አገም ጠቀም የበዛበት የጠ/ሚሩ ንግግር እና አመት የሞላው ለውጣችን ያሬድ ኃይለማርያም

አገም ጠቀም የበዛበት የጠ/ሚሩ ንግግር እና አመት የሞላው ለውጣችን ያሬድ ኃይለማርያም

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ከአንዴም ሁለቴ ደግሜ ሰማሁት። ንግግራቸው በርካታ ቁምነገሮችን የያዘ እና በርካታ አገራዊ ጉዳዮችንም የዳሰሰውን ያህል በበርካታ ጉዳዮችም ላይ አገም ጠቀም ያለ አቋም እና አገላለጽ ተስተውሎበታል። በአንዳንዱ ጉዳይ ደግሞ አንድም ሆነ ብለው አለያም ለነገሩ በቂ ትኩረት ካለመስጠት ይመስላል እውነትነት የጎደላቸው እና በማስረጃም ያልተደገፉ ነገሮችን ሲናገሩ ሰምቻለሁ።

በጌዲዮ ተፈናቃዮች እና ርሃብ ዙሪያ፣ በአዲስ አበባ ይገባኛል ጥያቄ ላይ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች በሚል አቋም የያዘውን የህብረተሰብ ክፍል የቃኙበት ሁኔታ፣ በአዲስ አበባ ከሕግ አግባብ ውጪ መታወቂያዎች ስለመታደላቸው፣ በአገሪቱ እየታየ የመጣውን ሥርዓት አልበኝነት እና የመንደር ጉልቤዎች እያሳዩት ስላለው ከሕግ በላይ የመሆን አዝማሚያ፣ የሚመሩት ድርጅታቸው ኦዴፓ ምንም ሳያፍር በአደባባይ ስለገለጸው የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ እና የዲሞግራፊ ጉዳይ፣ ቤታቸው በሕገ ወጥ መንገድ እየፈረሰባቸው ስላለው ወገኖች፣ መፈንቅለ መንግስት በሚል አንሻፈው የገለጹት የአዲስ አበባ ባለአደራ ኮሚቴ ሁኔታ፤ እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ ነገሮችን ያስቀመጡበት መንገድ ሌላውን ሰው አይደለም እራሳቸውም ያመኑበት አይመስልም።

ይህ ሁሉ ችግር ባለበት አገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዜጠኞችን ሲሸሹ ቆይተውም ቢሆን የተነሱላቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ጊዜ ወስደው መመለሳቸው ግዴታቸውም ቢሆን መልካም ጅምር ነውና ይግፉበት። አንዳንዶቹ ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ አግኝተው ቢሆን ኖሮ ሌሎች ችግሮችን ወልደው ብዙ ጥያቄዎችን ባላስነሱ ነበር።

ለማንኛውም ጠቅላዩም ሆኑ የተጀመረው ለውጥ አንድ አመቱን ስለያዘ በመጠኑ ለውጡ ያለበትን ደረጃ መቃኘት እና ወደፊት እንዴት እንቀጥል በሚለው ሃሳብ ዙሪያ መወያያዩ ይበጃል።

– ለውጡ የት ደረሰ?

ይህ ለውጥ የሕዝብ ትግል ውጤት ስለሆነ ባለቤቱም ሕዝብ ነው። ውጤቱ የሰመረ እንዲሆን እና እንዳይደናቀፍ መጠበቅም ያለበት ሕዝቡ ነው። ይህ ለውጥ በተሳካ ሁኔታ ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና ካመራት ሻንፒዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ለውጡ መስመሩን ስቶ የሌሎች አንባገነኖች መፈንጫ ወይም የአክራሪ ብሔረተኞች መጋለቢያ ፈረስ ከሆነም የሚከስረው፣ የሚዋረደው እና አዲስ መከራ የሚጋፈጠው ሕዝብ ነው። በግለሰቦች ግድፈትም ሆነ በመሪዎች ስህተት ለውጡ ችግር እንዳይገጥመሁ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። ዳር ቆሞ መሪዎቹን ማንጓጠጥም ሆነ ስህተታቸውን ብቻ እየነቀፉ ለውጡ ገደል ገብቷል እያሉ ማሟረት ፋይዳ የለውም።

