ከ300 በላይ የሺሻ ዕቃዎች ተወገዱ

ከ300 በላይ የሺሻ ዕቃዎች ተወገዱ

በአዲስ አበባ – ኢቢሲ | ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በወረዳ 09 ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ከ300 በላይ የሺሻ ዕቃዎች መወገዳቸውን የወረዳው ቢሮ ኃላፊ ኢንስፔክተር ገብረሚካኤል ወልደጊዮርጊስ አስታውቀዋል።

ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት በተወሰደው እርምጃም የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎች፣ ዕፅ፣ እንዲሁም ጫት በወረዳው በሚገኝ ገላጣ ስፍራ ላይ በጥንቃቄ መወገዱ ተገልጿል፡፡

በወረዳው በስፋት የሚስተዋለው አዋኪ ድርጊት፣ ሺሻ ማስጨስና ጫት ማስቃም መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፤ በተለያየ ጊዜያት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ቢሞከርም፤ ግለሰቦች ቤት በሚያከራዩበት ወቅት ተከራዩ ለምን ዓላማ እንደሚያውለው አለማጣራት ይስተዋላል ብለዋል። የወረዳው ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ኃላፊ የሆኑት ዋና ሳጂን ታሪኩ በበኩላቸው በርካታ ጊዜ በወረዳው የተለያዩ ወንጀሎች ከተሠሩ በኃላ ሺሻ ቤቶቹ መደበቂያ ይሆናሉ ብለዋል።

እነዚህ ቤቶች ወንጀለኞች መሸሸጊያ ከመሆናቸውም በላይ ዕፁን ከተጠቀሙም በኃላም በተለያዩ ወንጀሎች ላይ ሲሳተፉ እንደሚስተዋልም ተገልጿል፡፡ ህብረተሰቡም ለራሳቸው ልጆችና ነገ ሃገር ተረካቢ ለሆነው ትውልድ በማሰብ ይህን አዋኪ ድርጊት ከፀጥታ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ እንዲከላከል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ኃላፊ ሻምበል ተክላይ አረጋዊም እንደሚሉት በክፍለ ከተማው ውስጥ ከሚገኙት ወረዳዎች መካከል ሺሻና ጫት ቤት በስፋት የሚስተዋልበት ወረዳ 09 አንዱ እንደሆነ ተናግረው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ለ3ተኛ ጊዜ እያስወገደ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እየተካሄደ እንደሚገኝ አክለው ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፦ የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የሕዝብ ግንኝነት ዳይሬክቶሬት

LEAVE A REPLY