ለኦህዴድ ልጓም ከወዴት ይምጣ? || በመስከረም አበራ

ለኦህዴድ ልጓም ከወዴት ይምጣ? || በመስከረም አበራ

በሃገራችን ፖለቲካ ልማድ ስልጣን የያዘ አካል ያሻውን ለማድረግ የሚያግደው ነገር የለም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ስልጣንን ሊገሩ ሚችሉ የዲሞክራሲ ተቋማት አቅም አለመዳበር ነው፡፡ ደርግ ያሻውን ሲገድል የኖረው፣ ህወሃት እጁ የቻለውን ሁሉ ሲዘርፍ የከረመው፣ አሁን ደግሞ ባለተራው ኦህዴድ ለዚሁ ልማድ እየተንደረደረ ያለው ስልጣን እንዳያባልግ ልጓም ማስገባት ስላልተቻለ ነው፡፡ስልጣንን ያለገደብ የልብን ለመስራት የመጠቀሙ ፖለቲካዊ ልምድ እንዲቀር ካልተደረገ አምባገነን እየቀያየርን በመኖሩ እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የምንፈልገው ነገር ስላልሆነ እንዲቀር መስራት አለብን፡፡

የስልጣን ገደብ አልቦ አድራጊ ፈጣሪነት እንዲቀር ለመስራት በመጀመሪያ በስልጣን አለመገራት የሚመጣውን ችግር ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ስልጣን ባለመገራቱ ሃገራችን ቀይሽብርን የመሰለ ዘግናኝ ሁነት አሳልፋለች፣ ህወሃት በእስርቤቶች ያደረገውን  ክፉ ጭካኔ፣ ጆሮ የሚያስይዝ ዘረፋ፣ ሃገር እስከማፍረስ የደረሰ ዘረኘነት ወለድ ብልሹ ፖለቲካ አስተናግዳለች፡፡ ህወሃትን ተክቶ ስልጣን ላይ ተሰየመው ኦህዴድም በዚሁ መንገድ ለመጓዝ መንገድ ጀምሯል፡፡

ይህ ዝንባሌው በብዙ መንገድ ይገለፃል- ስልጣን ጠቅልሎ ለጎሳው ሰዎች በመስጠት፣ የጎሳውን የፖለቲካ ጥቅም ለማስከበር ሃገሪቱን እንደ ሃገር መቆም ጭምር የሚጎዱ መግለጫዎች በማውጣት፣ ስለተናገረው እና ስላደረገው ድርጊት መጠየቅን በመሸሽ አንዳንዴም ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ፣ የጎጡ ታጣቂዎች/ጎረምሶቸ /አክቲቪስቶች/ ፖለቲከኞች ለሚያጠፉት ጥፋት ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ጥፋቱን ማለባበስ፣ በተቃራኒው ከጎጡ ውጭ ያሉ ሰዎች ህግን ተከትለው በሰላማዊ መንገድ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ችኩል እና አፋኝ እርምጃዎች መውሰድ ኦህዴድ ወደ ልጓም አልቦ ስልጣን እያዘገመ እንደሆነ ጥቂቶቹ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ነገሩን አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ ኦህዴድ እንዲህ ወደ ልጓም አልቦ ስልጣን እተየጓዘ ባለበት ወቅት ሰፊውን ህዝብ ጨምሮ  በሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ዘንድ የኦህዴድ አካሄድ ወዴት እንደሆነ ለመረዳት አለመቻሉ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ኦህዴድ በሚያሳየው እጅግ ተለዋዋጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው፡፡ፓርቲው ወደስልጣን ሲመጣ የጎሳ ፓርቲ መሆኑን እሰኪረሳ ድረስ ሊብራል የሚያስመስለውን ዲሞክራሲያዊነት እና እኩልነት እየደጋገመ ሲሰብክ ሰነበተ፡፡ ይህን የሚያመሳክሩ ጥሩ የሚባሉ እርምጃዎችንም ወሰደ፤ለምሳሌ የሚዲያዎች መከፈት እና የእስኞች መፈታት፡፡

