” በተለይ ገደላገደሉና ተራራው ሲቃጠል ቆሞ ከማየት በቀር ምንም ማድረግ አልቻልንም። እሳቱን ምንም ሊያስቆመው አልቻለም። ፈጣሪ ዝናብ ከሰማይ ካላወረደ ምንም ምን ማድረግ ይቻላል? ጭራሽ አሁንማ ጫካውን እየጨረሰ ወደ ቆላማው የአርሶ አደሩ ቀየ እየተጠጋ ነው። ቤትና ማሳውን ሁሉ ሊያቃጥል ይችላል። ምን አልባት ለሰው ተደራሽ የሆኑ ደልዳላ አካባቢዎችን ማትረፍ ከቻልን ብለን ዛሬ በደባርቅና አክልባቢው የእሳት ማጥፋት “የክተት ዘመቻ” አውጀናል። ብቸኛ መፍትሔው በሄሊኮፍተር ማጥፋት ቢሆንም መንግሥት ምንም እያለ ባለመሆኑ ሕዝቡ በዘመቻ ነቅሎ እየወጣ ነው።”
(የሰሜን ጎንደር ዞን እና የደባርቅ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ዛሬ ሚያዝያ 2/2912 ዓ/ም ጧት ያደረሱን መረጃ)
…
የግርጌ ማስታወሻ፦
(፩) ፓርኩ የሚተዳደረው በፌዴራል መንግሥት ነው።
(፪) ኢትዮጵያ የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፍተር የላትም። ከሌሎች ሀገራት ለመከራየት ከባለፈው ቃጠሎ ጀምሮ በፌዴራል መንግሥት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ቢታወቅም ምላሹ እስካሁን አልታወቀም።
(፫) የክልሉ መንግሥት ልዩ ኃይል ከማሰማራት ጀምሮ የሚችለውን እያደረገ ነው። የሰሜን ጎንደር ዞንና የደባርቅ ወረዳ አስተዳደር ከሕዝቡ ጋር እየደከመ ነው። የዞኑና የወረዳው ፓርኮች ጽ/ቤትም የቻሉትን እየደከሙ ቢሆንም እሳቱ ከሰው አቅም በላይ በመሆኑ አስቸጋሪ አድርጎታል።
(በሰው ኃይል የሚቻሉ አማራጮች ሁሉ እየተሞከሩ ቢሆንም ሰው ሊደርስበት በማይችለው ገደላደል የተዛመተው እሳት በነፋስ እየታገዘ በፍጥነት በመዛመት ላይ ነው። ዙሪያውን በመቆፈርም ሆነ በመመንጠር ለማስቆም የሚቻለው ሰው ሊደርስበት በሚችል ቦታ ብቻ ነውና።)
…
.
ምን ማድረግ ይችላሉ?
– በአካል ወደ ሰሜን ተራሮች በመሄድ እሳት ለማጥፋት መረባረብ፤
– እሳቱን ለማጥፋት የሚያግዙ ቁሳቁሶችን ማቅረብ፤
– እሳት በማጥፋት ላይ ለሚገኙ ወጣቶች የምግብና ውኃ ማቅረብ፤
– ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ፓርኩ በመሄድ በጉልበት ፓርኩን ከአደጋ ለመታደግ ለሚንቀሳቀሱ በጎ ፈቃደኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ማቅረብ፤
– ፓርኩ ከተጋረጠበት አደጋ በመታደግ ለወደፊቱም በቋሚነት ደህንነቱን ለመጠበቅ የሚያስችል ድጋፍ ማድረግ፤
– በማኅበራዊ ሚዲያዎች ፓርኩ እየደረሰበት ያለውን ውድመት በማጋራት ዓለም አቀፍ የአካባቢ ተቆርቋሪዎችን ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ፤
የሚችሉትን ሁሉ ያድርጉ፡፡