እስረኞች ሁሉ ተፈቱ። ዴሞክራሲም ተወለደ። በደስታ ሰከርን። አሁን አሁን ግን የጫጉላ ጊዜ እየጨረስን ይመስለኛል። ዶ/ር አብይ የምነቅፍብዎት አንድ ነገር አለኝ። በሕግ የጊዜ ሂደት ሳይሆን ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ሕዝብን በወከባማፈናቀል የብርሃን ስራ አይመስለኝም። ጉዳዮን ወደ ፍርድ ቤት ይምሩትና ዜጎች መንግስትን ፍርድ ቤት ቆመው የሚሞግቱበት እውነተኛ ነፃና ፍትሀዊ ሀገር እንድትሆን ፈር ቀዳጅ ይሁኑ። ከዚያ ባለፈ ሕዝቡን ሜዳ ላይ ከመበተን፥ የሚያርፉበትን ስፍራ ጭምር ማሰብ ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊ የመሆን ክብር በምድራችን እንዲነግስ አድርገው ሲያበቁ፥ በእርስዎ ብሩህ ዘመን እንዲህ ዓይነት ጭካኔ የማይታሰብ ነው። ይህ ዓይነት ሥራ ከእርስዎ ስብዕና ጋር አይሄድም። በዝምታ ሊያልፉትም አይገባም። የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ በመጠየቅና ለመፈናቀል ችግር ማስተካከያ በመስጠት ይሻገሩ ዘንድ እለምንዎታለው።
ዶ/ር አብይ አህመድ ገና በኢሕአዴግ ሳይመረጡ “ጆሮ ያለው ይስማ” በማለት የእርስዎን ወደ ስልጣን መምጣት ስመኝ ነበር። ምኞቴ ሰምሮ በጠቅላይ ሚኒስቴርነት መምራት ሲጀምሩ ከስጋት ይልቅ ተስፋ አይሎብኝ ብዙ ብዙ ብያለው። እስካሁን ድረስ እርስዎ መደመርን ሲሰብኩ፥ ዘራፍ ማለትን ወደ ጎን ትተው፥ በሀሳብ ልዕልና አሸንፎ መደመርን ለማሳለጥ ትዕግስትን ጨብጠው ነውና አከብርዎታለው።
እኛ የለመድነው “ስንኖር ጎሣዊ”፥ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን አምክነን “አፈር” ነን ማለትን ነበር። እርስዎግን ብቅ ብለው “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፥ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን” ያሉት ራዕይ ብርሃን ፈነጠቀ። በፍቅር ተደምረን በይቅርታ እንሻገር ብለው ያከናወኑት ድርጊቶች በታሪክ ቦታ አላቸው ብዬ አምናለሁ። እውነተኛ ምርጫ አካሄደው ከተሸነፉ ከስልጣን ለመውረድ ቁርጠኛ እንደሆኑ አልጠራጠርም። በእኔ ግምት የተጣለብዎትን የዲሞክራሲ አዋላጅ የመሆንሃላፊነትዎን በብቃት እንደተወጡ አምናለሁ። ግን ይህ ሁሉ ሆኖ ዛሬ ዛሬ እርስዎ ፊት የተጋረጠው እንቅፋት እጅጉን ያሰጋኝጀመር። ምክንያቱም ያስወለዱትን ዴሞክራሲ የሚገድልና ይልቁንም ወደ ብርሃን ከመሻገር ይልቅ ወደ ድቅድቅ ጨለማ እንድንዘፈቅ የሚያደርግ የዘራፍ ፈተና ውስጥ ለመግባት ዳዴ እያልን ስለሆነ ነው።
