ኢህአዴግ እና የሰብዓዊ መብት ነገር | በመስከረም አበራ

ኢህአዴግ እና የሰብዓዊ መብት ነገር | በመስከረም አበራ

አሮጌው ህወሃት መራሽ ኢህአዴግ ከአዕላፍ ነቀፌታዎቹ አንዱ በሰብዓዊ መብት ላይ ያለው እንደ ዱር አውሬ የሚቃጣው አቋሙ ነበር፡፡ኢህአዴግ በራሱ ህዝብ ላይ ያደረሰው አረመኔያዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዓለም ላይ በእርኩስነታቸው ከሚታወቁ መንግስታት መደዳ ቀዳሚው ሳያደርገው አይቀርም፡፡ ቀዳሚ የሚሆንበት አበይት ምክንያት በዓለም ታሪክ ብቅ ብለው የነበሩ እንደ ናዚ ያሉ ጨካኝ መንግስታት የጭካኔ በትራቸው ያረፈው በራሳቸው ህዝብ ላይ ሳይሆን “ሌላ” በሚሉት ህዝብ ላይ ስለነበረ ነው፡፡ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ግን ለመናገር እንኳን  በሚያሳቅቅ የመከራ ድስት ውስጥ ከድኖ ሲቀቅል የኖረው የራሱን ህዝብ ነበር፡፡

“በአምባገነኑ ደርግ በመጨቆኑ አዝኜ ጫካ ገብቼ፣ተራራ ቧጥጨ ታገልኩለት” የሚለውን ህዝብ መፈጠርን በሚያስረግም ግርፋት፣ቁም-ስቅል፣እስራት፣ስደት እና መከራ ያሳለፈ ነፃ አውጭ ነኝ ባይ ህወሃት/ኢህዴግ ብቻ ነው፡፡በኢህዴግ እስር ቤቶች የአጋንንት ሰራዊት እንኳን ተመካክረው ሊፈጥሩት የማይችሉት የጭካኔ ትዕይንት በክቡሩ የሰው ልጅ ላይ ተፈፅሟል፡፡የሰው ልጅ ጀርባ በኤሌክትሪክ ገመድ ተተልትሏል፣ሰው ከነነፍሱ እባብ ባለበት በጉርጓድ ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጓል፣ሴት ወንዱ ተገዶ ተደፍሯል፡፡ ባጠቃላይ በነፃ አውጭ ነኝ ባዩ አሮጌው ኢህአዴግ ዘመን ስልጣን፣ድንቁርና እና ብልግና ሲቆራኙ የሚፈጠረው ጥፋት ሁሉ ደርሷል፡፡የሰው ልጅ ክቡርነት ተረስቶ፣ ሰው ምናምንቴ፣ ስልጣን ደግሞ ክቡር ሆኖ ኖሯል፡፡

ከእስር ቤት ውጭ ያለው ዜጋም ቢሆን በመፍራት በመንቀጥቀጥ የኖረ፣ካድሬ ደስ ባለው ቀን ያሰረበትን ዘመዱን መጠየቅ እንደ ሰማይ ርቆት፣ጭቆናው ገላጋይ የሌለው መርገም መስሎት፣እስር ቤት ባይገባም ቤቱን እስርቤት አድርጎ በስነልቦና መረበሽ የሚማቅቅ  ነበር፡፡ኢህአዴግ ያሰረውን አስሮ ያላሰረውን የታሳሪ ቤተሰብ ስልጣኑ በፈቀደለት መጠን ሁሉ የሚያንገላታ፣መንግስትነትን የማይመጥን እኩይ ማንነት ባለቤት ነበር፡፡አረመኔው ኢህአዴግ በጭቃ ጅራፉ ገርፎ፣ስሙን አክፍቶ ላሰረው ዜጋ ስንቅ እንዲያቀብል የሚፈቅደው ከቤተሰቡ በእድሜው የገፋውን ሰው መርጦ ነበር፡፡

