የኦቦ ለማ የኋላ ማርሽና የጃዋራዊያን አቧራ | ሳምሶን አስፋው

የኦቦ ለማ የኋላ ማርሽና የጃዋራዊያን አቧራ | ሳምሶን አስፋው

| ቋጠሮ | “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” በሚለው መሪ ቃል ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ከውድቀት አፋፍ እንዳዳኑ የተነገረላቸው፤ ገጣሚው የውዳሴ ስንኝ ያሰናኘላቸው ፤ ባለቅኔው ስለጀግንነታቸው የተቃኘላቸው፤ አቀንቃኙ “አንድ ሰው ተገኝ” እያለ ያቀነቀነላቸው፤ ሽማግሌው “አንተን ያየ ቡዳ አይኑ ይፍሰስ!” ብሎ እንቱፍ እንቱፍ ብሎ የመረቃቸው፤ ታሪክ አዋቂው “ኢትዮጵያዊው ሙሴ” ሲል የክብር ስያሜ የሰጣቸው ኦቦ ለማ መገርሳ፦ ከዚህ ሁሉ ክብርና ሞገስ በኋላ ማርሽ ቀይረው በዘር ጣራ ስር ማደራቸው መላውን ኢትዮጵያዊ እያነጋገረ ነው።

ሰሞኑን በኦሮሞኛ የተናገሩትና በአማርኛ ተተርጉሞ የቀረበው ነገር ምንም አይነት ማስተባበያ ሊሰጥበት የሚችል አልሆነም። ምንም አይነት ወጌሻም ሊጠግነው አልቻለም። ኦቦ ለማ በግልጽ የተናገሩት እያደረጉ ያሉትን በመሆኑ ምን ለማለት ፈልገው ነው?  በሚል ከሃሳብ መፋለስም ሆነ ከትርጉም መዛባት የሚመነጭ ጥያቄ ሊነሳ አይችልም። out of context…” የሚለው የፖለቲከኞች የተለመደው ማስተባበያም  ሊያድናቸው አቅም አልኖረውም።

“ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ” ወይስ “ኢትዮጵያዊነት ሱሚ ነው!”

በ’ርግጥ ኦቦ ለማ የኦሮሚያ ርዕሰ-መስተዳድር በመሆናቸው ኃላፊነታቸውም በዋናነት የኦሮሞን ሕዝብ ማገልገል ነው። በመሆኑም ለኦሮሞ ህዝብ ምን ሰሩ? የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው ለኦሮሞ ህዝብ የሰሩትን በዝርዝር ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ያደረጉትም ይህንኑ ነው። ይህ መሆኑ ማንንም አያስከፋም። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የጋራ ነች ለምንል ዜጎች ከሶማሌ የተፈናቀሉት 500 ሺህ የኦሮሞ ተወላጆች በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሌላውም የኢትዮጵያ መሬት መስፈራቸውን በመርህ ደረጃ የምንቃወመው አይደለም ። ተቃውሞው የተለኮሰው ወይም ውዝግቡን የቀሰቀሰው! የሰፈራው እንቅስቃሴ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ያለመ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ብሄር በከተማ ፖለቲካ የበላይነት እንዲኖረው በእቅድ የተሰራና እየተሰራ መሆኑን በኦቦ ለማ አንደበት በግልጽ መነገሩ ነው። የተቃውሞ ምክንያት ! ኦሮሞውን ለማስፈር ሌላውን ብሄር ማፈናቀሉ ላይ ነው።(የለገጣፎን ማፈናቀል ልብ ይሏል)።

ይህ ብቻ አይደለም ፦

·         በቅርቡ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት አንዱ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ ከኦቦ ለማ ንግግርም አልፈው በመሄድ  ጠ/ሚ አቢይም ለማ መገርሳም ሆኑ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኩማ እየሰሩ ያሉት የኦሮሚያን ጥቅም ለማስጠበቅ በመሆኑ ልንደግፋቸው ይገባል በማለት ለኦሮሞ ተወላጆች  በኦሮሞኛ በገሃድ ሲናገሩ መደመጣቸው፤

