የአዲስ አበባ ወንዞችን ተፋሰስ ለማልማት በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ለሚሳተፉ ባለሃብቶች የቀረበው የጥሪ ካርድ ላይ አዲስ አበባ ሸገር በሚል አወዛጋቢ ስም ተከሽና ቀርባለች፡፡ ግብዣው የፌደራል መንግስቱ እንደመሆኑ መጠን የጥሪው ካርድ አዲስ አበባን ሸገር በሚል የተከሸነ ስም መጥራቱ ሕገ መንግስታዊ ድጋፍም ሆነ መሰረት የለውም፡፡ በግልጽ እንደሚታወቀው የፌደራል መንግስቱ አቋሞች መነሻቸውም ሆነ መዳረሻቸው ሕገ መንግስቱ እንደመሆኑ መጠን፤ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ጥርጣሬ ላይ የሚጥሉ አወዛጋቢ መጠሪያዎችን መጠቀም የሚያስተላልፈው መልዕክት ገንቢ አይደለም፡፡
በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባና በፊንፊኔ መካከል የሚያመቻምች አማካይ ሰም በመፈለግ የጥሪው ካርድ ላይ ለአዲስ አበባ ሸገር የሚል ስያሚ መስጠት በማንኛውም መስፈርት ስህተት ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰረትም አዲስ አበባ ማዕከላዊ ስም የላትም፡፡ አዲስ አባባ ፊንፊኔም ሆነ ሸገር አይደለችም፡፡ ሕገ መንግስቱ እስከጻና ድረስም፣ አዲስ አበባ በፊደራል መንግስት መቀመጫነቷ መሰረት የጸና ስሟን ይዛ መቀጠል ይኖርባታል፡፡
የሕገ መንግስታችን አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 1 አዲስ አበባን አስመልክቶ በሚደነግገው መሰረት “የፌደራሉ መንግስት ከተማ አዲስ አበባ ነው፡፡” ይላል፡፡ የማያሻማና የማያደናግር ድንጋጌ ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ መሰረት አዲስ አበባ ፊንፊኔ፣ በረራ፣ ሸገር፣ መናገሻ ወይም ሌላ ተቀጥላ ስም የላትም፡፡ አዲስ አበባን በተለያየ ስም መጥራትንም አይፈቅድም፡፡ በሕገ መንግስቱም መሰረት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፌደራሉ መንግስት ጋር ኦፊሴላዊ መጻጻፍ ሲያደርግ የፌደራሉ መቀመጫን መጥቀስ ያለበት በአዲስ አበባነቷ ብቻ አለመሆኑ ሕገ መንግስቱን የሚጥስ አካሄድ ነው፡፡
ከሕገ መንግስቱ ውስጥ የሚፈልጉትን መርጦ ማክበርና ማወደስ ወይም የማይፈልጉትን መርጦ መጣስና ትርጉመ ቢስ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ አለኝ የሚለውን ልዩ ጥቅም ለማስከበር ሕገ መንግስቱን ተገን አደርጎና እየጠቀሰ እንደሚሟገት ሁሉ ፤ የአዲስ አበባ መጠሪያም የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አሻራና ውግንና የታተመበት ሕገ መንግስታዊ ስም መሆኑን መርሳት “ከስጋው አልፈልግም ከመረቁ አውጦልኝ” የማለት ያህል ነው፡፡
