ድሬደዋ ዛሬም ተቃውሞ በሚያሰሙ ወጣቶች እንቅስቃሴ ሥር ውላለች

ድሬደዋ ዛሬም ተቃውሞ በሚያሰሙ ወጣቶች እንቅስቃሴ ሥር ውላለች

ቪኦኤ ዜና፡- ድሬደዋ ከተማ ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ ተቃውሞ በሚያሰሙ ወጣቶች እንቅስቃሴ ሥር ውላለች። ከትናንት ሌሊት ጀምሮ “መርመርሳ” በተባለ የመኖሪያ ሰፈር በጣም የተጋጋለ ውጥረት እንደነበር ነዋሪዎች ይናገራሉ። ውጥረት መኖሩ ለመከላከያና ለፌደራል ፖሊስ ሪፖርት በመደረጉ የከፋ ጉዳት ሳይከሰት በቦታው ቢደርሱም ንጋት አካባቢ መረጃው ለሌላው የከተማው ሕዝብ በመዛመቱ ተቃውሞው እየጨመረ መምጣቱን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።

መከላከያና ፖሊስ ብዛት ባላቸው በተፋጠጡ ወጣቶች መካከል በመቆም ግጭቱን ለማብረድ ሲሞክር እንደነበር ገልፀው አለፍ አለፍ ብሎ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር ተናግረዋል። ረፋዱ ላይ አንድ መንደር ውስጥ “መሳሪያ አለ” የሚል መረጃም በመሰራጨቱ ጠዋት ላይ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ይታይባቸው የነበሩት አብዛኞቹ የከተማዋ አካባቢዎችም ቀስ በቀስ ተቃውሞውን በመቀላቀል እኩለ ቀን ላይ የአብዛኛው አካባቢ መንገዶች ለትራፊክ ዝግ ሆነዋል። በአሁኑ ሰዓትም ወደ ከተማዋ የሚያስገባው ዋናው መንገድ ዝግ ሆኗል።

ወጣቶችም ቁጥራቸው እየተበራከተ ዋና መንገዶችን በድንጋይ፣ በእንጨትና በተለያዩ ነገሮች መዝጋታቸውን ዘጋቢያችን በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል። ጎማ በየቦታው በመቀጣጠሉ ከተማዋ በጭስ ታፍና ውላለች።

የተሰባሰቡት ወጣቶች የድሬደዋ ከተማ አሁን የምትተዳደርበትን 40፣40፣20 የካቢኔ መዋቅር በመቃወም “ድሬደዋችንን መልሱልን” ሲሉ ተሰምተዋል። ከተማዋ ውሃ፣ መብራት፣ መንገድና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ችግር ያለባት መሆኗን በመጥቀስም ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር ዘጋቢያችን ከስፍራው አድርሶናል።

LEAVE A REPLY