‘የመጨቆን መብት’ ብሎ ነገር የለም፤ ነገር ግን መብት እንዲሆን የሚታገሉ አሉ። አንዳንዶቹ ይኼን የሚያደርጉት ኾነ ብለው ነው፤ ብዙዎቹ ግን ባለማወቅ ያራግቡታል። ይሔን የምጽፈው ኾነ ብለው እሳቱን ለሚለኩሱት ሳይሆን ባለማስተዋል ለሚያራግቡት ነው።
ነገርዬው ስርዓተ መንግሥታት ከተጀመሩ ወዲህ እስከዛሬ የዘለቀ ነው። ዓለም ዐቀፋዊም ነው። አንዳንዶች ስርዓት (order) በማስያዝ ሥም ነው ጭቆናን የሚያበረታቱት፣ ሌሎች ሥልጣኔ ለማስፈን፣ ሌሎች ደግሞ ድህነትን ለመቅረፍ፣… ሌሎችም እልፍ ሰበብ አስባቦች አሉ፤ ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ግን በውስጠ ታዋቂነት “እኔን ምሰሉ” የሚል ጭፍለቃቸው ነው። “ከእኔ የሕይወት ዘይቤ የተለየ የሚኖሩ ሁሉ የተሳሳቱ ናቸው፤ እናም በኃይልም ቢሆን መታረም አለባቸው” የሚል መታበይ ውስጣቸው አለ።
አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ሲቀራመቱ፥ ለራሳቸው፣ ለዓለም ሕዝብ እና ለቅኝ ተገዢዎቹ አፍሪካውያንም ጭምር የሰጡት ሰበብ “እናሠልጥናቸው” የሚል ነው። ሃይማኖታቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውን እና ሌላም ሌላም ነገራቸውን አፍሪካውያን ላይ የጫኑት “የእኛ ነው ትክክለኛ” ከሚል መታበይ ነው። ያንን ተቀብለው ያራገቡ አፍሪካውያን ግለሰቦችም አሉ። ርቀን ሳንሔድ የእኛው አፈወርቅ ገብረየስ የፋሽስት ጣልያን የአምስት ዓመቱ ወረራ ጊዜ “የቄሳር ጦማር” በተሰኘ ጋዜጣ ላይ “ጣልያን ይዞልን የመጣው ሥልጣኔ ነው” እያሉ ሲሰብኩ ነበር።
ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት፣ በተለይ ኢሕአዴግ “ልማታዊ መንግሥት” ነኝ ብሎ ካወጀ በኋላ፥ ‘የኢትዮጵያውያን ችግር ድህነት ነው፣ መፍትሔው ደግሞ ልማት ነው። ዴሞክራሲ ደሞ ልማትን ያንቀራፍፋል፣ ስለዚህ እየጨቆንኳችሁ ላልማ’ እያለ ሲከራከር ነበር። ይህንኑ አብረው ሲያቀነቅኑ የነበሩ ‘ተጨቁኜ ልበልፅግ’ ያሉ ጭቁን ዜጎችም ነበሩ።
ልክ እንደ መንግሥታት፣ እንደ ማኅበራት ሁሉ ግለሰቦችም አሉ፣ ‘ጭቆና ዕድል ይሰጠው’ የሚሉ። የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ከቻሉ በራሳቸው፣ ካልቻሉ በሌሎች (በሚያስከትሏቸው አምሳያዎቻቸው) ትብብር ማንበርከክ፣ ሰብኣዊ መብቶቻቸውን እና ክብራቸውን ማዋረድ የሚሹ። በተለይ እዚህ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንደጉድ ይርመሰመሳሉ፤ አልፎ አልፎ መደበኛው ብዙኃን መገናኛም ሽፋን ይሰጣቸዋል።
‘የጭቆና መብት’ አራማጆች የጭቆና መብት ጥያቄያቸውን በተለያየ ብልጭልጭ ማሸጊያ ነው የሚያቀርቡት። ማሸጊያው ሁሌ አንድ ዓይነት አይደለም፤ እንደ ዐውዱ ይለዋወጣል። አስፈላጊ ሲሆን በሰላም ሥም ያሽጉታል፣ ካልሆነ ጭቆናው በአገር ደኅንነት ሥምም ሊደረግ ይችላል። ካልሆነ ደግሞ ሃይማኖት የሚል ማሸጊያ ይመዘዝለታል፣ ይህም በማይሠራ ጊዜ ባሕል አለ። አንዳንዴ ሁሉም ማሸጊያዎች ተደራርበው ሊመጡ ይችላሉ። ትርክታቸው “ለሰላም ሲባል ይወገዱ” ነው፣ “ለአገር ሲባል ይረገጡ” ነው፣ “ሃይማኖታችንን ሊያጠፉብን ነው” ወይም “ባሕላችን አይፈቅድም” ይባላል፤ አንድ ሃይማኖት እና ባሕል ያለን ይመስል። ዋና ዓላማው ግን “እኔን የማይመስሉ ሰዎች ላይ ጭቆናው ይፋፋም” የሚል ትግል ነው። ይህንን ‘የጭቆና መብት’ አራማጆች ሰደድ እሳት ደግሞ “እፍፍ…” እያደረገ አናዳጁ ብዙ ነው።