ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የደረሰውን የግፍ እርምጃ አስመልክቶ
***
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለገጣፎ ለገዳዲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የኢሕአዴግ አስተዳደር በነዋሪው ኅብረተሰብ ላይ በልማት ስም እየወሰደ ያለውን ግፍ የተሞላበት ተግባር “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” አጥብቀን እናወግዛለን። አንድ ዓመት ሊሞላቸው አንድ ወር የቀራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አመራር የኢሕአዴግን አገዛዝ ይዤ “ለውጥ አመጣለሁ” የሚሉት ሂደት እጅጉን ከጥያቄ ውስጥ እየገባ ነው። በሥልጣን ዘመናቸው በሀገሪቷ እየተካሄዱ ያሉትን በኢሕአዴግ አጠራር ክልላዊ ግጭቶች የበርካታዎችን መፈናቀል ብቻ ሳይሆን ሕይወትን እየቀጠፈ እንደሆነ እንገነዘባለን። የዘርና የቋንቋ ክልል ብሎም ህወሓት ሠራሹ ዘርን ተገን ያደረገው የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥትን አስቀጥላለሁ ያሉት ጠ/ሚር ዶር ዐቢይ አሕመድ በአገዛዛቸው ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሂደት እየታዘብን እንገኛለን።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ ወቅት ጀምሮ አዲስ አበባን “በፊንፊኔ” ስም ለኦሮሚያ እናደርጋታለን የሚለው የተደጋገመ ወሬና ዜና የአዲስ አበባን ነዋሪ ኅብረተሰብ ስነልቦና ለመቆጣጠር የሚደረግ ዘመቻ አድርገን እንወስደዋለን። በዚህም መሠረት ከቀን ወደ ቀን አዲስ አበባን ለመቆጣጠር በአዲስ አበባ ነዋሪ ላልሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች ያለአግባብ የሚደረገው የነዋሪነት መታወቂያ እደላ፤ ለቀጣዩ ኢሕአዴጋዊ የዘር ምርጫ አዲስ አበባን ለኦሮሚያ ክልል አሳልፎ በመስጠት ሀገሪቷን ለመከፋፈልና ወደ ሌላ የእርስ በርስ ግጭት እንድታመራ የሚያደርግ ቅድመ ዝግጅት መሆኑን ልናስገነዝብ እንወዳለን።
ለ27 ዓመት ኢሕአዴግ/ህወሓት የአዲስ አበባን ሕዝብ በማሰቃየትና በማፈናቀል ለማድቀቅ የተጠቀመውን ፖሊሲ ዛሬ የ“ለውጥ አራማጁ” ክፍል ሲጠቀምበት ማየት እጅጉን ያስገርማል። አዲስ አበባ ለገጣፎ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ በሺዎች የሚገመቱ አባወራዎችን ቤት ሳይታሰብ በቡልዶ ዘር መናድና መደርመስ፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ የቤት እመቤቶች፣ አዛውንት ቤተሰቦችን አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎ ማስለቀስ ጀግንነት አይደለም። የተጎዱና ድሀ ኅብረተሰቦችን አቅፎ ካለቀሰ አመራር በአገዛዙ ሌላ ማስለቀስ አይጠበቅም። ስለ ዜግነት መብት የተቆረቆረ መሪ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን መፈናቀል፣ መሰደድ፣ መገደል አላየሁም፣ አልሰማሁም ሊል ከቶም አግባብነት የለውም።
በአዲስ አበባ ለገጣፎ ለገዳዲ አካባቢ የተገነቡ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙና የተገነቡ ናቸው ከተባለም ያለ አግባብ መብራትና፣ ውሃ በማስገባት፣ ግብር በመክፈል እውቅና የሰጣቸው የቀን ጅቦቹ አገዛዝ ኢሕአዴግ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። እነኚህ ቤተሰቦች ይነሱም ከተባለ በአንድ በኩል
ስንት ወቅታዊ ጉዳይ እያለ አሁን ጊዜው አይደለም፤ በሌላም በኩል ቢያንስ ለእነኚህ ነዋሪዎች አመቺ መኖሪያ አዘጋጅቶ እንጂ “ቢቻል ወደ እሥር ቤት በማስገባት” ነበር ሲባል የለውጡን ሂደት ምላሽ እያገኘንለት እንደሆነ እንገነዘባለን።
የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማም ሆነ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ አስተዳደር እነኚህ ነዋሪዎች ያለ አግባብ የመንግሥት ቦታ ላይ ቤት ገንብተዋል ከተባለ በፍርድ ከሶ ማስፈጸም ሲገባው እራሱ ወንጃይ፣ እራሱ ከሳሽ፣ እራሱ ፈራጅ፣ እራሱ ውሳኔ ሰጥቶ አፍራሽ ሆኖ ሲታይ ምን ያህል ፍትህ እንደተዛባ አመላካች መሆኑን እንጠቁማለን። የነዋሪዎቹ ከአስተዳደሩ በፍርድ ቤት በአግባቡ የመከራከርና የመሞገት የዜግነት መብታቸው ሳይጠበቅ በላያቸው ላይ ቤታቸውን የማፍረስ ሕገ ወጥ ድርጊት ነው ይልቁን መወገዝ ያለበት። የዚህ ዓይነቱ የማን አለብኝነት አካሄድ ከመንግስት አካላት ሲከሰት ሀገሪቷን የሚገዛው አካል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊመለከተው እንደሚገባ ልንገነዘብ አግባብ ነው። አገዛዙን ከአስተዳደር መዋቅሩ ነጥሎ ማየት አይቻልምና።
“አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” በሀገራችን ኢትዮጵያ ለመንቀሳቀስ ስንገባም ሆነ አሁንም የኢሕአዴግን አገዛዝ ለመታገል እንጂ ለማቀፍ እንዳልሆነ ደግመን ደጋግመን አሳውቀናል። አቋማችን በሀገራችን ዘርንና ቋንቋን ተገን ያደረገ አከላለል አብቅቶ፣ ኢትዮጵያዊነትን ቅድሚያ የሰጠ ሀገራዊና ሕዝባዊ አገዛዝ ተግባራዊ ይሆን እንጂ። የዜግነት መብት ሲከበር እንጂ ዜጋ ሲያለቅስ ተመልካች ለመሆን አይደለም። በዚህም ሂደት ለበርካታ ዓመታት ያልተመለሱ የሀገሪቷ መሠረታዊ ጥያቄዎች ይፈቱ ዘንድ እንጂ ለአለው መንግሥት የምርጫ ፖለቲካ አድማቂና አጃቢ ለመሆን እንዳልሆነ በድጋሚ አቋማችንን ግልጽ እናደርጋለን።
ሰሞኑን እየተወሰደ ያለውን በአዲስ አበባ ለገጣፎ አካባቢ ነዋሪዎች ስቃይና እምባ እጅጉን እየተሰማን ለዚህም በአገዛዙ ሹማምንት የሚሠጠው ምላሽ እጅጉን ያቆስላል። ለመሆኑ 27 ዓመት እየገዛ ያለው ኢሕአዴግ መቼ ሕግ አክብሮ ያውቃልና ነው ንፁሐንን “ሕገ ወጥና ወንጀለኞች” ብሎ ለመፈረጅ የሞራል ብቃት ያገኘው?። በአገዛዙ ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ ሕንፃዎች በአለው አገዛዝ ብልሹ ዘረፋና ሌብነት ስንቱን ቤተሰብ እያስለቀሱና አውላላ ሜዳ ላይ እየጣሉ እንደነበር ሳይዘነጋ ዛሬም ይህ ሲደገም አሁንም ትግሉን አጠናክሮ ከመቀጠል ሌላ አማራጭ እንደሌለ እየጠቆምን ነው።
ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ እኚህ ዛሬ የተፈናቀሉት በአዲስ አበባ የለገጣፎ ለገዳዲ ቤተሰቦች መኖሪያቸው እሱም ካልሞላ ጎዳና ሁኗል። ሕፃናቶቻቸው ትምህርትን ወደ ልመና፣ ወጣት ሴቶች እያነቡ ክፍት ቦታ ከተገኘ ወደ ሴተኛ አዳሪነት፣ ወጣት ወንዶች እየተንገበገቡ ወደ ወያላነት እንደሚጓዙ አያጠራጥርም። “ተኖረና . . .” እንዲሉ ወላጆቻቸው እስከዛሬ ሲገፉት የነበረው የመከራ ኑሮ ሳያንስ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ሕይወትን በሰቀቀን፣ በእየዬ እንዲገፉት ተወርውረዋል። እውን አያድርስ! ምን ዓይነት ዘመን ላይ ነው ያለነው? ያሰኛል።
ቁስሉና ክብደቱ ሊሰማን፣ ሊያመን የሚችለው እስቲ በእያንዳንዳችን ቤተሰብ ላይ እንደደረሰ አድርገን እንውሰደው። ከሥራዎ ሰላም ሲገቡ፣ ሕፃናት ትምህርት ቤት ውለው ሲመጡ፣ የቤት እመቤቶችና የሠፈር ነዋሪዎቹ እያነቡ፣ አዛውንቶች እየተከዙ፤ ቤትዎ ከነንብረትዎ ቁልል ፍርስራሽ ሆኖ ሲመለከቱ፣ ህልምዎ እውን ሲሆን ምን ይሰማዎታል? “ለውጥ” መጣልኝ ሲሉ ዳግም መፈናቅል፣ ዳግም ልጆችዎ እንዳይማሩ ሲደረግ፣ በጥቅሉ ዳግም ሕይወትዎ ሲመሰቃቀል “አቤት” ቢሉ ከነሱ በላይ ያሉት እራሳቸው ሁነው ሲያገኟቸው ምን ይሰማዎታል?