ይህ በመጠነኛ ተግባራዊ እርምጃ የታጀበው ብዙ ስብከቱ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ የሚፈልገው ሰፊውን ኢትዮጵያዊ ሃሳቡን ጥሎ ኦህዴድ/ኦዴፓን ተስፋ  እንዲያደርግ አደረገው፡፡ ሃገሩ ወደ ተሻለ የፖለቲካ ልማድ እልፍ እንድትል የሚፈልገው ይህ ተስፈኛ ቡድን ኦህዴድ በአደባባይ ሌላ በጓዳ ሌላ (በአማርኛ ሌላ በኦሮምኛ ሌላ)እያወራ የሚያደርገውን እጅግ አደገኛ አካሄድ ለመረዳት እና አንድ አቋም ለመያዝ ተቸግሯል፡፡ በበኩሌ ይህ የሚያስቸግር ነገር መሆኑ ማብቃት ያለበት ይመስለኛል፡፡

ከዚህ በኋላ ኦህዴድ መመዘን ያለበት በሚያደርገው ድርጊት መሆን አለበት፡፡የሚያወራው ነገርም ቢሆን ወጥነቱ መፈተሸ አለበት፡፡ የንግግር ወጥ አለመሆን አፍ እና ልብ ልዩነት እንዳላቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ኦህዴድ ሰላም እና ፍቅርን በሰበከበት አፉ ድብልቅልቅ ያለ ጦርነት ሊያነሳ የሚችል ኮማንዶ መሆኑንም የሚናገር የንግግር ወጥነት የሌለው ፓርቲ ነው፡፡ በዚህ ላይ የማይሰማ መስሎት በር ዘግቶ ያወራውን ወዲህ ወዲያ የማያስብል ሃቅ ሊክድ የሚፋትር ሰሚን ለመናቅም የሚሞክረው ፓርቲ ነው፡፡ የተናገረውን ሊል እንዳልተናገረ ሲያስረዳን ለማመን ሞኘነት ተዘጋጅቶ መቀመጣችን ሊያበቃ ይገባል፡፡ ይህን ያቆምን ጊዜ ኦህዴድ/ኦዴፓም የስልጣን ፈረሱ ላይ ልጓም እንዳለ ያስብና የሚሰራ የሚያወራውን አስቦ ይሰራል፡፡ ይህ ደግሞ ለእርሱም ለእኛም የሚበጅ ነገር ነው፡፡

በኦህዴድ/ኦዴፓ የስልጣን ፈረስ ላይ ልጓም ለማስገባት እና እየሆነ ላለው የማንስማማበት የፖለቲካ አኳኋኑ ጠንከር ያለ አቋም መያዝ ያልተቻለው አብይ እና ለማ ከኦህዴድ የተለየ ለኢትዮጵያ ብሄርተኛው የሚቀርብ አቋም አላቸው ተብሎ ለእርግጠኝነት በደረሰ ሁኔታ በሰፊው በመታሰቡ ነው፡፡ ይህ እሳቤ አብይ እና ለማ በተዘጋ በር ውስጥ ሆነው አንሰማም ብለው ያወሩትን ነገር ሁሉ ያወሩት፣ያወሩት ነገር ሲሰማባቸው ደግሞ ሸምጥጠው የካዱት፣አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች የሚል መግለጫ ፈርመው የሚያወጡት፣ አዲስ አበባ የህዝቦቿ መሆን አለባት በሚሉ ሃይላት ላይ ጦርነት የሚያውጁት፣ አይን ያየውን በአዲስ አበባ የሚደረገውን ህገ-ወጥ የመታወቂያ እደላ ሸምጥጠው የካዱት ሁሉ በኦህዴድ/ኦዴፓ አክራሪዎች ተገደው ነው እስከማለት የሚደርስ “ለጋስ” እሳቤ ነው፡፡ እሳቤው ሲቀጥል አብይ እና ለማን ከኦህዴድ ውጭ ባለው ሰው ከተደገፉ ይህን ሁሉ እንዲያደርጉ የሚያስገዱዷቸውን የኦህዴድ/ኦዴፓ አክራሪዎች አሸንፈው እነሱ የሚያምኑበትን እኛም የምንፈልገውን የእኩልነት ፖለቲካ ሊያመጡ ይችላሉ፤ ስለዚህ ዝምብለን እንደግፋቸው ወይም በብርቱ አንተቻቸው የሚል ነው፡፡

