ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ‹‹የልዩነት ግንብን አፍርሶ የአንድነትና የፍቅር ድልድይን›› የመገንባት አላማ አንግበው በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ‹‹ለመደመር›› በሄዱበት አጋጣሚ በዋሺንግተን ኮንቬንሽን አዳራሽ ለመላው ዓለም በሚሰማ ታላቅ ድምፅ ከተናገሯቸው አይረሴ እና ዘመን ተሻጋሪ ወርቃማ ቃላት መካከል ‹‹ብልሁ እና አስተዋዩ ሲሳይ አጌና›› የምትለው ለእኛ የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ አባላት የትንሳዔ ብስራት ተደርጋ የምትቆጠር ዓረፍተ ነገር ነበረች፡፡
ለ27 ዓመታት ሀገራችንን በዘረኛና ከፋፋይ የአገዛዝ ስልት ረግጦ ሲያስለቅስ የቆየውን የወያኔ አምባገነናዊ ስርዓት ከአጋሮቻቸው ጋር ሆነው ላይመለስ ወደ መቃብር የወረወሩት ታላቁ መሪያችን ዶ/ር አብይ አህመድ በአዳራሹ ንግግራቸው የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናን ስም በኩራት ሲጠሩ በመላው ዓለም ተበትነን የምንገኝ የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች (የመከራ ልጆች) በሲሳይ አጌና ውክልና የእያንዳንዳችን ስም የተጠራና እውቅና የተሰጠን እንደሆነ አድርገን በመቁጠራችን ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል፡፡ ዕለቱንና የዚያን ሰሞንም ‹‹እንኳን ደስ ያለን›› ስንባባል ሰንብተናል፡፡
የወያኔን ስርዓት ሠላማዊ በሆነ የብዕር ጦር ስንፋለም በዚህም የሞትን፣ የእስርን፣ የግርፋትና የስደት አስከፊ ህይወትን ሳንወድ ስንጋት የኖርነው የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ስማችን ተጠቅሶ ለከፈልነው ዋጋ በአደባባይ ዕውቅና የተሠጠን በጉያችን በበቀለው በአምሳያችን ሲሳይ አጌና በኩል መሆኑ ምስጋናው የእውነት አድናቆቱም ከልብ እንደሆነም እንድናምን አድርጎናል፡፡ ምክንያቱም ስለእኛ ለመናገር ከሲሳይ የተሻለ ምሳሌ መኖሩን ማናችንም እርግጠኞች አይደለንም። እኛን ለመግለፅ ሲሳይ አጌናን ምሳሌ ማድረግ ትክክልና ሚዛናዊ ነው፡፡ በነፃው ፕሬስ ውስጥ ለተደረገው አድካሚና አደገኛ ትግል እንዲሁም ለተከፈለው ውድ ዋጋ የሲሳይ የጋዜጠኝነት ህይወት በቂ ማሳያ መሆን የሚችል ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ይህ ገብቷቸው ምናልባትም የራሳቸውን ጥናት አድርገው ነው ‹‹ብልሁ እና አስተዋዩ ሲሳይ አጌና›› ሲሉ በልበ ሙሉነት የተናገሩት። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በፓርላማ በተገኙ ጊዜም ‹‹እንደ ሲሳይ አጌና የሚሰሩትን ሪፖርት ሚዛናዊና ሙያን መሠረት ያደረገ ለማድረግ ብርቱ ጥረት የሚያደርጉ ብርቱ ጋዜጠኞች ዛሬም በየሚዲያው አሉ›› ያሉት የሲሳይን ጥረት፣ የሙያ ብቃትና ጥንቃቄ በመረዳታቸው ነው፡፡ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ማለት የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር በአደባባይ እንደተናገሩለት ነው፡፡ ወደ አሜሪካ ሄዶ የኢሳት ቴሌቪዥን አዘጋጅ ከመሆኑ ብዙ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ዓለምን ሲቀላቀል ጀምሮ ይኸው እንደተባለው ነው፡፡ ጋዜጦች ላይ ፅሑፍ መፃፍ ከጀመረበት የጋዜጠኝነት ‹‹ሀሁ…ዘመኑ›› ጀምሮ ብልህና አስተዋይ ነው፡፡
በ1980ዎቹ አጋማሽ አካባቢ /ነፍሱን ይማረውና/ የነፃ ፕሬሳችን የጀርባ አጥንት በነበረው ጌታመሳይ ገ/መስቀል (ኩሹ) ብርቱ ድጋፍ የነፃ ፕሬስን አለም የተቀላቀለው ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ለተለያዩ የፕሬስ ውጤቶች ወቅታዊና ተንታኝ የሆኑ ዘገባዎችን እየፃፈ ተወዳጅና ተናፋቂ ብዕረኛ ለመሆን የቻለው እንደብዙዎቻችን የአመታት ዕድሜን ከቆጠረ ልፋትና ጥረት በኋላ ሣይሆን መፃፍ በጀመረባቸው ሁለት ወይም ሶስት ወራት ውስጥ ነው፡፡ ፅሑፎቹ ከወቅታዊነትም ባሻገር በሳል እና ሚዛናዊ ትንታኔ የሞላባቸው ስለነበሩ ብዙዎቹ የጋዜጣ አዘጋጆች ፅሑፍ እንዲያቀርብላቸው አብዝተው ይጠይቁት ነበር፡፡ እርሱም በቻለው መጠን ሁሉ የሁሉንም ጥያቄ ለመመለስ ሞክሯል፡፡
ከፅሁፍ አቅራቢነት ወደ ጋዜጣ አዘጋጅነት እራሱን ያሳደገበት ሂደትም ፈጣን ነበር፡፡ የወቅቱን ጋዜጦች የፅሁፍ ለቀማ እና የቅድመ ህትመት ዝግጅት ስራ ያከናውን ከነበረው ብሩክ ዶሚኒክ ጋር ‹‹ኢትኦጵ›› ጋዜጣን ማዘጋጀት የጀመሩት ነፃ ፕሬስን ከተቀላቀለ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር፡፡ ቆይቶ ከብሩክ ዶሚኒክ ጋር ባደረጉት ስምምነት የኢትኦጵ ጋዜጣ አሣታሚነት (ባለቤትነት) ህጋዊ መብትን በእጁ ያስገባው ጋዜጠኛው ሲሳይ አጌና በኢትኦጵ ጋዜጣ በኩል እጅግ ከፍተኛ አድናቆትን ያስገኙለትን ዘገባዎች፣ ትንታኔዎች እና ሚስጥራዊ ሰነዶችን ሲያትም ቆይቷል። የወያኔ ስርዓትን አስቀያሚ መልኮች ያለፍርሀት ጋዜጣ ላይ አሳይቷል። የመጪውን ጊዜ አደጋዎች ከባለፈው ታሪካችን ጋር እያመሳከረ ህዝቡን ሲያነቃ መንግስትንም ሲሞግት ኖሯል፡፡
