ጆሞ ኬንያታ በ1931 ዉድብሮክ በሚገኘው የለንደኑ ኩዌከር ኮሌጅ ተማሪ በነበሩበት ዘመን ካስል ጎዳና በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ወርቃማውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ሰቅለው እንደነበር ጄሬሚ ሙሬይ በ1972 ባሰተመው የኬንያታ ባዮግራፊ ላይ መስክሯል።
ሙዚቀኛ ወይም ፀሃፊ ለመሆን ፍላጎት የነበረው የዚያኔው ተማሪ ኬንያታ ከአንድ አመት በኋላ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ተወግዶ እሳቸውም ንጉሰ ነገሥት ተብለው ዙፋን ሲደፉ ደስታውን መቆጣጠር አቅቶት እንደነበርና ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ልቡ የሳቸውን ፈለግ በመከተል ወደ ነፃነት አርበኝነት እንዳመራችም ይነገራል።
ኬንያታም ከ33 አመታት በኋላ ያሰበው ተሳክቶ፣ ሃገሩም ከብሪታንያ ከቅኝ ግዛት ነፃ ስትወጣና እሱም የነፃይቷ ኬንያ መስራች አባት ሲባል፤ የኬንያ የመጀመሪያው ኦፊሴላዊ የክብር እንግዳና የደማቁ የጃምሁሪ ክብረ በአል ልዩ ተጋባዥ ያደረገው ግርማዊነታቸውን ነበር። ወቅቱም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 1964።
በወቅቱም በወደብ ከተማዋ ሞምባሳ ደርሰው የነበሩትና እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ከቅኝ ግዛት ያመለጡት የወቅቱ የላይቤሪያ መሪ ዊሊያም ቱብማን የግርማዊነታቸው ጉብኝት እስከሚጠናቀቅ መርከብ ውስጥ እንዲቆዩ በፕሬዚዳንት ኬንያታ እንደተነገራቸው ይነገራል።
ግርማዊነታቸው ለኬንያታ በስጦታ መልክ ነጭ አሳማ ያበረከቱ ቢሆንም፤ አሳማ የማይወዱት ጆሞ በሚወዷት ንጉኖ (ላም) እንዲቀየርላቸው አድርገዋልም ይባላል።
ኬንያን ለ15 አመታት ያህል የመሩት ጆሞ በስልጣን ዘመናቸው ከሃገር የወጡት ለሁለት ጊዜያት ብቻ ሲሆን፤ የመጀመሪያው በ1964 እንግሊዝ በተካሄደው የኮሜን ዌልዝ ጠቅላይ ሚንስትሮች ጉባዔ ላይ ለመገኘት ሲሆን ሁለተኛውንና የመጨረሻ ጉዟቸውን ያደረጉት በ1969 “ጆሞ” በተባለችው የጦር ጄት ወደ ኢትዮጵያ ነበር።
ኬንያ በዋና ከተማዋ ናይኖቢ በስማቸው ጎዳና የሰየመችላቸው ታዋቂ ግለሰቦች 3 ብቻ ናቸው። እነሱም የኬንያ ሪፐብሊክ መስራች አባትና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታ፣ የኬንያ ሁለተኛው ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ናቸው።
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኬንያው ጉብኝት ወቅት ከታደሙት ህፃናት አንዱ ፕሬዚዳንት ኬንያታ ከአራተኛ ሚስታቸው ከሆኑት ማማ ንጊና ኬንያታ የተወለዱት ኡሁሩ ኬንያታ አንዱ ነበር። ኡሁሩ ከአባቱ ጆሞ ስለ ግርማዊነታቸው ዝና እየተነገረው ያደገ ነው። ግርማዊነታቸው ከኬንያ መልስ ብዙም ሳይቆዩ በወታደራዊ ጁንታ ከስልጣን ተወገዱ። በብዙ መከራ ውስጥ ያለፉትም ጆሞ ነሃሴ 22 ቀን 1978 ሞምባሳ በሚገኘው ቤተመንግስታቸው አለፉ። አፅማቸውም በቅዱስ እንድርያስ ቤተክርስቲያን በክብር አረፈ።
አባቱ ጆሞ ኬንያታ ሲያርፉ የ17 አመት ልጅ የነበረው ኡሁሩ ሃዘኑ ከባድ እንደነበረበት ይነገራል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሃገሩ ናይሮቢ በሚገኘው ቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት ከተከታተለ በኋላ ፤ ወደ ሰሜን አሜሪካ በማምራት ኢኮኖሚክስ፣ ፖለቲካል ሳይንስና የመንግስት አስተዳደር በአምኸርሰት ኮሌጅ ተከታተለ።
ኡሁሩ የአሜሪካን አገር ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ ሃገሩ ኬንያ በመመለስ ዊልሄም ኬንያ ሊሚትድ የተባለ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልክ ኩባንያ ቢያቋቁምም፤ በውስጡ የሚንቦገቦገው የግርማዊነታቸውና የአባቱ ጆሞን የሃገር መሪነት ጥበብ መተግበር ነበርና ወደ ፖለቲካው ፊቱን አዞረ።
እኤአ አቆጣጠር በ2001 የኬንያ ፓርላማ አባል ሆነ፣ ምንም እንኳን ልምድ የሚጎድለው ቢሆንም ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ በሚንስትር ማዕረግ ሹመት ሰጡት። አራፕ ሞይ ኡሁሩን በሞኒስትርነት መሾም ብቻ ሳይሆን ተተኪያቸው እንዲሆን በመፈለግ ይኮተኩቱት ጀመረ። ከአንድ አመት በኋላ በሃገሪቱ በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የካኑ ፓርቲን በመወከል ኡሁሩ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ራሱን አቀረበ።
