እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያን የተለያዩ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች በተለያዩ ዘመናት በዘመናዊ መሳሪያ እስከ አፍጫንጫቸው ታጥቀው በቅኝ ግዛት ይዘው ለማስገበር ያላደረጉት ጥረት አልነበረም:: የእኛም አያት ቅድም አያቶቻችን ጦር ሰብቀውና ወጨፎ ታጥቀው በባዶ እግራቸው አሾክና አሜኬላው ሳይበግራቸው ዳግም የማትገኘውን ህይወታቸውን መሰዋት አርገው ለኛ ለልጆቻቸው እሳልፈውልናል:: ይህንን የአያቶቻችንን እና የቅድም አያቶቻችንን ጀግንነትና ዝና እፍሪካዊያኖች ብቻ ሳይሆኑ በካሬቢያን ይኖሩ የነበሩ ዘረ አፍሪካዊያን የሆኑ ሁሉ እንደራሳቸው ድል ቆጥረውት እኛም ኢትዮጵያዊያኖች ነን አስከማለት የደረሱ እንዳሉ የታሪክ ድርሳናት ይጠቀሳሉ ::
ቅኝ ግዛት ለመያዝም የመጡት ምዕራቢውያንም በዘመኑ ጀግኖች አያቶቻችንና ቅድም አያቶቻችን የሃፍረት ሸማን ተከናንበው ከመመለሳቸው ባሻገር ይህንን የቅድም አያቶቻችንን ጅግንነት ምስክር ጭምር በመሆን በየአገራቸው ቋንቋ ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል: ሽንፈታቸውን ተተኪው ትውልዳቸው እንዲያውቀውና ሌላ ሽንፈት ውስጥ እንዳይገባ በሰፊው አስተምረዋል እያስተማሩም ናቸው:: ይህንን የአደዋ ሽንፈት የሚለውን መጣጥፌን እንድጫጭር ያነሳሳኝ እንድ ወንድሜ ባለፈው ሰሞን በምደር ውስጥ በሚሄድ ባቡር (subway) እየተጓዝን ሳለ በአሁን ሰዓት ስላለው የለውጥና የሽግግርን ዘመን በተመለከተ ስንወያይ ነበር ስለ ተለያዩ ሽንፈቶቻችን አንስተን ያወጋነው:: ይህ ወንድሜ በልጅነት ዘመኑ ከአገር በመውጣት እድሜውን ከግማሽ በላይ ያሳለፍውና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንና ከፍተኛ ትምህርቱን የተከታተለው በጣሊያን አገር ነበር ::
የሩቁን ትቼ ከ1953 እኢአ ጀምሮ ያለውን ሽንፈት ብንመለከት እንኳን እንደሚታወቀው ሁለት እውቅ ወንደማማቾች በዘመኑ የነበረወን ዘውዳዊ አገዛዝ ገርሥሶ ለመጣልና ሰፊውን የሃገራችንን ህዝብ ከጭቆንና ነጻ ለማውጣት የከፈሉት መሰዋትነትነትና ጀግንነት እስከ አሁን ላለው ትውልድ ሲታወስ ይኖራል:: በተመሳሳይ ሁኔታ አመታት ያስቆጠረውን ንጉሳዊ አገዛዝ ገርሥኦ ለመጣል የተደረገው ሙከራ አብዛኛውን የጦር ሃይል አይደለም በአካባቢያቸው ያሉቱን ከፍተኛ ባለስልጣኖች ያላካተተ በመሆኑ ያሰቡትን ከግቡ ሊያደርሱ አልቻሉም::
ይህን አይነት የቅንጅት አጥረት ሽንፈት ካልተባለ ምን ሊባል ይችላል? አብዛኛውን ግዜ የተለያዩ ጻሃፊዎች በወቅቱ ስለተደረገው የመንግስት ለውጥ ህሳቤና ሙከራ አጋነው ከመከተብ ባለፈ ስህተቱን እንደ ሽንፈት ተቆጥሮ ለትምህርትነት እንዲሆን በወቅቱ ሰፊው ህዝቡ እንዲያውቀው አልተደረገም ነበር:: በበቂ ሁኔታ በመጻፍ ለተከታዩ ትውልድ ያስተማሩ ቡዙዎች አይደሉም:: ሌላው ደሞ ንጉሳዊ አገዛዙ በ1953 የተቃጣበትን መፈንቅለ መንግስት በድል መወጣቱን አጋኖ ከመናገር ውጪ ለምን መፈንቅለ መንግስቱን አሰቡ ብሎ ስህተቱንና ድክመቱን እንደ ሽንፈት ቅጥሮ ከመፈተሽና በሆደ ሰፊነትና እንደ መንግስት በማሰብ እነዚያን ብርቅዪ ኢትዪጵያኖች በእስር በመቅጣትና አስተምሮ ከመፍታት ይልቅ ለአንዴና ለመጨረሳ ግዜ እንዲያሸልቡ በሞት ቀጣቸው ይህ ሽንፈት ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል?
