ከኢትዮጲስ ጋዘጣ – አዲስ አበባ
የችግር ጫፍ እያሸተቱ እንደጦጣ የሚንጠለጠሉ የፖለቲካ ቆማሪዎች፤ ውለው ሲያድሩ አደብ ይገዛሉ ብለን ነበር። የእለት ተለት ግብራቸው ግን ይህንን እሳቤ ስህተት አድርጎታል። ለለውጥ ሳይሆን ለነውጥ የተደመሩ ስለመሆናቸው ግብዝናቸውና እኩይ ተግባራቸው ምስክር ሆኖናል።
ሰሞናዊው የፊንፊኔ ካርድ መዘዛ ምናልባትም የመጨረሻዋ መቆመርያ ልትሆን ትችላለች። ሸገር ሁሉንም ጎሳ በጥላዋ ስር ሸሽጋ ይዛለች። በቀጭን ክር ሳይሆን በረጃጅም ስሮችዋ አጋምዳ አቆይታለች። ይህችን ታሪካዊ ከተማ በአፈ-ታሪክ ትርክት ለመበጠስ የሚደረግ የሙከራ ስርጭት እየታየ ነው። ግን ሩቅ አያስኬድም።
ታሪክን ሳይሆን ይልቁንም የፈጠራ ድርሳን ይዘው ትላንትን ለዛሬ ባለእዳ ማድረግ የሚሹ መኖራቸው አይደነቀንም። የገቡበት የፖለቲካ ንግድ የሚወረወርላቸው ድርጎ መንጠፍ ሲጀምር ይህን ሊያደርጉ ግድ ይላቸዋል።
እርግጥ ነው። በራስ እንጂ በተውሶ ማንነት የሚፈበረክ ነገር ተረት እንጂ ታሪክ ሊሆን አይችልም። ተረት ደግሞ ያው ተረት ሆኖ ነው የሚቀረው። በዝቅተኛ ንቃተ-ህሊና በሚገኝ ህብረተሰብ ውስጥ ችግሩ ጥሎት የሚሄደው አሻራ ግን ቀላል አይሆንም።
ከሁለተኛ መንግስት እወጃ በኋላ፤ ሕዝብ ለመንግስት ሳይሆን ለጽንፈኛው እንዲገብር የማድረጉ ስራ በስፋት ተተግብሮ አይተናል። የውሃ መስመር አግቶ ሕዝብን በጥማት ከመጨረስ ጀምሮ፣ ዜጋን ዘቅዝቆ እስከመስቀል የደረሱ ጭካኔዎችን ለማየት በቅተናል።
አዎ! ሁለት መንግስት። አንዱ ሲያጥር ሌላው ሲያፈርስ፣ አንዱ ሲያነድ ሌላው ሲያጠፋ፣ አንዱ ባንክ ሲዘርፍ ሌላው ሲመለከት፣ አንዱ ሲገድል ሌላው ቆሞ ሲታዘብ፣…. በእህህ ብቻ መንፈቅ አለፈ።
ሕዝብ ያንን ሁሉ መከራ ከኋላ ጥሎ የእፎይታን ትንፋሽ እንኳ ገና ሳይስብ እነሆ ለአዲስ አበባ ጦርነት ዝግጅቱ መጠናቀቁ እየተነገረን ነው።
ጃ-War ሁለት አማራጮችን ሰጥቶናል። አንደኛው አማራጭ ምርጫ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፍጥጫ። በሁለቱም መንግድ እንደ ማይክ ታይሰን እንዘርራችኋለን ብሏል። ሃሳቡን እዚህ ላይ ቢቋጨው ሸጋ ነበር። የምርጫው ነገር ካልተሳካልን አንላቀቅም ብሎ ቀዩን መስመር ርግጦ ቆሟል። ታድያ ይህንን የጦር አበጋዝ “ተረጋጋ፣ እዚያም ቤት እሳት አለ” ማለቱ ሳይበጅ ይቀራል? ይህ ካልሆነ አዲሱ “ያዙኝ ልቀቁኝ” ዜማ ቅስፈቱ ከባድ ነው ሚሆነው።
የፖለቲካ ትርፍ ለማሰባሰብ የተደረገ የፖለቲካን ጉንተላ ቢሆንም፣ ባይሆንም፤ እሳቤው ግን አንዲት እርምጃ እንደማያራምድ ምስክሮች እንሆናለን። አክቲቪስት የሚል ማዕረግ ተሸክመው የአካኢስት ገጸ ባህርይ መጫወት ለጥቂት ግዜ ሊሰራ ይችላል። አዲስ አበቤን በመቅበር የተጭበረበረ ሂሳብ ለማወራረድ መቃጣት ግን ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል። ሸገር ተቀምጦ ከአዲስ አበቤ ጋር ለመሳፈጥ መሞከር በራስ ላይ ቃታ እንደመሳብ ነው።
