ትኩረት የተነፈገው የንግድና ኢኮኖሚው ዘርፍ | ይነጋል በላቸው

ትኩረት የተነፈገው የንግድና ኢኮኖሚው ዘርፍ | ይነጋል በላቸው

ብዙዎቻችን ብዙውን ጊዜ የምንጽፈውም ሆነ የምንናገረው ስለፖለቲካችን ነው፡፡ ስለወያኔ የቀድሞ አገዛዝና የግፍ ዶፍ አዘውትረን እናነሳለን፡፡ ስለ ለውጡ እንቅስቀሴና የጉዞ አቅጣጫ ነጋ ጠባ እናወሳለን፡፡ ሥጋታችንንና ደስታችንን በሚመለከት ከየጓደኞቻችንና ከምንቀርባቸው ሰዎች ጋር እንወያያለን፡፡ ጥሩ ነው፡፡

ንግዱንና ኢኮኖሚውን ግን ትተነዋል ወይም ከትኩረት አቅጣጫችን አውጥተነዋል፡፡ መንግሥትም በፖለቲካ ጉዳዮች ስለተወጠረ ይመስላል ይህን መሠረታዊ የዜጎች የኅልውና ነገር በወጉ አላተኮረበትም፡፡ እናም አሰለጦችና ምልናባትም የለውጡ ተፃራሪዎች ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ንግዱንና ኢኮኖሚውን በፈለጉት መንገድና አቅጣጫ እየመሩ ሕዝብን እያማረሩ ይገኛሉ፡፡ ችግሩ ደግሞ ቸል ተብሎ ሊታለፍ የማይገባው እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡

ዛሬ ጧት ነው፡፡ የተሣፈርንባት የጓደኛየ መኪና መንገድ ላይ ትበላሻለች፡፡ የጥገናው ሥራ ከርሱም ከኔም አቅም በላይ ይሆንና ባለሙያ እንጠራለን፡፡ ችግሯ ቤንዚን ወደ ሞተሩ በቅጡ አለማስተላለፍ ነው፡፡ የጎደላት ነገር መኖሩ ተነገረንና ተያይዘን ለግዥ ሄድን፡፡ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ በብር 15 ትገዛ የነበረች አንዲት የቤንዚን መርጫ ነቁጥ እምታህል ነገር አሁን ብር 250፣ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ በብር 5 ይገዛ የነበረ ግማሽ ሜትር የቤንዚን ሆዝ አሁን 86 ብር … ሆኖ አገኘንና ሁለታችንም በአግራሞት እየሣቅን ገዝተን ወደ መኪናዋ ተመለስን፡፡ ይህ ነገር መፍትሔ ካልተፈለገለት እጅግ አደገኛ አካሄድ መሆኑ ገባን፡፡ እኔም ሰሚ ባገኝ ብዬ ይህችን ማስታወሻ ለመጻፍ ብዕሬን አነሳሁ፡፡ ቢያንስ “እንዲህ ብለን ነበር” ማለቱም ጠጋ ነውና የሚሰማንን እንናገራለን፤ ብልኅ ከተገኘ ችግሮችን በጊዜው ለማተስካከል ይሞክራል፡፡ ካልሆነም የእግዜሩን ብቻ መጠበቅ ነው፡፡ ሌላ ምን አማራጭ አለ?

