የጌታቸው አሰፋ ስውር እጆችና ብሔራዊ አደጋ | ክንፉ አሰፋ

የጌታቸው አሰፋ ስውር እጆችና ብሔራዊ አደጋ | ክንፉ አሰፋ

                         /ኢትዮጲስ ጋዜጣ የቅዳሜ እትም/

በኢትዮጵያ የለውጥ ሃዲድ ላይ እንደጅብራ የተገተሩ ሁለት እንቅፋቶች እንዳሉ ማንም አይክደውም። መቀሌ ለፌደራል መንግስት ያለመገዛት እና ጌታቸው አሰፋ ከርቀት የሚነዳቸው ትሮጃን ፈረሶች። እነዚህ እንቅፋቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የባቡሩን ፍጥነት ቢቀንሱት፣ አልያም ቢያቆሙት ሊደንቀን አይገባም። ራሳቸው ባበጁልን የባንቱስታን ክልሎች ከርቀት በሚለኩሱት እሳት የተፈጠረው መፈናቀል ጀምሮ የፌደራል ሰራዊትን እስከ ማገት ደርሰዋል። ፌደራል መንግስት የሚጫወተው የእሽሩሩ ፖለቲካ ምን ያህል ርቀት ሊያስኬድ እንደሚችል አናውቅም።

ህወሃት ሲያሻት ኢትዮጵያን መፍጠር ሳያሻትም ማፍረስ እንደምትችል በተግባር ለማሳየት ስትሞክር፣ ማእከላዊ መንግስቱ ደግሞ ኢትዮጵያን ያቆማት ምሰሶ መቀሌ ያለመሆኑን በተግባር ማሳየት አልቻለም።

“ኢትዮጵያ ልትበተን ትችላለች” የሚለው የነጮቹ መላ ምት የሚነሳው እዚህ ላይ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት የዋሺንግተኑ “ፎረይን ፖሊሲ” መጽሄት፤ “በኢትዮጵያ የጎሳ ፌደራሊዝም ፈተናዎች” በሚል ርዕስ በለቀቀው ጥናታዊ ጽሁፍ ኢትዮጵያ ቀጣይዋ ዩጎዝላቪያ የመሆን እጣ እንደሚጠብቃትስጋቱን ገልጿል። ጽሁፉ ይህን ርዕስ በዚህ ፈታኝ ወቅት ያነሳው ያላንዳች ምክንያት አልነበረም። “በጎሳ ግንብ የታጠሩ የፌዴራል መንግስቱ ቦንቦች፣ ነጻ የፖለቲካ አየር መንፈስ ሲጀምር ሊፈነዳዱ ይችላሉ” ከሚል አሳማኝ ያልሆነ ስጋት በመነሳት ነው። እርግጥ በዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪ መጽሄት ላይ የወታው ይህ ዘገባ ጥንቃቄ ስለማድረግ ሚሰጠው ምክርም አለ። ለድምዳሜው እንደ እማኝ የወስደው፣ ያለቅጥ ተወጥሮ የነበረው የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ማሰርያ ክር ባንድ ግዜ ሲላላ፤ የባልካን አገሮችን እንዴት አድርጎ እንደባታተናቸው ነው።

እርግጥ ነው። የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ፈዴሬላዊ ስራዓት አወቃቀር ልክ እንደኛ ማንነትን መሰረት ያደረገ ነበር። አንምባገነኑ ፕረዚደንት ጆሲፕ ቲቶ ከሞተ በኋላ የዩጎዝላቭ ኢኮኖሚ መፈራረስ ጀመረ። የሥራ አጥነት ማደግ፣ የዋጋ ግሽበትና ድህነት ተዳምሮ የፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ፤ ለዘረኝነት መስፋፋት ግብዓት ሆኗል። ይህ በተራው በሪፐብሊኳ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ጎሳዎች መካከል አለመግባባት ፈጠረና በመጨረሻ ሃገሪቷ ተበተነች።

