ሠላም ለናንተ ይሁን!
ኢትዮጵያ የአውሮፓን አይሁዶች ከሂትለር እልቂት ታድጋለች! (ትርጉም)
የኢየሩሳሌም ፖስት (The Jerusalem Post) በ27/1/19 ባስነበበው ዕትሙ ይዞት የወጣው ታሪክ ‘ርዕስ’ ነው – ከላይ የቀረበው። ይዘቱ እንዲህ ይከተላል። በአውሮፓ በናዚዎች የሚካሄደው ዕልቂት ጡዘት ላይ በደረሰበት ኦገስት 1943 (እኣአ) ኢትዮጵያውያን አይሁዶች (ፈላሻዎች) በመሪዎቻቸው አማካይነት ንጉሠ ነገሥት ሃይለ ሥላሴን በመቅረብ አስደማሚ የሆነ ጉዳይ አቀረቡላቸው። የአውሮፓ አይሁዳውያንን ኢትዮጵያ በስደተኝነት እንድትቀበልና እነሱም በፈላሻዎች መኖሪያ መጠለያ እንዲያገኙ ንጉሡ እንዲረዱ የሚል ነበር ጥያቄያቸው።
በዋርሶ (Warsow) የጌቶ (Ghetto) አመፅ ከተካሄደ ሶስት ወር በሁዋላና የናዚዎች ማሰቃያዎች አራቱ የኦሽዊትዝ ማቃጠያዎች (Auschwitz crematoria) በሥራ ላይ ከዋሉ ሁለት ወር በሁዋላ የዛሬው ጄሩሳሌም ፖስት በቀድሞው መጠሪያው ፓልስታይን ፖስት (Palestine Post) ኢትዮጵያ አይሁዳውያን ስደተኞችን መቀበሏን የሚያትት ዘገባ ይዞ ወጣ።
ኦገስት 8/1943 የታተመው ይህ ጋዜጣ ሲያብራራ “የአይሁዳውያንን ወደ ኢትዮጵያ የመሰደድ (Jewish Immigration to Abyssinia) አማራጭ በሎንዶን የሚገኙት የኢትዮጵያ ሚኒስትር ከአቶ ሃሪ ጉድማን (Harry Goodman) እና ከእስራኤል የአጉዳቱ ዶ/ር ስፕሪንገር (Dr. Springer of Agudath) ጋር ተወያይተዋል” ብሏል። “የአውሮፓ አይሁዳውያንን በፈላሻዎች መንደር እንዲጠለሉ ለማድረግ የፈላሻ መሪዎች ፈቃደኝነታቸውን ገልፀዋል” ሲል አብራርቷል ጋዜጣው። (ፈላሻ) በኢትዮጵያ የሚኖሩ አይሁዳውያን መጠሪያ ነው።
በሎንዶን የተጀመረው ውይይት አዲስ አበባ ላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ቀጥሎ የንጉሡን ድጋፍ ያገኘ ሲሆን ኢትዮጵያ በ1941 ከጣልያን ወረራ ነፃ ስትወጣ ስደተኛው ንጉሠ ነገሥትም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው መንበረ ዙፋናቸው ላይ ነበሩ። እንደ ዘገባው ማብራሪያ አንድ ሺህ አምስት መቶ (1500) ስደተኛ ግሪኮች (የግሪክ አይሁዳውያንን ያካተተ) በ1943 (እአአ) ኢትዮጵያ ገብተዋል ብሏል።
ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ በ1936 ኢየሩሳሌም በሚገኘው የንጉሥ ዳዊት ሆቴል ተቀምጠው ስለነበር በሀገሪቱ ስለሚኖሩት አናሳ አይሁዳውያን ያውቁ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ንጉሡ አፍቃሪ ፅዮን (ፅዮናዊ) ከሆነውና የጌድዮን ግብረ ሃይል የተባለውን ጦር በመምራት ከጣልያኖች ጋር ለመዋጋት ወደ ኢትዮጵያ ከገባው ጄኔራል ዊንጌት ጋር በቅርበት አብረው ሰርተዋል። የኢትዮጵያ የዘመኑ መሪዎች የፈላሻ ማህበረሰብ መሪዎችን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የአይሁዳውያንን ሠቆቃ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር።
ምንም እንኴን ኢትዮጵያውያን አይሁዶች (ፈላሻዎች) በጣሊያን ወረራ ዘመን የገፈቱ ቀማሾች ቢሆኑም ቅሉ በ1943 (እአአ) ንጉሡ ከአውሮፓ የሚሰደዱትን አይሁዶች እንዲታደጉ ለማስደረግ ችለዋል። በዚያን ወቅት በናዚዎች መረብ ውስጥ የወደቁ አይሁዶችን ማዳን አዳጋች ነበር።
በዘገባው ውስጥ የተጠቀሰው ሃሪ ጉድማን (Harry Goodman) ታዋቂ የሆነ የOrthodox Agudath Israel World Organization አባል ነበር። ሳምንታዊ በሆነው Jewish Weekly የተለያዩ ፅሁፎችን የሚያቀርብ ሲሆን በናዚዎች ቁጥጥር ስር በምትገኘው አውሮፓ ውስጥ ለሚገኙ አይሁዳውያንም የአየር መልዕክት ያስተላልፍ ነበር። በአንዳንድ መዛግብት ላይ M.R.Springer የተባለ ግለሰብ በእንግሊዝ (UK) ከሚኖሩ የቼክ (Chech) አይሁዳውያን ጋር ግንኙነት እንደነበረው ተወስቷል።
የጣልያኑ አምባገነን ቤኒቶ ሙሶሎኒ በ1930 የኢትዮጵያ ወረራ ወቅት አይሁዳውያንን በኢትዮጵያ የማስፈር እቅድ ብልጭ ብሎበት ነበር። በዚያን ወቅት ከ50,000 (ሃምሳ ሺህ) በላይ አይሁዳውያን በጎንደር አቅራቢያ በሚገኙ ሰፈሮች እንደሚኖሩ ይታመናል።
ይህ ኢትዮጵያ በ1943 የአውሮፓ ስደተኛ አይሁዳውያንን ለማስፈር ያደረገችው ጥረት ሙሉ ታሪክ በሚገባ ምርምር ያልተካሄደበት/ያልተደረገበት በመሆኑ ዝርዝር ታሪኩ ገና አይታወቅም፤ ሲል ጄሩሳሌም ፖስት ዘገባውን ቌጭቷል።
(ፎቶው፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ አይሁዳውያን የአምልኮ ሥነ ሥርዐት ሲያካሂዱ የሚያሳይ ነው)
የካቲት 2011 (ማርች 2019)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com