1. የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 302 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በቅርቡ እንደሚለቀቅ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡ ሪፖርቱን ይፋ የሚያደርገው ትራንስፖርት ሚንስቴር ነው፡፡ ውጤቱ ለአውሮፕላኑ የተገጠመለት ( MCAS )ሶፍትዌር ከካፒቴኑ ቁጥጥር ውጭ አውሮፕላኑ አፍንጫውን ቁልቁል ዘቅዝቆ እንዲከሰከስ እንዳደረገው እንደሚገልጽ ይጠበቃል፡፡ ቦይንግ ኩባንያ ሶፍትዌሩን አሻሽያለሁ ብሏል: በሚዲያ ዘመቻ ራሱን ለመከላከል እየሞከረ ነው፡፡
2. የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልን ሊከስ መሆኑን ካፒታል አስነብቧል፡፡ ለቢትወደድ ባሕሩ ነጋሽ ቤተሰቦች መቃብር ቦታ ለማዘጋጀት ሲባል 25 ጥንታዊ ሀገር በቀል ዛፎች ተቆርጠዋል፡፡ ለዚህም የካቴድራሉ አስተዳደር 17 ሺህ ብር ተከፍሎታል፡፡ እስከ 45 ዐመት ዕድሜ ያላቸው 6 ዝርያ ዛፎች ናቸው የተቆረጡት፡፡ ብሄራዊ ቅርስ በሆኑ ቦታዎች ዛፎችን ያለ መንግሥት ፍቃድ መቁረጥ ባንድ ዛፍ 5 ሺህ ብር መቀጮና 10 ዐመት እስራት ያስቀጣል፡፡
3. በደቡብ ምስራቅና በምስራቅ አርብቶ አደር አካባቢዎች ከጥር እስከ ግንቦት የሚጠበቀው በልግ ዝናብ ባለመጀመሩ ወይም በመዛባቱ ስጋት መፍጠሩን ዐለም ዐቀፉ የረሐብ ቅድመ-ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ጥምረት ገልጧል፡፡ ሙቀት በጣም ጨምሯል፡፡ በቦረናና ጉጂ ዞኖች ከየካቲት አጋማሽ እስከ መጋቢት አጋማሽ መጠነኛ ዝናብ ቢጥልም በቂ አይደለም፡፡ በደቡብ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዝናቡ በ2 ሳምንት ዘግይቶ ነው የጀመረው፡፡ በጠቅላላው በተጠቀሱት ቦታዎች ዝናቡ ከአማካይ በታች ስለሆነ የማሳ ዝግጅትና የአጭር ጊዜ የበልግና የረዥም ጊዜ የመኸር ሰብሎች ዝግጅት ደካማ ነው፡፡
4. መንግሥት የሪፎርም ፕሮግራሞቹን በጥንቃቄ እንዲያቅድ የዐለም ባንክ ከፍተኛ ሃላፊ አሳስበዋል፡፡ የባንኩ የኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ቼይላ ፓዛርባሲዮግሉ ባለፈው ዐርብ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ የመንግሥት ሪፎርም ዕቅዶች ጥሩ ቢሆኑም ቅደም ተከተላቸውን ጠብቆ የመሄዱና የትግበራቸው ነገር ግን በጣም ፈታኝ እንደሚሆን ለሪፖርተር መናገራቸውን ጋዜጣው አስነብቧል፡፡ መንግሥት ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ ለንግድ ልማትና መሰል ጉዳዮች እንቅፋት የሆኑትን ችግሮች ተረድቶ ማስተካከልና ወደ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ማስፋፋት ይገባዋል ማለታቸውም ተጠቅሷል፡፡
5. የኢትዮጵያ ሱማሌ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ) መደበኛ ጉባዔውን ትናንት ጀምሯል፡፡ አዳዲስ የሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ይመረጣሉ፡፡ የፋይናንስ ሚንስትሩ አሕመድ ሸዴ ድጋሚ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው እንደሚመረጡ ይጠበቃል፡፡ እስካሁን የፓርቲው አባል ያልነበሩት ርዕስ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር ደሞ ምክትል እንደሚሆኑ ተገምቷል፡:
6. ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነርነት 89 ዕጩዎች ተጠቁመዋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ዋና ኮሚሽነር አቅራቢ ኮሚቴ የዕጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁን እንዳስታወቁ ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ በመቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ተጨማሪ የሥራ ልምድና ትምህርት ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ ይሰራል፡፡
7. በቢሊዮን የሚገመት የገንዘብ ጉድለት የተገኘባቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ገንዘቡን ባንድ ወር ውስጥ እንዲመልሱ ተነግሯቸዋል፡፡ ቀነ ገደቡን ያስቀመጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የሚመሩት እና የኦዲት ክትትል የሚያደርገው ልዩ ኮሚቴ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕግ በሕግ የሚጠየቁ 190 ተቋማትን ለይቷል፡፡ በቅድሚያ 15 የፌደራል ተቋማትንና 20 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለሕግ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ሸገር ዘግቧል፡፡