የዩኒታ አማፂ ቡድን መሪ የነበሩት ጆናስ ሳቪምቢ የአንጐላ መንግሥት ጦር በወሰደባቸው እርምጃ ከተገደሉ በኋላ ለአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ማብቃት ምክንያት የሆነውን ክስተት ዓለም የሰማው የዛሬ 17 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡
አንጐላ ከ42 ዓመታት በፊት በከፍተኛ ተጋድሎና ትንቅንቅ ከፖርቱጋል ነፃነቷን ብትቀዳጅም ለረጅም ጊዜ የነፃነቷን ትሩፋት ሳታጣጥም ቆይታለች፡፡
ለአንጐላ ነፃነት ድርሻ የነበራቸው ኤም.ፒ.ኤል.ኤ ና ዩኒታ የተሠኙት የጦርና የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ እርስ በርስ ቁርቋሶ የገቡት ከነፃነቱ ጊዜ አስቀድሞ ነበር፡፡
ከነፃነት በኋላ ኤም.ፒ.ኤል.ኤ በአንጐላ ፈላጭ ቆራጭ ዩኒታ ደግሞ አማፂ ቡድን ሆኖ ለ30 ዓመታት ገደማ ሲተጋተጉ ኖረዋል፡፡
የዩኒታ አማፂ ቡድን መሪ የነበሩት ጆናስ ሳቪምቢ የአንጐላ መንግሥት ጦር በወሰደባቸው እርምጃ ከተገደሉ በኋላ ለአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ማብቃት ምክንያት የሆነውን ክስተት ዓለም የሰማው የዛሬ 17 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡
ሳቪምቢ በወጣትነት ዕድሜቸው ወደ ቻይና አቀኑ፡፡ በዚያ የቻይናን ቀይ ጦር የሽምቅ ውጊያ ስልቶች ቀስሙ፡፡
አንቱ የተሰኙ የጦር መላ አዋቂ ሆኑ፡፡ የቻይኖቹን የኮሚኒስታዊ ፍልስፍና ዝንባሌ እርግፍ አድርገው ትተው የውጊያ ስልታቸውን ብቻ ቀሰሙ፡፡
ሳቪምቢ የሶቪየቶች ተቀጥላ ነበር የሚባለውን የኤም. ፒ. አል. ኤን መንግስት ለመውጋት ሁነኛው ሰው ሆነው ስላገኟቸው ምዕራባዊያን አይዞዎት ከጐንዎ ነን እንደግፎታለን አሏቸው፡፡
እጃቸው ከገቡ ግዛቶች የሚያፍሱትን አልማዝ በኮንትሮባንድ እየቸበቸቡ የሽምቅ ውጊያ ቡድናቸውን ዩኒታን እስከ አፍንጫው አስታጠቁት፡፡
በአንጐላ መንግስት ወታደሮች ላይ ለቁጥር የበረከቱ ድሎችን ጨበጡ፡፡
በአንድ ወቅት ርዕሠ ከተማዋን ሉዋንዳን እስከመክበብ ደረሱ፡፡
ጦርነቱ አሸናፊና ተሸናፊ ቢጠፋው ተፋላሚ ወገኖቹ ተኩስ አቁመን ወደ ምርጫ እንግባ ተባባሉ፡፡
የተባባሩት መንግስታት በቅርበት በተከታተለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመጀመሪያው ዙር ሳቪምቢ በተፎካካሪያቸው በፕሬዝዳንት ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ ተቀደሙ፡፡
ሳቪምቢ እንዳህ ሲሆን የምን ምርጫ ነው ብለው ወደ ውጊያቸው ተመለሱ፡፡
የድል ወር ተረኛው የአንጐላ መንግስት ሆነ፡፡
ሳቪምቢ በትውልድ ቦታቸው በተካሄደ ውጊያ የመንግስት ጦር ባደረሰው ጥቃት በቀዳሚው ቀን መገደላቸውን ዓለም የሰማው የዛሬ 17 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡
ብዙዎቹ አንጐላውያን ሳቪምቢ ተገደሉ መባሉን አምነው ለመቀበል ተቸገሩ፡፡
ሥነ ምግባራዊ ባይሆንም የአንጐላ መንግስት በጥይት ወንፊት የሆነውን የሳቪምቢን አስከሬን በቴሌቪዥን እዩልኝ አለ፡፡
አሜሪካ ጦረኛው ሳቪምቢ መሞታቸውን አረጋግጫለሁ አለች፡፡ የአንጐላ የእርስ በርስ ጦርነት ከሳቪምቢ ጋር ተሸኘ፡፡
የቀድሞው የሽምቅ ውጊያ ድርጅት ዩኒታ ጥይት ማስጮሁን ትቶ ራሱን ወደ ፖለቲካ ማህበርነት ቀይሮ ከገዢው ኤም.ፒ.ኤል. ጋር ሰላማዊ ፖለቲካዊ ሙግት እያደረገ ነው፡፡
500 ሺህ ዜጐችን የጨረሰውና ብዙዎችን ለአካል ጉዳትና ከቤት ንብረት ለመፈናቀል የዳረገው የአንጐላ የእርስ በርስ ጦርነት አሁን ያለፈ ታሪክ ሆኗል፡፡