“ኢትዮጵያ የከሸፈች ሀገር እየሆነች ነው” ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ || ለቢቢሲ

“ኢትዮጵያ የከሸፈች ሀገር እየሆነች ነው” ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ || ለቢቢሲ

በደርግ ስርዓት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “ኢትዮጵያ በቀውስ አፋፍ ላይ ናት” የሚል ጽሑፍ ፅፈው በተለያዩ ድረ ገፆችና በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ነበር። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሻለቃ ዳዊት የጽሑፋቸው አላማ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ማስረዳት እንደሆነ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ እየወደቀች ነውም ብለዋል።

ሻለቃ ዳዊት፡ የጽሁፌ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ማስረዳት ነው። በሃገሪቱ የሚከናወኑ ብዙ ነገሮች ስላሉ ህዝቡ ተወጥሮ ያለው በዕለት ተዕለት ጉዳዮች ላይ ነው። እነዚህ ሁሉ ግን ተደምረው በጠቅላላ የሃገሪቱ ስእል ምን ይመስላል የሚለውን ለማሳወቅ ነው የፈለግኩት። እናም በደህንነት ረገድ፣ በኢኮኖሚና በአጠቃላይ በአመራር ደረጃ ያለውን ስንመረምረው ጠቅላላ ኢትዮጵያ የከሸፈች ሃገር ( failed state) ወይም ከቁጥጥር ውጪ የሆነች አፍሪካዊ ሃገር እየሆነች ነው። ቁጥሮቹን በሙሉ ጽሁፌ ላይ አስቀምጫለው።

እኔ ያደረግኩት በሜዳ ላይ የሚታዩትን ሃቆች አውጥቶና ስእሉ ሲደመር የኢትዮጵያ አቅጣጫ ምን ይመስላል? የሚለውን ለመመለስ ነው የሞከርኩት። አቅጣጫው አደገኛ አቅጣጫ ነው። አመራሩ አስፈላጊና ከባድ ውሳኔ ካልወሰነ በስተቀር አዘቅት ውስጥ ገብታ ምናልባትም የእርስ በርስ ጦርነት ሊያመጣ የሚችል ሁኔታ ይፈጠራል። ይህንን ለማስቀረት መደረግ ስለላባቸው ነገሮችም ጠቁሜያለው።

ምናልባት መደረግ ያለባቸው ነገሮች አስቸጋሪና ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን በከባድና አስቸጋሪ ጊዜ ከባድና አስቸጋሪ ውሳኔ መወሰን ያስፈልጋል። በእንደዚህ አይነት ጊዜ ያሉ አመራሮችም መጥፎ ሁኔታ ላይ እንዳለን ሲያውቁ መደረግ ያለበት ውሳኔ መራራ ሆኖ፤ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ኢትዮጵያን የሚያድን ይሆናል እንጂ ስለፍቅር በመናገርና ህዝቡን በማባበል፤ ተስፋ በመስጠት ያጋጠመንን ችግር መፍታት አይቻልም ለማለት ነው።

ሃገሪቱ አዲሱ አስተዳደር ከመምጣቱ በፊት ከነበረው የባሰ ሁኔታ ውስጥ ናት ማለት ይቻላል?

ሻለቃ ዳዊት፡ አዎ፤ በጣም እንጂ፤ በትክክል። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን በመፈናቀል ደረጃ የወሰድን እንደሆነ፤ ድሮም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከመምጣታቸው በፊትም ነበረ። አሁን ግን በጠቅላላው በጣም እየባሰ መጥቶ በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ በሚባል ደረጃ ብዙ ሰው የተፈናቀለባት ሃገር ኢትዮጵያ ናት። እስከ አራት ሚሊየን ህዝብ ተፈናቅሏል።

በጠቅላላው ደግሞ የሃገሪቱ የደህንነት ሁኔታ ስንመለከት አንድ ሃገር ውስጥ በነጻነት መንቀሳቀስ የማይቻልበት ሁኔታ ነው ያለው። እንደዚህ አይነት ነገሮች ደግሞ የሚፈጠሩት እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ማዕከላዊ አፍሪካ ባሉ የከሸፉ ሃገራት ነው።

በግለሰብ ደረጃ ስንመለከተው ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በስጋት ነው የሚኖረው። ሲወጣም ሆነ ሲገባ በስጋት ውስጥ ሆኖ ነው። የኢኮኖሚውን ዘርፍ ያየነው እንደሆነ ሌላው ቀርቶ መድሃኒትና ነዳጅ ለመግዛት የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ ብቻ እንጂ ከዚያ ውጪ ባንክ ውስጥ ምንም መጠባበቂያ እንደሌለ ብሔራዊ ባንክ ተናግሯል።

ከዚህ በተጨማሪ አሁን እያስተዋልነው ያለነው መሰዳደብና መዘላለፍ በህዝብ መሃል ያለውን ተቃርኖ እያባባሰው ሄዷል። ይሄ ሁሉ የአመራርና የፖሊሲ ጉዳይ ነው። አመራርና ፖሊሲ እስካልተቀየረ ድረስ ይሄ ሊለወጥ አይችልም። እንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። ሃገሪቱ በእኔ እድሜ በኃይለስላሴም፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ እንደዚህ አይነት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሳ አታውቅም።

ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ይሄ ችግር ከዚህ በፊት ሲጠራቀም የመጣ እንደመሆኑ አሁን እንዴት በጣም አሳሳቢ ሊሆን ይችላል?

