የወጣቱ ታከለ ኡማ የባሌ ተራሮች “ጀብዱ”እና የእኔ ትውስታ | ጋዜጠኛ ዘሪሁን ተስፋዬ)

የወጣቱ ታከለ ኡማ የባሌ ተራሮች “ጀብዱ”እና የእኔ ትውስታ | ጋዜጠኛ ዘሪሁን ተስፋዬ)

እሑድ በማለዳው የሪፖርተርን ድረ-ገጽ ሳስስ፤ ሰፊ ሽፋን የተሰጠው የከንቲባ ታከለ ኡማ ቃለ-መጠይቅ ቀልቤን ሳበው። ከንቲባው የልጅነት አስተዳደጋቸውን፣ የዘር ሃረጋቸውን እንዲሁም የፖለቲካ ጅማሪያቸውን ጨምሮ ብዙ “ጀብዱዎችን” ዘርዝረዋል። የዘረዘሯቸው የወጣትነት ተሳትፏቸው፣ አንዳንዶቹ ፈገግ የሚያሰኙ ናቸው። ፍላጎት ያለው ሙሉውን ቃለ መጠይቅ በማንበብ ሃሳቡን መስጠት ይችላል። ለጥቆማ ያህል ግን የልጅነት ታሪክ ሲተረክ ግነት ባይኖረው ይመከራል። አብሮ አደግ ባልንጀራህ ሊሰማ ይችላል። በታሪኩ ሚና የነብረው ሰው ይታዘባል። ድሮ ድሮ የፍቅር ጋዜጦች የፊት ገጽ ላይ እንደሚወጡ አማተር ከታፊዎች “በሦስት ዓመቴ ‘Fly me to the Moon’ የሚለውን ዜማ ስሰማ ነፍሴ ለሙዚቃ እንደተሰጠች ይሰማኝ ነበር” ከማለትህ በፊት ዙሪያህን ቃኘት ማድረግ አይከፋም።

የጽሑፌ ዋና መነሻ የከንቲባው፣ የጓዶቻቸው እና የእኔ የባሌ “ውሎ” ነውና ወደሱ እንመለስ። ከአሁኑ ከንቲባ ከቀድሞው ብላቴና ታከለ ጋር በአንድ የታሪክ አጋጥሚ “እንደተገናኘን” ስለተጋድሏቸው በሰፊው በገለጡበት አንዱ አንቀጽ ላይ አነበብኩ። ከንቲባው እንዲህ ይላሉ “.. . በተለይ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የባሌ ደን ተቃጠለ በተባለበት ወቅት ፖለቲካዊ ይዘት አለው ብለን በማመናችን ተማሪዎችን አስተባብረን እሳት ለማጥፋት ጥረት አድርጌያለሁ…” ቀጠል አድርገውም “.. . ኦሕዴድ ይህንን ትግል መምራት አይችልም ብለን እናምን ስለነበር፤ በወቅቱ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የነበርን ወጣቶች ከባድ የኾነ እንቅስቃሴ እንፈጥር ነበር።”

ከንቲባው የጠቀሱትን የባሌ ተራሮች እሳት የማጥፋት ዘመቻ አስታውሳለሁ። አንዱ ተሳታፊ ነበርኩ። እርሳቸው ከአምቦ፤ እኔ ደግሞ ከአዲስ አበባ አንድ ሥፍራ ላይ ተገናኝተን ነበር ማለት ነው-በአካል ተገናኝተን ባናወራም። በእውነትም እርሳቸው እንደገለጡት የማራኪው ተፈጥሮ ደን ውድመት ፖለቲካዊ ይዘት ነበረው። በወቅቱ ወያኔና ባለጉዳዩ ኦሕዴድ ስለእሳቱ መነሻ ሁለት የተምታታ ሃሳብ ይሰጡ ነበር። እንደኛው የሃሰት መረጃ- ኦነግ ነው ያቃጠለው የሚል ሲኾን፤ ሁለተኛው ደግሞ-ኦነግ አይደለም፤ ገበሬው ለእርሻ ማስፋፋት ሥራ አቃጥሎት ነው የሚሉ የሃሰት መረጃዎች። በወቅቱ በሥፍራው ደርሰን እንዳረጋገጥነው፤ በኋላም ላይ በሠፊው እንደተነገረው ኦነግ ተሸሽጎበታል በሚል ተልካሻ ምክንያት በባሌ እና ቦረና ተራሮች ላይ ወያኔ እሳት እንደለቀቀበት እሙን ኾኗል።