·         ጃዋር አህመድ በትዕቢት ስሜት ተወጥሮ የኮንድሚኒየሙን ዕጣ መውጣት በመቃወም ዘር ከዘር የሚያጋጭ አደገኛ ቅስቀሳ ማድረጉ፤

·         ይህንኑ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል የጃዋርን ሃሳብ በመደገፍ የኮንድሚኒየሙ ዕጣ ክፍፍል እንዲቆም የሚጠይቅ መግለጫ ማውጣቱ ፤

·         የክልሉ ፕ/ት ለማ መገርሳ አሜሪካ ሜኒሶታ ተጉዘው የፌዴራል መንግስት ባለስልጣን ብቻ ሊፈጽመው የሚገባውን የቆንስላ ጽ/ቤት መመረቃቸውና የሌሎችም ያልተጠቀሱ ተግባራት ጠቅላላ ድምር ውጤት፦ ኦቦ ለማ መገርሳ የሚመሩት የኦሮሚያ መንግስት በጃዋራዊያን መጠለፉን የሚጠቁም ሆኗል።

እናም በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት የሚከናወኑትን እነኚህን አይን ያወጡ የ “ተረኛ ነን” እንቅስቃሴዎች የተመለከተው ኢትዮጵያዊ ዜጋ፤ “ቲም ለማ”  በሚል የለውጡ ቡድን በስማቸው የተሰየመላቸው ኦቦ ለማ መገርሳ ከ10 ወራት በፊት  “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ” ወይስ “ኢትዮጵያዊነት ሱሚ ነው!” ያሉት ብሎ ቢጠይቅ አይፈረድበትም። የለውጡ መሪ ነበሩና የሳቸው ቀኝ ኋላ ዞሮ መገኘት ለውጡ ተቀለበሰ የሚል ስሜት ቢፈጥር የሚያስገርም አይሆንም።

ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር፡፡

እዚህ ላይ ነፍሱን በአጸደ ገነት ያስቀምጣትና ከታዋቂው ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረ-ዮሐንስ (ገሞራው) በርካታ የብእዕር ትሩፋቶች አንዷን ልዋሰው ወደድኩ፦

ያሰብከው ዓላማ አልሆን ብሎ ሲከሽፍ መንገዱሲጠጥር ፡
ጠጣሩ እንዲላላ በረገበው በኩል የላላውንወጥር፡

ኃይሉ ከዘመናት በፊት የቋጠራት ስንኝ ዘመን የማይሽረው ምክር ይዛለች። ይህችን ምክር ኢትዮጵያዊው ሁሉ ሊጠቀምባት ይገባ ይመስለኛል። ለ27 ዓመታት በጎሳ ፖለቲካ ተወጥሮ የነበረውን የኢትዮጵያ ሰማይ ለማላላት የላላውን ኢትዮጵያዊነት መወጠር ግድ ይላል። “ቲሚ ለማ” በሚል የወል ስም ይጠራ የነበረው የለውጥ ኃይልም የተጠቀመው ይህንኑ የሃይሉ ጎሞራውን ምክር እንደ ነበር ልብ ይሏል። የለውጥ ኃይሉ ለ27 ዓመታት የጠጠረውን የጎሳ ፖለቲካ ያላሉት ለ27 ዓመታት ላልቶ የቆየውን ኢትዮጵያዊነት በመወጠር ነው፡፤ እነ ጃዋር ደግሞ በተቃራኒው ባለፉት 10 ወራት እየተወጠረ ያለውን ኢትዮጵያዊነት ለማላላት እየላላ ያለውን ጎሰኝነት መወጠር ግድ እያላቸው እንደሆነ እያየን ነው ።