እስካሁን እንድንኖር የተደረገው በየጎራችን ተከፋፍለን “ሁሉም ለራሱ” በሚል እሳቤ ነበር። ታዲያ “ስንኖር ጎሣዬ” ከሚለው አመለካከት በቃልና በስራ ሁላችንም ተግባብተን ወደ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ” ለመሻገር፥ አሻጋሪ መንገዱን የሚጠርገውዴሞክራሲ ብቻ ፍቱን መድሃኒት እንዲሆን ታስቦ ዴሞክራሲ ተወለደ። ታዲያ ዴሞክራሲ ተወለደ እንጂ የተወለደውን ዴሞክራሲ ተጠቅመንና በቅንጅት ተደራጅተን ራዕዩንበሕዝብ ድምፅ አሸናፊነት ዕውን ለማድረግ እምብዛም ብዙ መንገድ አልሄድንም። እርስዎ ለማካሄድ የሚሮጡለት ምርጫ አዲስ የሕዝብ መንግስት ለመመስረት ብቻ ሳይሆን፥ የሚመረጠው መንግስት የሚያስተደዳድረው “ኢትዮጵያዊነትንም” በአብሮነትና በዴሞክራሲ ሂደት እንዲወለድ ለማስቻል ነው ብዬ አምናለሁ።
ዶ/ር አብይ ዘራፍ የማይሉ መሪ መሆንዎ ያስገርመኛል፥ያስደስተኛልም። አንዳንዴ ግን በዝምታ የሚሄዱት መንገድለእንቆቅልሽዎ መላ እስካልፈጠሩ ድረስ ረዥም አይሆንም ብዬእፈራለሁ። ምክንያቱም ዘራፍ ማለት የተጠናወታቸው ፖለቲከኞችና አክትቪስቶች አሉንና። ሲሆን ሲሆን በተሻለ አሳብ ለመግባባት ወደ ውይይት፥ ካልሆነ ደግሞ በሕዝብ ድምፅ ለመዳኘት ወደ ፉክክር መግባት እንድንችል አቅም የሚሰጠንንዴሞክራሲን ገና አልተዋወቅነውም። አሁንም የየግልአጀንዳዎቻችንን ሕዝብ ላይ ለመጫን ዘራፍ ማለት ይቀናናል። በምድራችን የተወለደውን ለጋ ዴሞክራሲ በመጠቀምናበማሳደግ ወደ መግባባት መሄድ የሚያስችለውን የዴሞክራሲ ጉዞ ፋታ እንዳያገኝ ደንቃራ መሰናከያ ድንጋይ እንፈጥራለን። የተወለደውን ዴሞክራሲ ገድለን ጡንቻ ማግነንን እንደ አንድ አማራጭ የያዝን ይመስላል። ምናለበት ዴሞክራሲ ይዳኘናል ብለን የምናምንበትን ሀሳብ ለሕዝብ ማስተማርና ሁሉንም ጉዳይ ለውይይት ማቅረብ ጊዜና ቦታ መስጠት ብንችልበት?
ጥያቄው አሁን እንዴት ካለንበት አጥፍቶ ከመጥፋት፥ የመጠፋፋት ጨለማ ውስጥ ወጥተን፥ በፍቅር ብርሃን ተደምረን ወደፊት መሄድ እንችላለን ነው። መልሱ ደግሞ ሲሆን ሲሆን ለተሻለ ሀሳብ ለመሸነፍ በዴሞክራሲ እሴት ወደ ውይይት መሄድ፥ ያ የሚያግባባ መፍትሄ የማያመጣ ከሆነ ደግሞ በሕዝብ ምርጫ ለመዳኘት በሁሉ መስክ ዴሞክራሲ እንዲገዛን ራሳችንን ለዴሞክራሲ መስጠትን መተግበር ነው። ይህም ዕውን እንዲሆን ደግሞ መቀናጀቱን ማጠናከር ያስፈልጋል።
በዘራፍ አዋጅ ሀገር ለመንዳት ወይም እርስ በርስ ለማዋጋትና ለመዋጋት ከማሰብ፥ በመደመር ስሌት አካሄድ፥ ሲሆን በውይይት ሳይሆን በህዝብ ዳኝነት፥ መግባባት ላይ እንደርስ ዘንድ የዴሞክራሲ እሴት እንጠቀም። ከሚያጣሉን ጉዳዮች አንዳንዶቹን ለምሳሌ ያህል ከዚህ በታች መጥቀስ ይቻላል።
1ኛ/ ሕዝብን የማፈናቀል አባዜ መቼና እንዴት ይቆማል?