ሻለቃ ዳዊት፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣት ጋር ተያይዞ የህዝቡ ችግር የነበረውን አስወግዶ አዲስ ምዕራፍ ለኢትዮጵያ ይከፍታል የሚል እምነት ነበር። ስለዚህ ቃል በተገባው መሰረት የተባለው ነገር ስላልተደረገ ችግሩ ቀስ እያለ መፈንዳት ጀምሯል። ይህ ማለት ግን ችግሩ የአንድ ሰው ጥፋት ነው፤ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ችግር ነው ለማለት ሳይሆን እሳቸው ወደ ስእሉ ሲገቡ ችግሩን አስወገደው ሃገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግራሉ የሚል እምነት ነበረ። ቃል የተገባው ነገር አልተፈጸመም። ባለመደረጉ ደግሞ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል።

እርሶ የጠቀሷቸው ነገሮች በሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ ናቸው የሚሉ ሰዎች አሉ

ሻለቃ ዳዊት፡ አልተሸጋገርንም፤ ለውጥም የለም። ለውጥ ማለት የስርአት ለውጥ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም የጠየቀው የስርአት ለውጥ ነው። እዚህ ችግር ውስጥም የከተተን የነበረው ስርአት ነው። አብዛኛዎቹ ነገሮች እንዳሉ ናቸው። እስከ ዛሬ ድረስ ተቀየሩ የሚባሉት ነገሮች በስርአት አቅጣጫ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በግል በወሰዷቸው እርምጃዎች ነው። ነገር ግን ይሄ ለለውጡ ሁኔታውን ለማመቻቸት ነው እንጂ በራሱ እንደ ለውጥ ልንመለከተው የምንችለው ነገር አይደለም።

እስካሁን ለተፈጠሩት ችግሮች በሙሉ ኢህአዴግን ተጠያቂ ማድረግና ኢትዮጵያ በአዲስ ህገመንግስት አዲስ ምርጫ ውስጥ እንድትገባ ማድረግ ነው ትክክለኛው ለውጥ። ጠቅላዩ በስልጣን ለአንድ ዓመት ቆይተዋል፤ በአንድ ዓመት ውስጥም ምንም ነገር አልታየም።

ይህ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፍኖተ ካርታ ስለሌላቸው ወዴት አቅጣጫ እንደሚኬድ አያውቁትም። ሕገ-መንግሥቱ እንዴት እንደሚሻሻልና ወደ አዲስ ምርጫ እንዴት መሄድ እንደምንችል ትክክለኛ አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚችል ፍኖተ ካርታ ያስፈልገናል።

መሰረታዊ የህግ ለውጦች ካስፈለጉ ሙሉ የህዝብ ውክልና ያለው መንግስት ነው መንግቱን መቀየር ያለበት?

ሻለቃ ዳዊት፡ በአሰራሩ መሰረት ለውጥ የሚመጣው ወይም ሕገ-መንግሥትን የሚፈጥረው መንግሥት ሳይሆን ሕገ-መንግሥቱ ነው ስልጣን ያለው መንግስት መፍጠር የሚችለው። አሁን ለውጡ ይካሄድ ሲባል ባለው ሕገ-መንግሥትና ባለው መንግሥት ለውጥ ሊካሄድ አይችልም። ለውጥ ሊመጣ የሚችለው አዲስ ሕገ-መንግሥትና አዲስ መሰረታዊ ሃሳቦች ተፈጥረው ሲታዩ ነው።

ያለው መንግሥት እንዳለ ሆኖ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። እነዚህን ሁሉ ችግሮች የፈጠረው ጠቅላዩ የሚመሩት ኢህአዴግ ነው። ምናልባት እሳቸው በቀጥታ ላይመለከታቸው ይችላል፤ ነገር ግን ፓርቲው ለብዙ ነገር ተጠያቂ ነው። ስለዚህ ሕገ-መንግሥቱ ፈርሶና አዲስ መንግሥት መጥቶ ነው ለውጥ ልንመለከት የምንችለው።

ሁሉንም ሰው የሚያስማማ ነገር ማምጣት ይቻላል? ሕገ-መንግሥቱን ማንሳቱ ወደሌላ ቀውስ አይመራም?