እኛ “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” የሕዝብ ስሜት ስሜታችን፣ የሕዝብ ቁስል ቁስላችን፣ ዕምባቸው ዕምባችን፣ የሀገር ስቃይ ስቃያችን ነውና እየተፈፀመ ያለውን የማፈናቀል ሂደት አስፍተን ስናየው አዲስ አበባን ለማተራመስና ነዋሪዋን ለማሰቃየት የተቀነባበረ የዘረኝነት አገዛዝ ውጤት አድርገን ወስደነዋል። በመሆኑም ስለ ሀገር አንድነት፣ ስለ ልማት የምንሰብከው እውን ከውስጣችን ከሆነ፤ ልማት ማስለቀስ አይደለም፣ የኢትዮጵያ አንድነት በዘርና በቋንቋ ሸንሽኖ አይመጣም እንላለን። ሕዝብ የሚወደንም ሆነ የሚጮህልን ሳይገባው ቀርቶ ወይም ተሞኝቶ አይደለም። ከማንም በላይ ምን እየተደረገ? ያለውን የሚያውቀውና የሚረዳው ባለቤቱ እራሱ ነውና ለውጥ የሚመጣው በማሞካሸትና፣ በመሸንገል እንዳልሆነ ልናሳስብ እንወዳለን።
ዛሬ በሀገራችን ቅድሚያ መሰጠት ያለበት መብላት ያቃታቸውን ቤተሰቦች መመልከት፣ ኑሮ ዳገት የሆነባቸውን የመንግሥት ሠራተኞች ማየት ሲገባ የብሱኑ ለረሀብና ለጎዳና ተዳዳሪነት መዳረግ መፍትሔ እንዳልሆነ ልንጠቁም እንወዳለን። “የእንትናን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” ነውና ይህን ሀገሩን ወዶ፣ ኢትዮጵያዊነቴን፣ ባህሌን፣ ሃይማኖቴን፣ ልጄን፣ ጎረቤቴን ያለ ምስኪን እየነካካን ችግር ባንጠራ ይመረጣል እንላለን።
በመጨረሻም በአዲስ አበባ ለገጣፎ ለገዳዲ አካባቢ ነዋሪ ለሆናችሁና በግፍ አውላላ ሜዳ ላይ ለተጣላችሁ ወገኖቻችን “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” የተሰማንን ከፍተኛ ሐዘንና ቁጭት ልንገልጽላችሁ እንወዳለን። ይህ ዛሬ የደረሰባችሁ አድራጎት ለ27 ዓመት የኢሕአዴግ አገዛዝ እንደ ፖሊሲ ሲጠቀምበት የነበረ የአዲስ አበባን ሕዝብ የማሰቃየት፣ የመቅጣት፣ ሞራል የመስበር ሂደት ውጤት ነው። ኢሕአዴግ በያዘው የዘረኝነት ሕገ መንግሥት መሠረት አዲስ አበባን “ፊንፊኔ” ለማድረግ በዚህ ከቀጠለ የአዲስ አበባ ሕዝብ ገና የመከራው ክምር ከፊቱ ተደቅኗልና ለእልውናው ብሎም ለሀገሩ ሲል ከወገኖቹ ጋር በጋራ መቆም እንደሚኖርበት አጥብቀን እናስገነዝባለን።
የዜጎቻችን ዕምባ ዕምባችን ነው!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ
የካቲት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. (February 23, 2019)
ስልክ (703) 300 4302 USA
ኢሜል፡ ethiopiachen2009@gmail.com