በግሌ ይህን እሳቤ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ የመጀመሪያው ምክንያቴ አብይ እና ለማ የኬኛ ፖለቲካን ከሚያራምዱ አክራሪ ከሚባሉት ሌሎች የኦህዴድ አባላት እምብዛም የተለየ ፍላጎት ያላቸው ስለማይመስለኝ ነው፡፡ ይህን የማመሳክረው ደግሞ ሁለቱ ግለሰቦች በንግግራቸው ወጥ ያለመሆናቸው፣ ማድበስበስ እና ማስቀየስ የሚያበዙ፣አንዳንዴም ሰሚን ሞኝ አድረገው የሚመለከቱባቸውን ነገሮች ስለማስተውል ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ተስፈኛው ህዝብ አክራሪው ኦህዴድ አስገድዷቸው እንዳደረጉት በሚያወራላቸው ድርጊቶች ዙሪያ ጥያቄ ሲቀርብልቸው ማድረጋቸው ትክክል መሆኑን የሚናገሩበት ፈርጣማነት (ለምሳሌ ከሶማሌ ክልል የመጡ ተፈናቃዮችን አዲስ አበባ ማስፈር ስህተት እንደሌለው፣ እንደውም ገጠሬን ከተሜ ለማድረግ ጥሩ እንደሆነ ጠሚው የተናገሩበት ፈርጣማነት) ወይ ደግሞ ጉዳዩን ለማድበስበስ እና ለማስቀየስ የሚጥሩት ጥረት(ለምሳሌ ጠ/ሚው የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተ የሚያሳዩት ሙልጭልጭነት፣ በጌዲኦ ህዝቦች ላይ ኦነግ ያደረገውን ጥፋት ለማድበስበስ የሚያደርጉት መተጣጠፍ፣ አቶ ለማ ዲሞግራፊክ ለውጥ ለማምጣት መስራታቸውን የተናገሩበትን ንግግር ያድበሰበሱበት መንገድ) ከትዝብቶቸ ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

የእኔ ትዝብት ስህተት ቢሆን እና አብይ እና ለማ ሁሉንም ነገር የሚያደርጉት ተገደው ነው የሚለው እሳቤ ትክክል ነው አንበል፡፡ እዚህ ሰዎች ተገደው አክራሪዎቹ የሚሏቸውን ነገር እያደረጉ ሄደው ሄደው የኢትዮጵያዊነት አንድያ አምባ የሆነችውን አዲስ አበባን የኦሮሞ ንብረት እስከ ማድረግ ድረስ የደረሰ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ከእነሱ ፍላጎት ውጭ የሆነ፣ ተገደው ያደረጉት ነገር ነው ከተባለ የአክራሪ ተብየውን እሳቤ ተገዳድረው እነሱ በእውነት ያምኑበታል የሚባለውን የሚያደርጉት መቼ  እና እንዴት ነው? ወደውም ይሁን ተገደው አክራሪው የሚላቸውን እየፈፀሙ ህጋዊ ባልሆነ ሁኔታ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ንብረት እስከማድረግ ከደረሱ ምን ቀርቶን ነው በመደገፋችን የምንቀጥለው? እንደሚባለው አብይ እና ለማ የተለየ ሃሳብ ያላቸው የዲሞክራሲ ሰዎች ቢሆኑ እንኳን ሁለት ብቻ ሆነው አእላፉን በኦሮሙማ የደቆነ የኦህዴድ ካድሬ  መርታት እንዴት ይሆንላቸዋል?

የአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች የመጨረሻው ስኬት አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛት ማድረግ ነው፡፡ ይህን ደግሞ አብይን እና ለማ ስልጠን ላይ በሰየሙበት ሁኔታ ሊያስፈፀሙት ጠንክረው እየሰሩ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አብይን እና ለማን የምንደግፈው አክራሪ የተባሉት አብይን እና ለማን ተክተው የሃገሪቱ መሪዎች እንዳይሆኑ ነው? አክራሪ ተብየዎቹ ስልጣን ላይ ቢዎጡስ አዲስ አበባ የእኔ ናት ከማለት በላይ፣ ኦነግ በሃገር ዳርቻ እተየዟዟረ ሃገር እንዲያምስ ከመፍቀድ፣ ኦሮሞ ያልሆነ ሰው በኦሮሚያ መኖሩ ጭንቅ እንዲሆንበት ከማድረግ በላይ ምን ያደርጋሉ? ምናልባት እንደ ለማ እና አብይ ሳይሆን እንደ በቀለ ገርባ ይናገሩ ይሆናል እንጅ በድርጊታቸው ብዙ ልዩነት ያለው ነገር የሚያመጡ አይመስለኝም፡፡

ዝም ብለን አብይን እና ለማን በመደገፋችን እንቀጥል፣ ከረር ያለ ትችትም አንተቻቸው የሚለው አካሄድ በአብይ እና ለማ ለስላሳ አንደበት ተከልለው የልባቸውን ለሚሰሩ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ያሻቸውን እንዲያደርጉ መልካም እድል መስጠት ይመስለኛል፡፡ አብይ እና ለማ የእኛ ድጋፍ ካልተለያቸውና ጊዜ በተሰጣቸው ቁጥር አሉ የሚባሉትን አክራሪዎች ሊያሸንፉ ይችላሉ የሚለው አካሄድ ለዜግነት ፖለቲካ ፈላጊው ዜጋ ከሰጥቶ መቀበል ይልቅ መሸነፍን የደገሰ መንገድ ነው፡፡ ሰጥቶ መቀበል ማለት መሰረታዊ ፍላጎትን አስጠብቆ መለስተኛ ፍላጎትን ለሰላም ሲባል ትቶ ሁሉንም አሸናፊ በሚደርግ መንገድ መጓዝ ነው፡፡ መረታት ማለት ደግሞ ተገዳዳሪን ለማባበል ሲባል ዋና ፍላጎትን ሁሉ እንደዋዛ አስረክቦ ተሸንፎ መግባት ነው፡፡

አሁን የያዝነው አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞችን በለማ እና አብይ በኩል እናባብል የሚለው አካሄድ የሚቀርበው ለሽንፈት እንጅ ለሰጥቶ መቀበል አይደለም፡፡ ለዚህ ዋነኛ ማስረጃው አብይ እና ለማ አዲስ አበባን እስከመስጠት ድረስ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞችን ፍላጎት ለማርካት ሲሰሩ በአንፃሩ ለዜግነት ፖለቲከኛው መልካም ንግግርን ከመናገር የዘለለ ያስመዘገቡለት ድል አለመኖሩ ነው፡፡የኦሮሞ ብሄርተኞች ከፍተኛው ድል እኛ ለፍላጎታችን ይቆማሉ ባልናቸው አብይ ፊርማ አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች የሚል መግለጫ ማስወጣታቸው ነው፡፡ በአንፃሩ የፖለቲካው የማዕዘን ራስ የሆነችውን አዲስ አበባን ቢያንስ በመግለጫ ያስረከበው የዜግነት ፖለቲካ አቀነቃኙ ጎራ የአብይ/ለማን ለጆሮው እንዲስማማ አድርገው የሚደሰኩሩትን ዲስኩር  በፍላሽ ቀድቶ ከማዳመጥ የዘለለ ያገኘው ጥቅም የለም፡፡ ሰርክ የሚወራለት አብይ ያደረጉት እስረኛ መፍታት እና ሚዲያ እንዲናገር የመፍቀዱ ነገር ለሁለቱም ጎራ የመጣ ቱርፋት እንጅ ለዜግነት ፖለቲካው ብቻ የወረደ በረከት አይደለም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ትርፍ ዲሳራ ሲሰላ የነአብይ ወደ ስልጣን መምጣት ለኦሮሞ ብሄርተኝነት ጎራው ተጨባጭ ድል ሲያስመዘግብ ለዜግነት ፖለቲካው ይህ ነው የሚባል ተግባራዊ ድል ያላመጣ ነው፡፡