ቲቶ ቀብሮት የነበረ የክልል ቦንብ ሰዓት ጠብቆ እየፈነዳ ዩጎዝላቪያን ከአለም ካርታ ላይ እንዳጠፋው ሁሉ መለስ ዜናዊ የቀበረው የክልል አጥር ለዛሬዩቱ ኢትዮጵያ ፈተና እንደሆነ የሚክድ የለም። አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝን እንደ ዳዊት እየደገሙልን ያሉ “የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎች” ይህ ክስተት በእኛም ምድር እንዲደገም የሚገፉት ሕልም ነው።

“ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲ ቅንጦት ነው” ከሚለው አንባገነናዊ አተያይ ባለፈ፤ ቢያንስ የኢትዮጵያ “ትፈርሳለች – አትፈርስም” ውሃ ማይቋጥር እሰጥ እገባ መነሻ ሃሳብን ፈጥሮላቸዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ይህንን አያመለክትም ብለን ራሳችንን ብናሳምን እንኳ፤ የዩጎዝላቪያን ውድቀት ልንማርበት እንጂ ንቀን ልናልፈው አይገባም። ሲ.አይ.ኤ. የዩጎዝላቪያ ልትበታተን እንደምትችል አስቀድሞ ተንብዮ እንደነበር አንዘነጋውም።

የባልካን ሃገሮች ቅዠት በኢትዮጵያ እንዳይደገም፤ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ሩጫቸውን በጥንቃቄ ማስኬድ እንዳለባቸው የ”ፎረይን ፖሊሲ” መጽሄት አምደኛ አጥብቆ ይመክራል። ሕግ ያስከብሩ፤ ስርዓትን ያስይዙ ማለቱ ይመስላል።

የማካራሪ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር፣ ፕሮፈሰር ማህሙድ ማምዳኒ፣ በኒውዮርክ ታይምስ ላይ የለቀቁት ጽሁፋቸው ከዚህ አተያይ ብዙ የሚርቅ አይደለም። የኢትዮጵያ ፌደራል ስርዓት በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንድሚገኝ ነው ጸሃፊው የደመደሙት። የደርግ አህዳዊ መንግስት የኢትዮጵያን ችግር ጨርሶ አልፈታውም። ቋንቋን መሠረት ያደረገው የህወሃት መንግሥት አወቃቀርም ችግሩን ትንሽ እንኳ ወደ ፊት ፈቅ አላደረገውም ይላሉ ፕሮፈሰር ማህሙድ ማምዳኒ።

አናሳው የትግራይ ህዝቦች ነጻነት ግንባር (ህወሃት) ሃገሪቱን በበላይነት ይመራ የነበረው የእንግሊዝን የከፈፍሎ መግዛት ስትራቴጂ መጠቀሙ ነው አንደኛው ሸፍጥ። ህገ መንግስቱን ደግሞ ከየስታሊንዋ ሶብየት ህብረት “ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች” ቅኝት መቅዳቱ ሌላኛው ጥፋት እንደሆነ በስፋት እና በጥልቀት ይተነትናል። አዲሱ ትውልድ ቢያንስ ለሃያ ሰባት አመታት ከጎጥ አልፎ እንዳያስብ አድረገው ነው የሰሩት። አደጋው እና የመበተን ስጋቱ የሚመነጨው ከዚህ ነው።

ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ሌላ፤ ፌደራልዝምን በዘር መስመር ያስኬዱት ደቡብ ሱዳን፤ ኔፓል እና ፓኪስታን ናቸው። ሁሉም ይህንን የጥፋት እቅድ በሃገር ላይ ሲጭኑ ሕዝባቸው እንደላቦራቶሪ አይጥ ቤተሙከራ ነው ያደረጉት።