ይሄኔ በልጆቻቸው መጦር የሚገባቸው፣ለራሳቸው ያለ ድጋፍ መንቀሳቀስ የማይችሉ አቅመ ደካማ አዛውንት የታሳሪ ወላጆች ስንቅ ተሸክመው ከከተማ ዳር ባሉ እስርቤቶች ይንከራተታሉ፡፡እነዚህ አዛውንቶች  በዚህ መንከራተታቸው ጊዜ ሁሉ ከእብሪተኞቹ ነገስታት አልፈው እነዚህን እርኩሶች በላይዋ ላይ የሾመችውን ሃገር ጭምር የሚረግሙ ይመስለኛል!በህይወቴ የኢህአዴግ እርኩሰት ጎልቶ እንዲታየኝ ካደረጉኝ ምክንያቶች አንዱ ይህ አዛውንቶችን በማንከራተቱ ራሱን ጎበዝ አድርጎ የማየቱ ነገር ነው፡፡በዚህ የተነሳ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ተስማምቶ አመታትን  ያስቆጠረ ሰው ሁሉ እስከዛሬ ይቀፈኛል፡፡የኢህአዴግ ካድሬነት ከመሰረታዊ የሰውነት ባህሪ ጋር የሚጋጭ የሚመስለኝም ለዚህ ነው፡፡

መሰረታዊ የሰብዓዊነትን መርህን ችላ ብሎ ለስልጣን መደራደር ኢህአዴግን ኢህአዴግ ያደረግው ዋና ማንነቱ ነው፡፡ተለወጥኩም ተለነቀጥኩም ቢል ኢህአዴግ ከዚህ ማንነቱ ፈቅ ነቅነቅ አይልም፡፡ተለወጥኩ ያለው የዶ/ር አብይ ኢህአዴግ በሰብዓዊመብት ላይ አለቅጥ ሲያሾፍ የኖረውን  ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄርን አምባሳደር አድርጎ ሾሞ ሸልሞ አሳይቷል፡፡አዲሱ ገ/እግዚብሄር ለሰብዓዊ መብት የቆመ ተቋምን እመራለሁ ብለው ወንበር ላይ ተቀምጠው በዛው መስሪያቤት ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ሽፋን ሲሰጡ የነበሩ ተራ ዋሾ ሰው ነበሩ፡፡ሰባ ሰባት ሽህ አማሮችን ስንት አመት ከኖሩበት ጉራፈርዳ ወረዳ በአንድ ሌሊት ነቅሎ ከህፃን እሰከ አዋቂ ዜጎችን ለመከራ የዳረገውን፣በዚሁ ዝናው ባዕዳን እንኳን አምባሳደርነቱን አንቀበልም ያሉትን  ሽፈራው ሽጉጤን ሃገር እየቀያየረ የሚሾመው አወዳሹ የበዛው የዶ/ር አብይ መንግስት ስለ ሰብዓዊነት ግድ ይለዋል ብሎ ምክንያታዊ ሰሚን ሊያሳምን የሚችል ሰው የለም፡፡በሱማሌ ክልል ከአብዲ ኢሌ ጋር ያደረጉት እኩይ ስራ አልበቃ ብሏቸው አቶ ሙስጠፋን አላሰራ ያሉት አቶ አህመድ ሽዴ በተለይ በኋለኛው ሙከራቸው የተነሳ በፊት ላደረጉት በሱማሌ ክልል ለደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁሉ ተጠየቂ ሊሆኑ ሲገባ አሁንም በንጉስ እልፍኝ ይሽሞነሞናሉ፡፡ወርቅነህ ገበየሁ የተባለውን የ1997 ባለዝና ገዳይ አስገዳይ እንደ ደህና ጌጥ በየምዕራቡ ሃገር ይዞ የሚዞሩት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርላማ ተገኝተው “እኛ ጥፍር ነቃዮች ህገ-ወጦች ነን” ያሉት ከአንጀት ነው ካንገት አጠያያቂ ነው፡፡

መቼም ለዶ/ር አብይ መንግስት ጠበቃው ብዙ ነውና እነዚህን በሰብዓዊ መብት ላይ ጉልህ ወንጀል የሰሩ ሰዎች መሾሙ ሃገር ለማረጋጋት ብሎ ነው፣ሁሉም በአንዴ አይሆንም፣አንዳንዱን ጥፋት መተው ነው የሚል አይጠፋም፡፡ በበኩሌ በሰው ልጅ ክቡርነት አጥብቄ የማምን ነኝና ገንዘብ ከዘረፈው ይልቅ የሰው ልጅን ሰብዓዊ መብት የረገጠው ሰው ይበልጥ ወንጀለኛ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ስለዚህ አንድ ቀን እንኳን ከተጠያቂነት ነፃ ሆኖ ሲንጎራደድ ማየት አልሻም፡፡ሲቀጥል በኢህአዴግ እልፍኝ የሰብዓዊ መብት ነገር እጣ ፋንታ የሌለው ጉዳይ ስለሆነ መጠየቁ ቀርቶባቸው እነዚህ ሰዎች ከነክፉ ወንጀላቸው እንደማንኛወም ሰው እየወጡ እየገቡ መኖሩ አንሷቸው ስለ መሾማቸው ሿሚው አብይ ራሳቸው ከተራ ካድሬያዊ ሽኩቻ ባለፈ ሰው ፊት የሚያቀርቡት ምክንያት ያላቸው አይመስለኝም፡፡

