አዲስ አበባ [ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ]
በረራ ከተማ ነች፣ ፊንፊኔም ፍልውሀ፣
አዲሳባ አገር ነች፣ ያእላፍ ጌታ፣ ድሀ።
በረራ ያኔ ድሮ ከተማ፣ ፊኔፊኔ ምጥጥ ሜዳ፣
አዲስ ሰማይ-ቡዋጣጭ እምንበረድ ግድግዳ።
ሰማይና ምድር እንዴት ተወዳድሮ
የሚለን አጅሬ እንኑር በድሮ።
ካሁንዋ አዲሳባ አሁን ቢወዳደር
ፊንፍኔም መስክ ነች፣ በረራም ነው ከተማ።
በረራም የጥንቱ ከተማ፣ ፊንፊኔም ፊንፊኔ
አዲስም አዲስ ነች አስተውል ወገኔ።
የሶስቱ ቦታዎች እንደ ዱባና ቅል
አበቃቀላቸው ነውኮ ለየቅል።
በረራም ፊንፊኔም የት አሉና ዛሬ?
አዲስ ነች ያበበች ሆና ያሁን ፍሬ።
ጎጆና ሳር፣ ጨፌው ያንት የነበር ድሮ፣
ዐታይም ሰልጥኖ፣ ባስፋልት በህንጻ አምሮ?
በሱ የፈሰሰው ምእልፊት ወርቅ፣ ገንዘብ፣
ላንት የዛሬው ምቾት መሆኑን ተገንዘብ።
መልሱልኝም ካልክ የእኔን መንደር፣ ሜዳ
መክፈል ትችላለህ ወርቅ ገንዘብ እዳ?
በነጻ ቢመለስ ያንተ ‘ርሻና መንደር፣
አትፈልግም ወይ ባዲስ ውለህ ማደር?
ሰፍታ ባማረችው፣ በዘመነችዋ ውብ አዲስአበባ
እመንደርህ ቀርተህ ውስጥዋም አትገባ?
ይልቅ አቅል ገዝተህ ኑር ከወገኖችህ ጋር
አይበጅም ለብቻ ለመኖር ያለ አጋር።
ሁሉም ያገር ሰው ነው ባለቤትዋ ያዲስ
የግሌ ናት ማለት ይቅር ፈጽሞ ከእንግዲስ።
03/03/2019