የጎሳ ፌደራሊዝሙ ችግር እንዳለ ሆኖ፤ የውጭ ጸሃፊዎች በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ አንድ ያልተረዱት ነገር እንዳለ ይሰማናል። ሁለቱም ጸሃፊዎች ከነሱ የእይታ መነጽር ውጪ የሆኑ እክሎችን በውል ያጤኑት አይመስልም። የጎሳ ፌደራሊዝም ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት ቀውስ መንስኤ ሊሆን ይችል ይሆናል እንጂ ዋናው ችግር ይህ አይደለም። ለችግሩ ሁሉ ገፊ ምክንያት የሆነው ሕወሃት ነው። በ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የአህያ አስተሳሰብ “ሃገሪቱን ካልገዛሁ አፈርሳታለሁ!” በሚል ቅዠት የተጠመደውም ይኸው ቡድን ነው።

“ያስፈራል፤ ግን ኢትዮጵያ አትፈርስም!” ብለዋል ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም። ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ የሚመኙ ጭንጋፍ ልጆች እንዳሏት በመግለጽ። “ቱርክና ግብጽ መጥተው ሄደዋል፣ ፖርቱጋል መጥቶ ሄዷል፣ እንግሊዝ መጥቶ ሄዷል፣ ኢጣልያ መጥቶ ሄዷል፣ ጠላቶች እየመጡ በመጡበት ተሸኝተዋል።” ይላሉ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም።

ፕ/ር ሀይሌ ገሪማም “ኢትዮጵያ ባንተ አልተጀመረችም። ባንተም አትፈርስም!!” ሲሉ ለሟርተኞች ምላሽ ይሰጣሉ።

“አንተ ትፈርሳለህ እንጂ፤ ኢትዮጵያ አትፈርስም።” የሚለው የዶ/ር ዐብይ አህመድ ጠንካራ አገላለጽ በውስጡ ቁጭትን ብቻ የያዘ አይደለም። ሕዝባችንን እርስ በርስ የገመደው የደም ትስስር፣ ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖታዊ ትውፊት፣ ስነ ልቦና አወቃቀራችን… መለያየት እንዳንችል አድርጎ እንደሰራን በመግለጽ ነው።

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ይህ ያስተሳሰረን ገመድ እንደላላ ግን ማንም ሊክደው አይችልም። የሳሳውን ብልት እየፈለጉ ለመቆራረጥ ያሰፈሰፉ ሃይሎች እንዳሉም አንዘንጋ። ፌደራል መንግስት ጥርስ አውጥቶ ፍትህን ካላስከበረ ችግሩ የከፋ ይሆናል። መንግስት አብዲ ኢሌ ላይ ያሳየውን ጡንቻ ጌታቸው አሰፋ ላይ መተግበር ካልቻለ ሶማሌ የፈደራሉ የእንጀራ ልጅ፤ ትግራይ ደግሞ የጡት ልጅ ናት የሚለውን ጆርጅኦርዌላዊ ብሂል አምነን ልንቀበል ነው። ጆርጅ ኦርዌል፣ በእንሣ እርሻ መጽሃፉ “እንስሳት ሁሉ እኩል ናቸው። አንዳንድ እንስሳ ግን ከሌሎቹ የበለጠ እኩል ናቸው።” በሚል የአሳማዎችን የበላይነት ነግሮናል። ኢትዮጲያውያን ዘንድ ”ክልሎች ሁሉ እኩል ናቸው፣ አንዳንድ ክልሎች ግን የበለጠ እኩል ናቸው” የሚለው መርህ አሁንም ገዥ ሆኖ ቀጥሏል።

