“የሱ ሁለት ዓይን እንዲጠፋ የኔን አንድ ዓይን አጥፋ” | ሙሸ ሰሙ

“የሱ ሁለት ዓይን እንዲጠፋ የኔን አንድ ዓይን አጥፋ” | ሙሸ ሰሙ

የዋለ ያደረ ለእልቂት ያመቻቸን የቤት ስራ ሳያንሰን፤ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዙርያ ከግራና ከቀኝ የሚወረወሩት ጦር አውርድ ቱማታዎች ለመተላለቅ ምን ያህል በቋፍ ላይ እንዳለን የሚያስጠነቅቁ ሆነው አግኝቺያቸዋለሁ። በጥላቻ፣ በስግብግብነትና በክፋት ተሞልተው ዓይናቸው ደም የለበሱ የጥፋት ኃይሎች ደካማነት ከልሂቅ እስከደቂቅ እንደ ዛር እየሰፈነብን ነዉ።

ጦር ከተሰበቀ፣ ደም በከንቱ ከፈሰሰ፣ ሰው ከሞት በኃላ የትናንቷም ሆነች የነገዋ አዲስ አበባ ተረት ልትሆን እንደምትችል ለመገመት አዳግቶናል።

ያለማሰለስ ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት፣ ስለ መከባበር፣ ስለ መቻቻልና ስለ ጥሞና የሚሰበከው መረጋጋት እንዳይሳነንና ጣታችንን ከቃታው እንድናርቅ መሆኑ ተሰውሮናል።
ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በተደጋጋሚ በየክልሉ እንዳየነው በየጎጣችን ተሰትረን አሸናፊ የሌለበት የመንደር ጦርነት ቀስቅሰን ከተላለቅን በኃላ ጸሐይ ሳይጠልቅ በጸጸት ተይዘን በፍርስራሾቻችንና በአስከሬኖቻችን ዙርያ ተሰብስበን ስንላቀስ በየሚዲያው ለመታዘብ በቅተናል።

የተጋደልነውና ንብረታችንን ያወደምነው ልጆቻችንን የሰዋነው በከንቱዎች ቅስቀሳ፣ ለከንቱ ዓላማና፣ እንዲያው በከንቱና በዋል ፈሰስ እንደነበረ ከኪሳራ በኃላ እንደ ሕዝብና እንደ ሃገር ውጤቱን ለመታዘብ በቅተናል ።
ዓመት ባልሞላ ጊዜ አሰቃቂ ጦርነት ካስተናገዱ ሃገሮች በላይ በሃገር ውስጥ መፈናቀልና ስደት አስተናግደን የዓለም መዘባበቻ ሆናል።

የተጎዱትን ስንረዳ፣ የተፈናቀሉትን ስናቋቁም፣ የሞቱትን በጥልቅ ሃዘን ስንሸኝ በከንቱ ጆሮ የሰጠናቸው ቀድሞውኑም ጆሮ የማይገባቸው ከንቱዎች እንደነበሩ በጥልቀት የተረዳን ይመስል ነበር። እውነታው ግን ይህ እንዳልሆነ አሁንም እየታዘብን ነው።

ሰላማችን የሚደፈርሰውና ውድቀት የሚከተለው ጥቂት ደካማ አዕምሮዎች ክፍተቱን ተጠቅመው የበላይነት ለመወስድ በሚቀሰቅሱት እሳት እንደሆነ ዛሬ ላይም ውሉን ስተን በጦሳቸው ዙርያ እየተወዛገብን መሆኑ ማሳያ ነው።
ደርግ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻልና የመከባበር መሰረት የሆኑትን ቤተ ክርስትያናትና የመስጅድ ደጃፎችን ዘግቶ፣ ጥቂቶች በቀሰቀሱትና እራሱም ባልገባው የርዓዮተ ዓለም ቱማታ ውስጥ ተዘፍቆ፣ ሕዝባችንን በከተማና በገጠር ጦር እንዲማዘዝና እንዲጋደል በማድረግ ለዘመናት የዘለቀ ቂምና ቁርሾ፣ ሰቆቃ አስታቅፎን እራሱም እንደ ጨው ዘር ተበትኖ ቀርቷል።

“ኢህአዴግ” በዘር ከፋፍሎ፣ ከጥላቻና ከልዩነት ዛሮች ውስጥ አንዱንም ሳያስቀር ዓይነት በዓይነት አስፋፍቶ፤ የሃይማኖት መሪዎችን፣ የሃገር ሽማግሌዎችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን በገንዘብ፣ በዘር-ፓለቲካ በክሎ፣ የመፈክሩ አንጋች ከማድረጉም በላይ ቦታቸውንና ሚናቸውን በማደበላለቅ የስነልቦና ቀውስ ሰለባ አድርጎ ማህበራዊ መሰረታችንን አናግቶታል። አሁን ላይ ለደረስንበት ፍጥጫም አብቅቶናል።

ዛሬም ላይ ሆነን የለውጥ ንቅናቄ የመቻቻልና እውቅና የመስጠት ጉዞ በእርምጃ ቢጀመርም እንደ ሃገር፣ እንደ ሕዝብ ስከን ብለን ጅምር እርምጃውን ከመውተርተር አውጥተን ወደ ግስጋሴ መለወጥ ያቃተን ይመስላል። ጅምሩ መሰረት አድርገን ወደ ፊት ለመራመድም ሆነ ስንዝር አርቀን ልማስተዋልና ለማመዛዘን ተቸግረናል።
ዛሬም መተማመንና ምክንያታዊ መሆን አቅቶን እንደተፋጠጥን፣ ጦር አውርድ እያዜምን ወድርና ወጥር እንደተባባልን ነው።

በተለይ የሚያሳዝነው ደግሞ እንደ አፈ-ታሪካችን “የሱ ሁለት ዓይን እንዲጠፋ የኔን አንድ ዓይን አጥፋ” ከማለት አለመቦዘናችን ነው።

LEAVE A REPLY