በሳተናው ድረ-ገጽ የአማረኛው ገጽ ላይ ” የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሥራ አስፈፃሚና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አብረው መሥራት እንደማይችሉ በፊርማቸው አረጋገጡ” በሚል ርእስ በአጭሩ የተፃፈ ፅሁፍ አነበብኩ። ከእኛው ከራሳችን ኋላቀርነት የሚመነጨውን የአገሬን የፖለቲካ ባህል ኋላ ቀርነት በሚገባ የምገነዘብ በመሆኔ ቢያሳዝነኝም አልገረመኝም። እንደማነኛውም የአገሩ ጉዳይ እንደሚያሳስበው የአገሬ ሰው የተገነዘብኩትንና የታዘብኩትን ከእኔው ጋር ከማስቀረው በአጭሩ እንደሚከተለው አስፍሬ ለአንባቢያን እንዲደርስ አደረግሁት።
ፀሃፊዎቹና ፈራሚዎቹ ስህተት ነው የሚሉትን ህዝብ እንዲያውቅ የማድረግ መብቱ የራሳቸው ነው። የድርጅቱ (አርበኞች ግንቦት 7) መሪዎችና አባላት ከነችግራቸውም ቢሆን የግል ህይወትንና ቤተሰብን መስዋትነት ከፍለውና አስከፍለው ያደረጉትን አስተዋፅኦ ዋጋ በሚያሳጣ ዘመቻ ላይ መሠማራት ግን ለነእሱም (ለፀሃፊዎችም) ነሆ ለአገር በፍፁም የሚበጅ ነገር አይደለም።
በየራሳቸው ምክንያት ድርጅቱን ጥለው መውጣታቸውና ያዋጣናል በሚሉት መንገድ ለመታገል የመወሰኑ ምርጫም የእንሱና የእነሱ ብቻ ነው። እራሳቸውን እንከን የለሽ በማስመሰል የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸውንና መሪዎቻቸውን ስም በማጥፋት ዘመቻ ላይ መሰማራታቸው ግን የፖለቲካ አስተሳሰብ ድንቁርና (ድውይነት) እንጅ ጨርሶ ጤናማነት አይደለም።
ይህ በሆነና ባልሆነው ሰብብ ከድርጅት እየወጡ የአፍራሽነት ዘመቻ ማካሄድና አንጃ የመፍጠር እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ ባህሪ ወይም ሰብእና ከእንግዴህ በዚች ምድር (ኢትዮጵያ) ማብቃት ይኖርበታል። ይኸ “እኔ ካላደረግሁት ፍርስርሱ ይውጣ”የሚለው ክፉ የፖለቲካ ደዌ ከእንግዴህ በዚች መከረኛና ጎስቋላ አገር ጨርሶ ቦታ ሊኖረው አይገባም። አዎ! ይህ አይነቱ እጅግ ኋላ የቀረ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለአሁኗ ኢትዮጵያ ጨርሶ የሚመጥን አይደለምና ልንፀየፈው የግድ ነው ።ስህተት አይነገር እያልኩ አይደለሁም። እያልኩ ያለሁት በአግባቡና ለነፃነትና ለፍትህ እውን መሆን ለሚደረገው የጋራ ትግል በሚጠቅም አቀራረብና ይዘት ይቅረብ ነው።
በዚህ እጅግ በስሜት ትኩሳት በተለወሰው “የእውቁልን” ፅሁፍ የቀረበው ማስረጃ ስህተትን በድርጅት ውስጥ ሆኖ ለማስተካከል ከቅንነት የተደረገ ጥረትን የሚያሳይ ሳይሆን ለኤርትራ መንግሥት የተፃፈ ደብዳቤ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ፀሀፊዎቹ (ፈራሚዎቹ) ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላና እንዲህ አይነት አስቀያሚ ዘመቻ ከማወጃቸው በፊት የሚሉትን ችግር በተመለከተ ከድርጅቱ መሪዎች ጋር ለመወያየት ምን ያህልና እንዴት ጥረት እንዳደረጉ አልነገሩንም። ዋናው ማስረጃቸው ለኤርትራ መንግሥት እንዲያውቅልን ያሉትንና እራሳቸው በተሰማቸው መጠን አርቅቀው የተስማሙበት ደብዳቤ ነው። ለዚህ የተሰጠ ምላሽ ወይም ሌላ ተጨባጭ ማስረጃ ከሌለ በስተቀር በደብዳቤው ላይ እንደ ችግር የተጠቀሱት ጉዳዮችን እውነትነት ጨርሶ ማረጋገጥ አይቻልም። ለዚህ ነው ይህ በቅሬታ አቅራቢ ተፅፎ የተፈረመ ግን በሌላ ማስረጃ ያልተደገፈ የክስ ዘመቻ ብዙም ውሃ የሚቋጥር አይደለም ማለት ትክክል የሚሆነው።
ዋናው ጉዳይ ይህ ለምን ሆነ ሳይሆን የራስን ድርጅት በሥነስርዓትና በገንቢነት ካለበት ድክመት ነፃ እንዲወጣ ከመታገል ይልቅ “ብለን ነበር“ ለማለት የሚረዳ ደብዳቤን እንደትልቅ ማስረጃና የእራስን ደካማ የፖለቲካ ሰብእና መሸፈኛ መጠቀም በምንም አይነት መለኪያ ጤናማ ፖለቲከኝነት አይደለም።
እውነተኛ አርበኛ በእንዲህ አይነት ቅጥ የሌለው የፖለቲካ ጨዋታ አይጫወትም። አዎ! እውነተኛ አርበኝነት ከእንዲህ አይነት የዘቀጠ የፖለቲካ ጨዋታ ጋር ጨርሶ ግንኙነት የለውም።