ይህ በእንዲህ እያለ ሽንፈታችን በሚገባ ሳይፈተሽና ሳይታወቅ በ1960ዎቹ መጀመሪያ በአገር ውስጥም ባሉ በውጪም አገርም በትምህርት ላይ ባሉና ያ የትውልድ በመባል በሚታወቁት ታላላቅ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለሁለተኛ ግዜ የዘውዳዊ አገዛዙን ግርስሦ ለመጣል በአደረጉት እርብርቦሽ በአገራችን ለረዥም ግዜ የኖረውን ዘውዳዊ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ በ1966ዓ/ም ከዙፋኑ አውርደው ጣሉት:: እነዚህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የተቃኙት በውጪ ፍልስፍናና እርዮት አለም ስለነበረ የህዝባችን ስነ ልቦናና የህዝባችንና እውቀትና እድገት ያላገናዘበ አካሄድ በመጀመራቸው ያሰቡትንና ሊያመጡ ያቀዱትን አገራዊ ለውጥ በወታደሩ ሊነጠቁ ችለዋል ይህም ሌላው በወጉ ለትምህርት ያልዋለ ሽንፍታችን ነው ::
የወጣቱን የለውጥ ጥያቄ የነጠቀው ወታደራዊ ደርግ ያለፉትን ሽንፈተቶች በቅጡ ስይመረምርና ሳያጠና ቢኖሩ ገፋ ቢል ከአስር ዓመት ባለይ የማይቆዩትን አዛውንቱን ንጉስ አፍኖ ለመግደል እሽቅድምድም ውስጥ ገባ:: በማስከትልም በንጉሱ ዘመን አገሪቱን የት ያደርሳሉ የተባሉትን አንቁ የኢትዮጵያ ልጆች ማለትም ስልሳዎችን ሚኒስትሮች በፍርድ ቤት ተዳኝተው ሳይሆ በድምጽ ብልጫ ጣት በማውጣት በሞት ይገባቸዋል ቀጣቸው ይህ እንደ ህዝብም እንደ አገርም ሽንፈታችን ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል:: ይህንንም ሽንፈት በተገቢው ሁኔታ ለትምህርትነት እንዲውልና ከሽንፈታችንም በሚገባ ሁኔታ እንድንማር በስፋት የጻፈም ያስተማረም በብዛት የለም ምናልባት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ተችተው ጽፈው ይሆናለ እንጂ ህዝቡ እንዲማርበት የተድረገበት አጋጣሚ እምብዛም የለም::
በማስከተልም ለውጡ እንዲመጣ ቡዙ ትግልና መሰዋትነት የከፈለውን ያ የዘመኑን ወጣት የርዮት አለሙ ከወታደራዊው ደርግ የተለየ በመሆኑ በቀይ ሽብር በሚል መርሆ ተተኪ ያልተገኘለት ወጣት በሞት እንዲቀጣ አደረገ በኔ እምነት መሳሪያ እና የጦር ሀይል ያለው መንግስት ሆደ ሰፊና ታጋሽ ሆኖ የርዮት አለም ልዩነት አላቸው የሚባሉትን ወጣቶች በማሰርና በማስተማር መመለስ ሲችል እነዚህን ወጣቶች በመግደል አገርንም ወላጆችንም የወላድ መሀን አድርጎ አስቀረ ይህንን ዓይነት ሽንፈታችንን ለመበቃቀል ተጠቅመንበት እንደሆነ እንጂ እንደ ትምህርት ወስደነው ሌላ ሽንፈት እንዳይደገም አልተማርንበትም::