ምናልባት ሃገራችን ካለችበት ክፉ የዘረኝነት ፖለቲካዊ አየር የተነሳ እነዚህን ሰዎች ተጠያቂ ማድረጉ የመጡበትን ዘር የሚያስቆጣ ሆኖ የሚያመጣው ችግር እንዳይኖር ተፈርቶ ነው የተሾሙት የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ይህ በነዚህ ሰዎች ሁኔታ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ህወሃት ከሌላው ፓርቲ በተለየ ሁኔታ  ወከልኩት በሚለው ህዝብ ዘንድ ጥብቅና የሚቆምለት ስለሆነ በአቶ አዲሱ ገ/እግዚአብሄር ተጠያቂነት ምክንያት የሚነሳ ዘረኝነት ወለድ ጉም ጉም ባይጠፋም ሌሎቹ ሰዎች በስልጣን ዘመናቸው ባደረጉበት ማስመረር ምክንያት የወጡበት ህዝብ ራሱ ለፍርድ የሚፈልጋቸው ናቸው፡፡የጄል ኡጋዴን መከራ ናፍቆት ለአህመድ ሽዴ ጥብቅና የሚቆም ሱማሌ አይገኝም፡፡ሽፈራው ሽጉጤም ቢሆን በወጣበት ህዝብ ዘንድ ወድቀህ ተነሳ ያማይባል ስመ-ክፉ ሰው ነው፡፡የመለስ ዜናዊ የግድያ አጋፋሪው ወርቅነህ ገበየሁም ቢሆን ወዳጅነቱ ለዶ/ር አብይ ይሆናል እንጅ ለማንም ጎጥ ሰው አይደለም!

የሰብዓዊ መብትን ጉዳይ በተመለከተ ዶ/ር አብይም እንደማንኛውም ኢህአዴግ ቅም የማይላቸው ሰው እንደሆኑ ማሳያው ከላይ የተጠቀሰው ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ይልቅስ የ1997 ዓም ምርጫን ተከትሎ  በተደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ በዳኛ ፍሬ ህይወት ሳሙኤል ሰብሳቢነት በተቋቋመ ገለልተኛ ኮሚሽን የተደረገውን ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ሪፖርት ተቀብለው በሃሰተኛው ቦታ እንዲተኩ በተደጋጋሚ ከኮሚሽኑ አባላት የሚቀርብላቸውን ጉትጎታ ችላ ማለታቸው ነው፡፡እነዚህ የኮሚሽኑ አባላት አሁን የለውጥ ሃይል ነኝ የሚለው የነዶ/ር አብይ ቡድን አንገቱን ደፍቶ፣ከግፈኛው መለስ ዜናዊ ጋር አብሮ፣ ግፍን ሁሉ አሜን አሜን በሚልበት በዛ አስፈሪ ዘመን አንገታቸው ላይ የተሳለ ቢለዋ ሊያርፍ እንደሚችል እያወቁ ከእውነት ጋር ብቻ ያበሩ፣በሞራል ልዕልና የለውጥ ሃይል የተባለውን ጭምር የሚያስከነዱ ሰዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ያለጊዜው ጭምር የፀኑ ሰዎች የኢህአዴግ ካድሬ ሁሉ ምስል ቀርፆ ሊያመልከው የደረሰው መለስ ዜናዊ በመንበሩ ቁጭ ብሎ እያለ ነው ነፍሳቸውን ሸጠው የህዝብን አደራ ብቻ አንግበው ከሞት ጋር የሚፋጠጡበትን አስፈሪ መንገድ የተጓዙት፡፡በዚህ ጉዟቸው ውስጥ የተረጋጋው ኑሯቸው ተናግቷል፣ለዱብዳ ስደት በመዳረጋቸው ቤተሰባቸው ተበትኗል፣ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል፡፡ለህዝብ ሲሉ ይህን ሁሉ ስላደረጉ ሊመሰገኑ ሲገባ ሊሞቱለት የቆረጡትን፣ብዙ የለፉበትን ነገር ተራ ጥቆማ አድርጎ  ማቃለል ራስን ማስገመት ነው፡፡በርግጥ በሃሰት ፖለቲካ፣ በጌታ ፈቃድ እያደረ የኖረ የኢህአዴግ ባለስልጣን ለእውነት ሲባል የሚከፈልን መሰዕዋትነት ለመረዳት እና ተገቢውን ክብር ለመስጠት ሊቸግረው ይችላል፡፡ይህን መሰረታዊ ኢህአዴጋዊ ባህሪ እንደተሸከሙ የለውጥ መሪ ነኝ ማለቱ ግን የሚገጥም ነገር አይደለም፡፡