“ግብግብ እና ፍጥጫን በድል መወጣትን እናቅበታለን።” ይለናል ጃ-War። በትዕቢት የሚደነፋብን ዛቻ በዚህ ብቻ አላበቃም። ለዚህም “ወያኔ ምስክራችን ነው” ሲል እማኝ አቅርቦልናል። የሰሞኑ ማስፈራርያ መቋጫ መሆኑ ነው። ይህንን ሰው ፍጹም ቅጣት ክልል ውስጥ ማኖ ያስነካው ትርክት እዚህ ላይ ይጀምራል። ሕዝብን ከአንድ አንባገነን ቡድን ጋር የማነጻጸር እሳቤ። ይህ እጅግ አደገኛ ነው። ከሺዎች ማይልስ ሆኖ እየመራ ህወሃትን አሸንፍያለሁ የሚለውን ጀብደኝነት ለግዜው ወደ ጎን እንተወው። ወያኔን የቀበረው ክንዱን በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ እዘረጋለሁ ሲል ግን መቀበርያውን ራሱ ከሚቆፍረው ጅሉ ሞሮ ጋር ልንለየው ይቸግረናል።
በምርጫ እኛን ማሸነፍ ዋጋ ያስከፍላል ነው ያለው ጃዋር። እነደልማዱ “ይህንንም ለስትራቴጂ ነው ያልኩት” ብሎ ካልተመለሰ በስተቀር አስረግጦ ነግሮናል። “ዐብይ አህመድ ወራዳ ሰው ነው። ይውረድ” ያልኩት ለስትራቴጂ ነው ብሎ እንደዋዛ መታለፉን አንዘነጋም። አድማጭን መናቅና ዝቅ አድርጎ መመልከት ካልሆነ በስተቀር ይህ ስንኩል ምክንያት እንኳ ውሃ አይቋጥርም። አልበርት አይንስቴይን ሲናገር “ሁለት ነገሮች ማብቂያ የላቸውም። ጽንፈ-አለም እና ድድብና። ግን በጽንፈ-አለም ላይ እርግጠኛ አይደለሁም።” ይላል።
በኦሮሞ ህዝብ ስም ከሚነግዱት ውስጥ በፖለቲካ ንግዱ የተሳካለት ሰው ነው። ግና የኦሮሞን ትልቅ ሕዝብ በዚህ ሰው ቁመና መወሰን ወንጀል ይሆናል። ይህ ሰው በሰዎች ሰቆቃ እንጀራቸውን የሚጋግር መሆኑን መርሳት የለብንም። እዚህም እዚያም በሚለኮስ እሳት ላይ ነዳጅ ቢሞጅር አይድነቀን። ምክንያቱም ግርግሩ እና የጨበሬ ተስካሩ እልም ብሎ ሲጠፋ ለፖለቲካ ንግድ ምቹ ሁኔታ አይኖርም።
ጃዋር ዝቷል። የህዝብን ምርጫ አንቀበልም ሲል ዝቷል። “ባላንጣህ መሳት ሲጀምር መሃል ገብተህ አታቋርጠው” ይላሉ ፈረንሳዮች። ሰፊውን ሜዳ ለዛቻ እና መዘበቻ መልቀቅ ሳይበጅ እንደማይቀር መምከራቸው ነው። ካላቆምከው እንዳልተገራ በቅሎ በራሱ ግዜ ተሰባብሮ መውደቁ አይቀርም።
ሃሳብ ያለው ሃሳቡን አደባባይ አውጥቶ ይሞግታል። ይሸነፋል ወይንም ያሸንፋል። አንዱ የሌላውን ሃሳብ ቢቃወመውም ያከብርለታል። ጥግ ይዞ በራሱ ምኞት የሚዝት ሰው ግን የሚሸጠው ሃሳብ የሌለው ድኩማን ብቻ ነው። ማጠፍያውን ለማርዘም ደግሞ የዘር ካርድ መምዘዝ ቀላሉ መንገድ ይሆንለታል።
“ልዩ ጥቅም” የሚሉት አባዜ ህወሃት ከፋፍሎ ለመግዛት የተጠቀመችበት ዜጋን ማሰርያ ገመድ ነበር። “ጨቋኝ እና ተጨቋኝ” ከሚሉት ከስታሊን ግራ ዘመም ልቦለዳዊ ትርክት የተቀዳ ማታለያ። በአንድ ጥላ ስር ሆኖ፣ እርስ በርስ ተዋልዶ እና ተከባብሮ የሚኖር ሕዝብ መሃል አንደኛው ልዩ ተጠቃሚ ሌላው ተመልካች የሚሆንበት እሳቤ ሊኖር አይችልም። ካለም ከአፓርታይድ ርዕዮተ-ዓለም ተለይቶ አይታይም። አዲስ አበባ አንድን ብሄር ብቻ ነጥሎ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚደነግግ ማስረጃ የለም። ሊኖርም አይችልም። ይህንን እሳቤ በታሪክ፣በህግም ሆነ በስነ-ምድራዊ አቀማመጥ የሚያዋዛ ካለ ያውጣውና ይከራከር።
ልዩ ጥቅም የሚል መዛበቻ እንጂ ሊጨበጥ የሚችል አመክንዮ አደባባይ ወጥቶ ሊያቀርብ የሚደፍር እስካሁን አላየንም። የሃሳብ ፍጥጫን መጋፈጥ አንድ ነገር ነው። በራስ ዛብያ እየተሽከረከሩ እናሳያችኋለን የማለትን ዛቻ ሌላ። በአሸናፊነት መንፈስ የተቃኘ የፖለቲካ አውድ ተሸናፊነትን ስላለማምጣቱ ዋስትናው ምን እንደሆነ ቢነግረን?