ከንቲባው ይሄን የባሌ ተሳትፏቸው በደፈናው የወጣትነት ዘመናቸው “ጀብዱ” አድርገው አልፈውታል። እርሳቸው እና አብረዋቸው በብሔር የተወከሉት ወጣቶች ሚና ምን እንደነበር አስተዋሽ ሳያስፈልጋቸው አልቀረም። ጀብዱ የተባለው ምንድ ነው? ጀብደኛውስ? የሚሉትም ጉዳዮች ቢነሱ መልካም ይመስለኛል። ( የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አንድ ግለሰብን መርጦ ለመወንጀል ወይም ቁርሾ ለመቀስቀስ ሳይኾን የወቅቱ አጋጣሚ በዘር ፖለቲካ ላይ የተንጠለጠለው ሁለመናችን እንዴት የኔን መሰሉን ወጣት ሕይወት አቅጣጫ እንደቀየረ፤ ጥላቻ ምን ያህል ንጹህ ወጣቶችን እንደበከለ እና አጋጥሚውም ምን ያህል አደገኛ ክስተት እንደነበረ ለማሳየት ነው።)

1992 ዓ.ም። ወያኔ በባሌና ቦረና የተፈጥሮ ደኖች እሳት ለኩሳ ጸጥ ብላለች። የደኑ አስከፊ ሁኔታ መረጃው የደረሳቸው የሁለተኛ ደረጃ እና የኮሌጅ ተማሪዎች በአስተባብሪዎቻቸው አማካኝነት ስንቃቸውን ቋጥረው ወደ ሁለቱ አቅጣጫዎች ተመሙ። ግማሹ ባሌ ሮቢ፤ የተቀረው ደግሞ ቦረና። በአጋጣሚ እኔ የሄድኩት ባሌ ነበር። ደኑ ይቃጠል የነበረው ከባሌ ሮቢ ከተማ ራቅ ብላ በምትገኝ መናንገቱ (?) በተባለች ቀበሌ ሲሆን፤ ከዚህች የገጠር ሥፍራ አዳራችንን አድርገን በየእለቱ ማለዳ ከሁለት ሰዓታት በላይ በእግር እየተጓዝን ነበር እሳቱን የምናጠፋው። የሚበላ እና የሚጠጣ ደግሞ ከማረፊያችን ጣቢያ (አውላላ ሜዳ ነው) የቀሩ ተማሪዎች በአህያ ጭነው ነበር እዛው የሚቃጠለው ደን ድረስ አረፋፍደው የሚያመጡልን። በአካባቢው ስንደርስ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የተራራ ሰንሰለቶች አመድ ኾነዋል። ወደ ደኑ እየተጠጋን ስንመጣም እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነበር የሚስተዋለው። ግማሽ አካልቸው እሳት የበላው የዱር እንስሳት በብዛት ይታዩ ነበር።

እሳቱ ለአመታት በቅጠል እርጋፊ እና ግንድ ለም የኾነው መሬት ምቹ ኾኖት ኖሮ ውስጥ ለውስጥ እየተጓዘ ነበር ደኑን የበላው። የቆምንበት ምድር ሳይቀር ውስጡ እሳት ነበር ማለት ይቻላል። የኛ ድርሻ በአካፋ እና ዶማ መሬቱን እስከ ጥግ ድረስ እየቆፈሩ እሳቱ ውስጥ ለውስጥ እንዳይስፋፋ ማገድ ነበር። ይህም ኾኖ አቅማችን ውስን ነውና፤ ከአናታችን በላይ ያለው ዕድሜ ጠገብ ዛፍ ሲቃጠል ከመቁለጭለጭ ውጪ አንዳችም የምናደርገው ነገር አልነበረም። እጅግ ልብ የሚያደማ ክስተት ነበር። ውሃ ሲጠማንም አመድ ከለበሰው ኩሬ በሸሚዛችን እያጠለልን ነበር የምንጠጣው።

ሁለት ቀናትን እንዲህ በትግል ላይ ብንኾንም በተማሪዎች ላይ የከፋ ችግር አልገጠመንም ነበር። አርሶ አደሩ በአለፍ አገደም እየመጣ አቅጣጫ በመጠቆም ተባብሮናል። አልፎ አልፎም ውሃ ሲጠማን የጎጆውን ሳንቃ እየጠበጠብን ውሃ ጠይቀን ቤት ያፈራውን ጠላ ወይም ወተት ጠጥተናል። በኦሮምኛ ወይም በአማርኛ መግባባት ሲቸግረንም በምልክት ቋንቋ ተጋባብተን የምንሻው ተደርጎልናል። የባሌ አርሷ አደር ሸዋ ወይም ሰሜን ከምታገኘው አርሷ አደር አዳች ልዩነት የለውም- በደግነቱ።

ችግር የተከሰተው በሦስተኛው ቀን ነው። ምንም ነገር በአፋችን ሳይዞር (በባዶ ሆዳችን) ሁለት ሰዓታት ተጉዘን ከሥፍራው ደርሰን ሥራችንን እስከ ምሳ ሰዓት አከናውነን ምግብ ጓደኞቻችን ያመጡልናል ብለን ብንጠብቅ አንዳች ዝር የሚል ተማሪ የለም። ለወትሮ በአህያ እየጫኑ ያመጡልን ነበር። እስከ አመሻሹ ድረስ በባዶ ሆዳችን ታግለን አቅም ሲክዳን አንድ ሰዓት ተጉዘን አንዱ አቅራቢያ መንደር ገብተን የሚበላ ለመጠየቅ ተገደድን። ከቤተሰቡ ርቆ የማያውቅ ተማሪ ሆድ ብሶታል። በመጨረሻ የተባረኩ አርሶ አደሮች በማዳበሪያ ዳቦ፤ በላስቲክ ውሃ አሲዘው ሰደዱን። መንገድ ላይ አረፍ ብለን፤ እርሱን አሻምደን (ያረፍንበት ሥፍራ በጉንዳን የተወረረ ነበርና አስቂኝ ትዕይንቶች የታዩበት፤ ዳቧችንም በጉንዳን ተወሮ እያራገፍን የበላንበት ነበርና አይረሳም)አቅማችን ሲበረታ እያዘገምን ወደ ማደሪያችን ደረስን።

ወደ ማደሪያችን ደርሰን የሰማነው “ጀብዱ” ጉድ አስባለን። ምግባችንን ሠረተው በአህያ እንደላኩ፤ ነገር ግን ሌሎች ተማሪዎች “ለወራሪዎች አይሄድም” ብለው እንደቀሟቸው “ምግብ አብሳይ ተማሪዎች” አረዱን። ተማሪ ደነገጠ። ያልጠበቅነው ነበር። በውነቱ ቡድናችን በበጎ ፍቃደኛ የዘመተ እንጂ ማን ምን እንደኾነ እንኳ የሚተዋወቅ አልነበረም። ብሄር የሚባል ነገር እንኳ ክመካከላችን የሚገባው ሰው እንዳልነበር በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። እንኳን ለአቅመ ፖለቲካ፤ ወግ ላለው የተቃራኒ ጾታ ግንኑነት እንኳ አልበሰልንም ነበር።

በበነጋው ድንጋጤው ያለቀቀው ተማሪ ጉዞውን ወደ ደኑ አደረገ። እንደወትሮው ግን ትግሉ ከእሳት ጋር አልነበረም። አዲስ ከሌላ ሥፍራ የተቀላቀሉ የተባሉ ተማሪዎች ነገር ግን በብሔር ተደራጅተው የመጡ እኛን ማስፈራርት ጀመሩ። “በአማርኛ አታውሩ” አሉ። “አገራችን ልትወሩ ነው ወይ የመጣችሁት?” አሉን። ድንጋጤም ፍርሃትም አራደን። ከደን እሳት የባሰ “እሳት” ትውልድ ገጠመን። ምሽት ላይም የኢትዮጵያን ባንዲራ አታውለበልቡም ብለው ቀሙን። ባንዲራውንም እሳት አድርገው ሲሞቁት አይናችን አየ። የኦነግ ባንዲራ ምን ይመስል እንደኾነ ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ያዩት ያንጊዜ ይመስለኛል። ለሳት ማጥፊያ የታሰበ ገጀራ/ሜንጫ አይናችን እያየ ተቃጣብን።

