ምን እንደምል አላውቅም || መሳይ መኮንን

ምን እንደምል አላውቅም || መሳይ መኮንን

ስለምን እንደምጽፍ እርግጠኛ አይደለሁም። ጊዜው ግን እንዴት ይንቀራፈፋል? ከኢትዮጵያ ከተመለስኩ ሶስት ሳምንት ሊሆነኝ ነው። ድብርታም ሳምንታት። ቀፋፊ። ጭንቅላትን እንደበረዶ የሚያቀዘቅዘው፡ አእምሮን እንደተበላሸ ሰዓት ቀጥ አድርጎ የሚያቆመው፡ ከፊትም ከኋላም ጭልም ባለ ነገር የታጀበው የኢትዮጵያ ሁኔታ ስሜቴን አኮማትሮት፡ ኮምፓስ እንደሌለው መርከብ ከወዲህና ከወዲያ ይልገኛል። እንደዚህ በተስፋ መቁረጥ ነፍሴ እረፍት ያጣችበት ጊዜ የለም። ብዙ ክፉ ነገሮችን አይቼአለሁ። በግልም ሆነ በሀገሬ ጉዳይ የሚያስጨንቁ፡ የሚያስደነግጡ አጋጣሚዎች ተከስተው አልፈዋል። እንደዚህን ወቅት ግን አቅም ያጣሁበት ጊዜ የለም። የምጽፈው፡ የማነበው፡ የማየው የምሰማው አይጥመኝም። ቃላት ስሜቴን መግለጽ አቅቷቸው ይልፈሰፈሱብኛል። ሁሉ ነገር ተስፋን የሚነጥቅ ነው። ቢሆንም ልሞክር።

የኢህአዴግ ስብሰባ ነገ ይካሄዳል። የተኮራረፉት አባል ድርጅቶች የሚገናኙበት ስብሰባ ነው። ሀገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ አጀንዳቸው አድርገው እንደሚወያዩ ይጠበቃል። እየተናበቡ አይደለም። ህወሀት በአካልም በመንፈስም ከሌሎቹ ርቆ፡ ይፋዊ ያልሆነ ነጻ መንግስት መስርቶ ቁጭ ብሏል። አዴፓና ኦዴፓም እንደአጀማመራቸው ፍቅር በፍቅር ሆነው አልቀጠሉም። ደኢሕዴንም የተከታይነት መስመሩን የሙጥኝ እንዳለ አለ። ህወሀት ውህደት የሚባል ነገር እንዳታስቡ ሲል መግለጫ ሰጥቷል። ይለይለት የሚል ይመስላል ህወሀት። ሰሞኑን ካወጣው መግለጫ አንጻር ህወሀት ከሌሎቹ ጋር አብሮ መቀጠል የፈለገ አይመስልም።

ድምጸ ወያኔ ላይ ቃለመጠይቅ የሰጠው የህወሀት ቃለቀባይ ጌታቸው ረዳ የሚናገረውንም ካየን ህወሀት ወደ ቤተመንግስት ከተመለስኩ ኢትዮጵያን ወደ ሰላምና መረጋጋት አመጣለሁ ዓይነት መልዕክት ሊያስተላልፍ የከጀለ ይመስላል። እኔ ነኝ ሀገር አረጋግቼ ማስተዳደር የምችል ዓይነት አጀንዳ ቀርጾ ተዘጋጅቷል። ዶ/ር አብይ ሀገር መምራት አልቻሉም የሚል አቋም ወስዶ በነገው ስብስባ የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ድረስ ውሳኔ ላይ እንዲደረስ ተዘጋጅቶ ነው ወደ አዲስ አበባ የሚያመራው። ለዚህም ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ከአመራር ድክመት የመጣ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

ህወሀቶች እየሆነ ባለው የሚከፋቸው አይደለም። እንደውም በኢትዮጵያ የተከሰተው እጅግ አስፈሪ ሁኔታ ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል። ገበያው ደርቶላቸዋል። ሬዲዮና ቴሌቪዥናቸው በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም የተነሱትን ግጭቶች ማራገቡ ላይ ተጠምደዋል። ሀገር ልትፈርስ ነው፡ ኢትዮጵያ አለቀላት የሚሉ በምሁራን ጭምር የተጻፉ የሟርትና የቀውስ ትንታኔዎችንና ቃለመጠይቆችን እየለቀሙ ማስተላለፍ ተቀዳሚ ተግባራቸው አድርገውታል። የህወሀቶች ዘመን የተሻለ ነው የሚል ግንዛቤ እንዲፈጥርላቸው ቀውሱን በእጅ አዙር ከመቆስቆስ እስከ ማራገብ የሚደርሱ የፕሮፖጋንዳ አቅጣጫዎች ላይ ወጥተው እየገሰገሱ ነው።

