– በፍቅር የተጀመረው ጉዞ መንደሮችን አቆራርጦ ትግራይ ምድር ደርሷል።
– የትግራይ እናቶች በእልልታ ዘማቾችን እየተቀባበሉ በመቀበል ተጠምደዋል
– በ20 ቀናት የሚጠናቀቀው ከ አዲስ ዓድዋ ሩጫ ተጀመሯል
ምክትል ከንቲባው ሊንጂነር ታከለ ኡማ ለዓድዋ ከተማ ከንቲባ በብራና የተፃፈ ደብዳቤ በገስጋሽ ራጮች ልከዋል።
አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም በሽኝቱ ተገኝቶ አድናቆቱን ገልጿል።
ከአዲስ አበባና ከሐረር የተነሱ የዘንድሮ ጉዞ ዓድዋ 6 ዘማቾች ከራያ ቆቦ እስከ ማይ ነብሪ የገጠማቸው ይህ ነበር።
* ሮቢት
የራያ ሮቢት ከተማ ነዋሪዎችና አስተዳዳሪዎች እንደ ሲሪንቃ የግብርና ተመራማሪዎች የቆቦን ጉዞ በፍቅር ጠልፈው ከተማቸውን የድል እለት አስመስለውታል። ባህላዊ የራያ ቆቦ ሙዚቃ ቡድን አባላት ተጓዦችን በመቀበል ልዩ ልዩ ጣእመ ዜማዎችን በማሰማት፤ በስክስታና ጭፈራ የዛለውን የተጓዦች ሰውነት ሲያነቁ አምሽተዋል። ተጓዦች ድካሙን ረስተው የዘፋኝነቱን ቦታ ሳይቀር ተረክበዋል። ከተጓዦች መሐል ሰለሞን ባዩ የተባለው ባለ ዘረፈ ብዙ ተሰጥኦ ወጣት የማሲንቆ ጨዋታ በመታጀብ የደመቀ ፍቅር ልውውጥ ተደርጓል።
“ፈለግ ተከትለን” የተሰኘው የጉዞ ዓድዋ መዝሙር ከተጓዦች አልፎ ታዳሚዎች በጋራ የሚያዜሙት ዜማ እየሆነ መጥቷል። ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅት የራያ ቆቦ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን በመሳሪያ በማጀብ ከታዳሚዎች ጋር ተጓዡች እኩል ዘምረዋል።
የሮቢት ዝነኛ የማር ጠጅ ከፍየል ጥብስ ጋር ተወራርዶ በደስታና በፌሽታ ባመሸው የአቀባበል ስነሥርዓት ላይ ተጓዦች ወሳኝ የሚሏቸውን መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
“የራያ ቆቦ ነዋሪዎች የሀገራችንን አንድነት የሚያጠናክር ተግባር ሁሌም እንደምትፈጽሙ ዛሬ እኛን ተቀብላችሁ በመሸኘት ያሳያችሁት ፍቅር ምስክር ነውና በእጅጉ ተደስተናል” በማለት የጉዞ ዓድዋ ዋና አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ መልእክቱን የገለፀ ሲሆን የራያ ቆቦ ወራዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስዩም መስፍን በበኩላቸው “የአያቶቻችንን የጋራ መስዋእትነት ለመዘከር ከአዲስ አበባ እና ከሐረር ተጉዛችሁ እዚህ ሮቢት ከተማ በመድረሳችሁ የተሰማኝን ደስታ በመግለጽ፤ ጉዟችሁ በስኬት እንዲጠናቀቅ ምኞታችንን እንገልጻለን” ብለዋል።
* አላማጣ
~ከራያ ሮቢት እስከ አላማጣ ከ55 ኪ.ሜትር በላይ የሚፈጀው ረዥም መንገድ ያለምንም ችግር አቆራርጠው አላማጣ ከተማ የደረሱት ተጓዦች የከተማው ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዝመራ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት አቀባበል አድረገዋል።
~በትግራይ ውስጥ ባሉ የትኛውም ቦታ በሰላም ጉዞው እንደሚጠናቀቅ በማረጋገጥ ንግግር ያደረጉት የከተማው የፀጥታ ዘርፍ ዋና ኃላፊ “በፀጥታ ጉዳይ አንዳችም ስጋት ሳያድርባችሁ በሰላም ዓድዋ እንደምትደርሱ እናረጋግጣለን” በማለት ንግግር አድርገዋል። በጣፋጭ የእራት ግብዣ እና በጥሩ መኝታ አቀባበል ያደርጉት የከተማው ባለስልጣናት በማግስቱ ያለውን ጉዞ አጅበው የሚጓዙ ሰዎች ማዘጋጀታቸውን በመግለጽ ጉዞው የተሳካ እንዲሆን ተመኝተዋል።