በህወሃት ስውር እጆች የሚንቀሳቀሱ የንግድ ተቋማት፤ በአንድ እጃቸው የንግድ ስራቸውን በሌላ እጃቸው ደግሞ እሳት መለኮሱን አሁንም ቀጥለዋል። የአፋር ሰመራ ነውጥ፣ የሞያሌ ትርምስ፤ የወለጋ ስርዓት አልበኝነት፣ የሶማሌ አለመረጋጋት፣ ወዘተ፣… ለውጩ አለም ጎልተው የማይታዩ ምስጢሮች ናቸው። ከሰማይ የወረዱ ችግሮች ግን አይደሉም። ስፊ የፖለቲካ ምህዳር ተገኝቷል ተብሎ፤ በሜዳው ላይ ጌታቸው አሰፋ ከሩቅ የሚነዳቸው ፈረሶች እንዲጋልቡበት ነው የኦነው። ይህ ለውጭ ጸሃፊዎች በግልጽ የሚታይ አይደለምም።

የህወሃት ቡድን ከፌደራል ስርዓቱ ፈላጭ ቆራጭነት ከተባረረ ወዲህ በየክልሉ ባልካንን ለመፍጠር ከመጣር አልቦዘነም። ተልእኮው በከፊልም ቢሆን መሳከቱን የምንመሰክረው መንግስት አልባዋ ሶርያ ውስጥ እንኳ ያላየነው ጉድ በኛ ምድር ስናይ ነው። ከሁለት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በሃገር ውስጥ የተፈናቀለባት ሃገር ናት ኢትዮጵያ።

ከዚህ ሁሉ ጀርባ ማን እንዳለ ፌደራል መንግስቱ ጠፍቶት አይደለም። የመንግስትን ትእግስት እና ልምምጥ እንደፍርሃት ቆጥረውት “መንግስት የለም” እስከማለት ደርሰዋል። የላላው እየጠጠረ ሲሄድ፤ ጠጣሩ እየላላ መምጣቱ የተፈጥሮ ህግ መሆኑን ካልዘነጋነው በስተቀር ወንጀለኛን ሜዳ ላይ ለቅቆ ማንቀላፋት አይቻልም። ጌታቸው አሰፋ ለሁለት አስርተ-አመታት የዘረጋው ውስብስብ የመረጃ መረብ ውስጥ አሁንም ቁልፍ ቦታዎችን በስውር እንደያዘ ይነገራል።

ዶ/ር ደብረፅዮን ይደጋግሟት የነበረውን “ኢትዮጵያ ልትፈርስ ትችላለች” ዜማ ቀይር አድርገው ወደ መድረክ ብቅ ብለዋል። የዚህች ዜማ ኮፒ ራይት አልተከበረም እንጂ መጀመርያ ስትቃኝ የነበረው በአብዲኢሌ ነበር። የአብዲ ኢሌ የማያዛልቅ ጸሎት … ሲሆን፤ በአዲስ ቅኝት መጡ።

“ከምንም በፊት ሠላም ይቅደም። ፓለቲካው ሊቆይ ይችላል” ሚሏት የፖለቲካ ጨዋታ መድረኩን ይዛለች። የመጫወቻ ካርድን የመቀየር ስልት መሆኑ ነው። ለተለመደው ማዘናግያ ካልሆነ በቀር፣ ህግና ደንብን እየረገጡ ሰላምን መስበክ አይቻልም። ትግራይ ክልላዊ መንግስት ጌታቸው አሰፋን አልሰጥም በማለት ቁርጡን ከነገረን በኋላ፣ ስለ ሰላም ሊሰብክ የሚችልበት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም።

የአመት በጀቱን ሰባ በመቶ ከፌደራል መንግስት ያሚያገኝ ክልል ወንጀለኛን ስጥ – አልሰጥም ልምምጥ እና ምልጃ ውስጥ መግባት አልነበረበትም። በነሱ አተያይ፤ ፌደራል መንግስት የሚባለው ነገር ወይ ፈርሷል አልያም ተንቋል። ዶ/ር መረራ ጉዲና ቢቢሲ ላይ ቀርበው ሲናገሩ “የፌደራል መንግሥት በወንጀል የጠረጠረውን ግለሰብ ክልል አላስረክብም ማለት ሌላ መንግሥት መፍጠር ነው የሚሆነው፤ ይህ ደግሞ ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀጣይነት ፈታኝ ነው።” ብለዋል።

