የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ጠንካራ የተባለ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ !!

የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ጠንካራ የተባለ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ !!

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/ ፡ – የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን በመጠናቀቅ ከዚህ በፊት ከሚያወጣቸው መግለጫዎች ለየት ባለ መልኩ ጠንካራ የአቋም መግለጫ በማውጣት ስብሰባውን መጠናቀቁ ተገለጸ።

በተለያዩ የክልሉ ችግሮች ዙሪያ በሰፊው መወያየቱን በመግለጫው ያሰፈረው የአዴፖ መገለጫ በክልሉ በሙስናና ብልሹ አሰራር ህዝብን ያለምንም ምህረት ሲመዘብሩ ነበሩ አካላት ላይ ማስረጃ በማሰባሰብ እርምጃ መውሰድ መጀመሩንና በቀጣይም በሰብአዊ አያያዝ ላይ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ሁለት ስልት ያለው ሰይፍ ይዞ እንደሚታገል እና  ተጠያቂዎችን በሰከነ መልኩ ሕግ ፊት ለማቅረብ እንደሚሰራ ይፋ አድርጓል።

የወሰንና የማንነት ጉዳይ “ሌሎች ይሰሩታል፤ በህገ-መንግስቱ ይፈታል” ከሚሉ ለዘብተኛ አቋሞች በመውጣት ለመታገል መወሰኑን  በመግለጫው  የገለጸው አዴፖ በትኩረትና የአካባቢውን ታሪካዊ ዳራ ጭምር ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ የማንነት ጥያቄው እንዲፈታ ቀጣይነት ያለው ትግልና ክትትል እንደሚደረግ፤ ቃል ገብቷል።

በመቀጠልም በአገር አቀፍ ደረጃ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመው የወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል።

በሌላ በኩል መግለጫው በምእራብ ጎንደር እና ልዩ ልዩ ቦታዎች ፓርቲው በጸጥታ ስራ ላይ ብቻ እንዲያተኩር እና መሰረታዊ የልማት ስራዎች እንዳይሰሩ የሚያደርጉ ቡድኖች እና ግለሰቦች መኖራቸውን ገልጾ በንቃት እንደሚታገል አመልክቷል።

በምእራብ ጎንደር ግጭት መንስኤ የሆነው ሱር ኮንስትራክሽንም ሆነ ያለ አግባብ በዜጎች ላይ እርምጃ የወሰዱ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የተጀመረው ማጣራት በፍጥነት እንዲጠናቀቅና እርምጃ እንዲወስድ አጠናክሮ እንደሚሰራ አስምሮበታል።

የለውጥ ሂደቱ በተሳካ መልኩ እንዲቀጥል አዴፓ ከሌሎች አጋርና እህት ድርጅቶች ጋር አብሮ እንደሚሰራ ገልጿል።

የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሙሉ የአቋም መግለጫ!!

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥር 13-15/2011 ዓ.ም ድረስ መደበኛ ስብሰባ አካሂዷል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ለውጡ በደረሰበት ደረጃ፣ በተለይም ለውጡ በአስገኛቸው አገራዊና ክልላዊ ቱሩፋቶች እንዲሁም ለውጡ ባጋጠሙት ፈተናዎችና በ12ኛው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ያስተላለፋቸውን ውሣኔዎች አፈፃፀም ገምግሟል፡፡ በዝርዝር ከገመገመ በኋላ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል ፡-

