በርካታ ዘመድ ወዳጆቼ በተፈጠረው ሁኔታ ደንግጣችሁ የደወላችሁልኝ በሙሉ እጅጉን አመሰግናለሁ። በጫና ምክንያትና ማውራት ስላስጠላኝ በርካታ ስልኮችን ባለማንሳቴ ይቅርታ አድርጉልኝ። የሆነው ነገር ቀላል ቢሆንም እልህ ውስጥ የሚያስገባ ነው። አሁንም ቢሆን ለአገሬ ከሰላም፣ ፍትህና ብልጽግና ውጭ ሌላ የምመኘው ነገር የለም። በእኔ እና በዳኒ ላይ የተፈጠረው ነገር ለሰላም ሲባል የተከፈለ ትንሽ ተግባር ነው። Daniel Tefera Sitotaw Reta በህወሓት የሚመራውን ኢህአዴግ በነፍጥ አምበረክካለሁ በማለት ኤርትራ ወርዶ ከ4 ዓመታት አርበኝነት ቆይታ በኋላ ባለፈው መስከረም ወር ወደ እናት አገሩ የገባ ቆራጥ ወንድማችን ነው።
ዳንኤል ወደ ኤርትራ ከመውረዱና የነፍጥ ትግል ከመምረጡ በፊት የተሟላ ኑሮ የሚኖር የሞላለት ያልጎደለበት በላሊበላ ከተማ ቱርጋይድ ነበር። ከውስኪ መጠጥ ይልቅ የጉድጓድ ውሀን፣ ከጮማ ምግብ ይልቅ አሸዋ የበዛበት ምስርን ተመግቤ፣ አሸዋ ለብሼ፣ ድንጋይ ተንተርሼ ነጻነቴን ማግኘት እመርጣለሁ ብሎ ነበር ኤርትራ የገባው። ዳኒ ቆራጥ ነው፣ ዳኒ ቅን እና የማይበገር ነው። የፈላ ጀበና የወረወሩት ጩጨዋች ይህን አሳፋሪ ነገር ያደረጉት ብሩክ እና ዳኒ ላይ ነው።
.
ቅዳሜ እለት በኅብረታችን ምስረታ ላይ የሆነውን ድርጊትና ከዚያ ቀደም ብሎ በእኛ ላይ የተነዛውን መሰረተ ቢስ ፕሮፖጋንዳ ያቀናጀው የአብን ም/ሊቀመንበር ነው። ሌሎች ሰወች ቢኖርም በዋናነት ድርጊቱ እንዲፈጸም ያደረገው እሱ እና የአማራ ክልል የጸጠታ እና የልዩ ኃይል በተዋረድ እስከ ዞን እና ከተማ ድረስ ያለው የጸጥታ መዋቅር ነው። እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም ቃላት እየመረጥኩ ዳር ዳሩን አልሄድም፤ ሀቅ እስከሆነ ድረስ ፊት ለፊት ነው የምናገረው። እነዚህ አካላት እኛን ጠላት እንደሆን አድርገው የውሸት መዐት ለታጣቂ ዘመዶቻችን በመንገር የከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ በሰጠው ስብሰባ ላይ መጠበቅ ሲገባን እኛን ለመግደል ከራያ ፋኖ በሚል ስም ታጣቂወቹ ደሴ እንዲመጡ ተደርጎ ነበር።
.
በእኛና በጉባዔያችን ላይ የተፈጠረው ነገር ከመከሰቱ 45 ደቂቃወች ቀደም ብሎ ለጀነራል አሳምነው ጽጌ ደውየ የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ገልጨላቸዋለሁ <<ቀደም ብለህ ለምን አላሳወቅከኝም>> ብለውኛል። ያ አሳፋሪ ድርጊት ከተፈጸመ በኋላም ወንጀል የፈጸሙ ወምበዴወችን ሊይዛቸው የፈለገ አካል የለም። ጀነራል አሳምነውና ጀነራል ተፈራ ሸንታም አማራ እየተባላችሁ በህወሓት ማጎሪያ ቤት የደረሰባቸው የፈሪ ስድብና እንግልት አጥንቴ ስር ዘልቆ ይሰማኝ ነበር፤ በእናንተና አብረዋቸው በተከሰሱት ሰወች ላይ ወያኔ ያደረሰውን ዘግናኝ ስቃይ በተመለከተ በወቅቱ ያነበብኩት ረጅም ጽሁፍ ይታወሰኛል። በዓይኖቼ እምባ እየወረዱ ያንን በሰው ልጅ ማንም ሊያደርገው የማይፈልገውን የስቃይ መዐት አንብቤያለሁ።
.
በዚያ አስፈሪ ዘመን ስለእናንተና ጓዶቻችሁ ማውራት እንደ ጀግና በሚያስቆጥርበት ጊዜ ከእስር ይፈቱ ዘንድ በተደጋጋሚ ጠይቄያለሁ፣ ጽፌያለሁ። አንዳንድ ጽሁፎችማ ትንቢታዊ እስኪመስሉ ድረስ ከእስር ወጥተው ዛሬ ያላችሁበት ደረጃ እንደምትደርሱ አስቀድመው የሚያትቱ ነበሩ። ከእስር ከወጣችሁ በኋላም አሁን ባላችሁበት ቦታ እንድትሾሙ በተደጋጋሚ ወትውቻለሁ ያልኩትም ሆኗል። ጀነራል አሳምነው አሁን ከተሾምክ በኋላ እንኳን <<ሕይወትህን ለማጥፋት በህወሓት የተመደቡ ሰወች በዙሪያህ አሉ በጥንቃቄ ተከታተላቸው>> ብየ ከመከላከያ ደኅንነት አካባቢ የተገኙ መረጃወችህን ደውየ ያሳወቅኩህ ከአንተ በላይ ለሕዝባችን አለኝታ ነህ ብየ ስለማምን ነው።
.
ይህን ያልኩት እንዲህ ስላደረግኩ አድሎ ያድርጉልኝ ለማለት አይደለም። ነገር ግን መንግስትና ሕዝብ የሰጣችሁን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት በሀገራችሁ ልጆች በእኔና በዳኒ ጥቃት ያደረሱ ወንጀለኞች ተይዘው ለሕግ እንዲቀርቡ እንዲያስደርጉ ነው።
የዛሬ 5 ዓመትም ለምን ትቃወማለህ ተብዬ በህወሃት ደህንነቶች ራሴን እስክስት ተቀጥቅጫለሁ ነገር ግን መንግስት አለ ብየ ስለማላምን ወደ ሕግ እንዲቀርቡ አልጠየቅኩም። አሁን ግን መንግስትም ሕግም አለ ብየ ስለማስብ እየጠየቅኩ ነው። እነዚህ በእኛ ላይ ጥቃት የፈፀሙ ልጆች ማን ማን ናቸው ለሚለው የቪዲዮም የፎቶም የሰው ማስረጃም ሞልቷል። እነዚህ ወንጀለኞች ተይዘው በሕግ ፊት ካልቀረቡ ግን አገርም መንግሰትም እንዳለኝ አልቆጥረውም። ወደ አካባቢየም ተመልሼ ለመምጣት አልችልም ፍላጎቱም የለኝም፤ ባለ ጠመንጃና ባለ ጉልበት ይኑርበት።
አመሰግናለሁ