“ሕገ-መንግስቱ ይከበር” እንደ ዳዊት የሚደግሟት ቃል ሆናለች። የሚጠሩት ሌላ ህገ መንግስት ካልሆነ በቀር፣ እነሱው ያወጡልን ህገ መንግስት ራሳቸው ከረገጡት ማን እንዲያከብርላቸው ነው የሚፈልጉት? “የህገ መንግስት የበላይነት እና የሌሎች ለህገ መንግስቱ ተገዥ ስለመሆናቸው” በህገ መንግስት አንቅጽ 9 ላይ ተቀምጧል። በአንቀጽ 51 ደግሞ ፌደራል መንግስት ህገ-መንግስቱን የመጠበቅ እና የመከላከል ሃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋል። ይህ ደንብ ለሶማልያ እና ለኦሮሚያ ክልል ብቻ ነው እንዴ የተደነገገው? ትግራይን አይመለከትም? የፌደራልን ጡንቻ እነሱ ዘንድ ስላላዩት “መንግስት የለም” ቢሉን እውነት አላቸው።

ኢትዮጵያችን አትፈርስም። እውነት ነው። ይህ ግን በምኞት ብቻ አይመጣም። ሃገር የምትኖረው ህግና ደንብ ሲከበር ነው። የሀገር መከላከያ ሰራዊት ካሚዮኖችና የታጠቀ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር እየታገተ ወደፊት መዝለቅ ዘበት ነው ሚሆነው።

ዘግይቶ ብቅ የሚለው ያሽምግልና ጉዳይም ፋይዳው ከማዘናግያነት አያልፍም። ፖለቲካ ትዳር አይደለም፤ በባልና ሚስት ጸብ። ፖለቲካ በሽምግልና የሚቋጭና የሚፈታ ትስስር አይደለም። ፖለቲካ ሃገርን የማስተዳዳር ጥበብ፤ ሕዝብን የመምራት ሳይንስ ነው። ሃገር ደግሞ የሚተዳደርበት ህግና ደንብ አለው።

ውሃ በማይቋጥር ገፊ ምክንያቶች እየደረደሩ የማይወጡበት አዙሪት ውስጥ ከሚገቡ፤ መሪር የሆነውን ሃቅ መዋጥ ብቻ ነው ነጻ የሚያወጣቸው። ተጠርጣሪ ወንጀለኞች በሙሉ ለፍርድ ይቅረቡ። ነጻ ነን ካሉም ፍርድ ቤት ነጻ ያውጣቸው።

የጌታቸው አሰፋ ጉዳይ ግን ያስደምማል። መንግስት የእስር ዋራንት ቆርጦበታል። እሱ ደግሞ ዶ/ር አብይ ላይ የሞት ዋራንት ቆርጧል። በመገናኛ ብዙሃን እሱን ሳያነሳ የዋለበት ቀን የለም። ማህበራዊ ሜድያው በየ ሰዓቱ ያነሳዋል። ጌታቸው ረዳ በቃለ መጠይቁ ሃጥያቱን እያጠበ ከአስር ግዜ በላይ አንስቶቷል። አቦይ ስብሃትም ሰሞኑን ለተጋሩ ፕረስ በሰጡት ቃል አራት ግዜ አንስተው አሞግሰውታል። ይህ ሰው በከፍተኛ ወንጀል ይፈለጋል። ይህ ሰው የገዥው ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ነው። ይህ ሰው ከፍተኛ ባለስልጠንም ነው። ይህ ሰው ስብሰባዎች ላይ እንኳ አይታይም።

ፌደራል መንግስት እሱን ማግኘት እና መያዝ ካቃተው፣ ቢያንስ በዩኔስኮ የማይታዩ ቅርሶች ላይ እንዲመዘገብ ያድርገው።

LEAVE A REPLY