችና አስደንጋጭ ውጤቶች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ በአጠቃላይ አሁን በሀገራችን ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በአንክሮ ካየነው/ከመረመርነው የከፋ ጥፋትና ውድመት ሊያስከትል፣ ብሎም የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነው፡፡ በዚህ ላይ በሰይጣናዊ ተልዕኮ የተጠመቁና ለዚህ ውጤት ተግተው የሚሰሠሩ ኃይሎች መኖራቸው ሲታሰብ ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢና አስፈሪ ያደርገዋል፡፡

ከላይ ለማመልከት እንደተሞከረው የሥጋት ደመናውና አደጋው በሁሉም ወገን ላይ የሚያንዣብብና ሁሉንም ወገን እኩል የሚሳስብ/የሚያስፈራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታና አካሄድ የማያሳስበው/የማያስፈራውና በጀመረው የጥፋት መስመር በጭፍን የሚጓዝ አካል/ኃይል (ካለ) ተራ የግልና/የቡድን ፍላጎቱን ከማሳካት ባለፈ ፍፁም ኃላፊነት የማይሰማው የሰይጣን መንጋ መሆን አለበት፡፡ ይህም ሆኖ፣ የተረጋጋ ማህበረሰብና ሰላም የሰፈነበት አገር በሌለበት የግልም ሆነ የቡድን ፍላጎትን ለማሳካት ማሰብ ከቀን ቅዠት ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡

ስለዚህ ምን ይደረግ? አሁን ላይ በስፋት እንደሚታየው/እንደተጀመረው ሁላችንም በየፊናችን በጎጥ ተደራጅተን ራሳችንን ከጥቃት እንከላከል? ወይስ እጃችንን አጣጥፈን የሚሆነውን እንጠብቅ? በርግጥ አንዱ በጎጥ ተደራጅቶ በሌላው ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በሚዘጋጅበትና ሥጋት በሚፈጥርበት ሁኔታ የሌላውን መደራጀት መንቀፍና መኮነን ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ ሁላችንም በየፊናችን/በየጎጣችን የምንደራጅ ከሆነ “እኛና እነሱ” የሚል ስሜት መፈጠሩ፣ ግንኙነታችን በተቀናቃኝነት ላይ የተመሠረተ (adversarial relation) መሆኑ፣ ከዚህ አንፃር የተቃኘው አካሄዳችንም ወደግጭት ማምራቱ አይቀሬ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ግጭት ደግሞ ጊዜያዊ የበላይነትን ከማሳዬት ባለፈ (እሱም የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው) ማንም (በቋሚነት) አሸናፊ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም ከእንዲህ ዓይነቱ ግጭት ልናተርፍ የምንችለው ሞትን/እልቂትን፣ ስደትን፣ የሀገር ሀብት ውድመትን፣ አጠቃላይ ሀገራዊ ውድቀትንና ተያይዞ መጥፋትን ብቻ ነው፡፡

ስለሆነም፣ ዛሬ ላይ ቆም ብለን ልንነጋገርበት የሚገባው፣ ይህን ሥጋትና አደጋ ተሸክመን/ታቅፈን እንዴት ወደ ውድቀት አፋፍ በዝምታ እንጓዛለን? በዚህ ሁኔታ የልጆቻችንና የመጭው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? እኛስ ምን ዓይነት ሀገርና ሥርዓት ነው የምናወርሳቸው? እነሱስ በምን ሃጢያታቸው ነው የእኛን ዕዳና ቅሌት/ውድቀት የሚሸከሙት? አሁን በምናደርገውና ነገ ታሪክ በሚሆነው ተግባራችንስ አያፍሩብንም ወይ? በታሪክስ እኛ እንዴት ነው የምንዘከረው? ምናልባት ላንዳንዶቻችን አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ሩቅና ለጊዜው የማያሳስቡን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይሁንና ጉዳዩን ከራሳችን የግልና/የቡድን ፍላጎትና ጥቅም ጋር አያይዘን ካየነው በራሳችን ደህንነትና ህልውና ላይ አደገኛ ቁማር እየተጫወትንና አደጋው ቅርብ መሆኑን ልንገነዘብ እንችላለን፡፡

ስለሆነም (በእኔ እይታ) አሁን ላለው አጠቃላይ ሁኔታና በሁሉም ወገን ላይ ለሚያንዣብበው ሥጋት ዋነኛው ምክንያት ዘውግ ተኮር አስተሳሰብና በየጎጣችን መደራጀታችን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህን ዘውግ ተኮር አስተሳሰብ በልጆቻችን አእምሮ ውስጥ የዘራነውና ኮትኩተን ያሳደግነውም እኛው ራሳችን ነን፡፡ ይህን የአስተሳሰብ አራሙቻ ከዚህ ትውልድ አእምሮ ነቅለን ልናጠፋው የምንችለውም እኛው ነን፡፡ ይህን ዘውግ ተኮር (የጥፋት) አስተሳሰብ በእኛ ዕድሜ/ዘመን ሙሉ በሙሉ ልናጠፋው ባንችልም የሚያስከትለውን አደጋና ጥፋት ልንቀንሰው እንችላለን፡፡ ይህን ማድረግ የምንችለው ደግሞ በአንድነት ስንቆምና ስንደራጅ ነው፡፡