አንዳንድ ዋጋዎችን ላስታውስና እያወዳደርን የት እንደምንገኝና ወዴትስ እየሄድን እንደሆነ ለመረዳት እንሞክር፡፡

በነገራችን ላይ የአብዛኛው ዜጋ የወር ገቢና የወር ወጪ በፍጹም የማይቀራረብ ነው፡፡ በኪነ ጥበቡ የሚኖረው ዜጋ እጅግ ብዙ ነው፡፡ የወር ደሞዙ ብር 1000 ሆኖ ሰኞን ወደ ማክሰኞ፣ ጥርንም ወደ የካቲት የሚለውጥ ምሥኪን ዜጋ ታገኛለህ፡፡ እንዴት ሆኖ ብለህ ስትጠይቅ የረባ መልስ አታገኝም፡፡ በሌላው ጎራ በሃያና ሃምሣ ሽዎች የሚቆጠር ብር በየቀኑ ከቤቱ ይዞ በመውጣት ምሽቱን አሥረሽ ምቺው የሚል ወለፈንዴ ሞልቷል፡፡ ሀገራችን የተዓምራት መፍለቂያ ሆናለች፡፡ እርግጥ ነው – ብዙ ሰው ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበትን መንገድ ይፈጥራል፡፡ በዚያ ላይ ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ከዘመድ አዝማድና ከወዳጅ ድጎማ የሚላክላቸው ወገኖች አይጠፉም፡፡ ደሞዛቸውን የማያውቁና በሙስና ብቻ እንደፈለጉ ተንቀባርረው የሚኖሩ ደግሞ አሉ – ቁጥራቸውም ቀላል አይደለም፡፡ ማሰብ ያለብን ግን እነዚህን የተለዩ ወገኖች ሣይሆን በአንጡራ ደሞዙ የሚኖረውን ከርታታ ዜጋ ነው፡፡ እናም በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው ጥሩ ኑሮ ለመኖር በትንሹ ከ20 ሽህ ብር የማያንስ አስተማማኝ የወር ገቢ እንደሚያስፈልገው እኔ እንኳን ለቁጥር ባለኝ የማይም ስሌት ተነስቼ መገመት አያቅኝም፡፡ በዚህም ገንዘብ ተንደላቅቆ ሳይሆን አንደጊዜውና እንደነገሩ ለመኖር ብቻ ነው፡፡ እንጂ ኑሮው ስለጦዘ ገንዘባችን ቅጠል ሆኗል፡፡ ግፋፎ ወረቀት ከሆነ ቆዬ፡፡ የአሁኑ መቶ ብር መልክ ብቻ እንጂ ከአፄው ስሙኒ ያንሣል፡፡ ቆዳ መልስ በሁለት ብር ግልገል ፍየል እንዳልተበላ ዛሬ አንድ ተራ ጥብስ ባልተቀናጣ ተራ ቡና ቤት ብር 80 ነው፡፡

ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ለግንዛቤ ያህል ቀጣዮቹን አብነቶች እንመልከት፡፡

የማነጻጽርላችሁ ከ10 ግፋ ቢል ከ15 ዓመታት በፊት ከነበረው ዋጋ ነው፡፡ አንድ ሊትር ቤንዚን አሁን 19 ብር ከ69 ሣንቲም ነው – በቅርብ ዓመታት ከነበረው የአራትና አምስት ብር ዋጋ ተነስቶ እንዴት እንደተወነጨፈ ልብ በሉ፡፡ አንድ ሊትር የምግብ ዘይት በአማካይ 70 ብር፤ ከበርሜል የሚቀዳ አንድ ሊትር የሞተር ዘይት ከ14 ብር ገደማ ወደ 100 ብር “አዝግሟል”፡፡ 300 እና 400 ብር ገደማ የነበረው አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ ዛሬ ከ3000 በታች ከተገኘ ሉተሪ ነው – በሰው በላው የደርግ መንግሥት 50 ብር ግድም ነበር፡፡ አምናና ታች አምና 280 ብር ይገዛ የነበረ ባለ አምስት ሊትር የኅትመት ሥራን ማከናወኛ ፈሣሽ ኬሚካል ዛሬ ብር 1800 እንደገባ ዕቃውን እያሳየኝ አንዱ የመሥሪያ ቤቴ አባል ነግሮኛል፡፡ በአጭሩ ገበያው አብዷል ማለት እንችላለን፡፡ የሚገርመው ደግሞ ተቆጣጣሪ አለመኖሩ ነው፡፡ ሠላሣ ብር የገዛሁት ባለ12 ቁጥር የአርማታ ብረት (ፌሮ) ዛሬ ከ400 ብር በላይ ነው፤ በ29 ብር የገዛሁት ባለ 10 ቁጥሩ ፌሮ አሁን 220፣  በ18 ብር የገዛኋት ባለ 8 የምትባለዋ የመጨረሻዋ ቀጫጫ ፌሮ ብር 220፤ 1200 ብር ከደብረ ዘይት ያስመጣሁት ባለ16 ሜትር ኩብ አሸዋ አሁን 9000 ብር… ነው፡፡ አያምጣብን እንጂ አዲስ አበባ የ3 እና 4 ሬክተር ስኬል የመሬት መራድ ቢጋጥማት ይሄ በዕቃ ውድነትና በገንዘብ ቁጠባ ምክንያት በሚፈጠር መስቆንቆን ወይም በሙስና ትስስር ከደረጃ በታች በሆነ ቁሣቁስ የተሠራ ሕንፃ ሁሉ በደቂቃ ውስጥ ወደ ፍርስራሽነት መለወጡ አይቀርም፡፡ ነገሮች ሁሉ የተያያዙ ናቸው፡፡