የመረጃ ዘመን ላይ ነን። የሰጡትን ሁሉ የሚቀበል፣ ያጎረሱትን ሁሉ ሳያለምጥ የሚውጥ እንዳለ ሁሉ ነገሮችን ሰነጣጥቆ ክፉውን ከደግ የሚለይ ትውልድ መፈጠሩን አንዘንጋ።
ጃዋር “ኢትዮጵያ ከኦሮምያ ትውጣልን” እያለ የመጣ ሰው እንደሆነ አንዘነጋም። ሕዝብን በጥቅል “የሚኒሊክ ወራሪዎች” ብሎ ከመፈረጅ አልፎ አናፍጦ የማንበርከክ ፉከራ አስከትሏል። ስልብ በጌታው ብልት ይፎክራል እንዲሉ ለመብት ሲታገል የነበረን ሃይል የግሉ ፈረስ አድርጎ መውሰዱ ደግሞ የንቀቱ ጫፍ የት እንደደረሰ ያሳየናል።
ድርጊቱ ወጣቱን ዝቅ አድርጎ ማየት ነው የሚመስለው። ይህ ትውልድ ግን ከሱ በእጥፍ የተሻለ አመለካካት ያለው ነው። ቄሮ ከሌላው ወገኑ ጋር ለመብት ተግሎ ሃገር ነጻ ያወጣ ሃይል እንጂ እንደ ከብት የሚነዳ እቃ አይደለም።
ሚሊዮኖች የያዘች ከተማ ላይ በትእቢት መዛት የኦሮሞን ሕዝብ ከሰማንያ ብሄር ጋር ለመጋጨት የሚሰናዳ ድግስ ይመስላል። እርግጥ በራስ ወዳዶች ቅዠት ምክንያት አንድ ሕዝብ በጥላቻ አይን ውስጥ አይገባም። ቄሮም ቢሆን ጃዋር ከውጭ ሆኖ በሪሞት ኮንትሮል የሚነዳው እና የሚመልሰው ግኡዝ አይደለም። ጠላት እና ወዳጁን ለይቶ ያውቃል።
ሰዎቹ አገራዊውን ጉዳይ በብሄር መነጽር ብቻ የሚመለከቱ አንድ የሚፈልጉት ነገር ስላለ ነው። የዚህ ቅኝት አቀንቃኞች ከሁሉም በላይ በለውጡ ደስተኛ መሆን ነበረባቸው። ምክንያቱም በለውጥ ሳብያ ከሁሉም በላይ ነጻ የወጡት እነሱ ስለሆኑ።
እንደ አክሱም ሃውልት አራት ቦታ ተከፍለው በቦሌ ከገቡ በኋላ “ፊንፊኔ ኬኛ” የሚሉት አጀንዳ ወደ አንድ መስመር አመጣቸው። ነገር አለሙን ትተውት አዲስ አበባ ላይ ፊጥ ማለት አማራቸው።
አለማየሁ እሼቴ “ኧረ እንዲያው ይመኙሻል” ሲል ስለ አዲስ አባባ ያቀነቀነው ዜማ ትንቢት ይመስላል። “በምኞት ቢጓዙ ወዴት ያገኙሻል”።
አዲስ አበባ የኛ ናት ብሎ የሚያምን ካለ አደባባይ ወጥቶ በውይይት ያሳምን። ከዛቻና ከልጅነት የብሽሽቅ ጨዋታ ወጥቶ በሃሳብ መከራከር ነው የሚያዋጣው። ምርጫም በለው ቅርጫ የአዲስ አበባ እድል የሚወሰነው በነዋሪው ሕዝብ ነው።