ዛዲግ ቀደመ! “ቦንብ ሼሉን” ወረወረ! | ኤርምያስ ለገሰ

ዛዲግ ቀደመ! “ቦንብ ሼሉን” ወረወረ! | ኤርምያስ ለገሰ

በለውጥ ዙሪያ የተፃፉ መጣጥፎችን፣ መፅሐፎችን እና ቪዲዬዎችን ማየት ቅድሚያ የምሰጠው ነው። ታዲያ ስለ ዘገምተኛ ለውጦች የሚያወሩ መፅሐፎችና የምሁራን ገለፃዎች ሳዳምጥ ሁሉም በሚባል መልኩ የአንድ ፈላስፋ ስም አይጠፋም። ሰውየው እንግሊዛዊው የስነ ህይወት ፈላስፋ ቻርለስ ዳርዊን ይባላል። Servival of the fittest!

” It is not the strongest species that survive, nor the most intelligent, but the ones who are most responsive to change.”

በዚህ የቻርለስ ዳርዊን ቲዬሪ መሰረት ግዙፍ፣ ጠንካራ ወይም ምጡቅ ስለተሆነ ብቻ ህልውና አይረጋገጥም። ይልቁንስ ዋናው ከጊዜና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር መለወጥና መጓዝ መቻል ሕልውናን ማስጠበቅ ነው። Survival of the fittest!

ወደ ገደለው ስገባ የቀድሞ የቅርብ ስራ ባልደረባዬ ዛዲግ አብርሃ የዛሬ ውሳኔ ከላይ የገለጥኩትን የቻርለስ ዳርዊን ህግጋት እንዳስታውስ አደረገኝ። እርግጥም ዛዲግ እንደ ህውሓት ግዙፍ ባይሆንም ቀድሞ ተገኝቷል። መቅደምን የመሰለ ነገር የለም።የሚቀድመው የበረታ ነው። ለማሰብ ቢከብድም ዛዲግ ህውሓትን ባይቀድም ኖሮ ምን ይሆን ነበር? ድሮ ድሮ ” አብዮት ልጇን ትበላለች” የሚለው ቀድሞ ይሰማ ነበር። ዘንድሮስ?

ሚስጥር እንደ ማውጣት አይቆጠርብኝና ዛዲግ አብርሃን ዛሬ ከጣለው “ቦንብ ሼል” በፊት አገኘው ነበር። ከሶስት ፣ አራት ወራት በፊት። አለ አይደል! ስለ ቤተሰብ፣ ስለ ኑሮ መወደድ፣ ስለ አየር ሁኔታ ለውጥ፣ ስለ እርጅና እናወራ ነበር። ውድ አንባቢያን ወጋችን ምፀት ከሆነባችሁ ግዴለኝም። እንደውም እንደ አልባሌ ቁጠሩት። እኔም ዛዲግን መሰል ሌሎች ወጣት ባለስልጣናት ጋር ወጌን እቀጥላለሁ። ስራው ተጀመረ እንጂ አላለቀም።

ወደ ዛሬ አስር አመት ታሪክ ልውሰዳችሁ። የዛሬ አስር አመት ዛዲግን ወደ ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ስናመጣው በጣም ወጣት ነበር። በወቅቱ የየትኛውም ፓርቲ አባል አልነበረም። በሌላ በኩል የህግ ምሩቅ ቢሆንም በሌሎች ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዬች ላይ እውቀት የነበረው እና ሃሳቦችን የማማከር ብቃት ነበረው። በዚህ ምክንያት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ውስጥ በነበሩ ካድሬዎች በተለይም ሀዱሽ ካሱ በሚባል ሰው ወገቡ ላይ እንደተጣበቀ ተባይ ተጠመደ። ሀዱሽ ለረጅም አመታት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበረ የህውሓት ተጋዳላይ ነው።

(ስለ ሀዱሽ ካሱ ለወደፊት ዛዲግ እስኪነግረን ድረስ ማወቅ ለፈለገ “ጥላሁን ያረፈ ቀን” በሚለው መፅሐፍ ላይ በምእራፍ አስር “የቀን ጅቦች” በሚል ርዕስ ያገኘዋል። ሀዱሽ በኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ውስጥ “የአሞራ ስጋ በመባል ይታወቃል። ቢቀቀል፣ ቢቀቀል፣ ቢቀቀል የማይበስል ስጋ። ነገር ከያዘ የማይለቅ ችኮ። መደዴ። ማሽንክ። ፈሪ። ፈሪና ድንጉጥ በመሆኑ ሁሉንም በጠላትነት የሚፈርጅ። ጨካኝ። ዛሬም በፌዴራል ስልጣን ላይ ሆኖ የሚሰራ። ያስቃል!)