ምግብና ሸቀጦች፣ የግንባታ ዕቃዎች፣ የህክምና መገልገያዎች፣ ህክምናው ራሱ(ለትንሽ የጤና ችግርህ በእግርህ እየሮጥክ የገባህበት ሀኪም ቤት  በህክምና ስህተት የገደሉህን ያንተን ሬሣ ቤተሰቦችህ እንዲወስዱ 50 እና 100 ሽህ ብር ሊጠየቁ ይችላሉ – አንተ ግን ያን ጉድ ስለማታይ ዕድለኛ ነህ!)፣ የአገልግሎት ክፍያዎች…. ከአብዛኛው ሕዝብ የገቢ መጠንና የመክፈል አቅም ጋር ፈጽሞ የሚመጣጠን አይደለም፡፡ ተራው የመንግሥትና የግል ተቀጣሪማ መኖር ካቆመ ሰንብቷል – ዋና ሥራው ማኗኗር ብቻ ነው፡፡ አብዛኛው ዜጋ በገዛ ሀገሩ የበይ ተመልካች ከሆነ ቆይቷል፡፡ ሁሉም ዜጋ እኩል የሚሆነው ሲሞት ብቻ ነው፡፡ አያ ሞት ብቻ ነው ትክክለኛ ፍርድ የሚሰጠው፡፡ እንጂ በሌላው ነገር ዜጎች ተለያይተዋል፡፡ ልዩነታቸው ደግሞ መሥፈሪያም የለውም፡፡ ይህን ችግር ለመርሳት መሞከር የግፈኞችን ኩባንያ ወዶና ፈቅዶ እንደመቀላቀል ይቆጠራልና በተለይ የሥራ ኃላፊዎች በአፋጣኝ ወደኅሊናችሁ ተመለሱ፡፡ ተመልሳችሁም ሕዝባችሁን ከሲዖላዊ የኑሮ ወላፈን አውጡት፡፡ በጉጉት እየጠበቃችሁ ነውና ፈጥናችሁ ድረሱለት!

