በአየር ኃይል በተከሰተ የምግብ መመረዝ የአንድ ሰው ሕይወት አለፈ

በአየር ኃይል በተከሰተ የምግብ መመረዝ የአንድ ሰው ሕይወት አለፈ

በርካታ ሠልጣኞች ሆስፒታል ገብተዋል

ሪፖርተር | በኢትዮጵያ አየር ኃይል ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ጠቅላይ መምርያ የትምህርት ማዕከል ምግብ ቤት በተከሰተ የምግብ መመረዝ፣ 270 ያህል ሠልጣኞች ታመው ሆስፒታል መግባታቸው ተሰማ፡፡

ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በትምህርት ማዕከሉ ምሳቸውን በመመገብ ላይ የነበሩ በርካታ ተማሪዎች በሕመም በምግብ አዳራሽ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ከ260 በላይ የሚሆኑ ዕጩ መኮንኖች ሆራ አካባቢ በሚገኘው የአየር ኃይል ሆስፒታልና በከተማው ሆስፒታል እንደተወሰዱ ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ሠልጣኞች ሕክምና ተደርጎላቸው እንደወጡ፣ የአንድ ተማሪ ሕይወት ግን ማለፉን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ ለሠርግ ዕረፍት ወጥተው የነበሩ የአየር ኃይል የሕክምና ዳይሬክተር፣ ዕረፍታቸውን አቋርጠው የሕክምና ሥራውን ሲያተባብሩ እንደነበር ታውቋል፡፡

ሠልጣኞቹ የአውሮፕላን ጥገናና የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች እንደሆኑ የገለጹት ምንጮች፣ ሠልጣኝ አብራሪዎች በወቅቱ በምግብ ቤቱ አዳራሽ ውስጥ እንዳልነበሩ ተነግሯል፡፡

የምግብ መመረዙ በምን ምክንያት ሊከሰት እንደቻለ የፓስተር ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው በማቅናት ናሙና እንደወሰዱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው፡፡ በባክቴሪያ የመጣው ወይስ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ወንጀል ነው የሚለው እየተጣራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ አማካሪ የሆኑት ኮሎኔል ባሻ ደገፋ ዜናውን አስተባብለዋል፡፡ ‹‹የታመመም የሞተም ሰው የለንም፤›› ብለዋል፡፡

አየር ኃይል በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ የሆነ የለውጥ ፕሮግራም በማካሄድ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡

LEAVE A REPLY