የበታችነት ስሜት በወለደው ምቀኝነት ደዌ የተመታው ሃዱሽ ከአንዴም ሁለቴ ወጣቱ ዛዲግን ሊያባርረው ሞክሮ ነበር። በተደጋጋሚም ኩርኩም ሲያደርስበት ነበር። በየቀኑ በሚቀርብበት ስድብና ማንጓጠጥ የተበሳጨው ዛዲግ መልቀቂያ አሰገብቶ ጠፋ። ከሁለት ሳምንት በኃላ በእኔ እና ሽመልስ ከማል ምክር፣ ተግሳፅና ድርድር ወደ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ተመለሰ። ከዛ ጊዜ በኃላ ከዛዲግ ጋር በየቀኑ ከ8ሰአት ፣ አንዳንዴም ከ10 ሰአት በላይ አብረን እናጠፋ ነበር። ከመላው ኢትዮጵያ መረጃ ከመሰብሰብ ጀምሮ፣ ሚዲያ ሞኒተሪንግ እና የእለት ሪፓርት ማዘጋጀት የዘወትር ህይወታችን ነበር። ስደት እስኪያለያየን ድረስ።

ብዙም ሳይቆይ በስደት ህይወቴ ዛዲግ በእኔ ቦታ መተካቱን ሰማሁ። ከዛም በኃላ የህውሓት አባል በመሆን እስከ የሚኒስትርነት ስልጣን መድረሱን ተመለከትኩ። የእናት ሆድ ዝንጉርጉር እንዲሉ ህውሓት በሚኒስትርነት ማዕረግ አድርሳም በእኩል አይን እንደማትመለከት ዛዲግ ተገነዘበ። በህውሓት ውስጥ የበኩር ልጅና የእንጀራ ልጅ የሚባል ነገር እንዳለ ገባው። በእንስሳት እርሻ መጽሐፍ ውስጥ “ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፣ አንዳንድ እንስሳት ግን የበለጠ እኩል ናቸው” የሚለውን አስታወሰ። በሂደትም ህውሓት የኢትዮጵያን ህዝብ በሚደፍሩ ባለጌዎች፣ ከዘር ወርደው አድዋ አክሱም ራያ እያሉ የሚያበላልጡ ፣ አገር ለማፈራረስ የተነሱ ፀረ ለውጦች መሆናቸው አረጋገጠ። ከእነዚህ ትናንሽ ጭንቅላቶች ጋር አብሮ መጓዝ ከታሪክ ተወቃሽነት እንደማያድነው አወቀ።

እርግጥም የታሪክ ተወቃሽነት የሚያመጣው ክፉ ድርጊት መፈፀም ወይም የድርጊቱ ተባባሪ መሆን ብቻ አይደለም። ክፉ ድርጊት እንዳይመጣ ለመከላከል ቁርጠኝነትና ፍላጐት ያልነበራቸውም ጭምር ከዚህ ጐራ የሚፈረጁ ናቸው። ዛዲግ የተጋፈጠው መራር እውነት ይሄ ነው። ዛዲግ የተጫወተው እጅግ በጣም ጥቂት የቆረጡ ሰዎች ራሳቸውን አቃጥለው የብርሃን ጭላንጭል የመስጠት ሚና ነው።

የዛዲግን ውሳኔ ከወራት በፊት ባውቀውም አሁንም ቢሆን አክብሮቴን በአደባባይ የመስጠት የሕሊና ግዴታ አለብኝ። አክብሮቴ ለዛሬው እርምጃው እና በቀጣይ የሚከፍለውን መስዋእትነት በማሰብ ብቻ አይደለም። ይልቁንስ የዛዲግን አርአያነት በመከተል ራሳቸውን ከህውሓት ጨለማ ውስጥ ለመውጣት ለሚፍጨረጨሩ የፓርቲው አባላት ” መስኮት ሰባሪ” መሆኑ ነው። የተሰበረ መስኮት ቲዬሪ (The broken window theory) ጥቂት ግንባር ቀደሞች መስኮት ሲሰባብሩ ከታየ ሌሎችም ይቀላቀሏቸዋል። ግንባር ቀደሞቹ ከሰሩት የላቀ በመስራት ስማቸው ከፍ እንዲል ይጥራሉ።

ክቡራትና ክቡራን ወጣት የህውሓት አባላት! የዛዲግን አርአያነት ተከትላችሁ ፓርቲያችሁ የጋረደባችሁን ጥቁር የልዩነት መስታወት ሰባብሩ። ሁከት፣ ትርምስ፣ ጭንቀትና እርጅና ከወረሰው የህውሓት ቤት ራሳችሁን ነፃ አውጡ። እንደ ወንድማችሁ ዛዲግ ቀድማችሁ ተገኙ። የቻርለስ ዳርዊንን Survival of the fittest! በልቦናችሁ ይደር። አሜን።

LEAVE A REPLY