አዎ፣ ለሕዝብ እጨነቃለሁ የሚል የመንግሥት አካልና የሥራ ኃላፊ የተራውን ሕዝብ የዕለት ከዕለት ሕይወት በወቅቱ አማርኛ መሬት ድረስ ወርዶ በመቃኘት መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ መሠረታዊ ፍላጎቱ ያልተሟላለት ሕዝብ በሁሉም ረገድ የወረደ ስብዕና እንደሚኖረው መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በአግባቡ ያልተመገበ ሰውነት ትምህርት አይገባውም፤ በአግባቡ ያላደገ ሕጻን ትልቅ ከሆነ በኋላ ተስተካከል ቢሉት ይሰበራል ወይም ይሰብራል እንጂ ሊቃና አይችልም፡፡ ብዙ ነገሮች ከአመጋገብና ከኑሮ ዘይቤ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ድህነት ደግሞ የሞራል ድንበርን አያውቅም፤ የሃይማኖት ምግባርን አይረዳም፤ የባህልና ወግ ትውፊትን አይገነዘብም  – እንደ እንስሳና ከእንስሳም በታች ያደርግና ሀገርን ወደከፋ አዘቅት ሊወረውር ይችላል፡፡ የተጎሳቆለ ሰውነት ይዘህ ዴሞክራሲን አሰፍናለሁ ብትል የሚሰማህ የለም፤ ሆድ እየጮኸ – ወስፋት እየተንጫጫ – ሰውነት እየታረዘ … ስለምርጫና ስለ ህገ መንግሥት ማውራት ቅንጦት ነው፡፡ ቀድሞ የመቀመጫየን ብላለች ዝንጀሮ፡፡ ስለዚህ በአካልም በአእምሮም በኅሊናም በሃይማኖትና በሞራልም እየጫጫን ለመሄዳችን ዋናው ጦስ የኢኮኖሚው ዘርፍ በቅጡ አለመያዙና ያንንም ተከትሎ በተፈጠረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህን ችግር ለማስተካከል ጊዜ ካለን እንሩጥ! አቅም ያለን፣ ሥልጣን ያለን ዕንቅልፍ አይመረን!

ይህ ችግር ለነገ የሚተው አይደለም፡፡ ኳሻርኳራዊው ሸፋፋ ኢኮኖሚያችንና  በጥቂቶች ፍላጎት እንደፈረስ የሚጋልበው የንግዱ ዘርፍ በአፋጣኝ ተገቢውንና ትክክለኛውን የመንግሥት ትኩረት ካላገኘ ከፊት ለፊታችን ብዙ ችግር ይጠብቀናል፡፡ በስመ ዶላርና የውጭ ምንዛሬ ዕጥረትና የገንዘብ ምንዛሬ መዋዠቅ  አዳሜ እየተነሣ ዋጋ የሚከምር ከሆነ ሀገር አትረጋጋም፡፡ አንድ ኪሎ የኢትዮጵያ ከብት ሥጋ በአማካይ 400 ብር እንድንመገብ የተገደድንበት ምክንያት ከብት በዶላር ስለሚመጣ አይመስለኝም፡፡ ውሻ በቀደደው ጅብ እየገባ በአልጠግብ ባይ ነጋዴዎችና አሻጥረኛ የሥራ ኃላፊዎች ሸፍጥ የተሞላበት ቁርኝት ምክንያት አላግባብ መጎዳት የለብንም፡፡ ደግመን ለማንፈጠርባት ቅጽበታዊ የምድር ኑሮ አንዳችን ሌላኛችንን በኑሮ የእሳት አለንጋ እየገረፍን መኖራችን የኋላ ኋላ ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ማወቅ አለብን – በዚህኛው ዓለም ባይሆን በዚያኛው፡፡ ግራና ቀኝ መተያየት ይገባናል፡፡ ለአንድ ልጁ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ለአሜሪካን ትምህርት ቤት (ICS – International Community School (American)) የሚከፍል ነጋዴ ወላጅ፣ በየሴሚስተሩ አውሮፓና አሜሪካ ቤተሰቡን የሚያዝናና ቅንጡ ነጋዴ፣ በየሣምንቱ መጨረሻ ሶደሬና ላንጋኖ ቤተሰቡን የሚያቀማጥል መካከለኛ ባለሀብት… በቀን አንዴ እንኳን አሸርባሸር ቀምሶ ማደር የሚሣነውን አጠገቡ የሚገኝ ድሃ ዜጋ ማስተዋል ካቃተው የአንድ ሀገር ዜግነቱ ይቅርና እንደሰው በሰውነት ደረጃ መቆጠሩ ራሱ ያጠራጥራል፡፡ አንጎል የተፈጠረው ለማሰብ ነው – አንገት የተፈጠረውም አዙሮ ለማየት፡፡ ስለዚህ ነጋዴውም መንግሥትም ድሃውን ያስቡት፡፡ የድሃው በኑሮ መጎዳት በቃላት መግለጽ እስከሚያቅት እጅግ ዘግናኝ እየሆነ ነው፡፡ …. የታየኝንና የመሰለኝን ተናግሬያለሁ፤ በቃ፡፡