የታህሳስ 2002 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድድር ሲጠናቀቅ ተስፈኛው ኡሁሩ በተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪው ምዋይ ኪባኪ በሰፋ ልዩነት ተሸናፊ ሆነ። ወደተቃዋሚ ፓርቲነት የተቀየረው የካኑ ፓርቲም የፓርላማ ተወካይ ሆነ። በ2007 ሞይ ኪባኪ በድጋሜ ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ድጋፍ በመስጠቱም ኪባኪ በ2008 በሚንስትርነት የሾሙት ሲሆን፤ የጥምር መንግስቱም ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የንግድ ሚንስትር በመሆን አገልግሏል።
ኡሁሩ የምክትል ሚንስትርነቱን ሳይለቅ ከ2009 እስከ 2012 የፋይናንስ ሚንስትር በመሆንም በኬንያ ፖለቲካ ልምድ እያካበተና ዕውቅናውና እየጎላ መጣ።
በመጋቢት 2013 በድጋሜ ተስፋ ባለመቁረጥ ለፕሬዚዳንትነት የተወዳዳረው ኡሁሩ ራይላ ኦዲንጋን በማሸነፍና እንደ አባቱና እንደ ግርማዊነታቸው የሃገር መሪ የመሆን ህልሙን እውን አደረገ፣ ባባቱ ዙፋንም ላይ ተቀመጠ።
ኡሁሩ አዲስ አበባ በሚገኘው አፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ ለቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የመታሰቢያ ሃውልት ምረቃ ላይ ከተገኙት አፍሪቃዊ መሪዎች አንዱ የነበረ ቢሆንም፤ ከሌሎች ሃገር መሪዎች በበለጠ ለእሱ ታሪካዊ ዕለት ሆናለታለች። በአባቱ የመሪነት ዘመን ዝናቸው ከአፍሪካ አልፎ በመላው አለም የናኘውና የአባቱ የነፃነት ተምሳሌት፣ የአፍሪካ አንድነት ፈጣሪና የመጀመሪያው የክብር ፕሬዚዳንት የሆኑት የግርማዊነታቸው ክብር በአለም በድጋሜ በሚገለጥበት ቅፅበት እሱ የሃገር መሪ ሆኖ በልጅነቱ በጃምሁሪ ክብረ በአል ከኋላቸው የተከተላቸው አባባ ጃንሆይንና አባቱ ጆሞ ኬንያታ በአይነ ህሊናው እየዞሩ በትዝታና በሲቃ ወደኋላ መልሰውታል።
የንጉሰ ነገስቱ ሃውልት በክብር ከተመረቀ በኋላ ኡሁሩ በፍጥነት በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙሃን ይቺ ቀን ምን ያህል የምታስደስት ቀን እንደሆነች ለማወጅ የቀደመው ርዕሰ መንግስትም ርዕሰ ብሔርም አልነበረም። በኦፊሴላዊ የትዊተር ገፁ:
” Honoured to have attended the unveiling ceremony of the statue of Emperor Haile Selassie at the AU Headquarters. The Emperor’s contribution to Africa’s liberation is the reason we are here today as a united Africa, as we seek collaborative ways to prosper our people and continent “
“በአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ የመታሰቢያ ሃውልት የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ በመገኘቴ ክብር ተሰምቶኛል። ዛሬ እዚህ በተባበረ አፍሪካዊ አንድነት እንድንቆም፣ ለሕዝባችንንና አህጉራችንን መለወጥ የትብብር መንገዶችን ለመፈለግ እንድንችል
ግርማዊነታቸው ለአፍሪካ ነፃነት ያበረከቱት አስተዋፅዖ ዋነኛ ምክንያት ሆኖናል።” ብለዋል።
በመጨረሻም የግርማዊነታቸው የመታሰቢያ ሃውልት በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ እንዳይቆም በአቶ መለስ ዜናዊ መሪነት ከፍተኛ ዘመቻ ቢካሄድባቸውም እስከመጨረሻው ሳይታክቱ የሃውልቱ መቆም ዕውን እንዲሆን ካደረጉት መካከል የፓን አፍሪካኒስቱ ክዋሜ ንክሩማን ልጆች የሆኑትን ጋናውያንን ማመስገን ተገቢ ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድም በትረ ስልጣን በጨበጡ 10 ወር ባልሞላ ጊዜ ይህ እንዲሆን በጎ ፈቃዳቸውን ማሳየታቸው ዕድለኛም ተመስጋኝም ያደርጋቸዋል።
አፍሪካዊነት ይለምልም።
(በፎቶው ላይ የአሁኑ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ከግርማዊነታቸው በስተኋላ የሚታየው ነው)