ህወሀቶች 27 ዓመት ኮትኩተው ያሳደጉት የዘረኝነት እህል ፍሬ አፍርቶ እያዩት ነው። ዓለም የተጠየፈውን የዘር ‘ፖለቲካ’፡ በህገመንግስት ጭምር እገዳ ተጥሎበት ከምድረ ገጽ ይጠፋ ዘንድ ሀገራት ትኩረት በሰጡበት በዚህ ዘመን ህወሀቶች የመንግስት መዋቅር አድርገው ኢትዮጵያን ከገደል አፋፍ አስጠግተዋታል። ዓይናቸውን በጨው አጥበው ኢትዮጵያ አሁን ለምትገኝበት ቀውስ የዶ/ር አብይን መንግስት ተጠያቂ ማድረጋቸው አስገራሚ ነገር ነው። ዶ/ር አብይ እነሱ ያቆሸሹትን ቤት ለማጽዳት የተነሳ መሪ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እንደተረዳው ለህወሀቶች ጠፍቷቸው አይደለም። የአቶ ጌታቸው የሰሞኑ ቃለመጠይቅ ህወሀት የአሸናፊነት ስነልቦና እንዳለው ለማሳየት ይፍጨረጨራል። እጁን እያወራጨና፡ በዕብሪት ተዝናንቶ ሲያወራ ህወሀት የመልዓክቶች ስብስብ እንጂ የወንጀለኞች ማህበር አይመስልም። ሃጢያቱን በሙሉ ለለውጡ አመራር አሸክሞታል።

በእርግጥ ሀቅ መነጋገር ጥሩ ነው። አቶ ጌታቸው እንዳለውም መሸፋፈን አያስፈልግም። ችግሩን አፍረጥርጦ ማውጣት ለመፍትሄው አንዱ ወሳኝ እርምጃ ነው። ሆኖም ቀና ልብ በሌለበት ቀንና ሌሊት ሲሰበሰቡ ቢያድሩ መፍትሄ አይመጣም። ኢትዮጵያ ብርቱ ህመም ላይ ነች። እንደዚህን ወቅት ህልውናዋ አደጋ ላይ ወድቆ የሚያውቅበት ዘመን የመሳፍንቶቹ የፍጥጫ ታሪክ ነው። ሰሜን ሸዋ ማጀቴ፡ አጣዬ፡ ወሎም ከሚሴ የሆነው ነገር የኢትዮጵያን ነገ የሚያስፈራ አድርጎብኛል። ጥሩ ምልክት አይደለም።

ኢትዮጵያ በነበርኩ ጊዜ ተስፋ የሚያስቆርጡ፡ እንደ ሀገር የመቀጠላችንን ጉዳይ አሳሳቢ የሚያደርጉ አደጋዎችን በቅርበት ተመልክቼአለሁ። ሁሉም የቤቱን አጥር ሰማይ ጠቀስ አድርጎ እያጠረ ይመስላል። ክልሎች ከህገመንግስቱ ውጪ የራሳቸውን ጦር ሰራዊት በገፍ እያሰለጠኑ ነው። የየብሄሩ ነጻ አውጪ በርክቷል። ትላንት ስለአንዲት ኢትዮጵያ ህልውና ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ ዛሬ በብሄር ቅርጫት ውስጥ ገብተው የነጻ አውጪ ካባ ደርበው የኢትዮጵያን ምጥ ማራዘም፡ ስቃይዋን ማበርታት አዲስ የትግል ስልት አድርገው ተያይዘውታል። እዚህም እዚያም የሚታየው ለኢትዮጵያ የምጽአት ቀን እንጂ ትንሳዔዋን የሚፈነጥቅ አይደለም። ሁሉም መስታወት ቤት ውስጥ ሆኖ ድንጋይ እየተወራወረ ነው። ስሜት የሚነዳት፡ የመንጋ አስተሳሰብ የተቆጣጠሯት፡ ደካሞች የነገሱባት፡ ባለራዕዮች አንገት የደፉባት፡ የብሄርና ጎሳ ትርክቶች ከጥላቻ ጋር ተለውሰው ሰማይዋን ያደነቆሩባት፡ ውዷ ሀገሬ ኢትዮጵያ ከገደል ጫፍ ላይ ቆማለች። ትንሽ ከገፏት ከጥልቅ ገደል የምትወድቅ ሀገር።