* ኮረም ሐሸንጌ
~ከዚህ ቀደም የኮረም ከተማ ከንቲባ የነበሩት የአሁኑ የትግራይ ክልል የደቡባዊ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኃይለ ምስጉን እና በኦፍላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ልበሎ የቅርብ ክትትል በኮረም ከተማ ነዋሪዎች በተለይም አቶ አበራ በየነ፣ አቶ አስናቀ ውበቱ። አቶ ክብሮም ካልአዩ፣ አቶ ዝናቡ ማልደይ እና ወ/ሮ ኃይማኖት ሰብስቤ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የከተማውና ወረዳው ነዋሪዎች ሁለት ፍየሎችን ከነህይወታቸው፥ የምሳ እና የእራት ግብዣና ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ለተጓዦች አበርክተዋል።
~ተጓዦች የግራትካህሱ ተራራን አቀበት ማራኪውን እና ነፋሻውን መልክዓ ምድር እያቆራረጡ በኮረም ባህላዊ መጠጥ ኮረፌ እስከ ሐሸንጌ የተዋዛው አስደሳች ጉዞ የተጓዦች ስሜት የሚነካ እንደነበር አዘጋጆቹ ይገልጻሉ።
~የከተማው ከንቲባ አቶ ዳርጌ መረሳ እና የከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀብቱ አብርሃ አማካኝነት ስለ ኦፍላ ኮረም ታሪካዊ ቦታዎች ገለፃና የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ቀርቧል።
~በትግራይ ውስጥ ብቸኛ የተፈጥሮ ሐይቅ የሆነው የሐሸንጌ ሐይቅ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጉልህ አሻራ ካላቸው ቦታዋች መሐል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ሐይቅ በደለል በመሞላት ከግዜ ወደ ግዜ አደጋ ውስጥ እየወደቀ መጥቷል። በእለቱም የከተማው ነዋሪዎችና አስተዳደር ባለስልጣናት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይህንን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅ እንዲነሳሱ ጥሪ አቅርበዋል።
* ማይጨው
ታሪካዊው የማይጨው ከተማ እንደወትሮው በልዩ የኢትዮጵያዊነት መስተንግዶ ተጓዦችን የተቀበለ ሲሆን በምሽቱ አሐዱ ሆቴል ውስጥ በተዘጋጀ የአቀባበል ስነሥርዓት ላይ ተጓዦችን በእንባ ያራጨ ንግግር የምሽቱ ክስተት ነበር። አዛውንቱ የማይጨው ነዋሪ አቶ አብርሐ ፀጋዬ ባደረጉት ንግግር የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።
“እንደምታዪት ሽማግሌ ነኝ። ዛሬ እንባዬን ምን እንዳመጣው ልነግራችሁ እፈልጋለሁ። በደርግ ዘመን የማይጨው ከተማ ነጋዴዎች የነበርን ሰዎች ተሰባስበን መንግስት ፈቅዶልን አንድ ኮሚቴ አቋቁመን ነበር። በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ግዜ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እናስከብራለን ያሉ ጀግኖች አጥር ሳይከልላቸው እዚህ ቦታ ላይ ደማቸውን አፍሥሰው እንደተቃቀፉ ሞተዋል። እነዚህን ጀግኖች ከወደቁበት አፈር አንስተን፤ ሙዚየም አሰርተን በክብር እንዲቀመጡ አደረግን። እና እነዚያ ተቃቅፈው የወደቁ ጀግኖች አያቶቻችን ተነስተው በእግራቸው ሲሔዱ ዛሬ በማየቴ በደስታ አለቀስኩ። እንኳን መጣችሁልን። ማይጨውና ትግራይ የእናንተን አይነት የኢትዮጵያ ፍቅር ሁሌም ይራባሉ። ፍቅር ይዛችሁ ስለመጣችሁ ሁሌም ህይወታችሁ የፍቅር ይሁን”
