መሬት ላራሹ! | ገለታው ዘለቀ

መሬት ላራሹ! | ገለታው ዘለቀ

የኢትዮጵያን የክልሎች ወሰን ጥያቄ የሚፈታው የመሬት ላራሹ ጥያቄ ሲመለስ ነው። የኢትዮጵያ ህገ-መግስት አንቀጽ 40 ንኡስ አንቀጽ 6 ላይ ሲናገር “የኢትዮጵያ መሬት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች…” ይላል። ይህ ማለት የሃገሪቱ መሬት በብሄሮች የተያዘ የቡድን ሃብት ነው ማለት ነው።

የደርጉ መንግስት መሬትን ከከበርቴው ነጥቆ ለመንግስት ያደረገ ሲሆን ይሄኛው መንግስት ደግሞ  ለቡድኖች ኣድሏል። እነዚህ ሁለት የመሬት ሃብት ዝውውሮች ችግሮች ኣሉባቸው። መሬት ላራሹ ማለት  መሬት ለሚሰራበት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወይም ለዜጋው ከነ ሙሉ መብቱ ይሰጥ የሚል እንድምታ ነው ያለው። ይህንን ጥያቄ መመለስና የመሬትን የሃብት ዝውውር ከቡድን ወደ ግለሰብ በማዛወር የወሰን ጥያቄዎችን እስከ ሃቹ መፍታት ይቻላል። ይህ የተቋቋመው የማንነት ኣስተዳደርና ወሰን ኮሚሽን ይህንን ኣሳብ እንዲያየው እጠቁማለሁ። በቡድን የተያዘው መሬት ወደ ግል ሲዞር የብሄሮች የወሰን ጥያቄ አለቀለት ማለት ነው። ስለዚህ ኮሚሽኑ በክልሎች መካከል መስመሩ የት ጋር ይሁን? ብሎ ከማሰብ ከአሁኑ መሰረታዊ የሆነ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ እንዲፈታ መንግስትን ማሳሰብ  ኣለበት። መሬት ላራሹ ከሆነ ኢትዮጵያውያን በወሰን አይጋጩም። መሬት የግል ይሁን ሲባል አንዳንድ ኮሙዩኒቲዎች መሬት ኣያስፈልጋቸውም ማለት ኣይደለም። መሬትን ከብሄር ባለቤትነት  አውጥቶ ነገር ግን አንዳንድ ኮሙዩኒቲዎች ደግሞ የመሬት ባለቤት እንዲሆነ ማድረግ ይቻላል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲዋን በሚመለከት የሚከተለውን ለውጥ ብታደርግ ብዙ እቆቅልሶቿ ይፈታሉ።

  1. መሬትን የግል በማድረግ (Privatization)
  2. ኣንዳንድ የግጦሽ ቦታውችን የአምልኮ ስፍራዎችንና የባህል መከወኛ ስፍራዎችን በቡድን እንዲያዙ ማድረግ
  3. ወንዞችን ተራሮችን ሰው ያልደረሰባቸውን ቦታዎች መንግስት እንዲይዝ ማድረግ ይገባል።

ይህ የመሬት ፖሊሲ በተለይ የወሰን ጥያቄን ግሩም ኣድርጎ ይፈታል። የማንነትና የአስተዳደር ጉዳዮችን ደግሞ በሁለትዮሽ የፌደራል ስቴት ( two federal states) ግንባታ መመለስ ይቻላልና ኮሚሽኑም መንግስትም የለውጡ ሃይልም ይህንን ኣሳብ እንዲያስበው እንመክራለን።ሁለትዮሽ የፌደራል ስቴት  ማለት በአንድ በኩል የብሄር ባህላዊ የፌደራል ስቴትና በሌላ በኩል ሲቪክ የፌደራል ስቴት ወይም የዜጎች የፌደራል ስቴት በመመስረት የማንነትና ኣስተዳደር ጉዳዮችን ማስታረቅ ይቻላል። ይህ መንገድ እጅግ ኣስፈላጊ ነውና ኮሚሽኑ ይህንን ከግንዛቤ እንዲያስገባ ከወዲሁ እጠይቃለሁ። የሁለትዮሽ የፌደራል ስቴት ግንባታው በሁለት ጽንፍ ያለውን ፖለቲካ በዶክተር አብይ አህመድ አገላለጽ “ዋልታ ረገጥ” ፖለቲካችንን ያስታርቃል። የዜግነት ፖለቲካንና የቡድን መብትን አቻችሎ ይይዛል።

ከፍ ሲል እንዳልኩት  የመሬት ላራሹ ጥያቄ ከተመለስና ከላይ ባነሳሁት መሰረት መልክ የመሬት ይዞታ ፖሊሲው ከተቀረጸ የአዲስ ኣበባ ጥያቄም ይፈታል። የመሬት ላራሹ ጥያቄ የከተማ ቦታንም ይመለከታልና ከተሜው የቦታው ባለቤት ሲሆን የአዲስ ኣበባ የባለቤትነት ጥያቄ እስከ ሃቹ ተፈታ ማለት ነው። የመሬት ፖሊሲያችን ሲፈታ መሬት ላራሹ ሲሆን ደቡብ ውስጥ ያሉ የወሰን ግጭቶች መፈናቀሎች ሁሉ ይቆማሉ። ስለዚህ ዛሬም መሬት ላራሹ! ዛሬም መሬት ላራሹ! ዛሬም መሬት ላራሹ! ……ወጣቶች ይህንን ጥያቄ አንግበው የቀዳሚውን ትውልድ ጥያቄ ሊቋጩት ይገባል።አዲስ ኣበቤዎች ይህንን ጥያቄ ሊያነሱ ይገባል። ገበሬው ይህንን ጥያቄ ሊያነሳ ይገባል።

የዶክተር ኣብይ መንግስት ወደ ለውጥ ሲገባ ከሚመለከታቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ይህ የመሬት ፖሊሲና የማንነት ጉዳዮች ናቸው። ማንነትን ከፍ ሲል እንዳልኩት በሁለትዮሽ ፌደራል ስቴት ቤቶች ጠብቆ የወሰኑን ጉዳይ በመሬት ፖሊሲ ለውጥ እስከ ሃቹ መዝጋት ይቻላል። መሬት ላራሹን የማይደግፍ ኦሮሞ፣ ኣማራ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ ኣለ ብየ ኣላምንም። የዜጎች የመሬት ሃብት ባለቤትነት(land ownership) ሲመለስ ልማት ይፈጥናል እንዳልኩት የወሰን ጉዳይ ያልቅለታል። እናም መሬት ላራሹ!

geletawzeleke@gmail.com

LEAVE A REPLY