ባለፈው አንድ አመት እጅግ ቀላል ግምት የማይሰጣቸው በርካታ በጎ ሥራዎች ተከናውነዋል። የዛኑ ያህል ብዙ ችግሮቻችን በጥናት ላይ የተመሰረቱ እና ዘላቂ መፍትሔ የሚፈልጉ ስለሆኑ እንዲሁ በግልቢያ እየነካካን ከሚዲያ ፍጆታ ያልዘለሉ ሆነው ታይተዋል። ገና በወፍ በረርም ሆነ በጥናት ደረጃም ያልነካናቸው በርካታ ችግሮች የቀጣዩ አመት ፈተናዎቻችን ሆነው አፍጠው አግጠው ይጠብቁናል።

በተጓዳኝ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች የታየው የእርስ በርስ ግጭት፣ ማፈናቀል እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ሌላ ጥቁር ዳመና እንዲያጠላ አድርጓል። የለውጡ መሪዎች እርስ በርስ መወነጃጀል እና መደናበር፣ የአክራሪ ብሔረተኞች በየአቅጣጫው ተጠናክሮ መውጣት እና ሌሎች ችግሮች ተደማምረው በለውጡ ሂደት ላይ ያለን ምልከታ የደበዘዘ እንዲሆን አድርጎታል።

ቀጣዩ አመት እጅግ ወሳኝ ወቅት ይመስለኛል። መንግስት፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ሚዲያዎች እና ሌሎች የህብረተሰቡ ክፍሎች የምንፈተንበት ወቅት ይመስለኛል። ከዚህ በኋላ የሽግግር ጊዜ ውስጥ ነን የሚለው ማሳበቢያ ብዙም አያራምደንም። ሁላንም እንደዜጋም እንደ ቡድንም የምንፈተሽበት ወቅት ይመስለኛል። ይህን አለም በቁራኛ እየተከታተለ ያለውን የለውጥ ሂደት በጥበብ፣ በእውቀት እና በዲሞክራዊያዊ መንገድ እንወጣዋለን? ወይስ ተደነቃቅፈን እንቀራለን?

– ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የለውጡ መሪዎችስ?

በሕዝብ ንቅናቄ ተገፍቶ የሚመጣ ለውጥ ሁለት አይነት መሪዎችን ሊያፈራ ይችላል። አንደኛው ከመነሻውም የለውጡ እንቅስቃሴ ጠንሳሽ እና አታጋይ የነበረ ሰው የለውጡ መሪ ሆኖ ይቀጥላል። እነ ማንዴላ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው ለዚህ። ሁለተኛው ደግሞ ለውጡ የሚያመጣቸው መሪዎች ይፈጠራሉ። ለዚህም ዶ/ር አብይ ተጠቃሽ ናቸው። ዶ/ር አብይ በሕዝብ ዘንድ የታወቁት በለውጡ ዋዜማ ላይ ነው እንጂ ከዚያ በፊት ሕዝብ አታግለው እና የለውጥ እንቅስቃሴ መሪ ሆነ አይደለም የመጡት።

በሕዝባዊ ንቅናቄ ውስጥ መሪ ወይም ዋና ተዋናይ ሆኖ የመታ ሰው ከመነሻውም የሕዝብ አመኔታን እየገነባ የመጣ ሰው ስለሆነ ለውጡን በሚመራበት ወቅትም ያው አመኔታ አብሮ ይከተለዋል። ሥራውንም ያቀልለታል። ሕዝብን ለማሳመን የሚያጠፋው ጊዜ እና ጉልበት አይኖርም። ሕዝብም ቢሳሳት እንኳ ይታገሰዋል። በጽናትም አብሮት ይቆማል። ሲያስፈልግም ሕይወቱን ጭምር የሰዋለታል።

