የዛሬ ዐርብ ዐበይት ዜናዎች || ከዋዜማ

የዛሬ ዐርብ ዐበይት ዜናዎች || ከዋዜማ

1. ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ጸጋየ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በቅርቡ ከዐለም ዐቀፍ አሸባሪዎች ጋር በመተባበር የሽብር ጥቃት ሊፈጹሙ ሲሉ የተያዙ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ አሸባሪዎች የሽብር ቦታ መርጠው፣ ስልት ቀይሰውና ፓስፖርት አዘጋጅተው ሳለ የደኅንነት ሠራተኞች በቁጥጥር ስር አውለው አክሽፈውታል፡፡ የውጭ አሸባሪው ቡድን ማን እንደሆነ ተጠይቀው አልሸባብ ነው ሲሉ መልሰዋል፡፡ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች ስላሉ ወደፊት ምርመራ ሲጠናቀቅ እንገልጻለን ብለዋል፡፡ በሙስና በኩል ትናንት 59 የሥራ ሃላዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸው በመንግሥት ግዥ በ400 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ጨረታ 23 ሚሊዮን ዶላር መንግሥት ማጣቱን ገልጸዋል፡፡ በተጠርጣሪዎች የቤት ፍተሻ የቤት ካርታዎችናየባንክ አካውንቶች ተገኝተዋል፡፡

2. ፌደራል ፖሊስ ከትናንት ጀምሮ 60 ያህል በሙስና የተጠረጠሩ የመንግሥት ሃላፊዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡ ከተያዙት ውስጥ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ይገዙ ዳባና ምክትላቸው ሰለሞን አይንማር ይገኙበታል፡፡ ከገንዘብ ሚንስቴር፣ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ኤጀንሲ፣ ከመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲና ከኢትዮጵያ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝም የተለያዩ ሥራ ሃላፊዎች ተይዘዋል፡፡

3. በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ “ግጭ” በተባለው ሳራማ ሜዳ እሳት ቃጠሎው በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ቀዳዲት በተባለው ገደላማ አካባቢ ያለው ግን አልጠፋም ብሏል የቀይ ቀበሮ ጥበቃ ፕሮጀክት የሰሜን ጽሕፈት ቤት ለሸገር ገልጧል፡፡ ጭላዳ ዝንጀሮዎች ግጭ፣ እሜት ጎጎ እና ቀዳዲት ከተባሉት አካባቢውች ሸሽተዋል፡፡ አንድ የቀይ ቀበሮ ቤተሰብም ከመኖያው ተፈናቅሏል፡፡ በተያያዘ ዜና ባህልና ቱሪዝም ሚስትሯ ሒሩት ካሳው የተመራ ልዑክ ወደ ፓርኩ አቅንቷል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እሳቱን ለማጥፋት ርብርብ ላይ ናቸው፡፡

4. ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ጌታቸው እስከተሾሙበት ሰዓት ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት መምህር ነበሩ፡፡ ተቋሙን ከግንቦት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሲመሩት የነበሩት ሰለሞን ተስፋየ ነበሩ፡፡

5. ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመሩን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ ከሁለት የውሃ ማፍያ ታንከሮች በአንደኛው 708 ቶን ያህል ቆሻሻ ተቃጥሎ ከ162 ሜጋ ዋት በላይ ለሙከራ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተችሏል፡፡ ዛሬ ማታ ደሞ ሙሉ የሙከራ ሥራውን ይጀምራል፡፡ ሙከራው ለ5 ቀናት ይቀጥላል፤ ሙከራው ማብቂያም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ጣቢያውን ወደ ብሄራዊ የሃይ ቋት ያካትተዋል፡፡

6. የ5 ተጎራባች ክልሎች የጸጥታ ሃይሎች ድሬዳዋ ላይ የጋራ ሰላም ጉባዔ እያካሄዱ ነው፡፡ የጉባዔው ዐላማ የተጎራባች ክልሎችን ጸጥታ ማጠናከር ነው፡፡ በጉባዔው ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ የሰላም ሚንስትሯ ሙፈሪያት ከሚል፣ የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ፣ የሐረሬ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ ተሳታፊ መሆናቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡

7. የኢሕአዴግ ምክር ቤት ከሰኞ ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን ያደርጋል፡፡ ምክር ቤቱ ያለፉት ወራት የድርጅቱን ሥራ አፈጻጸም ይገመግማል፡፡ በሀገራዊ ጉዳዮችም ላይ ይወያያል፡፡

LEAVE A REPLY