የግማሽ ቀን ውሎ | አቤል ዋበላ

የግማሽ ቀን ውሎ | አቤል ዋበላ

ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነሳ ከቤት መውጣት ይደብርሃል። ከኤርትራ የመጣው ሰውዬ ከስግብግብ አከራይህ ጋር የቆለሉት የቤት ክራይህን በሰላሳ ስትመታው፣ በቀን ሲሰላ ስንት እንደምትከፍል ስታስብ፣ ፌር አይደለም ትላለህ። ትንሽ አልጋ ላይ እየተንከባለልክ ኪሳራ ለመቀነስ ታስባለህ። ታጉረመርማለህ፣ የቴሌዥንህን ድምፅ ከፍ አድርገህ ጎረቤት ትቀሰቅሳለህ። ተመስገን በየነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሲል እንዳትጨርሰው ትለውና ተንደርድረህ ከቤትህ ትወጣለህ። የቀን ውሎህን ስታስብ ከኮርፖሬት ጋር ለመፋለም ወደ ፍርድ ቤት መሄድ እንዳለብህ ትገነዘባለህ። ቦሌ ክፍለ ከተማ ፍርድ ቤት እንደምትሄድ ሲገባህ መንገድህ ረጅም እና አሰልቺ እንደሚሆንብህ ይገለጥልሃል።

ቦሌ ክፍለ ከተማ እንደ ቦላሌ የሰፋ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ደግሞ የምድር ጥግ፡፡ መንገዱን እንዲገፋልህ ከኮርፖሬት ጋር ስለሚያካስስህ ጉዳይ ታብሰለስላለህ። የማያልቅ ክርክር፤ የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ እንኳን መለ ተበጀለት፡፡ የእኔ እና የተደመረው ተወልደ ክርክር ግን መጨረሻ አጣ፡፡ ከየት ለጅምር?

ኢንጅነሪግ እና ህክምና ያበላል ሲባል ሰምተህ የማይገባህን ኤሌክትሪክ፣ ሜካኒካል፣ ኢንዱስትሪያል፣ ቴክስታይል ታጠናለህ። ሌሊት ላይብራሪ ታድራለህ አይገባህም ነገር ግን ትመረቃለህ። ከመምህራን መካከል ከጂረኛ እና ኮርባጋ በቀር ማንም እንዳልገባው ስትገነዝብ ትፅናናለህ።

ስራ ትፈልጋለህ፣ ወርልድ ክላስ ሲባል ትስማለህ፣ ትመዘገባለህ፣ ትቀጠራለህ፣ የነተወልደን የዘር እና የጥቅም ሰንሰለት ትፀየፋለህ፣ ወያኔ የተባለ አካይስት ሀገሪቱን እያግማማት እንደሆነ ትገነዘባለህ። ሰው ሲታሰር ምናምን ትሰማለህ። ህዝቤ ፖለቲካን በሩቁ ማለቱ ያናድሃል። ብሎግ ማድረግ ምናምን ያምርሃል። ፌደራሊዝም እና ፌደራል ፖሊስ ያላቸው ዝምድና ይገባሃል።

ህገ መንግስት፣ ህገ አራዊት፣ ፉኩያማ፣ ሀቲንግተን፣ ማርካኪስ፣ ፓንክረስት፣ አረብ ፋቂህ፣ አባ ባህሪይ፣ ላጲሶ፣ ክፉሉ ታደሰ፣ ያ ትውልድ ምናምን ጂኒጃንካ ታነባለህ። የታሰረ ይፈታ ትላለህ፣ የህግ የበላይነት ትተረከካለህ። ዜና ትሰማለህ። መለስ ዜናዊ እንኳን ፍግም አለ ብለህ ትፅፋለህ፣ ምርጫ ይደርሳል። መንግስት ይደነብራል። ኃይለማርያም ዘተባለ የውሃ መሀንዲስ አንተን አስሮ ቢቢሲ እና አልጀዚራን ያስፈራራል። ማዕከላዊ ትገባለህ ተክላይ ያዛል። ምን ላርግልህ፣ ፈይሳ እና ርእሶም ሙድ ይይዙብሃል። ግርግዳ ግፋ ይሉሃል፡፡ ትገፋለህ፡፡ ግንቦት ሰባት፣ አስራ አራት፣ አስራ ሰባት፣ ሀያ ሰባት ትባላለህ፣ ኦነግ ትባላለህ፣ ከኦብነግ፣ ከአልሸባብ፣ አልቃይዳ ጋር ትታሰራለህ። ከጉሙዝ ጋር ትደንሳለህ፣ ኦሮምኛ ትዘፍናለህ፣ ከሱማሌ ጋር በምልክት ቋንቋ ታወራለህ። ተክላይ ሲደብረው አንተንም ማየት ሲያቅለሸልሸው ቅሊንጦ ወደጨርቆስ፣ ሐጎስ፣ ንጉሴ ይልክሃል። ከጉሊት ቸርቻሪነት አውጥቶ እዚህ ያደረሰኝ እናት ደርጅት አህዴድ የሚል ዳኛ አስራ ስምንት ወራት ፍርድ ቤት ያመላልስሃል።