በአንድነት እንደራጅ ስንል በአንድ በኩል የአንዱን አስተሳሰብና/እሴቶች በሌላው ላይ ለመጫን ነው ብለው የሚያስቡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአንዳንዶችን ድርሻና ሚና ለማሳነስ የሚመስላቸው ወገኖች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ግን፣ አሁን ባለንበት ዘመን ሁለቱንም ማድረግ አይቻልም፡፡ በዚህ ዘመን ማንም ተነስቶ አስተሳሰቡንና (የማንነት) ተፅዕኖውን በሌሎች ላይ መጫን፣ ወይም የሌሎችን ተገቢ ድርሻና ሚና ማሳነስ አይቻልም፡፡ በአነድነት እንቁም/እንደራጅ ስንል እያንዳንዳችን የሀገራችን ጉዳይ እኩል እንደሚመለከተንና እንደሚያገባን፣ ብሎም የጋራ ዕጣ-ፈንታችን በጋራ መወሰን እንዳለብን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በአንድ በኩል፣ በሀገር ጉዳይ ላይ የትኛውም ወገን የተለዬ ጥቅምና (vested interest) መብት እንደሌለው፣ በሌላ በኩል ለሀገር አንድነትና ህልውና ሥጋት ተደርጎ የሚታይ ወገን እንደሌለና/ሊኖርም እንደማይገባ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያዊነት የሚመሠረተው/ሊመሠረት የሚገባውም የእያንዳንዱን ዜጋ እኩልነት ታሳቢ ባደረገ እውነተኛ የዜግነት አስተሳሰብ ነው፡፡ የዜጎች እኩልነት ስንልም ሰብኣዊ፣ ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እኩል የሚከበሩበትንና እኩል ጥበቃ የሚያገኙበትን፣ እንዲሁም እኩል ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድሎች (equal opportunities) የተረጋገጡበት ሥርዓት ማለታችን ነው፡፡ በዚህ መሠረት የእያንዳንዱ ዜጋ መብትና ጥቅም ከተረጋገጠ/ከተከበረ እግረ-መንገዱን (by default) የተለያዩ የቡድን መብቶችና ጥቅሞች መረጋገጣቸው/መከበራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይህም ሆኖ፣ በተለዬ ምክንያት (in exceptional cases) የማናስጠብቃቸውና እውን (address) የማናደርጋቸው የቡድን መብቶችና ጥቅሞች ቢኖሩ ለእነዚህም እውነታዎች ዕውቅና መስጠት የሚችል ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡

በአንድ በኩል የሀገር አንድነትና ህልውናን ከማረጋገጥ፣ በሌላ በኩል ከዘውግ ተኮር አስተሳሰብና አደረጃጀት ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባውና አነጋጋሪ ጉዳይ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ነው፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር፣ የአሃዳዊም ሆነ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር (ጉዳይ) መነሻው “እንዴት አብረን እንኑር?” ከሚል ቀና ሀሳብ እንጅ፣ መለያዬትን/መበታተንን ታሳቢ በማድረግ አይደለም፡፡ ለዚህም በዓለም ላይ ያሉና/የተለመዱ በርካታ ልምዶችንና/ተሞክሮዎችን መጥቀስ የሚቻል ሲሆን አሁን በሀገራችን ተግባራዊ የተደረገው የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀርና አስተሳሰብ በዓለም ላይ/ከዚህ በፊት የማይታወቅ ወጣ ያለ ተሞክሮ (experience) መሆኑን ተንትኖ ማስረዳትና ተጨባጭ አስረጅዎችን እያቀረቡ መሞገት ይቻላል፡፡

ሆኖም ግን ይኸኛው በጣም ሰፊና ራሱን ችሎ መቅረብ ያለበት አነጋጋሪ ርዕሰ-ጉዳይ በመሆኑ ሌላ ጊዜ ብንመለስበት ይሻላል፡፡ እንደህግ ባለሙያ፣ በተደራጀ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንደነበረው፣ በዓለማቀፍ ህግ የማስተርስ ዲግሪውን (LL.M) እንደሠራና ከህግና ፖለቲካ አንፃር የሌሎች አገሮችን ልምዶች የመመርመር/የማወቅ ዝንባሌ/ፍላጎት እንዳለው ሰው; በፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ዙሪያ ያለኝን የግል ምልከታ (personal view) ለማጋራት እሞክራለሁ፡፡

ይኸኛውን ግን እዚህ ላይ ባቆመውና ብንነጋገርበት ይሻላል፡፡

LEAVE A REPLY