የኦቦ ለማ የኋላ ማርሽና የጃዋራዊያን አቧራ

ኦቦ ለማ በጃዋር አቧራ እይታቸው መጋረዱ በለውጡ የፈነደቀውን(የተደመረውን) አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ማሳዘኑ እውነት ነው። ይሁንና ኦቦ ለማ ከመጀመሪያውም የተደበቀ አላማ ይዘው የሰሩት የፖለቲካ ድራማ ነው ብሎ ለመቀበል ህሊናዬ አልፈቀደም። ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትን አድምቀው የተነሱት የአቢይና የለማ እንቅስቃሴ ያስፈራቸው ጸረ-ኢትዮጵያ የሆኑት ጽንፈኞች አቢይና ለማ 5000 የኦሮሞ ወጣት የተሰዋበትን ድል ለሌሎች አሳልፈው ሊሰጡ ነው በሚል በኦሮሞ ህዝብ ውስጥ ዘልቀው ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ይህ በቄሮ መከታነት ያካሄዱት ማስፈራራት የታከለበት ቅስቀሳ የክልል መንግስቱን ተቆጣጥሮ አቦ ለማንም እጅ መጠምዘዝ በመቻሉ አገራዊ ራዕይ ይዘው የተነሱት ኦቦ ለማ ከግዜ በኋላ የኋላ ማርሽ አሰገብተው ለኦሮሞ የበላይነት መንቀሳቀሳቸውን አውቀናል። ኦቦ ለማ ከጅምሩም በኢትዮጵያዊነት ሽፋን የኦሮሞን ብሄር የበላይነት ለማስፈን እየሰሩ ነበር የሚለውን አተያይ ልቀበለው ያልቻልኩት፤ እንደተባለው የፖለቲካ ድራማ እየሰሩ ቢሆን ኖሮ አሁን የተናገሩትም ነገር በአደባባይ ወጥተው መናገራቸው የሚያስከትለውንም ችግር ለመገንዘብ እንደማያዳግታቸው ካለኝ እምነት ነው። ተንኮል ካለ ጥንቃቄም አለና እንዲህ አይነት ተራ ስህተት ሊሰራ አይችልም።

ያም ሆነ ይህ አቦ ለማ “ለኦሮሞ ህዝብ ምን አደረክ?” ለሚለው ጥያቄ የሰጡት መልስ ክብርና ሞገስን ካስገኘላቸው ማንነታቸው ጋር መጋጨቱ የፖለቲካ ህይወታቸው ጥቁር ነጥብ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ይሁንና የኦቦ ለማ ስብራት የሚፈጥርባቸው ስሜት ወደ ካፈርኩ አይመልሰኝ ደረጃ እንዳይሸጋገር ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ሃሳቡን በጨዋ መልክ ከመግለጽ ባለፈ አላስፈላጊ መቧጠጦች ውስጥ ከመግባት መቆጠብ አለበት።  ስሜታዊ ሆኖ ሃይለ ቃል መለዋወጥ በራሱ ቢቻላቸው የኦሮሞ ተወላጆችን በሙሉ በጎሳ ኮሮጆ ውስጥ ለመክተት ለሚሯሯጡት ለነጀዋር እኩይ አላማ ተጨማሪ ጉልበት መሆን ነው።

ጠ/ሚ አቢይና ኦቦ ለማ በተለያየ ገጽ ላይ  ..

እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ እጅና ጓንት ሆነው እንደሚሰሩ የምናውቃቸው፤ አንዱ ለአንዱ ስልጣኑን እስከመልቀቅ ስለ ደረሰው ጉድኝታቸው የተመሰከረላቸው አቢይና ለማ፤ ሰሞኑን በአንድ ገጽ ላይ ያሉ አይመስሉም።  ጀርባ ለመሰጣጠታቸው መረጃም ሆነ ማስረጃ ባይኖረኝም፤ እንደቀድሞው እጅና ጓንት ናቸው ለማለት የማያስደፍሩ ምልክቶች ግን እያየሁ ነው።