ሻለቃ ዳዊት፡ ቀውስማ አሁንም ተፈጥሯል። ከዚህ የባሰ ቀውስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠር አይችልም። ስለዚህ ዋናው ነገር ለዘለቄታው ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር እንድትኖር ከባድ ውሳኔ መሰጠት አለበት። ዋናው ችግራችን የምንከተለው በዓለም ውስጥ የሌለ የብሄር ፌደራሊዝም ነው። ይህ ስርአት በዓለም የለም፤ በአፍሪካም የለም። ትንሽ ተቀራራቢ አሰራር ያለው ኮሞሮስና ናይጄሪያ ውስጥ ነው። እሱም ቢሆን በዋነኛነት በዘር ላይ የተመሰረተ አይደለም።

የብሄር ፌደራሊዝሙም ቢሆን ህዝቡን አማክሮ አወያይቶ አልነበረም ተግባራዊ የተደረገው። ሕገ-መንግሥቱን ሲያረቅቁት ትልቅ ስህተት ተሰርቷል። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ራሳቸው ተሳስተናል፤ ህዝቡን አላማከርነውም ነበር ብለዋል። እኔ እያልኩ ያለሁት ህዝቡ በደንብ ይመከርበትና አዲስ ሕገ-መንግሥት ይፈጠር ነው።

ይህንን የብሄር ፌደራሊዝም ይዘን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ይመጣል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ሰላም አለመገኘት ብቻ ሳይሆን እልቂት ይፈጠራል፤ ምንም ጥርጥር የለውም።

አሁን እየጠቀሱት ላለው ችግር መፍትሄው ምንድነው ይላሉ?

ሻለቃ ዳዊት፡ መፍትሄው በቀላሉ የሚገኝ ነገር አይደለም። የደፋር እርምጃ ያስፈልጋል። በእንደዚህ አይነት የችግር ጊዜያት የሚመጡ ብዙ መሪዎች ጠንካራ ውሳኔ መወሰን መቻል አለባቸው። ቀላል ነገር ቢሆን ኖሮ ማንም ሰው ያደርገው ነበረ።

በጽሑፌ ላይ ለመጠጥቀስ እንደሞከርኩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካልቻሉ፤ አልቻልኩም ብለው ከስልጣን ይልቀቁና አማራ ወይንም ኦሮሞ ያልሆነ ሰው ስልጣኑን ይረከብ። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ያለው ችግር በአማራና በኦሮሞ መካከል ያለው ፉክክርና በሁሉም ዘርፍ ያለው ሽሚያ ነው።

ወደ ሽግግር ሊያመጣን የሚችል መሪ ያስፈልገናል። ሁለተኛ ያለን አማራጭ ደግሞ፤ እሺ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቆዩ የሚባል ከሆነ ሕገ-መንግሥቱ ፈርሶና የኢህአዴግ ፓርላማ ተበትኖ እሳቸው በአዋጅ አሸጋጋሪ ሆነው የሃገሪቱን አጀንዳ ይዘው መሄድ አለባቸው።

አሁን ችግር የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበርም ናቸው። ሁለቱ አብሮ ሊሄድ አይችልም። መምረጥ መቻል አለባቸው። ወይ የኢትዮጵያ መሪ አልያም የኦሮሞ መሪ መሆን አለባቸው። የሁለቱም መሪ ሊሆኑ አይችሉም።

የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም አስጠብቃለሁ እያሉ የኢትዮጵያውያንን ጥቅምም አስጠብቃለሁ ማለት አይችሉም። በሌሎች ሃገራት እኮ ሙሉ ሃገሪቱን የሚወክል ፓርቲ ነው ያለው። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ይዘው፤ ከዘረኛ ፖለቲካ ወጥተው መምራትና ማሸጋገር ይችላሉ። ግን ይሄንን ለማድረግ ሕገ-መንግሥቱ መፍረስ አለበት።

የዘር ድርጅቶች የሲቪክ ድርጅቶች ሆነው የህዝቦቻቸውን መብቶች የሚያስጠብቁበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። የፖለቲካ ድርጅቶች መሆን አይችሉም የሚል ህግ መውጣት አለበት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እየሰሩ እንደሆነ አያምኑም?

ሻለቃ ዳዊት፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ናቸው። ስለዚህ ፓርቲያቸው የሚፈልገውን ነገር መፈጸም አለባቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያውያንን አጀንዳ መያዝ አለባቸው፤ ይሄ ደግሞ ይጋጫል። አሁን የምናያቸው ችግሮች ሁሉ የተፈጠሩት በሁለቱ ሃላፊነቶች መጋጨት ምክንያት ነው።

ይህንን ጠንካራ ውሳኔ ለመወሰን ብዙ ሥራና መነጋገር ይጠይቃል። የኢትዮጵያን አጀንዳ ይዞ በየሃገሩና በየክፍለሃገሩ መናገርና ሰዉን ማሳመን መቻል አለባቸው። መጀመሪያ ላይ እኮ ህዝቡ ከፈጣሪ በታች አድርጎ የተቀበላቸው ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ይዘው በመምጣቻው ነበር። አሁን ግን እሳቸው የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ህዝብንና የኦዴፓን ጥያቄ ይዘው ነው የመጡት።

LEAVE A REPLY