2ኛ/ የክልል ድንበር ጥያቄ መቼና እንዴት ዕልባት ያገኛል?
3ኛ/ ራስን በክልል መንግስት የማስተዳደር ጥያቄ መቼና እንዴት መልስ ያገኛል?
4ኛ/ በሃላፊነት ስፍራ የተቀመጡ ሰዎች የጎሣዎች ስብጥር ፍትሀዊነት አለው ወይ?
5ኛ/ የሕግ የበላይነትን የማስፈን ተግዳሮቶች እንዴት ይፈቱ?
6ኛ/ ሕዝብ የሚመርጠው ፕሬዚዳንት ይኑረን ወይስ ፓርቲ የሚመርጠው ጠቅላይ ሚኒስቴር ይኑረን?
7ኛ/ ባንዲራችን የትኛው ይሁን?
8ኛ/ አዲስ አበባ የማን ናት?
9ኛ/ የትኛው የፌዴራሊዝም ስርአት ለሁላችንም ፍትሐዊ ነው?
10ኛ/ ብሔራዊና የስራ ቋንቋዎች የትኞቹ ይሁኑ?
11ኛ/ ለአፍሪካ አንድነት ፋና ወጊ መሆንን እንደ ታሪካዊ ብሔራዊ ጥሪ እንውሰድ ወይ?
12ኛ/ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ የሚለውን ዘይቤ እንደ ሕዝብ ዕውቅና እንስጥ ወይ?
ወዘተ
ዶ/ር አብይን የምንደግፍም ሆን የምንቃወም ሁሉ አንድ ነገር እናስብ። ኢትዮጵያ ከዶ/ር አብይ በላይ ናት። እርሳቸው መልካም አደረጉም ክፉ ያልፋሉ። ኢትዮጵያ ግን ትቀጥላለች። ስለዚህ ኢትዮጵያን አስበን፥ ዶ/ር አብይ የሕዝብን ዳኝነት በሚፈልጉበት ሂደት ውስጥ በምርጫ ዴሞክራሲ ማሳለጥ ሥራ ሁላችንም እንድንተባበራቸው ያስፈልጋል።
ከዚያ በተረፈ ኢየሱስ ክርስቶስን የመሰለ ስብዕና ያለውን በአንድ ወቅት ሕዝቡ ሊያነግሰው ሲፈልግና፥ በሌላ ጊዜ ደግሞ ያው ሕዝብ ሊሰቅለው ሲፈልግ አይተናልና አምላክ ከዚያ ይጠብቀን። ይልቁንም ኢትዮጵያን ለመታደግ፥ ሌት ተቀን ያለ እረፍት ደፋ ቀና የሚሉትን እኚህን የኢትዮጵያ ልጅ በቃላችን ከማፍረስ ይልቅ፥ ሲያጠፉ በመምከርና ሲያለሙ ደግሞ በማበረታት፥ በሁለቱም ረገድ ሰውን መገንባት ስራችን ማድረግ የቅንነት ምልክት ነው። ከሁሉ በላይ በዴሞክራሲ ሜዳ ላይ ለመፋለም ሁላችንም በየፊናችን በሚያግባቡን ሀሳቦች ዙሪያ ተቀናጅተን ኢትዮጵያን ለመታደግ እንነሳ። እኛ የነገውን ዕድል ፈንታ እንደ ሕዝብ የምወስን እኛ ራሳችን እንደሆን አውቀን የዜግነት ግዴታችንን በንቃትና በመተባበር ካልተወጣን፥ ዶ/ር አብይ በኢትዮጵያ ትንሣኤ መንገድ ላይ የተደነቀረውን ወጥመድ ጥሰው ኢትዮጵያን ማሻገር ተራራ ይሆንባቸዋል።
ከሁሉ በፊት ሰብዓዊነት ይቀድማልና፥ የተፈናቀሉት ሰዎች ጉዳይ አደራ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አሰበ።
እኛም እንወቅበት!
እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ።
ኢሜል፥ Z@myEthiopia.com