1. ለአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ፖሊስ ኮሚሽነር ተሹሞላታል፡፡ ጌቱ አርጋው አዲሱ ኮሚሽር ሆነወ መሾማቸውን የዘገበው አዲስ ስታንዳርድ ነው፡፡ ኮሚሽነሩ ተሰናባቹን ኮሚሽነር ጀኔራል ደግፌ በዲን ይተካሉ፡፡
2. የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እሳት እስካሁን በቁጥጥር ስር አልዋለም፡፡ ከኬንያ የተገኘችው ሔሊኮፕተር ውሃ ለመቅዳት ወደ ደባርቅ ስትመለስ በክፍተቱ እሳቱ ተመልሶ እያገረሽ መሆኑን ሸገር የቀይ ቀበሮ ጥበቃ ፕሮጀክት የሰሜን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ “ሙጭ” በተባለው የፓርኩ ክፍል ያለው ቃጠሎ በዋሊያ፣ ድኩላና ሌሎች እንስሳት ላይ ከባድ አደጋ ደቅኗል፡፡ ቃጠሎው እስካሁን 700 ሔክታር ቦታ አዳርሷል፡፡ ከሔሊኮፕተሯ ጋር 10 እስራዔላዊያን ባለሙያዎች እሳቱን ለመቆጣጠር ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ትናንት ብቻ ከሔሊኮፕተር 5 ዙር ውሃ ተረጭቷል፡፡ እሳቱን ለሚያጠፉ ነዋሪዎች እህል ውሃ የሚያመላለስ ሔሊኮፕተር መንግሥት እንዲልክ ቢጠየቅም እስካሁን አለመገኘቱን አንድ የፓርኩ ሃላፊ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የሄሊኮፕተሮቹ ቁጥር ወደ 4 ካላደገ እሳቱን መቆጣጠር አይቻልም፡፡
3. የኢሕአዴግ ምክር ቤት ዛሬ ስብሰባውን ጀምሯል፡፡ የሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች አንድ መወያያ አጀንዳ መሆናቸው ታውቋል፡፡
4. ጦላይ ማሰልጠኛ ጣቢያ ሥልጠና ላይ ያሉ ከ150 በላይ የኦነግ የቀድሞ ታጣቂዎች መመረዛቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ችግሩ የተከሰተው ትናንት በቁርስ ሰዓት በሚጠጡት ሻይ ነው፡፡ 129ኙ ትናንቱን ለሕክምና ወሊሶ ሆስፒታል የገቡ ሲሆን 20ዎቹ ደሞ ዛሬ እንደገቡ የሆስፒታሉን ሐኪም ተናግረዋል፡፡ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት እንደታየባቸውም ተገልጧል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ኮምኒኬሽን ቢሮ ዛሬ ከቀትር በኋላ ባወጣው መግለጫ ሁሉም ታማሚዎች በጥሩ ጤንነት ሁኔታ እንደሚገኙ ኢቢሲ ዘግቧል፡፡ የህመማቸው መንስዔ እየተጣራ ቢሆንም የምግብ መመረዝ እንደሆነ የተወራው ግን የተሳሳተ መረጃ ነው ሲል አስተባብሏል፡፡
5. ዛሬ ማለዳ የወሊሶ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ የአድማው መንስዔ ጦላይ ማሰልጠኛ ጣቢያ ያሉ የኦነግ የቀድሞ ታጣቂዎች ተመርዘዋል የሚል ዜና መሰራጨቱ ነው፡፡ በአድማው ሳቢያ ከወሊሶ-አዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ-ወሊሶ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ ወጣቶች መንገዱንም ዘግተዋል፡፡ በከተማዋ የመንግሥት ተቋማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም አገልግሎታቸውን አቋርጠዋል፡፡
6. የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት አባል ጀኔራል ጃላል አል-ዲን የሚመሩት ልዑክ አዲስ አበባ መግባቱን DW ዘግቧል፡፡ የልዑኩ ጉብኝት ዐላማ ግን በይፋ አልተገለጸም፡፡ በተያያዘ ዜና ዛሬ ማለዳ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ባስተላለፉት መልዕክት ራሱን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሲል የሰየመውን አካል እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፤ ሱዳናዊያንም ልዩነታቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረባቸውን የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
7. ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪ ኢቫንካ ትራምፕ ጋር መነጋገራቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኻን ዘግበዋል፡፡ ኢቫንካ ከፕሬዝዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴ ጋርም ተወያይተዋል፡፡ የተለያዩ የሴቶች ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክቶችንም ጎብኝተዋል፡፡ ኢቫንካ ለጉብኝት ትናንት አዲስ አበባ የገቡት በአፍሪካ ስለ ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለመነጋገር ሲሆን ከኢትዮጵያ ቀጥለው ወደ ኮትዲቯር ያቀናሉ፡፡ ጉብኝታቸው በእሳቸው የሚመራው የሴቶች ዐለም ዐቀፍ ልማትና ብልጽግና ፕሮግራም አካል ነው፡፡
8. በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከትናንት ጀምሮ የጦር መሳሪያ ገደብ ተጥሏል፡፡ እገዳው ከዋና ዋና መንገዶች ግራና ቀኝ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ጦር መሳሪያ ይዞ መዛወወርን ያካተተ መሆኑን በአካባቢው የተሰማራው ጥምር ጸጥታ ሃይል አስታውቋል፡፡ እገዳው የተጣለው ከሸዋ ሮቢት ከተማ በአጣየና ከሚሴ በኩል አቋርጦ ወደ ትግራይ በሚወስደው አውራ ጎዳና ዙሪያ ነው፡፡ ከፌደራልና ክልል ጸጥታ ሃይሎች ውጭ ጦር መሳሪያ ይዞ በተገኘ ማንኛውም ሰው ርምጃ ይወስድበታል፡፡