የቃሊቲውን ከፍተኛ ጥበቃ የፌዴራል ማረሚያ ቤት በዚህ ሳምንት እንደታዘብኩት፣
በህግ ስም አገዛዙ በተለይ በወንጀል ጉዳዮች በሚፈጽማቸው ግፎች ተማርሬ የወንጀል ጉዳዮችን መያዝ ካቆምኩ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል፡፡ የወንጀል ጉዳዬችን ለሌሎች ጓደኞቼ እያሳለፍኩ መስጠት ከጀመርኩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
በመለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመን የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ጠባቂዎች በአብዛኛው የአንድ ሰፈር ቋንቋ የሚናገሩ፣ የጠላት አገር የጦር ምርኮኞችን እንጂ ወገናቸው የሆኑ ፍርደኛ ታራሚዎችን የሚጠብቁ አይመስሉም ነበር፡፡ የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች በአብዛኛው ለሰው ልጅ ቅንጣት ክብር የሌላቸውና ከመልካቸው ውጭ ሁለመናቸው እንደ መለስ ዜናዊ የአውሬ ነበር፡፡
ከአመታት በኋላ እንደቀድሞው እስረኛ ለማናገር ሳይሆን፣ ለሌላ አስተዳደራዊ ጉዳይ በዚህ ሳምንት ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተጉዤ በከፊል የተመለከትኩት ጉዳይ ግን ለየት ስላለብኝ ላካፍላችሁ ወድጃለሁ፡፡
ወደ ማረሚ ቤቱ የደረስኩት 2፡00 ከመሙላቱ በፊት ስለነበር በር ተከፍቶ ሰራተኞችም ሆኑ ባለጉዳዮች መግባት አልጀመሩም ነበር፡፡ ግቢው ተከፍቶ መግባት እስኪጀመር በሩ ላይ ሆኜ አካባቢውን መታዘብ ጀመርኩ፡፡ እነዛ የሰው ስጋ የለበሱ አጉረጥራጭ የቀድሞዎቹ አውሬዎች በአካባቢው በጭራሽ አይታዩም፡፡
መግቢያ ሰአት በመድረሱ ወታደራዊ ልብሶቻቸን የለበሱ የማረሚያ ቤቱ ተረኛ ሰራተኞችና የጥበቃ አባላት መግባት ጀመሩ፡፡ ወደ 2፡40 ሲሆን እኔም ጠበቃ መሆኔን የሚያረጋግጠውን የጥብቅና ፈቃዴን አሳይቼ ወደ ማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ገባሁ፡፡
ጉዳዬን በከፍተኛ ትህትና ከ15 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ጨረስኩ፡፡ ቢያንስ እኔ የተመለከትኩት የተወሰነው የማረሚያ ቤቱ ክፍል በመልካም ትህትና ባለጉዳዮቻቸውን በሚያስተናግዱና ሰው ሰው በሚሸቱ ሰራተኞች መሞላቱን ለመታዘብ በመቻሌ ደስተኛ ሆንኩ፡፡
ይሁን እንጂ እኔ ለመመልከት እድል ባገኘሁበት ከማረሚያ ቤቱ መግቢያ በር እስከ ማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ድረስ ባለው የተወሰነ ክፍል የታዘብኩት ሌላ ጉዳይ ደስታዬን ግማሽ አደረገብኝ፡፡ በዚህ ክፍል ከታዘብኳቸው የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት ‘የእናቴን ቋንቋ የሚናገሩ’ የሰፈሬ ልጆች ነበሩ፡፡
አብዛኞቹ ቦታው ላይ የቆዩ አይመስሉም፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም ኒውዮርክ ወይም ፓሪስ ለ ስኮላርሺፕ ተልከው አዲስ ቦታ እንደተገናኙ የቀድሞ ጓደኞሞች በጋለ ስሜት ሰላምታ ይለዋወጡ ነበር፡፡
በዚህም ምክንያት የነ ኮ/ል አብይ የለውጥ ፍኖተ ካርታ አላማ ኢትዮጵያን የፍትህ፣ የእኩልነትና የነጻነት አገር ማድረግ ሳይሆን፣ ሐጎስን በቶላ መቀየር ይሆን? የሚል ጥርጣሬ አደረብኝ፡፡
ትዝብቴ ቁንጽል እንጂ ሙሉ የማረሚያ ቤቱን ክፍል የማያካትት በመሆኑ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ መጠርጠር መብቴ ነውና፣ ጠርጥሬያለሁ!!!