በመጨረሻም አንድ ለየት ያለች ነጥብ በእግረ መንገድ ጣል ላድርግና ልሰናበት፡፡

ትናንት ማታ በናሁ ቲቪ – ይመስለኛል – ወንድሜ አቶ ሌንጮ ባቲ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር ሲወያይ ዐይን ጣለኝና የደረስኩበትን ሰማሁ፡፡ ግን ባልሰማ ደግሞ ወደድኩ፡፡ የወንድሜን ንግግር የሚሰሙ ብዙ ኦሮሞዎች፣ ብዙ ተጋሩ፣ ብዙ አማሮች ብዙ ሌሎች እንደሚኖሩ እገምታለሁ፡፡ ምን ሊሉና ምንስ ሊሰማቸው እንደሚችል አላውቅም፤ ባውቅ ደስ ባለኝ፡፡ እኔም በታሪክ አጋጣሚ ዕድሜየ ወደ ታሪክነት እየተለወጠ ያለሁ ግለሰብ ነኝና – አለመላው በደርግና በወያኔ ተጨርግዶ የኖርኩበት ዘመን ከአሥር ባይበልጥም – ከሚነገሩ እውነቶችና ውሸቶች መሀል የተወሰኑትን በአካል ባሳልፍኩት ገጠመኝ የማወቅ ዕድል ነበረኝ፡፡

ወንድሜ ሌንጮ ብዙ መልካም ነገሮችን ተናግሯል – ወደድኩለት፡፡ ያሳዘነኝ ግን – በገደምዳሜ ልጥቀስ – “ በዚያን ዘመን ኦሮሞን በሥልጣን ቦታ ማየት ብርቅ ነበር፡፡ አንድ ኦሮሞ እንዲያው እንዳጋጣሚ አስተማሪ እንኳ ሆኖ ካየን ግር እያልን በአድናቆት እንመለከት ነበር… ኦሮሞ በጣም የተጨቆነ እንደዜጋም የማይቆጠር ፍጡር ነበር…”፡፡ (“በስማም!” ብላችሁ አማትቡ፡፡)

በውነቱ እጅግ አፍሬያለሁ፡፡ እኔ የማውቃት ኢትዮጵያና አቶ ሌንጮ ባቲ የሚያውቃት ኢትዮጵያ ሰማይና ምድር ሆኑብኝ፡፡ እርግጥ ነው – እውነት አንጻራዊ ናት ልትባል ትችል ይሆናል፡፡ ይህን ያህል አንጻራዊ ሆና ነጭን ቀለም ጥቁር ታደርጋለች ብዬ ግን አላምንም፡፡ ለምንም ዓላማ መዋሸት ቢያስፈልግ ገደብ ልናበጅለት ይገባል – መዋሸት ያለ ነውና ሰው አይዋሽ አይባልም – ባይሆን መልካም መሆኑ እንዳለ ሆኖ፡፡ እንዳመጣልን የምንዋሽ ከሆነ ወይም ለምክንያት ሳይሆን ለስሜት ቅርብና ተገዢ ሆነን የተነገረንን ሁሉ ሳናጣራና ሳናመዛዝን እንዳለ የምናስተላልፍ ከሆነ ሰው ዝም ቢል ሣር ቅጠሉ ይታዘበናል፡፡ በዚያ ላይ ፈጣሪ የሚባል አለ፡፡ ፈጣሪንም ብንረሳና ባናምንም ትንሹ እግዚአብሔር የምንለው የገዛ ኅሊናችን አለ፡፡  ወንድሜ ሌንጮ ባለፈበት ዕድሜ እኔም በማለፌና የተባለው ነገር ስለመፈጸሙ ምንም ዕውቀት ስለሌለኝ ወይም እርሱ ሀሰት ስለተናገረ ከሁለት በአንድኛችን አፈርኩ፡፡ ያለው ነገር ትክክል ቢሆን ኖሮ ትንሽም ብትሆን ትውስታ ትኖረኝ ነበር፡፡ ግን ፈጽሞ ሀሰት ነው፡፡