በተለይ በተለይ በዛን ዘመን ስልጣን ላይ የነበሩ አባቶቻችን አንዳን ጹሁፎችን ሲጹፉ ምንም አንዳልሆነ አንኳን የሰው ህይወት በሰማይ የምትበር ወፍም እንደምታሳዝናቸው በጹሁፋቸው ግልጸዋል ይህ የሚያሳየው ከሽንፈታችን ላለመማር ቆርጠን የተነሳን መሆናችንን ነው:: ያ ትውልድ እያልን የምንጠራቸው ወንድሞቻችንም በወቅቱ እስከ አፍንጫው ድረስ መሳሪያ የታጠቀን ደርግን በከተማ ትግል በማካሄድ ገዳይም ተገዳይም መሆናቸው ሽንፈታቸው መሆኑን ከማመን ይልቅ የሚጹፉትና የሚናገሩት በአብዛኛው ትክክል ነን ስንገደል ምን እናደርግ መከላከል የግድ ይላል የሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ነው የሚያቀርቡት ይህ በራሱ ሽንፈታችን ከልሆነ ምን ሊባል ይችላል::
መራሹ ህወሀት/ኢህአዴግ ደርግን ገርሥሶ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የሰራቸው ስንኩል ስራዎችን ሁሉንም እዚህ ላይ መዘርዘሩ ለቀባሪው አረዱት እንዳይሆንብኝ አልፈዋለው:: በአጭሩ መራሹ ህወሀት/ኢህአዴግ እንደ ዱር አውሬ የሚቃጣው አቋሙ ነበረው መራሹ ህወሀት/ኢህአዴግ በራሱ ህዝብና አገር ላይ ያደረሰው አረመኔያዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዓለም ላይ ከሚታወቁ መንግስታት መደዳ ቀዳሚው ያደርገዋል ብል መሳሳት አይመስለኝም፡፡ ቀዳሚ የሚሆንበት አበይት ምክንያት በዓለም ታሪክ ብቅ ብለው የነበሩ እንደ ጀርመኑ ናዚ ያሉ ጨካኝ መንግስታት የጭካኔ በትራቸው ያሳረፉት በራሳቸው ህዝብ ላይ ሳይሆን በሌሎች አገር ሰዎችና ህዝብ ብለው ባሰቧቸው ላይ ስለነበረ ነው፡፡ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ግን ለመናገር እንኳን በሚያሳቅቅ መከራ ውስጥ እንደ ገና ዳቦ ከድኖ ከላይ ፍም ከታች ፍም አድርጎ ይቀጣቸው የነበረው የራሱን ህዝብ ነበር ብል ማጋነን አይሆንም የህወሀት/ኢህአድግ ዘመን እኮ አባትንና ልጅን፣ እናትንና ልጅን በዘርና በቋንቋ ምክንያት አባልቷል አለያይቷል አገርን ግንጥሏል እስገንጥሏል ክልል በሚል ሰበብ ስንት ኢትዮጵያኖች እትብታቸው ከተቀበረበት በዘራቸውና በቋንቋቸው ብቻ እንዲባረሩና እንዲፋናቀሉ አድርጎል በአሁኑም ሰዓት ድረስ እየተፈናቀሉ ይገኛሉ:: እህታችን ሎሪት የትነበርሽ በዓንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ስለ ዘመኑ የቋንቋ በሽታ ስታወሳ “ማንኛውም ሰው ከናቱ መሃጸን ሲወጣ የሚያውቀው ቋንቋ እርር ብሎ ማልቀስ ነው ቋንቋው ብላለች” ከዛ ውጪ ያለው ቋንቋ ከተወለደ ቦሃል እንደ አካባቢውና እንደ አገሩ በመስማት በመማርና በመናገር የሚያጎልብተው ነው ይህንንም በማድረጉ ለወቀስና ሊፈናቀልበት አይገባም ነበር ይህ ነገር ግን የተደረገና እየተደረግ በመሆኑ ሽንፈታችን እንደሆነ ተቆጥሮ ሰፊ ትምህርት ሊሰጥበት ይገባል::