እስከዚያው ትደቦቃለህ ትዋከባለህ፣ መቅዱስ ይኖረሃል። ትደቦቃለህ፣ ትቦካለህ፣ ከጀለስካ ጋር ስትቀድ ትውላለህ፣ መቅዱስ ይኖረሃል፣ ስምንት እና ትልቁን ታርፋለህ። መርከብ ትጭናለህ ታወርዳለህ፣ ኦባማ መጣ ተብለህ ቴሌቭዥን ታያለህ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግስትህን ሲያወድስ ትሰማለህ። ታራለህ፣ ትደብናለህ፣ ምን ታመጣለህ። ምርጫ ደርሶ መረራ ወያኔን ሲስገባለት አልጋ ላይ ቆመህ መግለጫ ትሰጣለህ። ትንታኔ ትጠላለህ፣ ጦሩ መቼ ይመጣል ነው ወሬው። መቼ ነው ጦሩ አርማጭሆን የሚያልፈው መቼ ነው ጥያቄው። ብር ሸለቆ ወታደሩ አምጿል ነው። ሁርሶ ከባድ ችግር አለ ነው። አዲስ በግራፋቲ ተጥለቅልቃ አደረች ነው። አምቦ ፍርድ ቤቱ እና የከንቲባ ቢሮ በህዝብ ተከቦ ነደደ ነው። ሰባት jት ከዳ ነው። የአለም ሀገራት ብድር ከለከሉ ትባላለህ፡፡

ይህን ሁሉ ሰምተህ ፍርድ ቤት ስትሄድ ላይፍ ጎስ ኦን አዝ ኢፍ ነቲንግ ሀብንድ። መንግስት ሲደብረው ይፈታሃል። የጎዞ ማዕቀብ ይጥልብሃል። ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያመላልስሃል፡፡ ኑሮህን ካቆመበት ልታስነሳው ትሞካክራለህ፡፡

ተወልደ ጋር ሄደህ ወደስራዬ መልሰኝ ትለዋለህ። ለደንበኞቼ ደኀንነት ሲባል ሽብርተኛ አልቀጥርም ይልሃል። ዳኛ ጋር ትሄዳለህ ሲያመነታ አመታት ይፈጃል። ትርሃስ ለአየር መንገዱ ትፈርዳለች፣ ደምለው ላንተ ይፈርዳል፡፡ የህግ አማካሪ ጋር ትሄዳለህ አያልቅም ወይ ትለዋለህ፤ አፈጻጸም፣ ይግባኝ፣ በይገባኝ ላይ ይግባኝ ነው፡፡ ትንሽ ትንሽ ይገባሃል፡፡ አሁንም አላላቀም ብለህ መጠየቅ እንዳለብህ ማስታወሻ ትይዛለህ፡፡ አሁንም አላለቀም፣ መንገዱም አላለቀም፤ እስካሁን ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ለመሄድ ታክሲ ውስጥ ቁጭ ብለሃል። ጎጃሜው ሹፌርም ምንም አይነት ሴንስ ኦፍ አርጀንሲ አይገባውም። ከእንጅባራ ቲሊሊ ከሚያደርገው ጉዞ የተለየ አዲስ ነገር የለም። ከሆሮ ጉዱሮ የመጣው ወያላ ሰውን በመዳበሪያ እንዳለ ጭድ ይከምረዋል። ከመግባትህ በፊት በአይኑ ኪሎህን ይመዝናል። ቦታ እንዳትፈጅ አድርጎ አንድ ጥግ ይወትፍሃል። አንድ አራት ሰዎች ሰውነታቸውን አጥፈው ካንተ የተረፈውን ቦታ ይሞሉታል። ቢችገርህ መስኮት ከፍተህ ግማሽ ትከሻህን ወደውጭ ታደርጋለህ።