በለውጥ ማግስት መሪ የሆነ ሰው፤ ሊያውም ሕዝብ ሲታገለው ከነበረ እኩይ ስርዓት ጉያ የወጣሰው የሕዝብን አመኔታ ማግኘት እና ይዞ መቆየት ትልቁ ፈተናው ነው። ሲናገርም፣ ሲራመድም፣ ሲቆምም ሲነሳም የሕዝብ አመኔታ ጉዳይ ያሳስበዋል። ስለዚህ ብዙ ጊዜውን፣ ጉልበቱን እና እውቀቱን የሕዝብን አመኔታ ለማግኘት ያባክናል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በየቀኑ የሚወጡ የእሳቸው የፎቶ ምስሎች እና መግለሻዎች፣ በየሄዱበት የሚሰጡዋቸው መግለጫዎች ውስጥ በአንክሮት ለተከታተለ ሰው ቁልጭ ብሎ ይታያል። ንግግሮቻቸውም ብዙን ጊዜ የሕዝብን አመኔታ ለማግኘት ታሳቢ የተደረጉ መሆናቸውን ብዙ ማስረጃ እያጣቀስኩ ላሳይ እችላለሁ። ይህ አካሄድ በራሱ ስህተት አይደለም። ምክንያቱም በሕዝብ ደም ከጨቀየ፣ በአገር ሃብት ከሞሰነ፣ ብሔራዊ ክብርን ካዋረደ እና ሕዝብን በዘር ከፋፍሎ ሲያባላ ከቆየ ድርጅት ውስጥ የመጣ ሰው አይደለም መላዕክም ቢሆን በሕዝብ ለመታመን የማይቧጥጠው ዳገት የለም። ሕዝብ ካላመነው የዛ መሪም ሆነ የስርዓቱ ግብአተ ተመሬት ቅርብ ነውና።

ትልቁ ችግር የሕዝብ አመኔታ በመጀመሪያ በጥሩ ንግግር ይካባል፤ በጥሩ ስራ በቶሎ ካልተደገፈ ግን እንደ እንቧይ ካብ ይናዳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በያዙ የመጀመሪያው ስድስት ወር እና ከዚያ በኋላ ያለው የስድስት ወር ጊዜ አንድ አይደለም። ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሕዝብ በአገሪቱ ወስጥ በተፈጠሩት በርካታ ችግሮች እና የአብይ አስተዳደር ባሳየው ቸልተኝነት ወይም አቅመ ቢስነት ተስፋ ወደመቁረጥ እና እሳቸውም ላይ መናደድ ጀምሯል። ይህንን እሳቸውም በቅጡ ያጤኑታል የሚል ግምት አለኝ።

በቀጣይ ምን ይሁን?

ከላይ እንደገለጽኩት ይህ ለውጥ በአብይ አስተዳደር ይመራ እንጂ የሕዝብ ለውጥ ነው። በመሆኑም ሁላችንም ለውጡ እንዲቀጥል እና ወደምንፈልጋት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በአፋጣኝ እንድናመራ የየበኩላችንን ማድረግ ይጠበቅብናል።

+ ሁሉም ሰው የለውጡን ሂደት በአይነ ቁራኛ መከታተ ብቻ ሳይሆን የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባል። ለዚህም ፈቃጅ አካል ሊኖርም፤ ልንጠብቅም አይገባም። እኔ ለአገሬ በጎ ነገር ለማድረግ የማንንም ፈቃድ አልጠብቅም።

+ ለውጡን የሚመሩትን አካላት ከለውጡ ነጥሎ ማየት ያስፈልጋል። አብይ ስህተት ሲሰራ ለውጡ የራሱ ጉዳይ ማለት ኢትዮጵያን የራስሽ ጉዳይ ብሎ እንደ መተው ነው። እነዚህን የለውጥ መሪዎች ትክክለኛውን ነገር እንዲሰሩ ማንቃት፣ ማሳሰብ፣ ማስጨነቅ፣ ጫና ማሳደር እና እንደየሁኔታውም በሕግ ጭምር ተጠያዊ እንዲሆኑ ማድረግ እንጂ ለውጡን በዜሮ ማባዛት የሚያከስረው እኛኑ እና ድሃ አገራችንን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፤

+ ስለራሳችን መብት እና ጥቅም ስንሟገት የሌሎችን መብት እና ጥቅም የማክበር ግዴታ እንዳለብን መረዳት ያስፈልጋል። አዲስ አበባ የአንተ አደለችም የእኔ ብቻ ነች የሚለውን አካል እንዲደራጅ እና ሃሳቡም በነጻነት እንዲገልጽ ሲፈቀደ በሌላ አውድ ለቆመው እና አዲስ አበባ የሁላችንም እና የአዲስ አበቤዎች ነች የሚለውም ወገን ሲደራጅ እና ሃሳቡን ሲገልጽ እኩል ሊደመጥ ይገባል።

ቸር እንሰንብት!

LEAVE A REPLY