ኦቦ ለማ የኦሮሞ ሕዝብ መሪ በመሆናቸው ከዶክተር አቢይ በበለጠ በአክራሪዎቹ በነጀዋር ጫናና ተጽእኖ መወጠራቸው እውነት ነው። ዶክተር አቢይም በዜግነት ፖለቲካ አራማጆችና በጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ፍጥጫ መወጠራቸው ዕውነት ነው። የጠ/ሚ አቢይ ወንበር ከክልላቸው ራቅ ያለ በመሆኑ የኦሮሞ አክራሪዎች እንደ ኦቦ ለማ በቅርብ እርቀት አግኝተው እጅ ጥምዘዛ ሊያደርጉባቸው አይችሉም። ሊያደርጉ ቢሞክሩም ጠ/ሚ አቢይ የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ በመሆናቸው የአክራሪ ኦሮሞዎች ማስፈራሪያ ወንበራቸውን የመነቅነቅ ቅጽበታዊ ጉልበት ሊያገኝ አይችልም ።

በዛው አንጻር ዶክተር አቢይም ምንም እንኳ የኦዴፓ ሊቀመንበር ቢሆኑም ድርጅታቸው ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ማሳረፍ እየቻሉ አይመስሉም። ለዚህ አባባሌ መገለጫ የማደርገው የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ጃዋርን ደግፎ መግለጫ በማውጣቱና ጠ/ሚ አቢይ ደግሞ የጃዋራዊያንን እንጣጥ እንጣጥ በጥብቅ በማውገዛቸው መካከል ያለውን የአቋም ልዩነት ነው ። ይህ ልዩነት በጠ/ሚ አቢይና በኦቦ ለማ ወቅታዊ አቋም ላይም እንደ ልዩነት ሊጠቀስ የሚችል ነው። ጠ/ሚ አቢይ በቅርቡ በማርች 8 የሴቶች ቀን አከባበር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ” የበጥባጮች ድምጽ ጎልቶ የሚሰማው አብዛኛው ህዝብ ዝም ስለሚል ነው! ኢትዮጵያ ግደሉ! የሚሉ አጥፊዎች እንጂ ጀግና የላትም!” የሚል የጃዋሪያንን ሰሞነኛ ድንፋታ ሸንቆጥ ያደረገ ወቀሳ አዘል መልእክት አስተላልፈዋል።

ከዚህ በተያያዘ የኦዴፓ አመራሮች ጠ/ሚ ዓቢይን  ጨምሮ የኦሮሞን የበላይነት እውን ለማድረግ ያቀደ “የተረኛ ነን” ድብቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ ናቸው የሚል አመለካከት እየተንሸራሸረ እንደሆነ አስተውያለሁ። በኔ እምነት ይህ አመለካከት ጫፍ የረገጠ ይመስለኛል። ቢያንስ ቢያንስ ጠ/ሚ አቢይ እስካሁን ያመኑበትን ተናግረው የተናገሩትንም እያደረጉ መሆናቸውን እንጂ የሴራ ፖለቲካ አራማጅ ስለመሆናቸው ምንም መረጃም ሆነ ማስረጃ መጥቀስ አይቻልም። ዶ/ር አቢይ ሊወቀሱበት ከቻሉም የሚወቀሱት መጠን ባለፈው ትዕግስታቸው እንጂ ለአንድ ዘር የበላይነት በመስራት አይደለም።  

በተቃራኒው ኦቦ ለማ በአክራሪው ቡድን እየተጠለፉ መሆናቸውን ስናስተውል በአሁኑ ወቅት ሁለቱ መሪዎች አንድ ገጽ ላይ አለመሆናቸውን ልንጠረጥር ግድ ይለናል፡፤ ሌላው ቢቀር አቢይና ለማ በጃዋራዊያን ላይ በወሰዱት አቋም ተለያይተዋል። በርግጥ አቦ ለማ ጀዋራዊያንን በቀጥታ የደገፉበትን አጋጣሚ መጥቀስ ባልችልም የኦሮሚያ መንግስት ጃዋርን በመደገፍ ያወጣው መግለጫ የለማን ይሁኔታ ሳያገኝ ሊወጣ አይችልምና አቦ ለማ ከጃዋር ጎን እንጂ በተቃርኖ አለመቆማቸውን ያመላክታል።

