‹‹አዲስ አበባ የሁላችንም የሆነች የጋራ መዲናችን ናት። ዘረኝነትንና ጨካኝ/አግላይ የዘውገኝነትን አሰላለፍን መታገል የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
‹‹የአዲስ አበባ ዕድገት ማንንም ሳይጋፋና ማንንም ሳይጎዳ ሁሉንም ሊጠቅም በሚችል መልኩ መሆን ይገባዋል፡፡ በከተማዋ ማደግና መስፋፋት ምክንያት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎችን በዝርዝር አጥንቶ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ በከተማዋ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች ሕዝቡን ባሳተፈ ሁኔታ ሕግን መሠረት አድርጎ በቀጣይ በውይይት መፈታት አለባቸው››፡፡
‹‹የተሳሳቱ አዝማሚያዎችንና የጥርጣሬ ምንጮችን ከስር ነቅሎ ለማስወገድ፣ ‹እኔ ያልኩት ካልሆነ› የሚሉ ግትር አቋሞችንና #ብልጣብልጥ የፖለቲካ አካሄዶችን መግራትና ማረም ለውጡ የሚጠይቃቸው ጉዳዮች ናቸው››።
‹‹አንዳንዱ ዘመኑን በግሉ ቁመት ልክ ሰፍቶ ሲጎድል ግጭት ጠማቂ፣ ሲሞላ መፍትሔ አፍላቂ ሆኖ የለውጥ አባወራነቱን ለብቻው ተከናንቧል፡፡››
‹‹በዘመናችን የተፈጠሩ ችግሮችን አሟልተን ሳንፈታ ነበሩ በምንላቸው የኋላ ችግሮቻችን ላይ ታጥረን መሳሳባችን ለአዲሱ ትውልድና ለተቀረው ዓለም የሚያስተላልፈው መልዕክት እጅግ አሳፋሪ ነው››።
‹‹የአማራ ሕዝብ ሲሻው ድንጋዩን አናግሮ፣ ሲሻው ዋሻ ፈልፍሎ፣ ሲሻው ድንጋይ ጠርቦ በዓለማቀፍ ደረጃ እስከዛሬ የሚደነቁትን የኪነ-ሕንጻ በረከቶች የታሪክ ከፍታው ማሳያ አብነቶች ናቸው። በአንጻሩ የዘመኑ የፖለቲካ ገበያ በሚያስተናግዳቸው እኩይ ውላጅ አስተሳሰቦችና ስንኩል ትርክቶች ምክንያት በተደጋጋሚ የሚደርስበትን የከረረ ሥነ-ልቦናዊ ድቁሳት ‹ሁሉም ያልፋል፤ ነገም ሌላ ቀን ነው› በሚል ቀና የአስተሳሰብ ስሪት ውስጥ ሆኖ መራር ጊዜያትን በትዕግስት ያለፈ አስተዋይ ሕዝብ ነው››፡፡
‹‹በዘመን ሰንሰለት የአማራ ሕዝብ ከሌሎች እህቶቹ ወንድሞቹ ጋር በመሆን በሀገር ኅልውና ግንባታ ሂደት በሰላም ጊዜ የልማት አቅም፣ በጦርነት ጊዜ ደግሞ ከወታደር ከፍ ያለ የአርበኝነት ታሪክ ሲሰራ የቆየ ሕዝብ መሆኑንም ተናግረዋል››፡፡
‹‹የአማራ ሕዝብ ክፉና ደጉን አልፎ ከደረሰበት የለውጥ ምዕራፍ ተስፋው እንዲከስም፣ ሰላሙ እንዲጠፋ፣ ዕድገቱ እንዲኮላሽ እንዲሁም የግጭት አምባ ሆኖ እንዲዘልቅ የጥፋት ድግሶች በተለያዬ መልክ የሚቀርቡለት ቢሆንም እንደ ስሜን ተራሮች ከፍ ብሎ፣ እንደ ዓባይና ጣና ረጋ ብሎ፣ እንደ ላስታ አለት ፅኑ ሆኖ ከሚመጥነው ጋር ታግሎ የሚመጥን ውጤት እያስመዘገበ መጓዝ ይጠበቅበታል››፡፡
.
‹‹የትግላችን ከፍታ የሚለካው በትንንሽ ተግባራት፣ በጊዜያዊ ብሶቶችና ስሜቶች ሳይሆን በመርህ ላይ ቆመን የክልላችንና የሀገራችንን ክብር ለማስጠበቅ የሚያስችለን የአሸናፊነት እርካብ ላይ በመውጣት ነው››።
‹‹በማይጠቅሙ አጀንዳዎች ተገፋፍቶና ተገዳድሮ አሸናፊነትን ከመመኘት ይልቅ ለጋራ በሚጥቅሙን ጉዳዮች ዙሪያ ተቃቅፎና ተደጋግፎ ወፍራም ድል የሚሸመትበትን ወርቃማ አጋጣሚ ከወገኖቻችን ጋር እየሮጥን በጋራ ድል እንድንጎናጸፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ዘመኑ የሚጠይቀውን የጋራ ሩጫ በስኬት ለመወጣት በትንንሽ አጀንዳዎች ባለመጠመድ፣ በዕለት ብሶቶች ባለወጠር፣ ባለፈ ታሪክና መውጫ በሌለው መንገድ ባለመቸከል ሁሉም የመፍትሔ አካል ይሁን››።
‹‹በዘመናችን የተፈጠሩ ችግሮችን አሟልተን ሳንፈታ ‹ነበሩ› በምንላቸው የኋላ ችግሮቻችን ላይ ታጥረን መሳሳባችን ለአዲሱ ትውልድና ለተቀረው ዓለም የሚያስተላልፈው መልዕክት እጅግ አሳፋሪ ነው››፡፡
‹‹ዓለም ኋላቀርነትን ብቻ ሳይሆን ወደኋላ መቅረትን ፈጽሞ በማይፈቀድበት አስተሳሰብ እየተመራ በሚገኝበት ዘመን ላይ ወደፊት አስፈንጥሮ ሊያሳፍረን በሚችለው አስተሳሰብና ተግባር ዙሪያ አጥብቆ መጓዝ ይገባል››፡፡
(ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ንግግር )