ሁሉም ነጻ አውጪ አለው። ኢትዮጵያ ግን የላትም። ስለመንደር ጎጡ ላንቃው እስኪተረተር የሚጮህ እንጂ ስለአንድነቷና ክብሯ የቆመ ጠንካራ ሃይል አሁን ላይ ኢትዮጵያ ተርባለች። ህወሀት ለ27 ዓመት የዘራው ቡቃያ ፍሬ ማፍራቱን የሚያረጋግጡ ምልክቶች የኢትዮጵያ ምድር ላይ ከፍ ብለው የሚይታዩበት ዘመን ላይ ተደርሷል። በእርግጥም የቅኝ ገዢዎች የበቀል በትር ከ100 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ላይ አርፏል። የአያት አባቶቻችንን ብርቱ ክንድ ቀምሰው አሳፋሪ ሽንፈት የተከናነቡት ነጮች የቀመሙትን የዘር መርዝ ህወሀት በመላ ኢትዮጵያ ላይ በመርጨት በባዕዳን ተልዕኮ አስፈጻሚነቱ በታሪክ ተመዝግቧል። በህወሀት ተስበው ወደ ዘር ቅርጫት ውስጥ የገቡትና ቀድመው አብረውት የጀመሩት የብሄር አቀንቃኞች ዛሬ እንደአሸን የፈሉባት ኢትዮጵያ ዳገት ላይ ሆና እያቃሰተች ትመስላለች። ወደላይ መውጣት አልቻለችም። ከዳገቱ አናት ከሚገኘው የታላቅነት ደሴት ለመድረስ የጀመረችው ጉዞ በዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች እጅና እግሯ ተይዞ ወደ ታች እየተጎተተች ናት። ከገደል የሚጨምራት በዝቷል። ጠልፎ የሚጥላት በርክቷል። የሚያድናት በእርግጥ እዚህ ዘመን ላይ አልደረሰላትም። የነገውም የኢህ አዴግ ስብሰባ ለኢትዮጵያ ፈውስ መድሃኒት ያመጣል የሚል እምነት የለኝም።

የኢትዮጵያ መፍትሄ ያስጨንቃል። ወዴት እንደምንሄድ አናውቅም። ሀገራችንን ዓይናችን እያየ የዩጎዝላቪያ እጣ ፈንታ ሊገጥማት ይችላል። እንደየመን ወደ ፍርስራሽነት ልትቀየር ትችላለች። እጃችንን አጨብጭበን ሀገራችንን ወደ ትንንሽ ደካማና እርስ በእርስ ወደ ሚተላለቁ ግዛቶች ልንሸነሽናት ተቃርበናል። በእኛ ዘመን ኢትዮጵያ ከካርታ ላይ ስሟ ሊጠፋ የሚችልበት አዝማሚያ ተፈጥሯል። ሀቁን መነጋገር ጥሩ ነው። ኢትዮጵያ ሄጄ የታዘብኩት ይህንን ነው። ምሁራን ተኝተዋል። ወቃሽና ረጋሚ እንጂ መፍትሄ አፍላቂ መሆን አቅቷቸዋል። ነጭና ጥቁር በሆነው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች አሰላለፍ ምሁራን ግራጫውን ይዘው መፍትሄ መስጠት አልቻሉም። ከነጩ አልያም ከጥቁሩ ተሰልፈው፡ የብሄር ታፔላቸውን ከፍ አድርገው እነሱም ስለመንደር ጎጣቸው የተዛባ ትርክት እያስተላለፉ በቀውሱ ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ ያለፈ ሚና ሲጫወቱ ማየት አልቻልንም። ፈጣሪ በትክክል ኢትዮጵያን ረግሟታልየሚያስብለውም በዚህን ወቅት ነው። ከዚህም ከዚያም ያለው መከራዋን የሚያብስ እንጂ መስዋዕት ሆኖ የሚያድናት ሊሆን አልቻለም። መፍትሄ ተብለው በምሁራን የሚቀርቡ ትንታኔዎች የሚያሳፍሩ ሆነው ሲገኙ ይበልጥ ነገ የሚያስፈራ ይሆንብናል።

የመፍትሄው የመጀመሪያ እርምጃ ኳስ በመሬት ማድረግ ነው። መስታወት ቤት ውስጥ ሆኖ ድንጋይ የሚወራወረው ሁሉ ያለበትን፡ የቆመበትን ማወቅ ግድ ይለዋል። የሚጠልዘው ኳስ፡ የሚወረውረው ድንጋይ የት ላይ እንደሚያርፍ ያወቀ አይመስልም። ስለዚህ ወደ መፍትሄ ለማምራት ቀና ልብ ካለን የመጀመሪያው እርምጃችን ስክነት ነው። ጥሞና ያስፈልገናል። የስሜት ግልቢያውን ዛሬ ሳይሆን አሁኑኑ ልናቆም ይገባል። መስከን የመፍትሄው ማስጀመሪያ መድሃኒት ነው። ቀውሱ ገበያ ከፍቶልናል፡ ቢዝነሱን አድርቶልናል ብለው ከአፍንጫቸው ስር ከፍ አድርገው ማየትና ማስተዋል የተሳናቸውም ግለሰቦችና ድርጅቶች ልብ ማለት ያለባቸው ቁልፍ ጉዳይ በዚህ ጨዋታ አሸናፊ እንደማይኖር ነው። ሁላችንም ተሸናፊዎች ነን።

በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ጸንቶ የሚቆም ሀገር አይፈጥርም። ኢትዮጵያን አፍርሰን የራሳችንን ሀገር እንመሰርታለን የሚል ቅዠት ውስጥ ገብተው ቀውሱን እያራገቡ ያሉ ሃይሎች ሰማይ ዝቅ፡ ምድር ከፍ ቢል የሚቃዡት ነገር መሬት እንደማይወርድላቸው ልንገራቸው ግድ ይላል። የተያያዝነው የ’በለው’ እና የ‘ፍለጠው’ እርምጃ ውጤቱ ዜሮ፡ ሁላችንንም ሀገር አልባ እንደሚያደርገን ጥርጥር የለውም። ለጊዜው ጭብጨባ አስክሮን፡ ቢዝነሱ ልቦናችንን ጋርዶት ሊሆን ይችላል። የውጤቱ የመጀመሪያው አሳት የሚጠብሳቸው እነዚህ የዛሬዎቹ ‘’የብሄር ነጻ አውጪዎች’’ ለመሆናቸው በድፍረት መናገር ያስፈልጋል። እናም መፍትሄው ከተፈለገ በዚህና በዚያ የተሰለፈው፡ ኢትዮጵያ እንደሀገር እንድትዘልቅ የሚፈልገውና የራሱን የብሄር ግዛት እመሰርታለሁ ብሎ ቅዠት ውስጥ የገባው ሁሉ ሰከን ብሎ፡ በጥሞና ሁላችንም አሸናፊ ሆነን የምንጨርሰውን የመፍትሄ ጨዋታ መጀመር አለብን። በዚህ ከተስማማንና ቀና ልቦና ከተላበስን ከዚያ በኋላ ያሉት ጉዳዮች ብዙም አያሳስቡንም። ከሰማይ በታች ባለ ማንኛውም ጉዳይ በጠረቤዛ ዙሪያ መፍታት የሚሳነን እንደማይሆን አምናለሁ። ዋናው ሀገራችን ትዳን እንጂ ሌላው እዳው ገብስ ነው እንዲሉ?!

የኢትዮጵያ ጉዳይ ዶ/ር አብይን ከመደገፍና ካለመደገፍ ጋር የሚያያዝ መሆን የለበትም። ዋናው ጥያቄ ኢትዮጵያ ትድናለች ወይስ አትድንም የሚለው መሆን አለበት። አሁን ከደረስንበት ቀውስ አንጻር የዲሞክራሲ ነገር አያሳስበኝም። የፍትህ ጉዳይ ቀጥሎ የሚመጣ ነው። ሁሉም ነገር ሀገር ሲኖረን የምናደርገው ነው። ኢትዮጵያን ማዳን ከእያንዳንዳችን ፊት የቀረበ የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል። ከገደል አፋፍ የተጠጋችን ሀገራችንን እንዴት እናድናት? ከዚህ በላይ የሚያስጨንቅ አጀንዳ ለኢትዮጵያውያን የለም። ትውልዱ ፈተና ተደቅኖበታል። አያቶቻችን ለውጭ ወራሪ ሃይል እጅ ሳይሰጡ፡ ዘርና ቆዳቸውን ሳይቆጥሩ ህይወታቸውን ከፍለው ያቆዩዋትን ሀገር በራሳችን ስንፍና ልናጣት አይገባም። አጽማቸው ይፋረደናል። ታሪካቸው ይወቅሰናል። በየሄድንበት ህሊናችን እረፍት አይሰጠንም። አደገኛ ጊዜ ላይ ነን። መሀሉ ላይ ነን። ማዕበል እያላጋን ነው። ወጀቡ ከወዲህና ከወዲያ እያጎነን ነው። መዳረሻችንን አናውቀውም። እንዳካሄዳችን ከሆነ ከፍርስራሿ ኢትዮጵያ ላይ መድረሳችን አይቀርም። መሃሉን ለመሻገር ሃይማኖተኛው ሱባዔ፡ ፖለቲከኛው ጉባዔ መግባት አለበት። በንጹህ ልብና በቀና መንፈስ ከተነሳን ኢትዮጵያን እናድናለን። ከዚያ በኋላ ሌላው ትርፍ ነው።

ኢትዮጵያን ፈጣሪ ከመጣባት አደጋ ይጠብቃት ዘንድ እንጸልይ!

LEAVE A REPLY