ሌላው ደሞ አንዳንድ መጥፎ ምሳሌ ለማቅረብ ወያኔ በገባ ሰሞን – በዘረኝነት የወረት ፍቅር ያበደች አንዲት ትግሬ እህታችን ከአንድ ወሎዬ አማራ የወለደችውን ሕጻን ሽንት ቤት ውስጥ ጨምራ ገድላለች:: ሰሞኑን ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ የምንሰማውና የምናየው የእስረኞች ሰቆቃ የህወሀት ሽንፈት ብቻ ሳይሆን የአገር ሽንፈት ነው ብዪ ነው የማምነው ይህንን ጉድ የሰማናውና ጉድ ጉድ ስንል የነበረው ህወሃት/ኢህኣዴግ ለስልጣኑ ሲል በዘር; በጎሳና በቋንቋ አገራችንን በመከፋፈል አገርን አውድሞ ስልጣኑን ለማቆይርት የሄደበት የከፋፍለህ ግዛ በሽታው ዐይንንም፣ ኅሊናንም፣ አእምሮንም፣ በጥቅሉ ሁለመናን የሚያሣውር መጥፎ በሽታና መጥፎ ዘረኝነት ሌላው ሽንፈት ነው::
በኔ ግምት ይህ ሽንፈታችንን በቅጡ ስላልተረዳን መድኃኒቱ ሞት ወይም በአንዳንዶች ላይ እንዳስተዋልኩት በእርጅና ዘመን አካባቢ ሊመጣ የሚችል ጸጸት ብቻ ሆኖ እየተመለከት ነው:: በኔ እምነት ድላችንን ነቅሰን በማውጣት እንደምንፈክርበትና እንደ ምንሸልልበት ሁሉ ሽንፈታችንንም ነቅሰን በማውጣት ሳንፈራና ሳንሸማቀቅ ላለው ትውልድና ለተተኪው ትውልድ በሚገባ ማስተማር አለብን ባይ ነኝ ምክንያቱም ያ ሲሆን ካሉን ውስብስብ ችግሮች አንዱንና ዋናውን ከውስጣችን አስወገድን መላት ነው:: ይህ በራስ ህዝብና በራስ አገር ላይ የደረሰ መከራን ሽንፈት ነው ብለን በትምህርትነት ውስደነው ይህን ዓይነት ድሪጊት እንዳይደገም ካላስተማርንና ካልተማርን መቼ ነው ሽንፈታችንን የምናውቀው?::
ሌላው በአሁኑ ወቅት በሽግግሩ ሰዓት እንደ ሽንፈት የምቆጥረው የሰሞኑን የአገራዊ እርቅ ኮምሽንን ይመለከታል እኔ እንደ አንድ ግለሰብ ጠቅላይ ሚንስትራችንን ዶ/ር አብይ አህመደ እየተጓዙበት ያለውን የአገር ማዳን መንገድ ከመጀመሪያው ጀምሮ ደግፌላው ወደ ፊትም እደግፋለው ስደግፍ ግን በምክንያት ነው እንጂ የማውቃቸው; የምቀርባቸው ስለ ደገፉ ሊሆን አይችልም:: ስለሆነም ዛሬ በዚህ ጹሁፌ የምናከብራቸውና የምንደግፋቸው ጠቅላይ ሚንስትራችን ላይ ሽንፈት አይቻለው እውነተኛ አገራዊ እርቅ ለማድረግ ይህን አይነት ስህተት ይሰራሉ ብዪ አልጠበኩም:: እርግጥ ነው የአገራችን ችግር ዘርፈ ቡዙ ነው ይህ ዘርፈ ቡዙ ችግር ትላንት አልተጀመረም የሚል እምነት አለኝ ቢሆንም ቅሉ በጹሁፌ መጀመሪያ የቆየውን ትተን ከ1953 ጀምሮ ያለውን ሽንፈታችንን እያወጣሁ እያወረዱክ ሳለ የተሻለ መሪ አገኘሁ ያለፈውን ድላችንን ብቻ ሳይሆን ሽንፈታችንን ያለ ፍርሃት የሚናገር የኛ የዘመኑ ጀግና እያልኩ ባልኩበት ሰዓት የአገራዊ እርቁን የሚመሩትን ተመራጮች ስም ዝርዝርንዝ ስመለከት የኔ እይታን በጹሁፍ አስነብቤ ስህተትም ከሆነ እታረማለው በማለት ይህንን እይታዪን የምንወዳቸውና የምንደግፋቸው የወቅቱ ጠ/ሚ አብይ አህመድ የስልጣን ዘመን ሽንፈት ብዮ ለመከተብ ተገደድኩ:: እንደ እውነቱ ከሆነ ስለ አገራዊ እርቅ ምንም ዓይነት ጠለቅ ያለ ጥናት የለኝም ነገር ግን ስለ አገራዊ እርቅ (truth and reconciliation) በተመለከተ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ሙህራኖች ለምሳሌ ፕ/ር ህዝቄል አሰፋ.እንዲሁም ፕ/ር ብርሃኑ መንግስቱ እንዲሁም ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸውና እንዳን ጹሁፎችንም ጽፈው አንብብያለሁ በተጨማሪ በሌሎች አገር ሙህራኖች የተጻፉን ጹሁፎችን በተወሰነ ደረጃ ተመልክቻለው በዛ ላይ እውቀት አለቸው ከምላቸው ጋርም ተወያይቻለው:: በሁሉም አቅጣጫ የተገነዘብኩት ለአገራዊ እርቅ የሚታጩት ሰዎች
- በችግር አፈታት ላይ ጥናት ያደረጉ እና የአስታራቂነትና(Arbitration) እውቀት በልምድ አለያም በትምህርት ያጎለበቱ ሰዎች::
- የማህበራዊ ኑሮ ጠብብቶች የህግ ባላሞያዎች(በዳኝነት) ስራ የረጅም ግዜ አገልግሎትና ተመክሮ ያላቸው
- በህብረተሰቡ ውስጥ ታላቅ ክብርና ታአማኒነት ያተረፉ ፣
- በሰብአዊ መብት ጥሰት ውስጥ በፍጹም ያልተሳተፉ (ተሳትፈዋል ተብሎ የማይጠረጠሩ)
- እጅግ የተወሳሰበ ተግባርን ለማካሄድና ረጅም ሰአት ለመስራት ጤነነትና የአእምሮ ብቃት አያቸው፣
- እጅግ ሰፊ መረጃወችን በጥልቀት ለማመዛዘን ብቃት ያላቸው
- በሀገሪቱ ውስጥ የተካሄዱ የመብት ጥሰቶችና ቅራኔወችን በተመለከተ በቂ እውቀት ያላቸው
- በእርቅ ተግባር ስራ ከተቻለም በቅራኔ አፈታት በቂ ልመድ ያላቸው
- የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎችን የሚያንጸባርቁ
- የሰብአዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸው ሰወችን ሁኔታ የሚገነዘብ ሆኖም ራሳቸው የዚህ ጥቃት ቀጥተኛና ከፍተኛ ተጠቂ ያልሆኑ (ትራማታይዝ ያልሆኑ)
- የፖለቲካ ድርጅት ከፍተኛ መሪ ያልሆኑ
(በነጠብጣብ የተቀመጡት ከአቶ ክሊሉ ወንድአፈረው የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን አበረታችና አሳሳቢ ገጽታወች የእርቀ ሰላሙ ጅምር ውጤታማነትን ከፍ ለማድረግ ምን ይደረግ?