የአብይ/ማን ወደስልጣ መምጣት ተከትሎ የኦሮሞ ብሄረተኝነት ያስመዘገበው ድል ከህግ በላይ ሆኖ በአዲስ አበባ ላይ ባለቤት ለመሆን መንደርደር ብቻ አይደለም፡፡ የሃገሪቱን ዋነኛ ስልጣ በኦሮሞ መኳንንት እጅ ማስገባት፣የዜግነት ፖለቲከኛውን እግር አስሮ ለኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች እንደልባቸው እንዲሆኑ መፍቀድ(ለምሳሌ መንግስት ለሃሮምሳ ፊንፊኔ እና ለባላደራ ምክር ቤት ያለው የተለያየ እይታ፤ ለኢሳት ዘገባዎች ያለው ቁጠኝነት እና ለOMN ለሚያስተላልፋቸው ፕሮግራሞች ያለው ለዘብተኝነት)፣የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች አፍራሽ ንገግሮችን ለመናገር እንኳን የሚሰማቸው የመዝናናት ስሜት እና ሌላው ላይ ሲሆን መንግስት ያለው ተቆጭነት ሁሉ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከነ አብይ/ለማ ወደስልጣን መምጣት ያተረፋቸው ትርፎቹ ናቸው፡፡

ይህ ሁሉ የማባበል ስራ መሰራቱ ሃገሪቱ ንዳትበታተን ለማድረግ ሲባል መደረግ ያለበት ትክክለኛ አካሄድ ነው የሚል በሰፊው የሚነገር ግን ደግሞ ልክ የማይመስለኝ ክርክር አለ፡፡ የዚህ ክርክር ትልቁ ስህተት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፓለቲከኞችንም ሆነ ሌላ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞችን እያባበሉ መኖር ይቻላል ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ ይህ እሳቤ ልክ ቢሆን ኖሮ ሁለተኛው የአለም ጦርነት አይካሄድም ነበር፡፡ ልክ ስላልሆነ ሂትለር የፈለገውን ሲሰጡ የኖሩት እንግሊዝ እና ፈረንሳይ የማታ ማታ ወደ ፈሩት ጦርነት መግባታቸው አልቀረም፡፡ የማባበል ፖለቲካቸውም የሂትለርን ጡንቻ ማፈርጠሚያ ጊዜ ሰጥቶ ባለጋራቸውን የማይጋፉት ተራራ አደረገባችው እንጅ የረዳቸው ነገር የለም፡፡

የዘር ፖለቲካ በተፈጥሮው የማይጠረቃ ፍላጎት ያለው እሳቤ ነው፡፡ የዘር ፖለቲከኛ የጠየቀውን እየሰጡ በማባበል ለመኖር መንገዱ ሲጀመር በስተመጨረሻው የራስን  ፖለቲካዊ ፍላጎትም አስረክቦ በዘር ፖለቲከኛ ስር ለማደር ለመስማማት መወሰን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ መጠየቅ የማይታክተው የዘር ፖለቲከኛ የራሴ የሚውን ሁሉ ጠይቆ ካበቃ በኋላ የሌላውንም የኔ ነው ማለቱ አይቀርም፡፡ በጀመርነው የኦሮሞ ብሄርተኞችን የማባበል አካሄድ አዲስ አበባ የእኔ ናት ከማለት አልፈው ወደ ወሎም፣ ጎንደርም፣ ራያም እያማተሩ ያሉት ለዚህ ነው፡፡ በማባበል፣ አብይን እና ለማን መድህን በማድረግ ይህን ማስቀረት፣ የምፈልገውን የእኩልነት ፖለቲካ ማምጣት አንችልም፡፡