የኮሚሽኑ አባላት መለስ ዜናዊ ያቀረበላቸውን፣የኢህአዴግ ካድሬ የእለት ተዕለት ኑሮው አካል የሆነውን የሃሰት ግብዣ እምቢ ብለው ከሃገር የወጡበት መንገድ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ነገሩ የሰዎቹን የእውነት ሰውነት የሚያሳይ፣ሌላ ሃገር ቢሆን ትልቅ ሽልማት የሚያሰጣቸ፣ለትውልድ ትምህርት የሚሆን ስራ ነው፡፡የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዳኛ ፍሬ ህይወት በተበደለው ህዝባቸው ላይ ሌላ ሃሰት ጨምሮ በህዝብ ቁስል እንጨት ላለመስደድ ሲሉ በቦሌ በኩል የወጡበትን መንገድ ለኢሳት ቀርበው ሲያስረዱ በበኩሌ ነገሩ ማለፉን ሁሉ ረስቼ በትልቅ ጭንቀት ተወጥሬ ነበር ያዳመጥኳቸው፡፡በዛች ቅፅበት ያቀዱት አንዱ ነገር ውልፊት ብሎ በመንግስት ውስጥ እጅ ቢወድቁ ሊደርስባቸው የሚችልውን ነገር ማሰቡ የሰውየውን የፍትህ ሰውነት ለመረዳት ያግዛል፡፡ምድረ ካድሬ እንደ አምላኩ የሚያረግድለትን፣ በቀለኛውን መለስ ዜናዊን እምቢ የማለታቸው ድፍረት ሳያንስ ኮሚሽኑ በማጣራቱ ወቅት በጥንቃቄ ያደራጃቸውን መረጃዎች ሁሉ ሰብስበው ይዘው ለመውጣት በሚገርም ድፍረት ማሰባቸው እና ማሳካታቸው ሁሌ የሚገርመኝ ነገር ነው፡፡ከዚህ የምንረዳው ለዳኛ ፍሬህይወት ፍትህ በደማቸው ውስጥ የሚዞር ነገር እንጅ  ለእንጀራ ሲሉ ብቻ የያዙት ጉዳይ እንዳልሆነ ነው፡፡እስከ ዛሬ ለፍትህ የሚሞግቱት ሌሎቹ የኮሚሽኑ አባላት እነ አቶ ምትኩ ተሾመ፣ዳኛ ወ/ሚካኤል መሸሻ፣አባ ቲዎፍሊዎስ ሁሉ የህዝብን አደራ ከመብላት ራሳቸውን ለመስዕዋት ያቀረቡ ድንቅ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡

በጣም የሚያሳዝነው እና የሚገርመው ተለውጫለሁ የሚለው  መንግስት እነዚህን ሰዎች በክብር ጠርቶ ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ ማድረግ ሲገባው በህይወታቸው የተደራደሩበትን ሪፖርት እያቃለለ መሆኑ ነው፡፡ይህ የሚያሳየው ለዶ/ር አብይ መንግስት ከየአቅጣጫው እየወረደ ያለው የበዛ የውዳሴው ድቤ አቅሉን እንዲስት እንዳደረገው ነው፡፡ይህ ደግሞ ለማም አይበጅም! ይብስ የሚገርመው ደግሞ ለወትሮው ለፍትህ እቆማለሁ የሚለው ተቃዋሚ ሃይልም ሆነ ህወሃትን ለማብጠልጠል ምክንያት የማይፈልገው ጋዜጠኛ ሁሉ ስለዚህ ጉዳይ ትንፍሽ አለማለቱ ነው፡፡ጭራሽ ለፍትህ እሟገታለሁ ሲል የኖረው ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ  የዶ/ር አብይ መንግስት በስራው ሁሉ ትክክል ነው እንደ ማለት የሚሞክረው የፖለቲካ አዝማሪነት ውስጥ እየገባ ነው፡፡ይህ አካሄድ ስለማያዋጣ የአጣሪ ኮሚሽኑን ተገቢ ጥያቄ ዳር ለማድረስ ሰብዓዊነት ይሰማኛል ባይ ሁሉ በሃቅ ላይ ፊቱን ባዞሮው የዶ/ር አብይ መንግስት ላይ ጫና ማሳደር አለበት፡፡ይህን ስለተባለ የአብይ መንግስት አይሟሟም!