በዚህ መንገድ መቀጠል የሚያስከትለው መዘዝ ቀጣይነት እንደሚኖረው አያጠራጥርም፡፡ ነገ የአማራ ክልላዊ መንግስትም በተራው ከፌደራሉ መንግስት ጋር በሚኖረው ግንኙነት አዲስ አበባን የሚጠቅስው በረራ በማለት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይገባል፡፡ ሌሎችም ክልሎች ወይም ብሔሮች ታሪካዊ ድርሳናትን እየፈተሹ፣ ከዛሬዋ አዲስ አበባ ጋር በሚያስተሳስራቸው የታሪክ አሻራ ቀጭን ክር ልክ ስያሜ በማፈላለግ ይህንኑ ዝንባሌ መከተላቸው አይቀሬ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ማያዎች አዲስ አበባን ወጂ፣ ትግረ ወርጂዎች ደግሞ እንዶጥና፣ ዛሬ ላይ የት እንደደረሱ በውል የማይታወቁትና ተገፍተው ዳር የወጡት ነገር ግን በአንድ ወቅትና ጊዜ በአዲስ አበባና በዙርያዋ ሲኖሩ የነበሩ የሸዋ ሱልጣኔት፣ የዳሞት፣ የጋፋት፣ የጉራጌና የፋጠጋር ሕዝቦችም ታሪካቸውን እንዲፈትሹና መጠሪያ እንዲያፈላልጉ የሚያበረታታ ነው፡፡
የአንድ ከተማ መገለጫ መሬቷና የተፈጥሮ ሃብቷ ብቻ ሆነው አያውቁም፡፡ ይልቁንም በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች፣ መስረተ ልማቶቻቸው፣ ስነ-ልቦናዊና ማህበረሰባዊ እሴቶቻቸው አልፎ ተርፎም ሌሎች መስተጋብሮቻቸውን ያካተተ ነው፡፡ አዲስ አበባ መሰረተ ልማቷን፣ መንገዶቿን፣ ሕንጻዎቿን፣ የውሃ፣ የስልክና የመብራት መስመር ዝርጋታዋንና አቅርቦቷን እንዲሁም ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ መስተጋብሯን ቀንሰን ለመሬቷ ብቻ በተለይ ባለቤት ለማበጀት እንዴት እንደሚቻል ከስሜት ውጭ ሳይንስዊ ትንታኔ መስጠት አይቻልም፡፡
የእኔነት ጥያቄም ሁለንተናዊ ይሁንታ ቢቸረውም በራሱ ምልዑና እርካታን የሚጎናጽፍ ውሳኔ ሊሆን እንደማይችል የሚጠበቅ ነው፡፡ የባለቤትነት ጥያቄ ይሁንታን ከተጎናጸፈ በኃላ በመቀጠል ልዩ ተጠቃሚነትና ቅድሚያ ለኔ ይሰጠኝ የሚል ውዝግብን ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ትናንት አዲስ አበባም ሆነ አዋሳ ሲገነቡ የተገነቡት ከመሬታቸው በፈለቀ ነዳጅ ወርቅ ወይም ሌላ የተፈጥሮ ሃብት ሳይሆን መጤ በሚባሉት ዜጎች ጊዜና ጉልበት ፣ ሃብት፣ የፌደራል መንግስቱ በሚመደበው ልዩ በጀትና ለረጅም ዘመን በሚከፈል ብድርና እርዳታ አንዲሁም በሚጣለው ከፍተኛ ግብር ጭምር ነው፡፡ ይህ ሁሉ እውን የሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩና በመቶ ሚሊዮን ከሚቆጠሩ ዜጎች ጎሮሮ እየተቆጠበ፣ ከማደግና ከመሻሻል እድላቸው እየተነጠቀ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ከሁሉም ድሃና ደካማ ኢትዮጵያዊ ጉሮሮ እየተቆጠበ የተገነባ ከተማ እንዴት አንድ ባለቤትና ልዩ ተጠቃሚ ሊኖረው ይችላል፡፡
ዛሬ ላይ አዲስ አበባ ተገንብታለች፣ ሐዋሳም እንዲሁ፡፡ የምንኮራባቸው፣ ሁላችንም የኔ የምንላቸው፣ ለህይወታችን መለወጥ መንስኤ መሆን የሚችሉ ከተማዎች ከመሆን ይልቅ ለሕልውናችንና ለሰላማችን ፈተና የደቀኑ የፍጥጫ አውድማ ሆነዋል፡፡ ዛሬ እነዚህን ከተሞች አስረክበን ነገ አማካይ ከተማ ለጋራ ፌደራላዊና ክልላዊ መንግስት አዲስ ከተማ ልንገነባ ነው? ባህር ዳርና ደብረማርቆስ ወይም ወልቂጤ አሊያም ሌላ ከተማ መረጥን እንበልና ከብዙ ውጣ ውረድ በኃላ ልክ እንደ አዲስ አባባና ሐዋሳ አልምተን ስናበቃ፣ ከተሞቹ የኛ ናቸውና አንተ ውጣ አንተ ግባ የሚል ጥያቄ ላለመቀስቀሱ ምን መተማመኛ አለን? እንደ ሃገርስ በዚህ መንገድ የጋራ የምንለው የክልልና የፌደራል ከተማ መቼና እንዴት ነው በመተማመን ልንገነባ የምንችለው? የኔ ነው የሚለው ጥያቄስ ማቆሚያ መቼና የት ነው የሚሆነው?