የምንፈልገውን የሰለጠነ፣ እኩልነት እና ዲሞክራሲ የሰፈነበት ፖለቲካ ማምጣት የምንችለው በስልጣን ላይ ያለውን ኦህዴድ/አዴፓን ስልጣን በመግራት ነው፡፡ የኦዴፓን/አዴፓን ስልጣን ለመግራት ስናስብ የሚያስቸግረን አብይ/ለማ  የልዩ ናቸው የሚለው ስህተት የማያጣው ስሜት ነው፡፡ ይህን እሳቤ ለመቋቋም እነዚሀ ሰዎች ልዩ ቢሆኑ እንኳን ሁለት ብቻ መሆናቸውን፣ ለእኛ የሚስማማንን የእኩልነት ፖለቲካ ለማራመድ ሃሳባቸውን የሚጋራ ሌላ  በርከት ያለ አጋር የሌላቸው በመሆኑ ስልጣን ላይ ያለው ኦህዴድ የሚይዘው የአብዛኛውን አባል መልክ  መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ኦህዴድ እኛ የምንፈልገውን መልክ የያዘ ድርጅት አለመሆኑን ደግሞ ማመሳከሪያው ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ የምንፈልገውን የእኩልነት ፖለቲካ ለማምጣት ኦህዴድ ከህወሃት ከተማረውን የእበልጣለሁ ባይነት መንገድ እንዲመለስ ልጓም ሊገባለት ይገባል፡፡

ኦህዴድ ከተያያዘበት የማያዋጣ አካሄድ እንዲመለስ ልጓም የማስገባቱ ስራ በመጀመሪያ ደረጃ መምጣት ያለበት ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ነው፡፡ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ውስጥ ስልጣን በመነጠቁ ያኮረፈው እና ከሌላው እህት ድርጅት ኦዴፓ ጋር ክፉኛ ባለጋራነት የሚሰማው ህወሃት ለዚህ ስራ የሚሆን ተፈጥሮ ያለው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ኦህዴድን የመግራቱ ሃላፊነት በቀዳሚነት የመወድቀው ብአዴን/አዴፓ እና ደኢህዴን ላይ ነው የሚሆነው፡፡እነዚህ ፓርቲዎች ኦህዴድን አደብ ለማስገዛት የመጀመሪያው እርምጃቸው መሆን ያለበት አጋር ፓርቲዎች ወደ አባልነት እንዲያድጉ መስራት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ፓርቲያቸው ኢህአዴግ  አስቸኳይ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ጠርቶ ሃገሪቱ ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታ በአራት ፓርቲዎች ብቻ የማይቻል ይልቅስ የአጋር ድርጅቶችንም ተሳትፎ የሚፈልግ ስለሆነ   እነዚህ ፓርቲዎች ከአባል ፓርቲዎች እኩል ድምፅ ኖሯቸው በሃገራቸው ጉዳይ ውሳኔ እንዲሰጡ ማስወሰን አለባቸው፡፡ ይህን ለማድረግ የኢህአዴግ ምክርቤት (ማዕለላዊ ኮሚቴ) ጉባኤ መጠራት ካለበትም ተጠርቶ አጋር ፓርቲዎች በሃገራቸው ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ የማድረጉ እንቅስቃሴ መጠናከር አለበት፡፡

የአጋር ፓርቲዎች በሙሉ ድምፅ እና ውሳኔ ሰጭነት በተገኙበት ሁኔታ የኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በሃገሪቱ ፀጥታ እና ደህንነት፣የህግ የበላይነት፣ ታጣቂ ፓርቲዎችን አደብ በማስገዛት ጉዳይ፣ በኦህዴድ በተለይ በአዲስ አበባ ላይ በሚያሳየው የአፈና  አካሄድ ዙሪያ በፓርቲው ቁጥጥር ኮሚቴ አማካይነት ሂሳዊ ምክከር መደረግ አለበት፡፡ አሁን ኦህዴድ እያሳየ ያለውን አይነት  በገዥነት ላይ የተቀመጠን ፓርቲ ጥፋቶች ለማረም የሚደረግ የውስጠ ፓርቲ እንቅስቃሴ መመራት ያለበት በፓርቲው ቁጥጥር ኮሚቴ እንጅ በራሱ በታራሚው ባለስልጣን ፓርቲ አይደለም፡፡