ከዚህ ትይዩ ግን በዜግነት (ኢትዮጵያዊነት) የፖለቲካ እምነት እና የፖሊሲ አቅጣጫ ለዴሞክራሲዊ ሽግግርና ምሥረታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ የሚያደርጉትን ኢትዮጵያውያን መብት ማክበር የግድ ነው ። የምናወራው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ስለማድረግ ከሆነ ። የእውነተኛ አርበኝነት ትርጉሙም ይኸው ነው። ከዚህ ውጭ የፈለገው አይነትና መጠን መስዋእትነት ቢከፈል የትም አያደርስም ። አርበኝነትም አይደለም።
ህወሃት/ኢህአዴግ “አያሌ ታጋዮቼ መስዋእትነት ከፍለዋል” ሲለን የሚኖረን ጥያቄ “ያ አያሌ የኢትዮጵያ ልጆች መስዋእትነት የከፈሉበት መስመርና አቅጣጫኢላማውን ስቶ በተቃራኒው የመከራና የውርደት ቀንበር ሲያሸክም ከእውነተኛአርበኝነት ጋር ምንና እንዴት ይገናኛል ?” የሚል ነው ።
አሁንም “በአርበኝነት ታግለናል ፣ መስዋእትነትም ከፍለናል” እያሉ በሌላ በኩል የመሰረቱትን (የሰሩትን) ድርጅት በውስጥ ታግሎ ከማስተካከል ይልቅ የማፍረስ (የማዳከም) የፖለቲካ አባዜ ውስጥ ለገቡ (ለሚገቡ) ወገኖች በቀጥታ ግልፁን መንገር የግድ ነው። አርበኝነት የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄ መነሻና መዳረሻ በሚገባ ተረድቶና ከራስ ፍላጎት በላይ አስቀድሞ እስከመስዋእትነት የሚያደርስ ተጋድሎ እንጅ የራስን ፍላጎት ቴምፕሬቸር እየለኩ ደስ ሲል የሚሰሩትና ደስ ሳይል ደግም የሚተውት ወይም የሚርቁት ከቶ አይደለም ብሎ መንገር የግድነው። ለዘመናት ከዘለቅንበት የመከራና የውርደት ሥርዓት ወጥተን እውነተኛ ህዝባዊት፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ካለብን።
እናም አርበኝነት “በርሃ ነበርኩ” በሚል የይገባኛል ጥያቄ ብቻ የሚለካ ከቶ አይደለም። የእውነተኛ አርበኝነት ትርጉሙ አገር የነፃነት፣ የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና እስከምትሆን ድረስ ጠንካራውን ይበልጥ እያጠናከሩ፣ የደከመውን እያበረታቱ፣ የተሳሳተውን በምክንያታዊነት በገንቢነት እያስተካከሉ ፣ የተራራቀውን እያቀራረቡ፣ ትግሥትና ጥበብ የጎደለውን እያሟሉ፣ ከጎሳ(ከመንደር) ፖለቲካ ልክፍት እራስን ነፃ እያወጡ፣ የተናጠልን ሳይሆን የጋራ (አገራዊ) ራእይንና እጣ ፈንታን ኢላማ እያደረጉ ወደፊት የመገስገስ የፖለቲካ ሰብእና ነው።
ይህ ሥራ ግን ከቶ ቀላል አይደለም ። ከየድርጅቱ በየምክንያቱ እያኮረፈ እራሱን በማግለል በጥላቻና በስም ማጥፋት ዘመቻ የተለከፈው (የሚለከፈው) ፖለቲከኛና ታጋይ ነኝ ባይ እየቀነሰ ሳይሆን እንደ አሜባ እየተራባ ሲጨመርበት ደግሞ የባሰውን ይከብዳል።
እንዲህ አይነቱን እኩይ አስተሳሰብና አካሄድ በቁርጠኝነትና በገንቢነት ታግሎ ከማሸነፍና ለአገራዊ የጋራ ራእይ እውን መሆን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ከማድረግ ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ የለም ። አዎ! በየምክንያቱ በመኮራረፍና ትንንሽ አንጃዎችን በመፈልፈል የተሞከሩ የነፃነትና የፍትህ እንቅስቃሴዎች በአጭሩ እየተቀጩ ለዘመናት የመከራና የውርደት ቀንበር አሸካሚ አምባገነኖች ሰለባ ሆነን የመዝለቃችን አስቀያሚ ተሞክሮ መሪር ትምህርት ሊሆነን ይገባል። በዚህ አይነት የፖለቲካ ባህላችንና አስተሳሰባችን ነው የአምባገነን ገዥዎችን እድሜ እያራዘመን የመከራና የውርደት ሰለባዎች ሆነን ዘመናት ያስቆጠርነው ። የማራዘሙ የፖለቲካ ታሪካችን የሩቅ ታሪክ አይደለም ። አሁንም ትግሉን ሀሁ ብለን ጀመርን እንጅ ወደ ኋላ ላለመመለሳችን ገና እርግጠኞች አይደለንም ።
በራስ ወዳድነትና የይገባኛል ጥያቄ ኩርፊያ ከየድርጅቱ እራስን በማግለል ከተቻለ የየራስን አንጃ የመፍጠርና ያ ካልሆነ ደግሞ የተደራጀውን የማፈራረስ እጅግ ክፉ የፖለቲካ ባህልና አስተሳሰብ ከአሁን በኋላ በዚህች መከራና ውርደት በተረባረቡባት አገር ጨርሶ ቦታ ሊኖረው አይገባም ።