1. በክልላችንም ሆነ በሃገራችን መሠረታዊና ቀጣይነት ያለው ለውጥ እንዲመጣ ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከመላው ህዝባችን ጋር በመሆን ተከታታይነት ያለው ትግል አኳሂዷል፡፡ ትግሉ ለዘመናት የተከመሩ ችግሮቻችንን ስርዓት ባለው መንገድ ለቅሞ የመፍታት እና ትርጉም ያለው ለውጥ የማምጣት እንደመሆኑ መጠን በአንድ ጀንበር የሚጠናቀቅ፣ ያለፈተናም የሚታለፍ ሆኖ እንደማይገኝ አስቀድሞ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የተጀመረው ጥልቀትና ቀጣይነት ያለው የለውጥ ጉዞ ፈተናዎች እየተጋረጡበት ይገኛል፡፡ በተለይም የተጀመረው ለውጥ ስር እንዳይሰድ፤ መሰረቱ እንዳይሰፋና ቀጣይነቱ እንዳይረጋገጥ ለማድረግ ፀረ-ለውጥ ቡድኖችና ግለሰቦች ሁሉን አቀፍ የሆነ አቅማቸውን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፡፡ የአማራ ክልልን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል በማድረግ ማተራመስ ቀዳሚው አጀንዳ ተደርጎ እንደተወሰደ ማዕከላዊ ኮሚቴያችን ገምግሟል፡፡ ፀረ-ለውጥ ሃይሎች የሚጠቀሙት ስልት ባለፉት ዓመታት የነበሩ ስህተቶችንና ይቅርታ የተጠየቀባቸውን ጉዳዮች ሁሉ እንደ አዲስ በማራገብ ህዝባችን በድርጅታችን ላይ ያሳደረውን ተስፋ በማስቆረጥ ጥላቻ እንዲፈጠር ማድረግ፤ በትንንሽ አጀንዳዎች በመጠመድ ህዝቡ ወደ ልማት ስራ እንዳይገባ በማድረግ፤ መንግስትም ሁሌ በጸጥታ ስራ ላይ ብቻ እንዲወሰን፤ በህዝባችን መካከል የተለያዩ ጥርጣሬዎች እንዲፈጠሩ እና አማራን የሚያዳክም የተለያዩ ሴራዎች በየቀኑ እንደሚፈለፈሉ፤ አንዱን ከሌላው ጋር የሚያጋጭ እና እምነት የሚሸረሽር ስራ የሚሰራ መሆኑን ድርጅታችን በግምገማው አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ለውጣችንን ለመቀለበስ ጥረት የሚያደርጉ ሃይሎችን ያለምህረት መታገል እንደሚገባ ስምምነት ተይዟል፡፡

ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም ከዳተኝነትና ለዘብተኝነት እንዲሁም ከይሉኝታ ፖለቲካ ወጥቶ በቁርጠኝነት የህዝባችንን ጥቅም ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተገንዝባችሁ፤ ለዚህ ተልዕኮ መሳካት ወሳኙ ቀዳሚ ጉዳይ በክልላችን ህግ የማስከበርና ሰላም የማረጋገጥ ተልዕኳችን በተሣካ ሁኔታ መፈፀም የሚገባን መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው ትኩረት ሰጥቶ ገምግሟል፡፡ ይህ ካልሆነ ማየት የጀመርነው የለውጥ ጭላንጭል መልሶ ሊጠፋ እንደሚችል ተገንዝበን መላው ህብረተሰብ በተለይም ወጣቶች የጀመራችሁትን ህግ የማስከበር ተግባር አጠናክራችሁ ከአመራራችንና ከፀጥታ አስከባሪዎቻችን ጎን በመሰለፍ ለውጡን በጋራ ከማንኛውም ጥቃት እንድንከላከል ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪውን ያስተላልፋል ፡፡

2. በምዕራብ ጎንደርና በማዕከላዊ ጎንደር የተፈጠረውን የዜጎቻችን ሞት፤ ንብረት መውደምና ከቀያቸው መፈናቀልን በተመለከተ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ በዝርዝር ገምግሟል፡፡ በተፈጠረው ችግርም ከልብ አዝኗል፡፡ ለተፈጠረው ችግር መነሻ ለሆነው የሱር ኮንስትራክሽን ድርጅትና በዜጎቻችን ላይ ያልተገባ እርምጃ በወሰዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የተጀመረውን የማጣራት ስራ በፍጥነት በማጠናቀቅና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለህዝባችን እንዲገለፅ ውስኗል፡፡ በሌላም በኩል በቀጠናው የሚታየው ባዕድ ጦርነትና ግጭት እንዲያበቃና ከዚህ በኋላ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን፤ ዜጎቻችን እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ኑሮአቸውን ተረጋግተው እንዲመሩ፤ በደረሰው ጉዳት የተፈናቀሉ እንዲቋቋሙ፤ አካላዊም ሆነ ሞራላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖቻችን ትኩረት ሰጥቶ በመደገፍ በቁርጠኝነት እንዲሰራ ማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ አሳልፏል፡፡

3. የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ውሳኔ ያስተላለፈበትን የወሰንና የማንነት ጉዳይ “ሌሎች ይሰሩታል፤ በህገ-መንግስቱ ይፈታል” ከሚሉ ለዘብተኛ አቋሞች በመውጣት በትኩረትና የአካባቢውን ታሪካዊ ዳራ ጭምር ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ጥያቄው እንዲፈታ ቀጣይነት ያለው ትግልና ክትትል እንደሚደረግ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመው የወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ የጉባዔያችን ውሳኔ ዳር ለማድረስ ማዕከላዊ ኮሚቴያችን በቁርጠኝነት ስራውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በድጋሜ አረጋግጧል፡፡

4. የአማራ ህዝብ በታሪክ አጋጣሚ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በስፋት ተሰባጥሮና ተዋህዶ እንደሚኖር የሚታወቅ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ህዝባችን ከየሚኖሩበት አካባቢ በተለያየ ምክንያት ተፈናቅለው በየአካባቢው በጊዜያዊ መጠለያዎች በችግር ውስጥ ህይወት በመግፋት ላይ እንደሚገኙ ማዕከላዊ ኮሚቴያችን በዝርዝር ገምግሟል፡፡ በመሆኑም ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የዕለት ቀለብ የማቅረብና መጠለያ የማመቻቸት ስራ የሚቀጥል ሲሆን ጎን ለጎንም ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታበት አግባብ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ለተግባራዊነቱም ሌት ከቀን ስራዎች እንዲሰሩ ተወስኗል፡፡

5. የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ ከአስፈለገ በኢኮኖሚ አቅሙ ጠንካራ የሆነ ህዝብ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ አመራር ማረጋገጥ እንደሚገባ ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በፅኑ ያምናል፡፡ ድህነት ሁለንተናዊ አቅምን እንደሚሰልብ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም የክልላችንን ኢኮኖሚ የማሣደግ ጉዳይ ተኪ የማይገኝለት ተልዕኮ ነው፡፡ የግብርና ልማት ሥራችን በተለይም የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ተግባራት የእያንዳንዱን አርሶ አደር ጎጆና አካባቢ ጭምር መለወጥ በሚችልበት ሁኔታ እንዲመራ ማድረግና ለመጭው ጊዜ የመኽር ሰብል በቂ ዝግጅት አድርጎ ምርትን ማሣደግ የችግሮቹ ሁሉ ማለፊያ በር እንደሆነ ተገንዝበን ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ማእከላዊ ኮሚቴው አፅንኦት ሰጥቶ ገምግሟል፡፡ ከዚህ አኳያ መንግስትና ፓርቲያችን የተደራጀ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቃቸው ታውቆ አርሶ አደሩና የግብርና ባለሞያዎች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ታጥቃችሁ በመስራት የክልላችሁን ህዝብ ከድህነት እንድታወጡ ጥሪ ቀርቦላችኋል፡፡ ስራ አጥነት የወጣቶቻችን አስከፊና መሠታዊ ችግር እንደሆነ ዘላቂነት ባለው መንገድ ችግሩ እንዲፈታ ለየት ያለ ሥራ መሠራት እንዳለበት ማዕከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ በተለያየ ምክንያት ከጊዜ ጊዜ ሲወሣሰብ የመጣው ይህ ችግር እውቀትን ፣ ገንዘብ /ካፒታል/ እና ጉልበትን በላቀ ሁኔታ አጣምሮ በመጠቀም ወጣቶች ከድህነት መላቀቅ የሚችሉበት ርብርብ መካሄድ እንዳለበት ማዕከላዊ ኮሚቴው ወስኗል፡፡ ለዚህ ውሣኔ ተግባራዊነት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ከአፋዊነት ያለፈ ልባዊ ሥራ በመስራት ተያይዘን ወደፊት እንድንራመድ ማዕከላዊ ኮሚቴው አሳስቧል ፡፡