እንዲህ ያለውን መደበኛ የፓርቲ ቁጥጥር ከማካሄዱ ባሻገር የኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች (አጋር የሚለው መጥፋት አለበት) ኦህዴድ እያሳየ ያለውን ህወሃትን የመተካት አምባገነናዊ አካሄድ ለመቆጣጠር የእርስበርስ ግንኙነታቸውን ማጠናከር አለባቸው፡፡የሃገር አንድነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከተውን የኦህዴድ ኦነጋዊ ዝንባሌ በመድፈቅ ረገድ በጋራም ሆነ በተናጠል ጠንካራ አቋም መሊኖራቸው ይገባል፡፡

በዚህ ረገድ ኦዴፓ የአዲስ አበባ የእኔ ናት የሚል መግለጫውን ተከትሎ ብአዴን/አዴፓ እና ደኢህዴን ያወጡት ጠንከር ያለ መግለጫ በጥሩ ጅማሬነቱ የሚያዝ ቢሆንም በቂ ግን አይደለም፡፡ እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች በሃገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ከኦህዴድ ጋር ሆነው የህወሃትን የበላይነት ለማስወገድ የታገሉ እንደመሆናቸው አሁን እያኮበኮበ ያለውን የኦህዴድ የበላይነት ለመዋጋትም ቀዳሚዎቹ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህ የሚሆናቸውን ጉልበት ለማግኘት ሁለቱ አባል ፓርቲዎች እርስበርስ ተናበው ከመስራት ባለፈ አጋር ድርጅቶችንም ከጎናቸው አሰልፈው ሃገርን ከአስፈሪ ውድቀት፣ ከእርስበርስ መተላለቅ የማዳን ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚመሩትን ህዝብ አስተባብረው ሰላማዊ ትግሎችን በማድረግ ተገዳዳሪ ጉልበት እንዳላቸው ማሳየት ይችላሉ፡፡

ኦህዴድ/ኦዴፓ የበላይነቱን ለማስተማመን እየሰራ ያለው፣የኦሮሞ ብሄርተኞችም የፖለቲካ ጥቅማቸውን እጅግ በተለጠጠ መንገድ ለማስከበር እተራወጡ ያሉት የሃገሪቱ ብዙ ቁጥር ያለውን የኦሮሞ ህዝብን ውክለናል በማለት ነው፡፡ይህን የብዙ ነኝ ትምክህትን ለመገዳደር እና ሃገርን ከውድቀት ለማዳን ሲነጣጠሉ ንዑስ የሆኑት ሌሎቹ የኢህአዴግ ፓርቲ ድርጅቶች በአንድ መቆም አለባቸው፡፡ እነሱ በአንድ ሲቆሙ የኦሮሞ ብሄርተኞች የብዝሃነት ትምክህት ያበቃል፡፡የኢህአደግ አባል እና አጋር ድርጅቶች ይህን ማድረግ ተስኗቸው አሁን እያደረጉ እንዳሉት ኦህዴድ የሚሰራውን  ዝም ብለው በማየቱ ከቀጠሉ ሃገራችን ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ ትርምስ መግባቷ አይቀርም፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች የኦህዴድን አካሄድ መግራት ከቻሉ እና በውይይት ከስህተቱ እንዲታረም ማድረግ ከቻሉ እዳ ቀለለ ማለት ነው፡፡ ካልሆነና ኦህዴድ በተያያዘው የአምባገነንነት እና የሃገርን ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል ቸልተኝነት የሚቀጥል ከሆነ ሃገሪቱ የሽግግር መንግስት ወደማቋቋም እንድትሄድ ፓርቲው ፍላጎት እንዲያሳይ ግፊት የማድረግ ህጋዊ ሰውነትም አላቸው እነዚህ ፓርቲዎች፡፡ እነሱ ተጠናክረው የአንድ ፓርቲውን አምባገነንነት ለመገዳደር ከሞከሩ የሃገሪቱ ህዝብም ከጎናቸው መሰለፉ አይቀርም፡፡

ከኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች በመቀጠል ኦህዴድን የማረቅ ሃላፊነት ያለው ህገ-መንግስትን የመተርጎምን ጨምሮ በርካታ የህግ ማስከበር ስልጣን ያላቸው የፌደራሉ  ከፍተኛ ፍርድቤት ፕሬዚደንት የወ/ሮ መዓዛ መስሪያ ቤት እና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ናቸው፡፡ ኦህዴድ መራሹ መንግስት እንደ ፓርቲ የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተ የሚያራምደው አቋም  ህገ-መንግስቱን የሚጥስ መሆኑን ጠቅሶ ወደመስመር እንዲገባ ለማድረግ ከፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት ፕሬዚደንት እና ከፌደሬሽን ምክርቤት የሚቀድም ሃላፊነት ያለው አካል የለም፡፡ እነዚህ አካላት ከመነሻው ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ባለመሆኑ አዲስ አበባ የንትርክ መነሾ ሆና ቀጥላለች፡፡ ይህ ንትርክ አድጎ እና ቀጥሎ ለሚያመጣው ጥፋት የወ/ሮ መዓዛ መስሪያቤትም ሆነ የፌደሬሽን ምክርቤት ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡

የኦህዴድን ስልጣን  በመግራቱ ረገድ ሶስተኛው ባለድርሻ የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በመሃል እጁ የያዘው የዲያስፖራው ማህበረሰብ ነው፡፡ሃገራችን የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ የምትልክ ቢሆንም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቷን ለማሟላት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የምትደገፈው በዲያስፖራው መሆኑ የማያነጋግር ሃቅ ነው፡፡ ዲያስፖራው የውጭ ምንዛሬውን በመከልከልም ሆነ ተከታታይ ሰልፎችን በማድረግ በህወሃት ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ ኦህዴድ የማያውቅ ስላልሆነ ዲያስፖራው ኦህዴድ እየሄደበት ያለውን አላስፈላጊ የአምባገነንነት መንገድ እንዲያቆም በተለያዩ መንገዶች መጠየቅ አለበት፡፡ኦህዴድ ከህወሃት በተሻለ የህዝብ ድምፅ ሰምቶ የመስተካከል ነገር ካለው መልካም፤ ካልሆነ ግን የውጭ ምንዛሬን እስከማገድ በደረሰ ጫና ዲያስፖራው ኦህዴድ መራሹን መንግስት ማስገደድ አለበት፡

የኦህዴድን አላስፈላጊ አካሄድ በመግራት ረገድ ከሁሉም በላይ ጉልበታም የሆነው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ኦህዴድ መራሹ መንግስት የሚያደርገውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በአንክሮ ተከታትሎ ከፍላጎቱ እና ጥቅሙ ውጭ የሆኑ፣ወደመተላለቅ ሊመሩ የሚችሉ አካሄዶቹን እንዲያርም በተለያዩ የሰላማዊ ትግል መንገዶች ትግሉን መቀጠል አለበት፡፡ ከህዝቡ ጎን ለጎን በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር የሚኖሩ ታዋቂ ግለሰቦች፣  ምሁራን እና የሲቪክ ማህበራትም እያደገ ያለውን የአንድ ፓርቲ የበላይነት እና ተያያዝ ጥፋቶች ለማስወገድ መንግስትን ታገስ ተመለስ ማለት አለባቸው፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህን ነገር ለመስራት ተቀዳሚዎቹ ባለድርሻዎች ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት ይህ ሃላፊነትም እምነትም የሚጣልበት ፓርቲ ስላልታየኝ ስለ እነሱ ምንም ማለት አልችልም፡፡

LEAVE A REPLY