ለነገሩ “እውነትን ተናግሮ ሰውን ከማጣላት፣ ሀሰትን ተናግሮ ማፋቀር የተሻለ ነው” በሚለው ስለማምን አቶ ሌንጮ የተናገረው ሀሰት ነገር እውነት ቢሆንም እንኳን አሁን ሊነገር አይገባውም ነበር – “ለምን አሁን?” “ምን ተፈልጎ?” መባልን ያስከትላል፡፡ አንድን በምናብ የተፈጠረን ችግር በእውን በሌለበት ሁኔታ እያነሱ መቆዘሙ ጤነኛነትን አያሳይም፡፡ ያለንበት ውስብስብ ችግር ከበቂ በላይ ሆኖ ሳለ የዛሬ ሃምሣና ስልሳ ዓመት ገደማ ተፈጽሟል በተባለና ባልተረጋገጠ ታሪክ ወርቃማ ጊዜን ማባከኑ አሁንም ትርፍ የሌለው እንዲያውም የረጋን ውኃ ለማደፍረስና ማንም እንዳይጠጣው ለማድረግ የታቀደ የሚመስል የማወክ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ንግግር ማንም ምንም አያተርፍም፡፡ ኦሮሞዎች ራሳቸው የሚታዘቡት ንግግር ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ የማወቅንና የመጠበብን ፀጋ በቅጡ ብንጠቀምበት እናተርፍበታለን እንጂ አንከስርበትም፡፡ አወንታዊ ውጤት ልናመጣበት በሚያስችለን ኃይል(Energy) አሉታዊ ውጤት ለማምጣት ለምን እንደምንተጋ ሳስበው ይገርመኛል፡፡

እንዲህም ስል በቀድሞ ዘመን ችግር አልነበረም ማለቴ አይደለም፡፡ ይነሱም ይብዙም ከየትኛውም ወገን የሚነሱ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አይከብደም፡፡ ጊዜውን ማየት ነው፤ የንቃት ደረጃን መረዳት ነው፤ የቴክኖሎጂንና የትምህርት የዕድገት ደረጃዎችን ልዩነት ማጤን ነው፤ ትውልድ ደግሞ ወደፊት ይጓዛል እንጂ ወደኋላው እየዞረ ማላዘን የለበትም፤ እንደዚያ መሆንም የዱሮው ኋላቀር  አስተሳሰብ ባርያ መሆን ነው፡፡ ፈረንጆቹ እንኳን ነፍስ አውቀው It’s no use crying over spilled milk ይላሉ፡፡ በሀገር ግንባታ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ “ጨቋኝ”ይባል ከነበረው በተግባር ግን በስሙ ከተነገደው የአማራ ነገድ የሚመጡ ዜጎች ራሳቸው የጭቆናው ተጋሪ እንደነበሩ እኔ ራሴም ምሥክር ነኝ፡፡ አጎቴ ጓንጉልና አክስቴ አንጓች አዲስ አበባ ሲመጡ በስማቸው ምክንያት ሰው ጥርሱን ተወቅሮ እየሳቀባቸው እንዴት እንደተሳቀቁና ወዲያውኑ ያን ጠንቀኛ ስማቸውን ወደ እስክንድርና ወደ ሠናይት እንደለወጡ የማውቀው እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ስለዚህ ጥቃቅን ነገሮችን እያስታወሱ ሰውን ሆድ ማባስ የጋራ ሀገር እንዳትኖረን ከሚሹ ወገኖች የሚሰነዘር መርዘኛ ሃሳብ በመሆኑ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ ሁልጊዜ የዋህ እንደሆንላቸው ከኖርን እነሱም እንደተጫወቱብን ይኖራሉ፡፡ በክፍተቶቻችንም እየገቡና አስፈላጊውን መራጃ እያቀበሉ በጀመርነው መንገድ እርስ በርስ እንድንጠፋፋ ያደርጉናል፡፡ ካለፉት 30 እና 40 ዓመታት ብዙ ካልተማርን እግዜሩ ራሱ ወርዶ ወንበር ዘርግቶ ቢያስተምረንም አይገባንም፡፡