*አዲሽሁ /አምባላጌ/
~ከ123 አመት በፊት በዓድዋ ዘመቻ የመጀመሪያው ውጊያ የተደረገበት እና ኢትዮጵያዊያን በድል ያጠናቀቁበት ታሪካዊው የአምባ አላጌ /እምባ አላጄ/ ተራራ ዛሬም ታሪክ መስካሪነቱን እንደቀጠለ ነው። ወደ ተራራው ለመድረስ በነበረው ጉዞ ላይ እንደወትሮው ሁሉ እናቶች ከየቤታቸው የሰበሰቡትን በመልክም በጣዕምም የተለያየ እንጀራ ከተለያዩ ወጦች ጋር ይዘው በየመንገዱ ተጓዦችን እየመገቡ ተቀብለዋል።
* ማይሹም
~ወደ ሔዋነ ማይ ነብሪ በሚደረገው ጉዞ መሐል ማይ ሹም በተባለች መንደር አንዲት የቅድስት ማርያም ገዳም ተተክላ ምርቃቷ ነበር። ከተጓዦች መሐል በሁሉ ነገር ንቁ የሆነው ተጓዥ ፋንታሁን እንዲህ አለ “ያሬድ ሹመቴ ምን ብሎን ነበር?… ‘ድግስ አይተህ አትለፍ’…” የጉዞ ዓድዋ 6 አባላት ተሳስቀው ወደ ገዳሟ አካባቢ ሲደርሱ አንድ መነኩሴ መጥተው ሁሉም ተጓዦች ወደ ድንኳኑ እንዲገቡ ጥሪ አቀረቡ። ሁሉም ያለማመንታት ወደ ውስጥ ገቡ።
~በርካታ ታዳሚ በነበረበት ድግስ ላይ ከተለያዩ የትግራይ ከተሞች የመጡ እናቶች የሌሊቱን እና የንጋቱን ስነሥርዓት ጨርሰው ከግብዣው በኋላ ጋደም ብለው ነበር። ፊታቸው በብርድና ፀሐይ የገረጣውን ደስታ ግን የሚነበብባቸውን ተጓዦች ሲመለከቱ ሁሉም በስስት ተነስተው አገላብጠው መሳም ጀመሩ። “ወይ ዞም ደቀይ ብጥኣሚ ዲኺሞም ነፍሶም ቆሲሉ እስኺ ካብቲ ፀበል አጥእምዎም” ሲሉ ለሁሉም ተጓዦች 48 ሰሀን አቀረቡ።
አንድ እናት በመሐል ተጓዦችን ከጥበቃ አባላቶቻቸው ጋር የሚያጅቡትን ረዳት ኮሚሽነር መንግስን ጥያቄ ጠየቁ “መን እዮም?” ኮሚሽነሩ መልስ ሰጡ “ናይ ዓድዋ ሰላም ተጓኣዝቲ እዮም” አዛኟ እናት በስስት ንግግራቸውን ቀጠሉ። “ሰላም ይሃቦም። ሃሳቦም ያስምርሎም”
ምግብና መጠጡ ከጥጋብ በላይ ከተፈፀመ በኋላ የጉዞው ዋና አስተባባሪ ምስጋናውን አቅርቦ “አንድም ድንበር ሳናቋርጥ በኢትዮጵያ መንደሮች አቆራርጠን እናንተ ጋር ደረስን።በየመንገዱ ሁሉም ሰላምታ ልኮላችኋል። የደሴ ምክትል ከንቲባም ሰላምታችንን አድርሱልን ባሉን መሰረትም ለእናንተ ሰላምታቸውን እናደርሳለን። በኢትዮጵያ እንድንኮራ ዳግም ስላደረጋችሁን ለሞቀው አቀባበላችሁ እግዚአብሔር ይስጥልን” በማለት ምስጋናውንና አቅርቧል። ከዘማቾቹ መሐል አበበ ሉሉ የተባለ ወጣት “ስብሐት ለአብ…” ሲል ምስጋናውን አቀረበ። የገዳሟ አስተዳዳሪ ቃለ ቡራኬያቸውን ከሰጡ በኋላ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።
“…እናንተ እንዳላችሁት ሀገራችን መንደሮች እንጂ ድንበሮች የሏትም። በዚህ ፍቅር ከሀረርም ከአዲስ አበባም እንደተነሳችሁ ሁሉ በየአመቱ ከሁሉም አጽናፍ በዝታችሁ ብትጓዙ ድንበር አፍርሳችሁ ሁሉንም መንደር እያደረጋችሁ ቀይ ባህር እንደምትደርሱ እርግጠኛ ነኝ። ይህ ሀሳባችሁ ደግሞ እንደሚሰምር በዛሬው በዓል ላይ ያለ ጥሪ በቀኑ መድረሳችሁ ትልቅ ምልክት ነው። እግዚአብሔር መንገዳችሁን ይባርክ”
* ማይነብሪ