ከሚል የግል አስተያየት የተወሰደ)
በዚህ አይነት ስሌት ለምሳሌ በኛ አገር በደርግ ግዜ የደርግ ባለስልጣን የነበሩ ሰዎች አሊያም በደርግ ዘመን የኢሕአፓ አሊያም የመኢሳን ወይም የኢጫት ወዘተ ከፍተኛ አመራር የነበረ ወይም ያነበረች እንዲሁም በኢህአዴግ/ህወሀት ዘመንም በከፍተኛ እርከን ላይ ያለ አሊያም ያለች ሌላው ቢቀር በአሁኑ በሽግግሩ ወቅት ተፎካካሪ ሆነው የሚቀርቡት ድርጅቶች ውስጥም ከፈተኛ አመራሮች ጭምር በአገራዊ እርቁ ኮምሽን ውስጥ መካተታቸው ቴክንካዊ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል የሚል እምተት አለኝ::
ከሁሉ በላይ በአሁኑ ሰዓት ያለው መንግስት ሽንፈቱ የምለው የተከበሩት ጠቅላይሚንስትራችን ከታጩት እንግዶች ጋር ውይይት ሲያደርጉ ይህንን አድምጫለው ::
” አቶ ሐ/ማርያምን እንድንጨምር ያደርግናው እዚህ ኮሚቴ ውስጥ ስራው ሎካሊ የሚታጠር ስራ አይደለም የውጪ ግንኙነት ይኖረዋል; ስልጠናም; የአቅም ግንባታም የፋይናስም:: ሮዋንዳም ማገዝ ትፈልጋለች ልምድ ስላላት; ደቡብ አፍሪካም ማገዝ ትፈልጋለች ልምድ ስላላት; አውሮፓዎችም ሃሳቡን ይወዱታል ማገዝ ይፈልጋሉ:: አቶ ሐ/ማርያም ደሳለኝ ቀደም ሲል የነበረውን ግንኙነት ተጠቅሞ ስልጠናና ፋይናስ ድጋፍ ከሌላ አገር ሊያገኝ ይችላል የአገርንም ችግር አመራር በነበረበት ሰዓት የሚያውቃቸውን ለኮሚቴው ግባአት መስጠት ይችላል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል:: ክብር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እውነት እንነጋገር ከተባለ አቶ ሀ/ማርያም በስልጣን ዘመናቸው እርሶ የተሰጦትን ስልጣን ነበር የነበራቸው በቅርቡ በህግ ቁጥጥር ስር የሚገኙት አቶ በረከት በተለያዩ ሚዲያዎች ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው “አቶ ሀ/ማርያም ሳያውቀው የታሰረም ሆነ የተገደለ የለም” ሲሉ ተደምጠዋል ታድያ በምን መመዘኛ ነው የተከበሩ ጠ/ሚራችን ዶ/ር አብይ አህመድ አቶ ሀ/ ማርያምን እንደዚህ ከባድ የሆነ አገራዊ ጉዳይ ላይ ያጮቸው?