ነገሩ ሲብስብን፣ ጥቂት ተወካዮች ወደ ባሌ ሮቢ ልከን “አቤት” አልን። ችግሩ ቀድሞ ደርሷቸው ኖሮ በቀጣዮቹ ቀናት እነሱን ወደ መጡበት ሸኝተው የኛን ቡድን ከተማው ውስጥ በሚገኝ ኮሌጅ አልጋ ሰጥተው አሳደሩን።

በሰተመጨረሻም የደነገጠ ተማሪ ወደ ሸገር ተመለሰ። ቦረናም የሄደው ተመሣሣይ የብሄር ተኮር ትንኮሳ እንደደረሰበት በምሬት ተናገረ። እንገታችን ከገጀራ መትረፉ ተአምር ቢሆንም ደኑን ከሳት ልንታደገው አለመቻላችን ትልቅ የልብ ስብራት ነው። ትላንትም ዛሬም ቢሆን ስለሱ ደን እንዳሰብኩ ነው። የስላቁ ጥግ ደግሞ ከባሌው እሳት ሁለት አመት ቀደም ብሎ እንጦጦ ላይ ዛፍ የተከልን እና ተስፋ የምናደርግ አዳጊ ልጆች ነበርንና ሰቀቀኑ መቼም አይወጣልንም።

ሸገር ከተመለስን ከቀናት በኋላ የወቅቱ የኦሮሚያ አስተዳዳሪ ኩማ ደመቅሳ ለይቅርታም ለምስጋናም ጠርተውን ነበር። ስብሰባው ጨፌ ኦሮምያ ነበር። ስብሰባው ሳይጀመር “በኦሮምኛ ይሁን በአማርኛ ይሁን” አይነት ግብግብ ሲነሳ ጥቂት ተማሪዎች “እግዜር ይስጥልን”ብለን ሹልክ አልን።

እንግዲህ ይህ ከተከሰተ ዓመታት በኋላ ነው ፣ ከንቲባው የሸገርን ቁልፍ ተቀብለው የባሌውን ጉዞ ከ”ጀብዶዎቻቸው” አንዱ አድርገው የገለጹት። እኔም ዛሬ ላይ ቆሜ ከንቲባው ይህ ነበር፤ አሁን ደግሞ ይህ ነው ብዬ ለመናገር ፍላጎቱ የለኝም። በታሪክ አጋጣሚም የስደተኞችን ታሪክ ስሰበስብ ስደት ላይ ያገኘኋቸው ተማሪዎች ነበሩ። ከልብ አውርተን፤ በሚቀለደው ቀልደን ተለያይተናል። ቁርሾም የለም። የልጅ የልጅ ነገር ነው የሰራችሁት ብዬ ከመናገር ውጪ አንዳች ቂም የለም። ነገር ግን በርግጠኝነት መናገር የምችለው ወያኔ ያጋየው ደንም፤ እርሱን ለማጥፋትም በብሄር ተደራጅተው የመጡት ተማሪዎችም ታሪክ እጅግ የሚያሳፍርና እንደ አንድ የፖለቲካ ስኬትም በፍጹም የማይወራ መኾኑን ነው።

እናም… ከንቲባ ታከለ… በባሌ ተራሮች ጀብዱ አልተሰራም። እርሶ እንደገለጡት ምናልባት የጠባብ ብሄርተኛው የጥላቻ ጥጉን የሰቀለበት ማማ ይኾናል። ለእኔ መቼም የማንተካው የተፈጥሮ ደናችን አመድ የኾነበት ነው። ለዚህ ደግሞ ወያኔም ኦሕዴድም ድርሻውን ይወስዳሉ። ስሱ ነፍስ የነበራቸው ወጣቶችም ጥላቻ የመረዘው ሰይፍ ምን ዓይነት እንደኾኑ ያዩበት ነው። …
…እናም እናም ደግሞ ከተሜነት እና ጎሰኝነት ለየቅል ናቸው… የጎሰኝነት ነፍስ ይዞ ከተሜነት የለም… የልብ ቅንነት ከሌለ የላይ የላይ ወከባ ከንቱ ነው።
እንዲህ ይተርከዋል

ሰላም!

| ቃሊቲ ፕሬስ |

LEAVE A REPLY