ይህ አስተያየት በፌዴራል መንግስቱና በኦሮሚያ መንግስት መካከል ያለውን የግንኙነት መስተጋብር ታሳቢ አድርጎ የተሰጠ አስተያየት ቢሆንም ፌዴራል መንግስቱን የሚመራው ኢህአዴግ ፤ ኦሮሚያን የሚመራው ደግሞ ኦዴፓ ነውና በድርጅቶቹም ውስጥ የሚኖረው የኃይል አሰላለፍና መስተጋብር ከዚህ ይለያል ተብሎ አይታሰብም።

እውነተኛ ሽብርተኛ ሲገኝ የጸረ-ሽብር አዋጁ የት ጠፋ!

ሽብርተኛ በሌለበት ምድር ጋዜጠኛውን፤ ሰላማዊ ታጋዩን፤ የሃይማኖት መሪውን፤ ብቻ ሁሉን ሁሉን ሽብርተኛ እያለ ሲፈርጅና፤ ሲያስፈርጅ፤ ሲከስና ሲያስፈርድ የነበረው ጸረ ሽብር አዋጅ ዛሬ ጃዋርን የመሰለ ትክክለኛ ሽብርተኛ ሲገኝ አዋጁ ራሱ በተራው መጥፋቱ “አልጋው ሲገኝ ባሉ አይገኝ..” እንዳለቺው…ሆኗል።

ዛሬ እያየነው ካለው ውዝግብና ውጥንቅጥ በመነሳት አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር የምንችል ይመስለኛል፡፤ ህጋዊም ይሁን ፖለቲካዊ እርምጃ ተወስዶ ጃዋርና ጃዋሪያን እየፈጸሙ ካሉት ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ጸብ አጫሪ እንቅስቃሴ ማስቆም ካልተቻለ ወደ ማይበርድ እልቂት መግባታቸን የማይቀር ነው። ከሁሉ በፊት የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እንደ ድርጅት ሃላፊነት ተሰምቶት እወክለዋለሁ የሚለውን የኦሮሞ ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲል ራሱን ከጽንፈኞች ተጽዕኖ አላቆ ለጋራ ሰላም መስራት አለበት ።

ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ የፌዴራል መንግስትም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ቅስቀሳ በሚያደርግ በየትኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን ላይ ተገቢውን የህግ እርምጃ በመውሰድ የህዝብን ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ አለበት ።

የኦሮሞ ህዝብም ከሌላው ወገኑ ጋር በሰላም አብሮ እንዳይኖር እንቅፋት እየሆኑ ያሉትን አጥፊዎች ሊያወግዝ ይገባዋል። እንደ መሳፍንት ዘመን ማንም ማንንም በኃይልና በጉልበት አሸንፎ በሰላም ሊቀመጥ እንደማይችል በተለይ አክራሪዎች ሊገነዘቡ ይገባቸዋል ።በጦርነት ሁሉም ተሸናፊ በመሆኑ ህዝብን ለእልቂት ማሰናዳትም ተሸናፊነት እንጂ ከቶውንም ጀግንነት አይሆንም።  እያልኩ
“ኢትዮጵያ ሰባብረናታል ያሉት ሁሉ እየሰባበረች የኖረች ሃገር ናት!”

በሚለው የፍልስፍናው ምሁር ዶክተር ዳኛቸው ድንቅ ምስክርነት የዛሬውን ጽሁፌን እቋጫለሁ!

ቸር ይግጠመን

LEAVE A REPLY