ታክሲው አሁንም አልደረሰም። ሾፌሩ አንዴ አበበ ግደይን ያስጮህብሃል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንቅጥቅጥ የሚያስወርድ ሙዚቃ ከፍቶ መሪው ላይ ይመሰጣል። የሰፈሩ ብዛት እና ስም ይጨንቅሃል። ጎሮ ነው፣ የረር፣ በረር፣ ቦሮ ነው፣ ፊጋ ነው፣ ዱጋ ነው፣ ቡጋ ነው፣ ምንድን ነው ይህ ሁሉ ቦሌ ክፍለ ከተማ ነው? ታክሲው አልፈህበት በማታውቀው ሰፈር ይሄዳል። ይሄ አዲስ አበባ ነው ወይ ብለህ ትጠይቃለህ፣ ቦሌ እና ባሌ ይምታታብሃል። ረግጠህ በማታውቀው መሬት ቄለም ቁጭ ብሎ ሜንጫ የሚሞርድልህ መኖሩን ስታስብ ጦሽ ብለህ ትስቃለህ። ተሰፋሪው እንደ እብድ ይመለከትሃል። በሰበቡ ቃኘት ታደርጋቸዋለህ፣ እናቶች አሉ፣ አክስቶች እና አጎቶችም አይጠፉም። የከሸፈ ሜካፕ ታያለህ፣ የታክሲው ሽታ ጫንጮን ያስታውስሃል።

እንዳያልፉት የለም ፍርድ ቤት ትደርሳለህ፣ የስራ ክርክር ችሎት ስትገባ ቀጠሮህ ነገ መሆኑን ትገነዘባለህ። የዚያን ጊዜ ከነጋ እህል ባፍህ እንዳልዞረ ይገባሃል፡፡ አዲስ አበባ የሚባል የማታውቀው ከተማ መሀል ራስህን ታገኘዋለህ፡፡ ብሩንዶ የሚል የተጻፈበት ቤት ታያለህ፡፡ ፒያሳ ትዝ ይልሃል፣ ጸዴ ጸዴዎች የሚገቡበት አንድኛ ክትፎ ቤት ነበር፡፡ በበሩ አልፈን ከአፋር ኬክ ቤት እንታደማለን፡፡ ልጅ ሆኜ ብርንዶ ሳልገባ አደኩኝ፡፡ አሁን የለም፡፡ በውስኪ ፋንታ ፍሪጅ ተደርድሮበታል፡፡ አሁንም አዲስ አበባ ነው ያለኹት የማላውቀው አዲስ አበባ፤ ተንደርድሬ ብሩንዶ የሚለው ቤት ገባኹ፡፡ የሰላቶ ክልስ የመሰለች ልጅ ልትታዘዘኝ መጣች፡፡ ዱለት ቢጤ አዝዤ ቁጭ አልኩኝ፡፡ ከጎኔ ያሉ ተሰናጋጆች አሉ፡፡ ሦስት ናቸው ቁርጣቸውን ጥብሳቸውን አዘዙ፤ አንደኛው ጫሊ ነው ስሙ፡፡ በስልክ ሲያወራ ሰማኁታ፡፡ በሬው ኦሮሞ ነው እንደማይል እርግጠኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን ከአሁን አሁን በሬው በኦሮሞ ሳር እና ውሃ ነው የደለበው እንዳይል ሰግቻለኹ፡፡ በጨዋ ደንብ ሂሳብ ከፍለው ወጡ፡፡ እኔም ተከተልኳቸው፡፡ ወደ ከተማ እየተመለስኩኝ ይህንን የውሎ ማስታወሻየን አሰፈርኩኝ፡፡

የተረክ አውድ:- #TrueStory
የአፃፃፍ ስልት:- ከ Yohannese T Degu የተኮረጀ

LEAVE A REPLY