ኢትዮጵያ ሽግግር ላይ በመሆኗ ዜጎቿ ተስፋን ሰንቀዋል:: ምንም እንኳን ስጋቶች በግራም በቀኝም የተደቀኑ ቢሆንም ነገር ግን የህዝቡ ተስፋ ሃያል ነው። በተጨባጭ እየተወሰዱ ያሉ የለውጥ ርምጃዎች ብዙዎችን አነቃቅተዋል። ታዲያ የከረምንበት ፖለቲካ ውጤትና ራቅ ካለ ዘመን ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ ችግር አለና ይህን የማሰናከያ ድንጋይ ገለል ኣድርጎ ዴሞክራቲክ ኔሽን ለመሆን ስርዓታዊ ለውጦችን ይጠይቃል። ወደ ዴሞክራሲ ለምናደርገው ሽግግር በርግጥ የስርዓቶች ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ኣለብን። ትርክቶቻችንን ከውጭ ወደ ውስጥ፣ ከውስጥ ወደ ውጪ እያገላበጥን አይተን የሚጠቅመንን ይዘን የማይጠቅመንን እያራገፍን በፍጥነት ወደ ዴሞክራሲ ማምለጥ ኣለብን።