የሆኖ ሆኖ አቶ ሌንጮ በተናገረው መልክ የተጋነነ ልዩነትና በደል እንዳልደረሰ እኔም በሕይወት የምገኝ ምሥክር ነኝ፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ስንናገር ቢቻል እውነት መሆናቸውን ብናረጋግጥ፣ ካላወቅን ሰውን ብንጠይቅ፣ በሰዎች መካከል ቅያሜና ግጭት የሚፈጥሩ ስለመሆናቸው ግንዛቤ ቢኖረንና ሰውን ከማጋጨት ብንቆጠብ፣ ለቅስቀሳ የምንፈልገውን ሃሳብ ለትዝብት በማይዳርገንና አጸፋው ልንቆጣጠረው በማንችለው ሁኔታ እንዳይመጣብን ብንጠነቀቅ መልካም ነው፡፡ ይህን መልእክቴን ወንድሜ ሌንጮ ባቲ ያገኘዋል፣ ይረዳኛልም ብየ እገምታለሁ፡፡ በኔ አካባቢ ለምሣሌ ብዙ የኦሮሞ መምህራን ነበሩ፣ ኦሮሞ ለብርቅነት ሳይሆን በብዛት ተሰልፎ ሀገሩን ያቀና፣ በጦርም፣ በሰላምም፣ በአስተዳደርም፣ በደኅንነትም፣ በከፍተኛ አመራርም፣ በንጉሥነትም … በሁሉም ዘርፍ ገብቶ ያገለገለና እያለገለ ያለ እንጂ በዚህ በአቶ ሌንጮ በተነገረው መልክ ስለኦሮሞ መናገር ለኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ ስድብ ነው – የተባለውንና የሚባለውን እውነት ለመድገም ያህል ያለ ኦሮሞ ኢትዮጵያን ማሰብ ከቶውንም አይቻልም፡፡ እንኳንስ የኦሮሞ ልሂቃንና በቁጥር አነስተኛ ከሆኑ ሌሎች ነገዶችም የወጡ ምሁራንም በሀሰት ሰነድ ሕዝባቸውን ለምሬትና ለዐመፅ ለመገፋፋት አልቃጣቸውም – ይህ ነገር በአፋጣኝ መታረም አለበት፡፡ እየተስተዋለ ቢሆን ጥሩ ነው …. ወዳጄ ፕሮ. ፍቅሬ ቶሎሣም በዚህ በኩል ዝም አትበል፡፡

… በመጨረሻም … በአእምሯችን ቋጥረን የያዝናትን ትንሽዬ የግል ፍላጎት ለማሳካት ስንል ብቻ ሰማይንና ምድርን የሚያለብስ የሀሰት ድሪቶ ከመስፋት ተቆጥበን ስለአሁኑና ስለወደፊቱ የጋራ ኑሯችን እናስብ፡፡ ከከረቸምንበት ጠባብ የብረት ሣጥን ራሳችንን ነፃ ካወጣን ይህም ይቻላል፡፡ የማይቻለን ነገር እውነትን በሀሰት ሸፍነን ለዘላለም ደብቀን ማኖር ነው፡፡ ራሷ አንድ ቀን ትገለጣለችና፡፡

LEAVE A REPLY