ህግና ሥርዓትን ማስከበር ሲባል? | ሞሐመድ አሊ መሐመድ

ህግና ሥርዓትን ማስከበር ሲባል? | ሞሐመድ አሊ መሐመድ

ህግና ሥርዓት አይከበር ያለ የለም። የመንግሥት መሠረታዊ ተልዕኮና ተቀዳሚ ተግባሩ ህግና ሥርዓት ማስከበር ስለመሆኑ ደጋግመን ጽፈናል። ከዚህ አንፃር የዶ/ር አብይ መንግሥት ብዙ ክፍተቶች እንዳሉበት አይካድም። በአንድ ቀን ውስጥ አሥራ ሰባት ባንኮች በጠራራ ፀሐይ ተዘርፈው እስካሁን ድረስ ዘራፊዎቹ ስለመያዛቸውም ሆነ የተዘረፈው ገንዘብ ስለመመለሱ የሰማነው ነገር የለም። በዜጎች ላይ አረመኔያዊ ግፍ የፈፀሙና የአገርን አንጡራ ሀብት የዘረፉ ወንጀለኞችን ይዞ ለህግ ማቅረብ አልተቻለም። እዚሁ መሐል አዲስ አበባ ተቀምጠው ህዝብን ከህዝብ ሊያጋጭ የሚችል (የጦርነት) ቅስቀሳ የሚያደርጉ አጉራ ዘለሎች ነኪ የላቸውም።

በዚህ ሁኔታ በለገጣፎና አካባቢው የድሆቾን ቤት በማፍረስ “ህግና ሥርዓት እያስከበርን ነው” ማለት ማንንም አያሳምንም። ይህ ማለት ግን በህገ- ወጥ መንገድ ቤት መሥራት (በሥራ ላይ ካለው ህግ አንፃር) ትክክልና የሚበረታታ ነው ማለት አይደለም። ህግ መከበር አለበት። ህጉን ለማስከበር ግን የግድ ቤት ማፍረስ አያስፈልግም። ከዚያ ይልቅ በህገ ወጥ መንገድ ቤት በገነቡት ላይ ተገቢውን ቅጣት ጥሎ ወደህጋዊ ሥርዓቱ እንዲገቡ ማድረግ ይቻል ነበር። በህገ-ወጥ መንገድ (በመንግሥት ይዞታ ላይ) የተገነቡ ናቸው በሚል ቤቶቹን አፍርሶ ዜጎችን ሜዳ ላይ መበተን ግን ራሱን የቻለ የህግ (የሰብኣዊ መብት) ጥሰት ነው።

ሲጀመር ዜጎች ምግብና መጠለያ የማግኘት መብት አላቸው። መንግሥትም ይህን የማቅረብ; ቢያንስ ሁኔታዎችን የማመቻቼት ኃላፊነትና ግዴታ አለበት። ይኸ ደግሞ ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸውና የህገ-መንግሥቱ አካል በተደረጉ አለማቀፋዊ የሰብኣዊ መብት ድንጋጌዎች በግልፅ የተቀመጠ ነው። ይህ ባለበት ሁኔታ መጠጊያና ለአንገታቸው ማስገቢያ ያጡ ዜጎች ገንዘባቸውን አውጥተው ቦታ ከገበሬዎች በመግዛት ጎጆ ቀልሰዋል። በዚህ መልኩም ለብዙ ዓመታት ኖረዋል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ በድንገት ተነስቶ በሰባት ቀን ውስጥ ቤታችሁን አፍርሱ ማለት ምን ማለት ነው? ይህንንስ ተከትሎ የድሆችን ቤት በቡልዶዘር ማፍረስና ህፃናትንና አቅመ ደካሞችን ሜዳ ላይ መበተን ምን ዓይነት ጭካኔ ነው? ይህን በማድረግ “ህግና ሥርዓትን እያስከበርን ነው” ሊባል ነው? ህግና ሥርዓትን እናስከብር ከተባለ የትኛው ነው የሚቀድመው? አሁን በዚህ አገር ከህግ በላይ ሆነው የሚኖሩ የሉም? በዜጎች ላይ ግፍ የፈፀሙ; ተደራጅተውና ተመሳጥረው አገር የዘረፉ; ያለአግባብ የበለፀጉ; እንዲሁም እዚያም እዚህም በህዝብ መሐል ግጭት ለመቀስቀስ በማንአለብኝ ባይነት የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ አጉል እብሪተኞች የሉም? ወይስ ነገሩ “የምታሸንፈውን ምታ ቢሉት ወደሚስቱ ሮጠ” እንዲሉ መሆኑ ነው? ይኸማ ከህግ የበላይነትና ከዜጎች እኩልነት መርህ ጋር አብሮ አይሄድም።

ህግና ሥርዓትን በማስከበር ዙሪያ ጥያቄ የለም። ጥያቄው ህግና ሥርዓትን ለማስከበር በሚል የሚወሰደው እርምጃ የዜጎችን ሰብኣዊ መብቶች ያገናዘበ መሆን አለበት ነው። ህግና ሥርዓት ይከበር ከተባለ ሌሎች አንገብጋቢና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ ጉዳዮች አሉ እያልን ነው።

ካልሆነ ግን አካሄዱ ትልቅ የጥያቄ ምልክት የሚፈጥር ይሆናል!!!

LEAVE A REPLY