የተከበሩ ጠ/ሚ አብይ አቶ ሀ/ማርያም ደሳለኝ ያንን ስልጣናቸውን ተጠቅመው አገራችንን ወደ ሰላምና መረጋጋት ከማሸጋገር ይልቅ በርሳቸው የስልጣን ዘምን ይመስለኛል ለመናገር እንኳን በሚያሳቅቅ የመከራ ድስት ውስጥ ከድኖ ህዝባችን ሲቀቅል የኖረው :: በደብረ ዘይት ቢሺፍቱ ላይ ያ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ያለቀው በሳቸው ዘመን ነው እናት ልጆ ተግድሎ በአስክሬኑ ላይ እንድትቀመት በጠምንጃ አፈሙዝ የተገደደችው በርሳቸው የስልጣን ዘመን ነበር:: የን ግዜ እቶ ሀ/ማርያም ምን ዓይነት እርምጃ ነው የወሰዱት? በውቅቱ በሌሎች ነው የሚመሩት አርሳቸው አቅም የለቸውም ከተባለ ይህንን ቃላቸውን ለሚመረጠው ኮምሽን እንደ ምስክር ሆነው ማቅረብ ሲገባቸው እርሳቸው የኮምሽኑ ተመራጭ ማድረግ ትልቅ ሽንፈት ነው ባይ ነኝ::
በማስከተልም የተከበሩ ጠ/ሚ አብይ ለተስበሳቢዎቹ እጭዎች እንዲህ በለው ነበር “እኛ ባለፉት ወራት ስናሥስ ስናሥስ ስናሥስ መለየት የቻልነው እንንተን ነው እናንተ ውስጥ ተሳስተን የቀላቀልናቸው ጢቂቶች ካሉ ያው ከአስራ ሁለቱ አንዱ ብላችሁ ማለፍ ነው ፐርፌክት ነገር የለም” ብለዋል::
እንደ እውነቱ ከሆነ በማንኛውም ሚዛን ቢመዘን የቀድሞው ጠ/ሚ አቶ ሐ/ማርያም ደሳለኝ እዚህ ኮሚቴውስጥ ማስገባት ቢያንስ ሞቹን ጠቅላይ ሚንስትር ተክተው በሰሩባቸው አመታት በተገደሉት ታስረው በተሰቃዩት መቀለድና ማሾፍ ከዛም በላይ የሞቱት ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ደም ደመ ከልብ አድርጎ ማስቀረት ነው የሚል እምነት አለኝ ይህንን ስል አቶ ሀ/ማርያም ይሰቀሉ ይወገሩ አሊያም ይታሰሩ ማሌቴ አይደለም እርሳቸው እራሳቸው ለተቆቆመው ኮምቴ ቀርበው በሳቸው ዘመን ለደረሰው ማንኛውም አገራዊ ጉዳት ተጠያቂና ይቅርታ ጠያቂ እንጂ ሌላውን ይቅርታ አስጠያቂ እንዲሆኑ ኮምቴውስጥ ማስገባት በማንኛውም ሚዛን ቢለካ ትክክለኛ ሚዛን አይደለም የሚል ሙግት ለተከበሩትና ለማከብሮት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለዶ/ር አብይ አህመድ አቀርባለው ፍርዱንም ለሚዎዶትና ለሚያከብሮት ለኢትዮጵያ ህዝብ; ለራሶት ሒሊናና ለታሪክ እተዋለው::
በማስከተል የተከበሩ ጠ/ሚ አብይ አህመድ እንዲያውቁልኝ የምፈልገው እየደገፍኮት ያለሁት በምክንያት ነው በምክንያት ደግፌቶለው ለአገራዊ እርቅ ላይ ባቀረቦቸው እጭዎች ላይ ባለኝ ምክንያት የተሰማኝን ቅሬታ የወቅቱ ሽንፈት ብዪ እንድገልጽ ተገድጃለው በኔ እምነት ስንደግፍም ሆነ ሰንተችም በምክንያት ላይ ተመርኩዘን መሆን አለበት ብዪ አምናለሁ ስለሆነም በምክንያት እየደገፍኮት በምክንያት እየተቸሆት በምችለው አቅም ህልሞት እንዲሳካ አብሬዎት ነኝ እያልኩ ሽንፈቶቻችን ላይ ቡዙ መስራት ይጠበቅብናል እላለው::