6. ሙስና እና ብልሹ አሰራር የስርአቱ መገለጫ ሆኖ እንደመቆየቱ መጠን የለውጡ ጉዟችንንም እያደናቀፈ አብሮን እንዲይኖር ሁለት ስለት ያለው ሰይፍ ይዞ መታገል እንደሚገባ ማዕከላዊ ኮሚቴው መክሯል፡፡ ከዚህ አኳያ የክልሉን ህዝብ ሃብት ያለምህረት ሲመዘብሩ በቆዩ አካላት ላይ በሰከነና በበሰለ መንገድ፤ ማስረጃዎችን መሰረት በማድረግ የፀረ-ሙስና ትግልና ህጋዊ እርምጃ መወሰድ የተጀመረ ሲሆን እርምጃው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ባደረሱ አካላትም ተጠናክሮ የሚቀጥልና በድርጊቱ ተሳታፊና ተባባሪ የነበሩ ቡድኖችና ግለሰቦችም በተመሳሳይ ለህግ እንዲቀርቡ ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትግሉን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ስለሆነም መላው ህዝባችን ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲና ከክልሉ መንግስት ጎን በመሰለፍ የተጀመረው የፀረ-ሙስና ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡

7. መላው የክልላችን ህዝቦች፤ ወጣቶች፤ ሴቶች፤ ባለሃብቶች፤ የመንግስት ሰራተኞች፤ አርሶ አደሮች፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ሲቪክ ማህበራት፤ የፖለቲካና የሚዲያ አክቲቪስቶች በሙሉ፡- አሁን የምንገኝበት ወቅት የሽግግር ወቅት በመሆኑ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ፤ በመቻቻልና በመተባበር መንፈስ መስራት፤ መደማመጥ የሚገባን ወቅት ነው፡፡ ይህን ሂደት አውቆም ይሁን ሳይረዳው የሚያደናቅፍ ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ሃይል አለ፡፡ በሂደቱም በክልላችን እያጋጠሙ ያሉ ህገ-ወጥ ድርጊቶች በዝርዝር ተለይተዋል፡፡ ክልላችን ሙሉ በሙሉ ሰላም የሰፈነበት መሆን አለበት፡፡ በዜጎቻችን ላይ ጥቃት እንዳይደረስ፤ ህገ-ወጥ ድርጊቶች እንዲታረሙ ህዝባችንን በማደራጀትና በማብቃት የምንቀሳቀስ ይሆናል፡፡ ከዚህ አልፎ ለሚመጣ ህገ-ወጥነት ህጋዊ እርምጃም የሚወሰድ መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ በመሆኑም ለአማራ ህዝብ ጥቅም ቆሜያለሁ የሚል ሃይል ሁሉ ለዚህ አቋም ተፈፃሚነት ከህዝባችን፤ ከፓርቲያችንና ከመንግስታችን ጋር በትብብር መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡

8. ወቅቱ መላ የአገራችን ህዝቦች አጋርና እህት ድርጅቶች ተደጋግፈንና አጥፊውን እያረምን እንድነታችንን አጠናክረን የምንቀጥልበት እንደሆነ ፓርቲያችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ያምናል፡፡ በተለይም ለረጁም ጊዜ የጉርብትና ብቻ ሣይሆን የተሣሰረ የደም ግንኙነት ከአለን የትግራይና የኦሮሞ ህዝብ ጋር በተባበረ ክንድ በመሥራት ለውጡን ቀጣይ የምናደርግ ሲሆን የአማራ ህዝብ ከነዚህ ህዝቦች ጋር እንዲነጠልና በጥላቻ መንፈስ እንዲተያዩ ለማድረግ የሚሰበከውን ዘመን ያለፈበት የጥላቻ ትርክት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንደማያምነበትና በፅኑም እንደሚታገለው ማእከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል ፡፡ ይህ ብቻ ሣይሆን የአማራ ህዝብ ወንድሞና ጎረቤት ከሆኑት ከአፍርና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝቦችና ከሌሎችም የሃገራችን ህዝቦች ጋር በመተባበር ህብረ ብሔራዊነትና ዴሞክሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚካሄደው ትግል ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ቃል በመግባት ጭምር ማእከላዊ ኮሚቴው ስብሰባውን አጠናቋል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ
ጥር 16 ቀን 2011 ዓ.ም
ባህር ዳር፤

LEAVE A REPLY