~በማይነብሪ የምሽት አቀባበል ስነሥርዓት ላይ የከተማው ነዋሪዎች የሔዋነ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ኃይለ በተገኙበት ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምስራቅ ትግራይ ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር መንግስ “ይህ ጉዞ ለእኛ በእጅጉ የምንፈልገው ነው። ትግራይ ሀገራችሁ ናት። አብሬ በእግር ተጉዤ እንዳየኋችሁ ሁላችሁም አንድ አይነት ናችሁ። ብሔር የላችሁም። የምታስቀድሙትም ኢትዮጵያን ነው። ይሔ በጣም የሚያኮራ ነው። እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም። የኔ ስራ የህዝቡን ደህንነት መጠበቅ ነው. እንደ እናንተ አይነት ሰላም የሚዘምርን ሰው መጠበቅ ደግሞ የኔንም ስራ ስኬታማ ያደርገዋል። ስለዚህም ሀገራችሁ ውስጥ በመሆናችሁ በፍቅር ዓድዋ ደርሳችሁ በአሉን እንደምታከብሩ እርግጠኛ ነኝ” ሲሉ ተደምጠዋል።
~በዚህ መልክ እየተካሔደ ያለው ጉዞ ያለ አንዳች ችግር አሁንም እንደቀጠለ ነው። ወንድማችን መንግስቱ ዘገየ ከአሜሪካ ለተጓዦሽ የስንቅ ድጋፍ በማድረግ ከሌሎች ደጀኖች መሐል አንዱ ሆኗል።
~ በተያያዘ መረጃ በሩጫ ገስግሰው በ20 ቀናት ውስጥ ዓድዋ ለመድረስ ከአዲስ አበባ የተነሱት 2ቱ የጉዞ ዓድዋ ሩጫ ገስጋሾች ሽመልስ ታደሰና በኃይሉ አድማሱ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ተነስተው ዛሬ 460 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኘው ጢሳ አባ ሊማ መንደር ደርሰዋል።
ከሳምንት በፊት በጽህፈት ቤታቸው አሸኛኘት ያደረጉላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ክቡር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለዓድዋ ከተማ አቻቸው በጥንቱ ደብዳቤ አላላክ ደንብ በብራና የተጻፈ ደብዳቤ አስይዘው የእንኳን አደረስዎት ጦማር ልከዋል።
በሽኝቱ ላይ የተገኘው ጀግናው አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም የሯጮችን ውሳኔ አድንቆ፣ እጅግ ከባድ አስቸጋሪ ተግባር ለመፈፀም መነሳታቸው በማንሳት “በጣም ከባድ ሩጫ ነው። ለ20 ተከታታይ ቀናት ማራቶን መሮጥ በእጅጉ ይከብዳል። እንዴት እንደምትችሉት መገመት ይከብደኛል” በማለት በሩጫ ወቅት መወሰድ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ሙያዊ ምክሩን ሰጥቷል።
~ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በበኩላቸው “ፕሮፌሽናሎቹ በቴክኒክ ስትሮጡ የዓድዋ ዘማቾች ደግሞ በልባቸው ይሮጣሉ” በማለት ሁሉንም ፈገግ አሰኝተዋል።
~የታላቁ ጀግና ራስ አሉላ አባነጋ ጦር በዓድዋ ድል ላይ የነበረውን ጉልህ ሚና ለማሰብ የንጉሰ ነገስቱ አፄ ምኒልክ ጦር እና የራስ መኮንን ጦር ለመዘከር ከአዲስ አበባ እና ከሐረር የተነሱትን የዘንድሮ ተጓዦችን ከመቐለ ከተማ የሚቀላቀሉት የሽሬ ልጆች ከመቐሌ እስከ ዓድዋ ድረስ ያለውን መንገድ ጉዞ ዓድዋ 6ን ተቀላቅለው በእግር ለመጓዝ ወደ መቐለ አምርተዋል።
“ታሪካዊ ጀግኖቻችን የልዩነታችን ምክንያት ሳይሆኑ የአንድነታችን መሰረቶች ናቸው”
#ፍቅር_ለኢትዮጵያ!
#ኢትዮጵያዊነት_ይለምልም