በመጨረሻም ወደ ተነሳሁበት አርዕስት ወደ “አድዋው ሽንፈት” ስመለስ ቅኝ ግዛት ለመያዝም የመጡት ምዕራቢውያንም በዘመኑ ጀግኖች አያቶቻችንና ቅድም አያቶቻችን የሃፍረት ሸማን ተንከባክበው ከመመለሳቸው ባሻገር ይህንን የቅድም አያቶቻችንን ጅግንነት ምስክር በመሆን በየአገራቸው ቋንቋ ጽፈው ለንባብ አብቅተው ልጆቻቸውም ከአያት ቅደም አያቶቻቸው ሽንፈት ትምህርት እንዲቀስሙበት አድርገዋል:: ይህንን የአደዋ ሽንፈት የሚለውን መጣጥፌን እንድጫጭር ያነሳሳኝ እንዱ ምክንያት ጣሊያኖች በአደዋ ጦርነት የተከናነቡትን ሽንፈት ምንም ሳይሸሽጉ ከ 1928 ባሃላ ለጠፈጠርው ትውልድ አስተምረዋል በሰፊው እያስተማሩ ይገኛሉ ለምሳሌ በጣሊያን ዋና ከተማ በሮም አንድ አደባባይ ይገኛል ይህ አደባባይ ይህን አይነት ጹሁፍ ይነበብበታል “The square is dedicated to the 500 fallen Italian soldiers who perished in the Battle of Dogali in 1887″. ከዚሂም የተነሳ ይመስላል ከ1928 ቦሃላ የተወለዱት ጣሊዊያኖች ሽንፈትን በትምህርትና አደባባይን ጭምር በመሰየም በሚገባ ስለተማሩ ዳግም የሰው አገርን በመውረር ወደ ጦርነት ሊገቡ የማይፈልጉት:: እኛ ኢትዮጵያውያን ድሎቻችንን በሰፊው እንደምናስተምር ሁሉ ሽንፍቶቻችንን ሁሉ የማናስተምረው ለምን ይሆን? ለምሳሌ ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመት የተዘራው በዘር ላይ የተመሰረተው መለያየት; በቋንቋላይ የተመሰረተው መለያየት በክልል የተመሰረተው መለያየት እንደ ሀገርም እንደ ህዝብም ሽንፈት ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል? ይህንን ሽንፈታችንን በአስቸኳይ ላለው ትውልድ የማስተማር ሀላፊነትና የዜግነት ግዴታ የሁላችንም ነው በተለይ በመንግስት ደረጃ ያሉት ባለስልጣኖች ከግል ዝናንና ከግል ጥቅምን ባለፈ ትኩረት ስጥተው ትውልዱ እንዲማር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ::
የምናከብራቸውና የምንደግፋቸው የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትርም ይሁኑ ለውጡ የፈጠራቸውና በአሁን ሰዓት አካባቢ በመምራት ላይ ያሉ “የለማ ቲሚ” የሚባሉት ወደ አስተዳደር ከመጡ ጀምሮ በአገራችን በኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ህዝቦች ቁጥር ከሶሪያ የህዝብ መፈናቀል ልቆ መገኘቱ በሰፊው እየተዘገበ ይገኛል ይህ ለጠቅላይ ሚንስትራችንም ይሁን ለቲሚ ለማ የወቅቱ ትልቅ ሽንፈት ስለሆነ ከሽንፈታቸው ተምረው ማስተካከል ካልቻሉ በያዙትም የድርጅት ስም ይሁን አሊያም አገራዊ ስምም ቀይረው ቢመጡ በሚቀጥለው አገራዊ ምርጫ ከስራቸው ያሉ እጩዎች አይደሉም ለራሳቸውም መመረጥ እጠራጠራለው ምክንያቱም ከስድስት ወር በፊት የነበራቸው ተወዳጅነት በእጅጉ እያሽቆለቆለ ነው ብል ማጋነን አይሆንም እያልኩ የዛሬውን ጹሁፌን ላጠቃልል::
አምላከ አቦው አገራችንን ኢትዮጵያ ከክፉ ነገር ይጠብቁልን አሜን!