አሁን የለውጥ ሃይል የሚባለው የኢህአዴግ ቡድን በ1997 ለደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢያንስ በዝምታ ድጋፍ የሰጠ ነው፡፡በአንፃሩ ዛሬ ስለ እውነት የሚማፀኑት የኮሚሽኑ አባላት በህዝብ ላይ የደረሰውን በደል ለማጋለጥ በነፍሳቸው የተደራደሩ ሰዎች መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የህዝብን ትግል ተተግነው የለውጥ አራማጅ ነን ያሉትን የዛሬዎችን ገዥዎች ሳይቀር የሚልቅ የሞራል ልዕልና ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡በመሆኑም ዛሬ ስልጣን ላይ የወጣው ቡድን የኮሚሽኑን ሪፖርት በመቀበል  የትናንት ጥፋቱን የማረም ግዴታ አለበት፡፡ካልሆነ ስለትናንቱ መጠየቅም እንደሚኖር ማሰብ ደግ ነው፡፡የኮሚሽኑ አባላት የተመሰከረለት ለእውነት የመቆም ፅናት ደግሞ ጉዳዩን የትም ድረስ የመውሰድ ብርታት እንዳለው ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ነገሩ ተጓትቶ ባዕዳን ደጃፍ ከመድረሱ በፊት የለውጥ አመራር ነኝ ባዩ የሃገራችን መንግስት ህይወት የተገበረበትን፣ቤተሰብ የተበተነበተን ትልቅ ጉዳይ ማቃለሉን ትቶ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ባይወድም ግዴታው እንደሆነ ማወቅ አለበት፡፡

የምንግዴው ኢህአዴግ ስንጣቂ መሆኑ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ብልጭ የሚለው የለውጥ አመራር የኮሚሽኑን ሪፖርት ተቀብሎ በሃሰተኛው ቦታ ለመተካት የተቸገረው ለምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡የዚህ ዋነኛው ምክንያት ሃሰት ላይ ተመቻችቶ ተኝቶ ለእንቅልፍ ያለመቸገር ለቆ የማይለቅ ኢህአዴጋዊ የክህደት ተፈጥሮው ነው፡፡በመቀጠል የዶ/ር አብይ መንግስት በአደባባይ ከሚያወራው የለውጥ ማንነት ጋር ልዩነት ያለው ውስጣዊ ማንነት ስላለው ሳይሆን አይቀርም፡፡ይህ ደግሞ ትርጉሙ አስመሳይነት ነው፡፡በሰው ደም ላይ ተመቻችቶ ተቀምጦ የስልጣንን ማረፊያ ማመቻቸት ተቀየርን ብለውም እንኳን የኢህአዴ ካድሬዎችን የማይለቃቸው  ልዩ ተፈጥሮ ነው፡፡ይህ ክፉ አመል ነው የሰብዓዊነትን ጉዳይ ችላ የሚያስብላቸው፡፡በተቀረ ሰዎች ለፍተው ደክመው፣መለስ ዜናዊ ከሚባል ጨካኝ አምባገነን ጋር አባሮሽ እየተጫወቱ ያጣሩትን የህዝብ እውነት ማድበስበስ ያከስር ይሆናል እንጅ የፖለቲካ ትርፍ አያመጣም፡፡አሁን በዶ/ር አብይ አመራር የተያዘው እውነትን ማድበስ ሁነኛ ምክንያቱ እንደ ወርቅነህ ገበየሁ ያሉ የ1997ቱ ግድያ መሪ ተዋናዮችን (የአሁን ዘመን ደግሞ የለውጥ አመራር አጋፋሪዎች) ተጠያቂ ላለማድረግ ነው፡፡በደሉን ረስቶ፣ጥፋትን ሁሉ ይቅር ብሎ ወንበር ላይ ላስቀመጠ ህዝብ ከመቆም እና ለወንጀለኛ ባለስልጣናት ሽፋን ከመስጠት የሚያዋጣው የቱ እንደሆነ ውሎ አድሮ ይለያል!

LEAVE A REPLY