ሲሳይ አጌና በሙያ ጓደኞቹ ዘንድ በልዩነት እንዲታይ ካደረጉት ብቃቶቹ መካከል ዶክመንት የማደራጀት ልምዱ ዋነኛው ነው፡፡ ስለአንዱ ጉዳይ (ማንኛውንም ጉዳይ ቢሆን) ለመፃፍ የፈለገ ጋዜጠኛ ለዚያ ፅሁፍ የሚረዳውን ልዩ ልዩ መረጃ ለማግኘት የሲሳይን ቢሮ ማንኳኳት የተለመደ ነበር፡፡ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲነሳ ከጦርነቱ በፊት ስለነበረ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ምናልባትም እስከጦርነት የደረሰው የኖረ ቁርሾ ምን መልክ እንደነበረው ለመረዳት ሲሳይን መረጃ ያልጠየቀ ጋዜጠኛ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተጠልፎ ኮሞሮስ ላይ ሲወድቅ በኢትዮጵያ ታሪክ አውሮፕላን የተጠለፈባቸውን ታሪካዊ ወቅቶች ወደኋላ ፈትሾ ሪፖርት ለመስራት ሲሳይን መረጃ ያልጠየቀ የጋዜጣ አዘጋጅ የትኛው እንደሆነም ትዝ አይለኝም፡፡ ለራሱ ሲሰራም (ፅሑፍ ሲያዘጋጅ) እንደሁ ነው፡፡ እዚህ ጋር ወይም እዚህ ቦታ እንዲህ ሆነ ሲሉት ከዚያ በፊት መቼ፣ የት እና እንዴት ያለ ነገር ሆኖ እንደሚያውቅ ለመረዳት በሰፊው የቢሮ መደርደሪያ የተደረደሩትን መረጃዎች ሲያገላብጥ ነው የምታገኙት፡፡
በየሳምንቱ ረቡዕ ዕለት ለንባብ የምትበቃው ባለሰማያዊ ቀለሟ ኢትኦጵ ጋዜጣም በእንዲህ ያሉ መረጃዎች ታጭቃ ነው ዘወትር ለንባብ ትበቃ የነበረው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሠፊ ተደራሽነትና የላቀ ተዓማኒነትን ለማግኘት የቻለችውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ለአንድ ጋዜጠኛ የሙያ ብስለትና ልህቀት ማንበብ፣ መፈተሽ፣ መጠየቅና መመራመር ወሳኝነታቸው የታመነ ነው፡፡ የማያነብ፣ የማይፈትሽ፣ የማይጠይቅና የማይመራመር ጋዜጠኛ እንደወፏ (ፓሮት) የሰማውን መልሶ ከመለፍለፍ የዘለለ ሚና ስለማይኖረው በሙያው የመከበርንም ሆነ ተፅዕኖ የመፍጠርን ዕድል ጨርሶ አያገኝም፡፡ ሲሳይ አጌና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ርቱዕ አንደበት ‹‹ብልሁ እና አስተዋዩ›› ተብሎ ስሙ የተጠራለት አንባቢ፣ ፈታሽ፣ ተመራማሪ፣ ጠያቂና ሚዛናዊ ለመሆን ባደረገው የዘመናት ጥረት እንጂ እንዲሁ ገደኛ ወይም ዕድለኛ ስለሆነ አይደለም፡፡ ለዚህ ክብር የበቃው በጥረቱ እና ለሙያው ባለው ታማኝነት ብቻ ነው፡፡ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ማህበራችን ኢነጋማ በአዲስ መልክ ሲቋቋም ሲሳይን ከስራ አስፈፃሚዎቹ አንዱ አድርገን የመረጥነው ብልህና አስተዋይነቱ ስለገባን ጭምር ነው፡፡
የሲሳይ አጌና ብዕር ለብዙኃኑ ህዝባችን የራስ አንደበት ተደርጎ የመቆጠሩን ያህል ለወያኔ ባለስልጣናትም የእግር እሳታቸው ነበር፡፡ የሲሳይ ፅሁፍ በጋዜጣ ታትሞ ለንባብ ሲበቃ ወያኔዎቹ ደማቸው ይንተከተካል፡፡ እንደፈለጉ በሚፈነጩበት ሀገር እንዲህ ያለ ‹‹ጠላት›› መኖሩ እንቅልፍ ስለማያስወስዳቸውም የጨበጠውን ብዕር እንዲጥልና የሞራል መንኮታኮት እንዲገጥመው ለማድረግ የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ አስረውታል፣ ገርፈውታል፣ ዝተውበታል፤ በመጨረሻም እስከጥግ ገፍተው ከገዛ አገሩ አባረውታል፡፡ እርሱ ግን በተደረገበት ነገር ሁሉ ተሸናፊ አልሆነም፡፡ ይልቁንም ሲገርፉት እየባሰበት፣ ሲዝቱበት እየጠነከረ፣ ሲያስሩትም እየፀና ነው የሄደው፡፡
በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም እንዲሉ የወያኔ ስርዓት አራማጆች ለውጡ መጣሁ ሲል ፈርጥጠው ወደ ምሽጋቸው በገቡበት በአሁኑ ጊዜ ተናካሽ ጥርስና ተናዳፊ ምላስ የነበረው በረከት ስምኦን ቀሪ ዕድሜውን በዘብጥያ ቁዘማ ሊያሳልፍ ወደ እስር ቤት የገባ ቢሆንም ባለፉት የወያኔ ግፈኛ አገዛዝ ዘመናት የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ላይ ታላላቅ በደሎችን በመፈፀም በረከትን የሚተካከለው የለም፡፡ ሲሳይ አጌናም የወያኔዎቹ በተለይም የበረከት ስምኦን በትር በተደጋጋሚ ሲያርፍበት ኖሯል፡፡ የሠራው ሀይጢያት እንቅልፍ ሲነሳው በውድቅት ሌሊት ተነስቶ አዲስ የፕሬስ ህግ ማርቀቅን ልማዱ አድርጎ የነበረው በረከት ስምኦን ከሲሳይ እስር፣ ግርፋት፣ ዛቻ እና ስደት ጀርባ ዘመቻውን የሚመራ እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን፡፡
የምናወራው ስለሲሳይ በመሆኑ እርሱ ላይ የደረሰውን ብቻ እንጥቀስ እንጂ ሁላችንም የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች በበረከት ስምኦን በትር ተወግረናል፡፡ ከእስር፣ ግርፋት፣ ዛቻ እና ስደት ክፉ እጣዎች ጋር ሌሊቱን ፅፏቸው በሚያድራቸው አፋኝ እና አሳሪ ህግና ደንቦችም ብዕራችንን እንድንጠየፍ ተገፍተናል፡፡
ሲሳይ አጌና የወያኔዎች ግፍ መረን እየለቀቀ መሄዱንና የሀጢያት ዝርዝሩ በኢትኦጵ ጋዜጣ ብቻ ተፅፎ የማያልቅ እንደሆነ ተገንዝቦ ‹‹አባይ›› የምትባል ተጨማሪ ጋዜጣ ማዘጋጀት ሲጀምር በረከት ስምኦን ህግ አርቅቆ፣ በፓርላማ አስፀድቆ ስራ ላይ አውሏል፡፡ አንድ ሰው ከአንድ ጋዜጣ በላይ ማሳተም አይችልም የሚል ህግ። በርግጥ ይሄ ህግ ዛሬም ድረስ በስራ ላይ እንደዋለ ነው የሚገኘው፡፡
ብዙዎቻችን በአዲሱ መንግስት ይሻሻላል ብለን ተስፋ ያደረግንበት በስራ ላይ የሚገኘው የፕሬስ አዋጅ ሆነ ተብሎ ግለሰቦችን ለመጉዳትና ከትግል ሜዳው ለማስወጣት የተረቀቀ እንጂ ሌላ ጠቃሚ ምክንያት ኖሮት በስራ ላይ የዋለ አይደለም፡፡ ህጉ ሲሳይንም ሌላውን ጋዜጠኛም ዝም ለማስባል የወጣ ነው፡፡
የለውጥ አራማጁ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ደግሞ ይሄን ሁሉ በሚገባ ያውቃል። ሣይፈልግ በግድ ተገፍቶ ከሀገር የሚወጣውን የኢሳቱን ጋዜጠኛ ‹‹ብልሁ እና አስተዋዩ ሲሳይ አጌና›› ሲል የጠራውም የተከፈለው ዋጋ ውድ እና ታላቅ ፅናትን የጠየቀ እንደነበር ስለገባው ነው፡፡ የሲሳይ ስም ሲጠቀስ ደግሞ በውስጡ እኛም አለን፡፡